Saturday, November 24, 2012

ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ ጋር ድርድር እንፈልጋለን አሉ Written by አበባየሁ ገበያው

 

በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ከመወያየታችን በፊት በምርጫው ዲሞክራሲያዊነትና ነፃ መሆን ላይ ልንወያይ ይገባል በሚል ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ጥያቄ ያቀረቡ 34 ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የምርጫ ምልክት ውሰዱ መባሉን ተቃወሙ፡፡ በምርጫ ቦርዱ ላይ እምነት ስለሌለን ከኢህአዴግ ጋር ያለቅድመ ሁኔታ ድርድር እንፈልጋለን ብለዋል - ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ፡፡የኢህአዴግ ጽ/ቤት ቢሮ ኃላፊና በጠ/ሚኒስትሩ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው፤ የምርጫ ስነምግባር ደንቡን ካልፈረሙ ፓርቲዎች ጋር አንደራደርም ብለዋል፡፡
ፓርቲዎች የምርጫ ምልክታቸውን እስከፊታችን ሰኞ እንዲወስዱ ምርጫ ቦርድ ያስታወቀ ሲሆን ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ ለቦርዱ ደብዳቤ በማስገባት ምላሽ እየጠበቁ ባሉበት ሰዓት የምርጫ ምልክት ውሰዱ መባላቸው አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ተቃዋሚዎች ላቀረቡት ጥያቄ ምርጫ ቦርድ “ምላሽ የሚሰጠው ተገቢ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ ነው” ሲል ለአዲስ አድማስ መግለፁ ይታወሳል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በቦርዱ ላይ እምነት እንደሌላቸው በመግለፅ፡- ከኢህአዴግ ጋር ውይይት እንደሚፈልጉና ከዛ በፊት የምርጫ ምልክት እንደማይወስዱ አስታውቀዋል፡፡
የመድረክ የስራ አስፈፃሚ አባልና የ34ቱ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ ለአዲስ አድማስ ሲያስረዱ፤ “ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምርጫዎች ችግር የነበረባቸው በመሆናቸው ከጊዜ ሰሌዳው በፊት በምርጫው ፍትሃዊነትና ዲሞክራሲያዊነት ላይ ውይይት እንዲደረግ ፒትሽን ተፈራርመን ለቦርዱ አስገብተን፣ ለሱ ምላሽ ሳይሰጥ ምልክት ውሰዱ መባሉ ተገቢ አይደለም” ብለዋል የምርጫ ቦርዱ ተአማኒነትና ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ ነው ያሉት አቶ አስራት ጣሴ፤ ከኢህአዴግ ጋር በተለያዩ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መወያየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ 34ቱም ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር በሚያግባቧቸው የጋራ አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት እየተዘጋጁ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አስራት ጣሴ፤ ውይይቱ ኢትዮጵያ ስላለችበት ተጨባጭ ሁኔታ በተለይ በሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት፣ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት እንዲሁም የኢትዮጵያ ህልውናና ሉዓላዊነት በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚያተኩር ገልፀዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመጪው ቅዳሜ በ“አንድነት” ቢሮ በሚያካሂዱት ስብሰባ ከኢህአዴግ ጋር ስለሚያደርጉ ውይይት እንደሚመክሩ ታውቋል፡፡ ኢህአዴግ በበኩሉ፤ የምርጫ ስነምግባር ደንቡን ካልፈረሙ ፓርቲዎች ጋር ውይይትና ድርድር አናደርግም ብሏል፡፡
maleda times | November 24, 2012 at 5:15 pm | Categories: AMHARIC NEWS | URL: http://wp.me/p2gxmh-16f
CommentSee all comments

              

No comments:

Post a Comment