Sunday, September 1, 2013

ሰላማዊ ትግልን የሚገድብ ህገወጥ መመሪያ ተግባራዊ






የአዲስ አበባ መስተዳድር ካቢኔ በተለይ የአንድነት ፓርቲን ህዝባዊ ንቅናቄ ለማፈን የሚያስችል አዲስ የሰላማዊ ሰልፍና የሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ መመሪያ በማዘጋጀት በህገወጥ መንገድ ተግባራዊ ማስደረጉ ታወቀ፡፡

ካቢኔው ያፀደቀው አዲሱ መመሪያ አንድነት ፓርቲ በመላ ሀገሪቱ እያደረገ ያለውን ስኬታማ ህዝባዊ ንቅናቄ ግምት ውስጥ የከተተ እንደሆነ ማንነታቸው እንዲገለፅባቸው ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ ኃላፊ ለአንድነት ፓርቲ አመራሮች ገልፀዋል፡፡ የፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊው እንደሚሉት ነሃሴ 10 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ካቢኔ የፀደቀውና ለኮሚሽኑ የተላከው መመሪያ ከሕዝብ ፊርማ ለማሰባሰብ፣በራሪ ወረቀት ለመበተን፣ በማይክራፎን ለመቀስቀስና ፖስተር ለመለጠፍ ውስብስብና የተለያዩ አካላትን ፍቃድ ማግኘትን የግድ የሚል ነው፡፡ ሃላፊው “መመሪያው በተለይ የአንድነት ፓርቲ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ውጤታማ እንይሆን በችኮላ ተግባራዊ የተደረገ ነው፡፡” በማለት ጨምረው አስረድተዋል፡፡
የመመሪያው አወጣጥ ህገወጥነት እንደተጠበቀ ሆኖ መመሪያው በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ሳይወጣና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ሳይሰራጭ፤ የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ህገወጡን መመሪያ እንዲያስፈፅም ከአዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ ጽ/ቤት ትእዛዝ መተላለፉ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዳበቃለት የሚያሳይ ነው፡፡

የመመሪያው ህገወጥነት አሳሳቢ በመሆኑ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና የፓርቲው ዋና ፀሀፊ አቶ አስራት ጣሴ ከአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ግርማ ካሳና ከኮሚሽኑ 3 ከፍተኛ ሀላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ህገወጡን መመሪያ ፖሊስ ኮሚሽኑ እንዲያስፈፅም መታዘዙን አረጋግጠዋል፡፡

“መመሪያው በ1983 ዓ.ም ከወጣው (አዋጅ ቁጥር 3/1983 ዓ.ም ስለ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ሥርዓት የወጣ አዋጅ ገጽ 12) አዋጅ ጋር የሚጣረስ ነው፣ በአዋጁ የአዲስ አበባ መስተዳድር የራሱን መመሪያ ማውጣት እንደሚችልም የሚገልፅ ነጥብ የለም፡፡ ” በሚል የአንድነት ፓርቲ አመራሮች የአዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ ጽ/ቤት ሃላፊዎችን ቢጠይቁም የከንቲባ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው “ለሰኞ ተመካክረን ምላሽ እንደጣችኋለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ዛሬ ከሰአት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስለመመሪያው የሚያውቀው ነገር እንዳለ በቦርዱ ጽ/ቤት በአካል ተኝተው ጥያቄ ቢያቀርቡም የቦርዱ ዋና ፀሀፊ አቶ ነጋ “ምርጫ ቦርድ እንዲህ አይነት መመሪያ ስለመውጣቱ የሚያውቀው ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አንድነት ፓርቲ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል በመላው ሀገሪቱ እያካሄደ ላለው ህዝባዊ ንቅናቄ ከህዝብ ፊርማ ሲያሰባስቡ፣በራሪ ወረቀት ሲበትኑና የመኪና ላይ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ከ72 በላይ የሚሆኑ አባላቱ በአዲስ አበባ ህገወጥ እስር ተፈፅሞባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
staff reporter | August 30, 2013 at 9:51 am | URL: http://wp.me/p2gxmh-2bK
Comment    See all comments