Friday, November 30, 2012

ሁለተኛው የኢህአዴግ መንግስት (ከአስራት አብርሃም)

 

“እናንተ፣ ያበሻ ሰዎች ተስፋን አትቁረጡ
ከስንት አመት ወዲያ…
መልሰው ሊገዙ ንጉስ ጦና መጡ”
ይህ ግጥም አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የተሾሙ ጊዜ በፌስቡክ ላይ የተለቀቀ ነው። የገጣሚውን ማንነት ማወቅ ባልችልም ሀሳቡን የገለፀበት መንገድ ግን ሳላደንቅ ማለፍ አልችልም። ግሩም ድንቅ ነው!
በታሪክ እንደሚታወቀው የወላይታ የመጨረሻው ንጉስ ካዎ ጦና ነበሩ። ግዛታቸውን ላለማስነጠቅ አያሌ የመከላከል ጦርነቶች አካሄዷል፤ በኋላ ላይ በአፄ ምኒልክ ጦር ተሸንፈው፣ ግዛታቸውም ለሸዋው ሰፋሪ ጦር አስረክበው ለግዞት ተዳርጓል። ከዚያ በኋላ የወላይታ የሚባል ንጉስ አልነበረም። ለዚህ ነው ገጣሚው “ተስፋ አትቁረጡ” የሚል ስንኝ ያስቋጠረው። ከወላይታ፣ ኢትዮጵያን የሚገዛ መጣ ለማለት ተፈልጎ የተገጠመ ይመስላል። እውነትም ሰውዬ ኢህአዴግ ሆኑ እንጂ ከወላይታ መምጣታቸውስ ደስ የሚል እና ተስፋ የሚሰጥ ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ “አቅም እስካለኝ ድረስ የአገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን ለመያዝ የሚያግደኝ ነገር አይኖርም” ብሎ እንዲያስብ የሚያደርግ ነውና። ክፋቱ ግን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደዚህ ስልጣን የመጡት በአቅም ብቃት ሳይሆን ለቀድሞው ጠቅላይ ሚንስቴር በነበራቸው ታማኝነት መሆኑ ላይ ነው። ይህን እውነት የሰውየው ነፍስ አባት በየዋህነት ለሪፖርተር ጋዜጣ ሰጥቷል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማስተዳደር ባቃታቸው ጊዜ ለአቶ መለስ ስልክ ደውለው “ኧረ እኔ አልቻልኩም ምን ማድረግ ይሻለኛል?” ብለው ያመለክታሉ።
አቶ መለስም ለዚህ የሰጧቸው መልስ ግን በጣም የሚገርም ነው። “እዚያ ለመኖር ሀሳብ ከሌለህ በስተቀር በእጅህ ያለውን ንብረት አስረክብህ ወደ ዚህ ና” ነበር ያሏቸው። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ማስተዳደር ካልቻሉ አልቻልክም ተብለው ወደ ቀድሞው ስራቸው እንዲመለሱ ማድርግ እንጂ ወደ ቤተመንግስት እንዲያድጉ መደረጉ በኢህአዴግ የእድገት መለኪያ ስራ ነው ወይስ ሌላ የሚያስብል
ነው። አቶ ኃይለማርያም ግን በዚህ ብቻ አላበቁም። እንደገና ወደ ነፍስ አባታቸው ደውለው “ምን ላድርግ ምክር ይስጡኝ” ይላሉ። ቄሱ ቀላል ሰው አይደሉም “መጀመሪያውስ ኢህአዴግ ልሆን ነው” ሲሏቸው “ግድ የለህም እግዚአብሄር በዚያ መንገድ እንድታገለግለው ፈልጎ ይሆናል” ያሉት እርሳቸው አይደሉ! ይህን ጊዜም “ለአቶ መለስ አማክረሃል” ይሏቸዋል። “አዎ እርሳቸውማ ወደዚህ ና
ብሎውኛል።” ቄሱም ትንሽ ካሰቡ በኋላ “ልጄ በሰውየው ልብ ውስጥ ገብተሃል ማለት ነው። ዝም ብለህ ሂድ” ብለው ምክር እንደሰጡ ተናግሯል። የአቶ ኃይለማርያም ህይወት አንድም በእኚህ ቄስ አንድም ደግሞ በኢህአዴግ የተያዘ ነው የሚመስለው። ያም ሆነ ይህ እነሆ ሁለተኛው የኢህአዴግ መንግስት ተመስርቷል። ዋነኛ ተግባሩም አቶ መለስ የጀመራቸውን የልማትና የፖለተካ
እቅዶች፣ የወ/ሮ አዜብ መስፍን አገላላፅ ልጠቀምና “ሳይበረዙና ሳይከለሱ” ማስፈፀም ነው። እኛ ጥፎ፣ ጭሮ አዳሪዎች ደግሞ አዲሱን መንግስት ካለን ፖለቲካዊ አቋም ተነስተን በማብጠልጠል የተለመደውን ሂስ የመስጠት ስራችን ቀጥለናል። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም ቢሆኑ ያሉት እንደዚያ ነው። “ከፓርቲዬን አቋምና አመለካከት ተነስቼ የማንኛውም ፓርቲ ሀሳብ
ማብጠልጠል እችላለሁ” ነው ያሉት። ችግሩ ግን መነሻችን የተሳሳተ ከሆነ ነው። አቶ ኃይለማርያም የፓርቲያቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንደመነሻ አድርገው ወደ ማብጠልጠሉ የገቡ እንደሆነ ስህተት ላይ ይወድቃሉ። በመሰረቱ “አቶ መለስ የፓርቲዬ አቅም” የሚሉት የራሳቸውን አቋም ነው። አቶ ኃይለማርያም ደግሞ ይህን የአቶ መለስን አቋም ነው “የፓርቲዬ አቋም” የሚሉት። መሰረታዊው ልዩነት
ይሄ ነው።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርላማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊቀርቡ ነው ሲባል ሰምተን “ደግሞ እኝህ ትሁት ሰው ምን ብለው ይናገሩ ይሆን?” ብለን በጉጉት ስንጠብቅ በስድቡም በአሽሙሩም አቶ መለስን አያስከነዷቸውም መሰላችሁ! እኔማ አንድ ተረት ነው ትዝ ያለኝ፤ ድሮ ነው፣ አንድ በመዋሽት የሚተዳደር ሰው ነበር አሉ። መቼም ሰው ሆኖ ማርጀት ያለ ነውና ይህ ሰው ስራውን ለልጁ ለማውረስ
ፈልጎ ልጁን “ና እስቲ የኔ ሳተና” ብሎ ወደ ውጪ ያወጣውና አውራ ጣቱን ወደ ሰማይ እያመለከተ “ተመልከት እዚያ ሰዎች እህል እየወቁ ነው” ይለዋል። ልጁን ይህን ጊዜ ምን ቢል ጥሩ ነው! “የት አሉ?” አይደለም ያለው። ዓይኑን በእጁ እያሸ “ዓይኔን ዓይኔን” ማለት ጀመረ። “ምን ሆንክ?” ይለዋል አባትየው ደንግጦ። “እብቁ ዓይኔ ውስጥ ገባ” ሆነ የልጁ መልስ! አባትየው ይህን ጊዜ ፈገግ ብሎ ልጁን
ተመለከተው በኩራትም “አንተስ ከእኔ በላይ ውሸታም ነህ፤ ትምህርትም አያስፈልግህ” አለው ይባላል። አቶ መለስ ይህ የአቶ ኃይለማርያምን የፓርላማ ንግግር ቢሰሙ ኖሮ የዚህ ልጅ አባት በልጁ የኮራውን ያህል ኩራት ይሰማቸው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያሰሩት ሰዓት ሳይቀር ራሱ የአቶ መለስ የነበረው ነው ሲባል ሰምቻለሁ። እጅ አሰነዛዘራቸውስ
ቢሆን ድንቅ አይደለም እንዴ! መውረስ ካልቀረ ሁሉንም ነው እንጂ! በቃ አቶ ኃይለማርያም ያልወረሱት ነገር ቢኖር አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እርሱም ምናልባት የግብፁ ፈርኦን ለዮሴፍ “ከእንትዬ በስተቀር ሁሉም ላይ እንድትሰለጥን ስልጣን ሰጥቼሃለሁ” እንዳለው ሆኖ ይሆናል።በእውነቱ ይህን ስመለከት የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተፈጥሯዊ ችሎታ ኃይማኖትና ፖለቲካ ባይሸፍናቸው ኖሮ ቲያትር መስራት
ሊሆን እንደሚችል አሰብኩ። እኛማ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሀይማኖተኛ ናቸው ሲባል ሰምተን “ፈሪሀ እግዚአብሄር ይኖራቸው ይሆናል” ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። መጨረሻ ላይ ያፈርነው እፍረትስ ለወዳጅ አይስጥ ነው! በዚህ አጭር የስልጣን ዘመናቸው ከአሰርቱ ትእዛዛት ውስጥ አራቱን በመጣስ ፀረ ኃይማኖት መሆናቸውን አስመስክሯል።
1. “እናቴ አልዳነችም” በማለት በእናታቸው እምነት ላይ ተሳልቀዋልና፤ “እናት አባትህን አክብር” የሚለውን ትዕዛዝ ጥሰዋል። 2. የተቀዋሚ መሪዎችን በግልፅም በአሽሙርም በመሳደባቸው “ጠላትህን እንደራስህ ውደድ” የሚለውን ቃል በግልፅ ጥሰዋል (እኔማ “እድሜያቸው የገፉ፣ መተካካትን የማያውቁ አንዳንድ የተቀዋሚ መሪዎች በአቋራጭ ስልጣን መጋራት ይፈልጋሉ” የምትለዋን ስሰማ
በሳቅ ፍርፍር ብዬ ልሞት ነበር። እስቃለሁ ብዬ ትን ብሎኝ ብሞት ከሁላም በላይ የኢህአዴግን መጨረሻ ሳላይ መቅሬቴ ነበር የሚቆጨኝ)
3. እነ አንዷለም፣ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነበቀለ ገርባ “የነፃነት ጀግኖች ሳይሆኑ አሸባሪዎች ናቸው” በማለታቸው “አትዋሽ” የሚለውን ሕግ ጥሰዋል።
4. በወሎ ለሰልፍ የወጡ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ዜጎችን እንዲገደሉ በማድረጋቸው “አትግደል” የሚለውን ዋነኛ ትዕዛዝ ሽሯል። በዚህ ከቀጠሉ ሁሉንም ትዕዛዛት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሽሯቸው እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። ይህ ነገር ስታይ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከእግዚአብር መንገድ ይልቅ “የታላቁን መሪ” መንገድ ለመምረጣቸው ጥሩ ማሳያ ነው። የሰማዩን ህግ እንዲህ
ከጣሱት የምድሩንማ ይረጋግጡታል ቢባል ነው የሚቀለው! አቶ መለስ መጨረሻ ላይ ከፕሮቴስታንቶች የአቶ ታምራት ላይኔን ልዋጭ አገኙ አይደል። አቶ ታምራት ላይኔ ከመለስ ምክትልነት ወደ
ኢየሱስ ተከታይነት ሲሄዱ አቶ ኃይለማርያም ደግሞ ከኢየሱስ ተከታይነት ወደ አቶ መለስ ተከታይነት መጥቷል። “ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም” ማለት ይሄ ነው!
አንድ የፕሮቴስታንት ሰባኪ “ጠቅላይ ሚንስትሩ ኃይለማርያም አይደለም፤ ኢየሱስ ነው!” ሲል፤ አሜን! አለ እዚያ የነበረው ሰው ሁሉ። ሰባኪው ከምን ተነስቶ እንደዚያ እንዳለ እንጃ፣ በመንገድ ሳልፍ ነው በመሀል የሰማሁት። አቶ ኃይለማርያም በቀን ለአንድ ሰዓት ያህል ፀሎት ያደርጋሉ፤ መፅሐፍ ቅዱስ ያነባሉ። ከዚያ ቀኑን ሙሉ ደግሞ የአቶ መለስ አብዮታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ ዴሞክራሲ ሲተገብሩ
ይውላሉ። የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአበሐር ማለት ይሄ ይሆን!

No comments:

Post a Comment