ኢሳት ዜና:-የሕወሐት ማዕከላዊ ኰሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ተወልደ ገብሩ (በቅጽል ስማቸው ተወልደ ዓጋመ) በገዛ ፈቃዳቸው ከፓርቲው መልቀቃቸውን ኢየሩሳሌም አርአያ ዘገበ።
የህወሀትን ገመና ፈልፍሎ በማውጣት የሚታወቀው ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋ ማርያም የድርጅቶቹን ምንጮች በመጥቀስ እንደዘገበው፤ አምባሳደር ተወልደ አጋመ በቅርቡ በተካሔደው የፓርቲው ጉባኤ ላይ የመልቀቂያ ጥያቄ በማቅርበ ከማዕከላዊ ኰሚቴ አባልነት ራሳቸውን እንዳገለሉአስታውቀዋል።
በአምባሳደርነት ሲያገለግሉ የቆዩት ተወልደ «አጋሜ» ከ 1993ዓ.ም በሑዋላ ያለ ሙያቸው ወደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተዛውረው ሢሰሩ ቆይተዋል።
የ አምባሳደር ተወልደ ባለቤት የሆኑት ሮማን ገ/ስላሴም በፓርቲው ሊቀ-መንበር ፦ « አይኗን ማየት አልፈልግም!» ተብለው ከፓርቲው ርቀው እንደነበርምንጮቹ አስታውሰዋል።
የሕወሃት አንጋፋ ሴት ታጋይ የነበሩት ሮማን የተሓድሶ «አቀንቃኝ» ሆነው ወደ መድረክ በመውጣታቸው በትግራይ የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ተደርገው በመለስ ከመሾማቸውም ባሻገር በፓርቲው ማዕከላዊ ኰሚቴ አባልነት መካተታቸውንም ምንጮቹ ጠቁመዋል።
አምባሳደር ተወልደ ለረጅም አመት ይበሳጩና ብዙውን ጊዜ በዝምታ ያሳልፉ እንደነበርም ምንጮቹ ጠቁመዋል።
አምባሳደር ተወልደ አጋሜ ከህወሀት ቢለቁም ፤ ባለቤታቸው ወይዘሮ ሮማን ግን አለመልቀቃቸው ታውቋል።
ቀደም ሲል የገቢዎች ሚኒስትር፣ሁዋላ ላይ ደግሞ የኢፈርት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የህወሀት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው በላይ ከጥቂት ወራት በፊት ፓርቲያቸውን በመክዳት ከነ ቤተሰባቸው ወደ አሜሪካ መኮብለላቸው ይታወሳል።
በህወሀት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ባለስልጣን የሆኑ ሰዎች በገዛ ፈቃዳቸው ድርጅቱን ሲለቁ የታዩት ከ አቶ መለስ ሞት በሁዋላ መሆኑ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
No comments:
Post a Comment