Thursday, June 20, 2013

ይኼ ሰው ጀግና ነው by Daniel Kibret



አበሻን በአንድ እግሩ ያስቆመ፤ ለሃያ አራት ሰዓታት የመግቢያ ትኬት ፍለጋ ያሰለፈ፤በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የብሔራዊ ቡድኑን ዐርማ የያዙ ቲሸርቶች እንዲቸበቸቡ ያደረገ፤ ሕዝብ እንደ መንጋ ንብ አንድ ዓይነት ዜማእንዲያዜም ያስቻለ፤ ሽማግሌን እንደ ሕጻን ያስጨፈረ፤ ሕጻንን እንደ ሽማግሌ ያስተከዘ፤ የፓርቲና፣ የዘር፣ የእምነትና የባህልንአጥር አስጥሶ ወገንን በአንድነት ገመድ ያስተሣሠረ፤ ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡

ተረስተን ነበረ፤ ረስተንም ነበረ፤ ርቀን ነበረ፤ ተርቀንም ነበረ፤ ተርተን ነበረ፤ተረት ሆነንም ነበረ፤ እግርን ከኳስ አውጥተን ለሩጫ ብቻ አውለነው ነበረ፤ እንዲያ በሩጫ ዓለምን አስደምመን፣ ኳስ ሜዳ ግንዘጠና ደቂቃ መሮጥ አቅቶን ደክሞን ነበረ፡፡ ሕዝባችን ከካምቦሎጆ ኳስ ወደ ዲ ኤስ ቲቪ ኳስ ፊቱን አዙሮ ነበረ፡፡ ይህንንቀይሮ በአፍሪካ ምድር ከ31 ዓመታ በኋላ ብቅ እንድንል ያደረገ፤ በዓለም መድረክ ‹እኛም አለንበት› እንድንል ያስቻለ - ይኼሰው ጀግና ነው፡፡
 ድሮም የዓለምን ታሪክ የሚቀይሩት ጀግና ግለሰቦች ናቸው፡፡ አገር በኮሚቴ አድጋ፣ታሪክ በቡድን ተቀይሮ አያውቅም፡፡ የዓለም ክፉም ሆነ በጎ ታሪክ የተለወጠው የመለወጥ ዐቅም ባላቸው ግለሰቦች ማርሽ ቀያሪነትነው፡፡ ሌላው አጃቢ፣ ተባባሪ፣ ተከታይና ፈጻሚ ነው፡፡ ቢስማርክ የሚባል ሰው ባይነሣ ኑሮ ጀርመን የምትባል ሀገር ተረት ትሆንነበር፡፡ ካሣ (ቴዎድሮስ) የሚባል ጀግና ባይነሣ ኖሮ የዘመናዊቷን ኢትዮጵያ ቅርጽ ማን ይቀይር ነበር፡፡ አብርሃም ሊንከንየሚባል ፕሬዚዳንት ባይነሣ ኖሮ የአሜሪካን የርስ በርስ ጦርነት ማን ይፈታው ነበር፡፡ ሌኒን የሚባል ሰው ባይወለድ ኖሮኮሚኒዝም የሚባለውን ነገር ከሃሳብ አውጥቶ ማን ሥጋ ያለብሰው ነበር፡፡ ጎርባቾቭ የሚባል ሰው ባይፈጠር ኖሮ ኮሚኒዝምን ማንታሪክ ያደርገው ነበር፡፡ ማንዴላ የሚባል ጀግና ብቅ ባይል ኖሮ የዛሬዋን ደቡብ አፍሪካ ማን ይፈጥራት ነበር፡፡ ቴዎዶር ኸርዝልየሚባል ይሁዲ ባይነሣ ኖሮ እሥራኤል የምትባለውን ሀገር ማን እውን ያደርጋት ነበር፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የሚባሉ ንጉሥ ባይነግሡኖሮ ለሁለት የተከፈለችውን አፍሪካ ወደ አንድ አምጥቶ ማን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት ያደርግ ነበረ፡፡
 በቅርቡ የታሪካችን ክፍል እየተደጋገመ አንድ ነገር ሲነገረን ነበር፤ እየተነገረንምነው፡፡ ‹ታሪክ የሚሠራው ሰፊው ሕዝብ ነው› ይባላል፡፡ እንዴው ለመሆኑ ሕዝብ እንዴት ተሰባስቦ፣ እንዴትስ ተመካክሮ፣ እንዴትስወደ አንድ አቋም ደርሶ ነው ታሪክ የሚሠራው? ሕዝብ ማለትኮ ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፣ ከአሶሳ እስከ ቶጎ ጫሌ ያለው ነው፡፤ የትተዋውቆ፣ መቼ ተገናኝቶ፣ እንዴትስ አድርጎ ተደራጅቶ ታሪክ ይሠራል፡፡ ሕዝብ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃልም ተናጋሪእንዲሆን የሚያደርጉትኮ ግለሰቦች ናቸው፡፡
 ሕዝብ ታሪክ እንዲያራምድ የታሪክ ሞተር የሚያስነሡ አውራ ግለሰቦች ያስፈልጉታል፤ሃሳብ የሚያመነጩ፣ ሃሳቡን የሚያሰርጹና ለሃሳቡ ግንባር ቀደም የሚሆኑ ግለሰቦች ያስፈልጉታል፡፡ የአፕል ካምፓኒ መሥራች ስቲቭጆብስ ብቅ ባይል ኖሮ የሞባይል ስልክን ታሪክ ማን ይቀይረው ነበር? ‹ዓለምን የቀየሩት ሦስት አፕሎች ናቸው፡፡ አዳም የበላውአፕል፣ በኒውተን ራስ ላይ የወደቀው አፕልና ስቲቭ ጆብስ የሠራው አፕል እስኪባል ድረስ የስልክን ተፈጥሮ የቀየረው እርሱአይደለም ወይ፡፡ እነ ማርክ ዙከርበርግ ተነሥተው ፌስ ቡክ የሚባል ማኅበራዊ ሚዲያ ባይፈጥሩ ኖሮ የዘመኑን የግንኙነት ባህልማን ይቀይረው ነበር?
 አዎን ሕዝብ አለ፡፡ ሕዝብም ግን ታሪክ ያራምዳል እንጂ ታሪክን አይሠራም፡፡ ግለሰቦችየፈጠሩትን፣ ያሰቡትን፣ የፈለሰፉትን፣ ያመነጩትን የሚያራመደው፣ የሚያቀነቅነው፣ የሚያስፈጽመው፣ ገንዘብ የሚያደርገውና ያንንሃሳብ፣ ፈጠራ፣ ፍልስፍና፣ ግኝትና ጥበብ የኑሮ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችለው ሕዝብ ነው፡፡
 ቡድን ታሪክ የማይሠራበት ምክንያት ታሪክ ለመሥራት ማሰብ ወሳኝ ስለሆነ ነው፡፡ ማሰብደግሞ ግላዊ እንጂ በቡድን ሊታሰብ አይችልም፡፡ በቡድን መመካከር፣ መወያየት፣ ማጥናት፣ መመራመር ይቻል ይሆናል፡፡ በቡድንማሰብ ግን አይቻልም፡፡ ሰው የተፈጠረው በየግሉ ነው፡፡ እንደ መላእክት በማኅበር አልተፈጠረምና በማኅበር ሊያስብ አይችልም፡፡በየግል የታሰበውን ግን በማኅበር መፈጸም ይቻላል፡፡ ቡድኖች፣ ማኅበራትና ተቋማት በግለሰቦች የሚመነጩትን ሃሳቦች የሚፈጽሙ፣የሚያዳብሩና ሕልው እንዲሆን የሚያደርጉ እንጂ ግለሰቦችን የሚተኩ ግን አይደሉም፡፡
 አንዳንድ ማኅበረሰብ ለግለሰቦች ቦታ የለውም፡፡ ‹ሰፊው ሕዝብ› የሚባል የማይጨበጥአካል አስቀምጧል፡፡ ሁሉንም ነገር ለሰፊው ሕዝብ ይሰጠዋል፡፡ ሕያው የሆኑትን ግለሰቦችን ገድሎ፣ ሕያው ያልሆነ ‹ሰፊ ሕዝብ›የሚባል አካልን ያነግሠዋል፡፡ ሰፊ ሕዝብ ድርሰት ይደርስ ይመስል፤ ሰፊ ሕዝብ ዜማ ያመነጭ ይመስል፤ ሰፊ ሕዝብ ይፈጥር ይመስል፤ሰፊ ሕዝብ ይፈላሰፍ ይመስል፡፡ የሕዝብ ሆነው የቀሩ ግጥሞች፣ ታሪኮች፣ አባባሎች፣ ዜማዎችና ባህሎች እንኳን ‹ሰፊ ሕዝብ› ውጦያስቀራቸው ግለሰቦች ባልታወቀ ዘመንና ባልታወቀ ቦታ ያመነጩት ነው፡፡ ግን ምን ያደርጋል ስንት ባለ ዜማዎች፣ ስንት ባለቅኔዎች፣ ስንት ጀግኖች፣ ስንት ታሪክ ነጋሪዎች፣ ስንት ተረት ደራሲዎች ተውጠው ቀርተዋል፡፡
 ይኼው የሐበሻ ጀብዱ የሚባል መጽሐፍ ቢተረጎም አይደል እንዴ ከሰላሌ የሄደ አብቹየተባለ ጀግና ማይጨው ላይ ታሪክ መሥራቱ የታወቀው፡፡ ሰላሌ ወርዳችሁ ብታስሱ ግን አብቹን የሚያውቀው የለም፡፡ ታሪኩን ሕዝብወርሶታል፡፡ ‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግና ነው› በሚለው ብሂል ተውጦ አብቹ ቀርቷል፡፡
 ባህላችን ለቡድኖች፣ ለማኅበራትና ለተቋማት የሚያደላ በመሆኑ አያሌ ግለሰቦችእንዳይሠሩ አድርጓል፡፤ የሠሩትም ቢሆኑ እንዳይታወቁ ውጧል፡፡ ሥራቸውን እንጂ ሰዎቹን ዕውቅና አንሰጣቸውም፡፡ ለመሆኑ ይህንንደረታችንን ነፍተን የምንኮራበትን የአኩስም ሐውልት ሐሳብ ያፈለቀው ማነው? ማን ነበር ጥበበኛው? ማን ነበር ቀማሪው? ማንስነበር ያቆመው? ሐውልቱን እንጂ ማንነቱን አላገኘነውም፡፡ የታደሉት ሀገሮች ሳያውቁት ለቀሩት ጀግና ወታደር ‹ላልታወቀውወታደር› የሚል ሐውልት ይሠሩለታል፡፡ እኛስ ምን ነበረበት ‹‹ላልታወቀው የአኩስም ሐውልት ጠቢብ›› የሚል ሐውልት ብናቆምለት፡፡ለመሆኑ ምን ምን ዕውቀት ያሉት ሰው ነው ያንን ለማሰብ የሚችለው? ታሪኩን በመላ ምት እንደገና ማነጽ ይቻላልኮ፡፡ ሰዓልያንናቀራጽያን በምናባቸው ማሰብ ይችላሉ፤ የታሪክ ምሁራን ከግኝቶቻቸው ተነሥተው መተለም ይችላሉ፡፡
 ልጆቻችን ሐውልቱን እንዲያደንቁ እንጂ ጠቢቡን እንዲያደንቁ አላደረግናቸውም፡፡የጎንደርን ሕንፃ እናደንቃለን እንጂ ስለ አርክቴክቶቹ፣ ስለ መሐንዲሶቹ፣ ስለ ግንበኞቹ አውርተን አናውቅም፡፡ ግንቡ በተአምርየተሠራ ይመስል፡፡ በፋሲል ግንብ ውስጥም እነዚያ ጠቢባን እነማን እንደሆኑ ሊያሳይ የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ አንዴፖርቹጋሎች አንዴ ግሪኮች አንዴ ፈረንሳዮች እያልን የመሰለንን ሁሉ በቡድን ስም ስንጠራ እንኖራለን፡፡ የጥበብ አሻራዎቻችንበሚገኙባቸው በታላላቅ አድባራትም ያሠሩት ሰዎች ስም እንጂ የእነዚያ ጠቢባን ስም ተረስቷል፡፡ ልክ በመጻሕፍቱ ላይ ያስጻፉትሰዎች እንጂ የደራስያኑ ስም ተረስቶ እንደቀረው፡፡
 ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ መመለስ የነበረብን ግን ያልመለስናቸው፡፡ እንዴው ለአፍ ታሪክያህል እንኳን የሐበሻ ቀሚስን ማን ጀመረው? እንጀራ መጋገርን ማን አመጣው? አምባሻ ዳቦ በማን ተፈለሰፈ? ሞሰብና ሰፌድ መስፋትንማን አመጣው? ዋሽንትን ማን ጀመረው? ክራርንስ ማን ፈጠረው? ቆጮን ማን ጀመረው? ክትፎስ የማን ፈጠራ ነው? ገንፎንስ ማንፈለሰፋት፣ ጭቆና ቆጭቆጫ፣ ቃተኛና ፍርፍር፣ ቆሎና ዳቦ ቆሎ ማን ይሆን ያመጣቸው? ሽሮና በርበሬ፣ ድቁስና ሚጥሚጣ፣ አዋዜናስናፍጭ ማን ነበር አስቦ የፈለሰፋቸው? እነዚህን ጥያቄዎች ብንጠይቅ የብሔረሰቦችና የጎሳዎች ስም፣ የአካባቢና የጎጥ ስም እንጂየግለሰቦችን ስም አናገኝም፡፡ እነርሱ ተውጠው ቀርተዋል፡፡
 ልጆቻችን አርአያ ሊያደርጉት፣ ሊከተሉትናሊፎካከሩት የሚችሉት ግለሰብን ነው፡፡ ማኅበርን ወይም ሕዝብን መከተል አይቻልም፡፡ ግለሰቦችን በዋጥናቸውና ባጠፋናቸው ቁጥር፣ለጀግኖቻችን ክብርና አድናቆት በነፈግናቸው ቁጥር ሌላ ጀግና ማግኘት አንችልም፡፡ ሰነፎች ‹ሕዝብ› በሚባል የማይዳሰስ መዋቅርውስጥ ገብተው ይደበቃሉ፡፡ ሕዝብ ተጠያቂነት የለበትምና፡፡ ሰነፎችም ተጠያቂነትን ሲፈሩ ሕዝብ ውስጥ ይደበቃሉ፡፡ እንደ ጀግኖችመሥራት ሲያቅታቸው የጀግኖችን ዋጋ ለሕዝብ ይሰጡና እነርሱም የዋጋው ተቋዳሽ ይሆናሉ፡፡
 እኔም እሑድ ዕለት በተደረገው የኢትዮጵያናየደቡብ አፍሪካ ጨዋታ ያየሁት ይኼንን ነበር፡፡ ቡድኑን አሠልጥኖና መርቶ ለድል ያበቃው አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ሳይሆን ሌሎችነበሩ ሲመሰገኑ የነበሩት፡፡ ከሌሊት ጀምረው ወረፋ ያዙት፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ለብሰው የደገፉት፣ ጨዋታውን ያስተላለፉት፡፡ለስፖርት ልዩ ፍቅር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነበሩ ስማቸው ከፍ ከፍ ያለው፡፡ እነዚህ ሁሉ ከፍ እንዲሉ ያደረገው ግን ሰውነትየሚባል አንድ ጀግና ተነሥቶ ነው፡፡ በስታየሙ ውስጥ ግን ‹ሰውነት ሆይ እናመሰግናለን› የሚል ነገር አላየሁም፡፡
 የአፍሪካ ዋንጫ ድሮም ነበረ፤ የዓለምዋንጫ ድሮም ነበረ፤ ከሱዳን ጋር ብዙ ጊዜ ገጥመናል፤ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ደጋግመን ተጫውተናል፡፡ አሁን ማርሹን የቀየረውማነው? ሰውነት የሚባል አንድ ታሪክ ሠሪ ነዋ፡፡ ማንቸስተርዩናይትድ ባለፈው ጊዜ ሃያኛውን ዋንጫ ሲወስድ ስታዲዮሙ ‹ፈርጉሰን ሆይ እናመሰግናለን፤ ፈርጉሰን ጀግና ነው፤ ፈርጉሰንለዘላለም በልባችን ይኖራል› በሚሉ መፈክሮች ተሞልቶ ነበር፡፡ ልክ ነው ፈርጉሰን የማንቸስተርን ታሪክ ለውጠውታል፡፡ ሰውነትምየኢትዮጵያ እግር ኳስን ታሪክ ለውጦታል፡፡
 ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ
ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይኼን ጊዜ አበሻ
 የተባለውኮ ያለምክንያት አይደለም፡፡ በታሪክ ውስጥ የወሳኝነት ድርሻ ላላቸው ሰዎችክብር ለመስጠት እንጂ፡፡ ሰውነት የሚባል አሠልጣኝ ተወልዶ ይኼው ታሪክ አየን፡፡ ትረካችን ተለውጦ ለአፍሪካ ዋንጫ መብቃትናአለመብቃት፤ ለዓለም ዋንጫ መብቃትና አለመብቃት ሆነ፡፡ ‹ስንት ለዜሮ ይሆን የምንሸነፈው?› የሚለው ሥጋት ቀረ፡፡ ከዚህ በላይምን ጀግንነት አለ? ከዚህ በላይ ምን የገጽታ ግንባታ አለ፡፡
 ተዉ ጎበዝ ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡
 እኛ በጠባያችን አንበሳውን ካዳነው ሰው ይልቅ የገደለውን ጀግና ስለምናደርግ ነውእንጂ፡፡ እኛ በጠባያችን ችግር ሲመጣ ለግለሰቦች፣ ድል ሲመጣ ለጋራ ስለምንወስድ ነው እንጂ፤ እኛ በጠባያችን ማኅበርና ቡድንግለሰብን ስለሚውጥ ነው እንጂ፡፡ ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ በአረንጓዴ ቀለም አሻራውን ያስቀመጠጀግና፡፡
በቅርቡ ስለ እግር ኳስ ሜዳዎች የሥነ ምግባር ችግር በተጠራ ስብሰባ ላይ ‹አሠልጣኝሰውነት መሰደብ የለበትም› ተብሎ ሲነሣ አንድ የእግር ኳሱ ባለሥልጣን ‹አሠልጣኝ ቢሰደብ ምን አለበት? አሠልጣኝን መስደብ ዛሬነው እንዴ የተጀመረው፡፡ ድሮም እነ እገሌና እገሌ ሲሰደቡ ነበሩ›› እያሉ ሲቀልዱ ሰማሁ፡፡ ‹እንኳንም እርስዎ የጤና ጥበቃሚኒስትር አልሆኑ› ብዬ ደስ አለኝ፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት ይቅር ሲባሉ ‹ሴት መገረዝ የጀመረችው ዛሬ ነው እንዴ› ይሉ ነበር፡፡ግግን ማስቧጠጥ ይቅር ሲባሉ ‹‹ግግ መቧጠጥ በኛ ዘመን ነው እንዴ የተጀመረው፤ ስንቱ ሲያስቧጥጥ አልነበረም እንዴ›› ይሉነበር፡፡ እንጥል ማስቆረጥ ይቅር ሲባሉ፡፡ እንጥል ማስቆረጥ ድሮም ነበረ፡፡ ምን አዲስ ነገር መጣ›› ይሉን ነበረ፡፡ ‹‹ ያለእድሜ ጋብቻ ይቅር ሲባሉ ‹‹ምነው እገሊትና እገሌ ያለ እድሜያቸው አልነበረም እንዴ የተጋቡት? ዛሬ ምን አዲስ ነገር መጣ››ይሉን ነበር፡፡ እግዜርም ዐውቆ ሰማዩን ዐርቆ ማለት ይኼ ነው፡፡
 ለነ ወልደ መስቀል ኮስትሬ ክብር እየነሣንየኢትዮጵያ ሩጫ እንዲያድግ የምንመኝ የዋሐን ጀግናን መግደልና ታሪክ ሠሪን ማጥፋት ለምዶብናል መሰል፡፡ በላይ ዘለቀን ገደልን፤አክሊሉ ሀብተ ወልድን ገደልን፣ አቤ ጎበኛን ገደልን፣ በዓሉ ግርማን ገደልን፣ አበበ አረጋይን ገደልን፣ ዮፍታሔ ንጉሤንገደልን፣ አለቃ ታየን ገደልን፣ ንግሥት ዘውዲቱን ገደልን፣ ከበደ ሚካኤልን ሀብታቸውን ነጥቀን በቁማቸው ገደልን፣ ሐዲስዓለማየሁን መጽሐፋቸውን እያሳተምን የእርሳቸውን ንብረት ቀምተን በቁማቸው ገደልን፣ ስንቶቹ ዘፈናቸውን እየሰማን እነርሱን ግንገደልን፤ ስንቶቹን ቲያትራቸውን እያየን እነርሱን ግን ገደልን፤ ስንቱን ስንቱን ገደልን፡፡
አገዳደላችን በሦስት መንገድ ነው፡፡አሳቢውን በማጥፋት፣ ሃሳቡን በማጥፋትና ሃሳቡን በመንጠቅ፡፡ ስንት አሳቢዎች ‹ዓሣውን ለማጥፋት ባሕሩን ማድረቅ› በሚለውብሂላችን ምክንያት ከነ ሃሳባቸው ተገደሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሃሳባቸው እንዳይሰማ፣ እንዳይነበብ፣ እንዳይሳካና እንዳይታይ በማድረግተገደሉ፡፡ በሌላ በኩልም አሳቢውን ዝም አሰኝቶ ሃሳቡን በመንጠቅና አሳቢው ተንገብግቦ እንዲሞት በማድረግ ስንት ጀግናአጥተናል፡፡ የነ አያ እገሌ ፈጠራዎች፣ ሃሳቦች፣ ድርሰቶች፣ ግኝቶች፣ ፍልስፍናዎች ተነጥቀው የነ አቶ እገሌ ሆነው ቀርተዋል፡፡የነ አያ እንትና ታሪክ ለነ ክቡር እንቶኔ ተሰጥቷል፡፡ የአሳቢዎችን ጥቅም ክብርና ዝና፣ አቀንቃኞች ወስደውት ‹‹የበሬንምስጋና ወሰደው ፈረሱ›› ተብሎ ተዘፍኗል፡፡
 አሁንም ሺ ‹ሰውነቶች› ወደፊት ተነሥተውየሀገራችንን የስፖርት መልክ እንዲቀይሩት ከፈለግን የዛሬውን ሰውነት እናወድሰው፡፡ ሰውነት ጀግና ነው፡፡ ታሪክ የለወጠ፣ሕዝብን ያስዘመረ፣ አገርን አንድ ቋንቋ ያናገረ፤ ቡድኑን መርቶ ውጤት የዘወረ፣ ኃላፊነትን ተሸክሞ ሀገር ያስከበረ፡፡ ከዚህበኋላ ያለው ውጤት እንኳን ቢቀየር ሰውነት ግን የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ አንድ አይተነው ወደማናውቀው የታሪክ ምዕራፍአድርሶታል፡፡ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ስታዲዮም በር ላይ የተሰለፍነው ሰውነት የሚባል ሰው ተስፋ ያለው ቡድንስለሠራኮ ነው፡፡ እንዲያ ስታዲዮም ገብተን የደገፍነው ሰውነት የሚባል ሰው የሚደገፍ ቡድን ስላዘጋጀኮ ነው፡፡
 ከነ ስሕተቱም፣ ከነ ጠባዩም፣ከነጉድለቱም፡፡ ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡

Comment   See all comments

Wednesday, June 5, 2013

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በአባይ ጉዳይ ላይ

ዛሬ ደግሞ…

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም
ጦርነት እንኳን ገና በልቶ ላልጠገበ ሕዝብና ለጥጋበኞቹም አይመችም፤ የተራበ ሕዝብ በጠገቡ መሪዎች ሲነዳ ግን ጦርነት ለአጉል ጀብደኛነት ዝና የሚጠቅም መስሎ ይታያቸዋል፤ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ለመግጠም በሚያሰፈስፉበት ጊዜ በርቱ እያሉ የሚያቅራሩ ሞልተው ነበር፤ ዛሬ አቀራሪዎቹም ሆኑ ጀብደኖቹ በኤርትራ ጦርነት ያለቀባሪ ስለቀሩት ሰዎች፣ ጠዋሪ ስላጡ እናቶችና አባቶች፣ አሳዳጊ ስለሌላቸው ልጆችና አካለ-ጎደሎ ለሆኑት የሚያስብላቸው አለ ወይ? የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት መነሣትና በኢጣልያ የግራዚያኒ ሐውልት እንዳይሠራ የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ከልክሎ ለሰልፍ የወጡትን አስሮ ያሳደረ አገዛዝ ለአገራቸው ለሞቱት ኢትዮጵያውያን የሚሰጠውን ዋጋ በመጠኑም ቢሆን ያሳያል፤ ስለዚህም ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ሲወዱ ራሳቸው በልጽገው ለልጆቻቸው ብልጽግናን እንዲያወርሱ ሕይወታቸውን ቢጠብቁ ለአገራቸውም ክብር ይሆናሉ፡፡
ለፍቅር መተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለጠብም መተዋወቅ ያስፈልጋል፤ የተሟላ መረጃ ቢኖረን የጥንት ታሪክ እየጠቀስን ሰዎችን ለጦርነት እንቀሰቅስም ነበር ብዬ አምናለሁ፤ ስለዚህም አንዳንድ አስፈላጊ መረጃዎችን ላቅርብ፤ —
1. የግብጽ የጦር ኃይል በዓለም አሥረኛ ነው፣ በአፍሪካና በመሀከለኛው ምሥራቅ የሚወዳደረው የለም፤ አንድ ሚልዮን ተኩል ያህል የጦር ኃይል አለው፤ በዓየር ኃይልም ከዓለም አሥራ አራተኛ ነው፤ በታንክ ብዛት አራተኛ ነው፤ በባሕር ኃይል ሰባተኛ ነው፤ በጦር በጀት አርባ ሦስተኛ ነው፤
2. በኢትዮጵያ ዙሪያ ጂቡቲ፣ ሶማልያ፣ ሱዳን የአረብ ማኅበር አባሎች በመሆናቸው ለግብጽ ማኅበረተኞች ናቸው፤ በወያኔ ፈቃድ የተገፋችው ኤርትራም የዚሁ ማኅበር ታዛቢ አባል ነች፤ ከቀይ ባሕር ማዶ ያሉት አገሮች ሁሉ ሀብታሙንና ኃይለኛውን ሳኡዲ አረብያንም ጨምሮ የግብጽ ማኅበርተኞች ናቸው፤ በዚህ ሁሉ መሀከል የተከታተፈች ኢትዮጵያ ብቻዋን ነች፤
3. የቤንዚን ሀብትና ከሀብቱም ጋር የሚገኘውን ወዳጅና ጡንቻ አንርሳ፤
ይህ ማስታወሻ ለማስፈራራት አይደለም፤ ማስፈራራትን አላውቅበትም፤ እንዲያውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ‹‹አትፍሩ›› ብሏቸዋል ተብዬ ተከስሼ ታስሬአለሁ፤ ስለዚህ አላስፈራራም፤ ጦርነት ከመጣብን ልናስቀረው እንሞክር፤ ሌላው ቢቀር እንድንዘጋጅ ጊዜ እናገኛለን፤ ገፍቶ ከመጣ ግን እንቋቋመዋለን፤ ለጦርነት አንቸኩል፤ ለኤርትራም ጊዜ ተናግሬ ነበር፤ የሰማኝ የለም፤ ጥጋብ ላይ ያሉ የሚርባቸው ዝና ነው፤ የሚያገኙት ግን ውርደትን ነው፡፡

Saturday, June 1, 2013

Egypt: Scores Protest At Ethiopia Embassy to Demand Expelling Ambassador by Abby


Scores of demonstrators staged a protest on Friday at the Ethiopian embassy headquarters in Cairo to demand expelling the Ethiopian ambassador to Egypt and call for halting the Renaissance Dam project, al-Masry al-Youm newspaper reported.
Ethiopia has begun implementing a project to build a $4.7 billion dam. The project entails diverting the Blue Nile which may affect downstream countries.
The demonstrators chanted slogans condemning Ethiopia's policies and lifted banners attacking the dam building process.
The embassy prevented the protesters from burning the Ethiopian flag after one demonstrator attempted to down the flag.
Source:al-Masry al-Youm
Abby | May 31, 2013 at 3:07 pm | Tags: Blue NileEgyptEthiopiaNile | Categories: Africa | URL: http://wp.me/p2gxmh-1VI
Comment   See all comments