- ከውጭ አህጉረ ስብከት ብፁዓን አባቶች ከግማሽ ያላነሱ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል
- የሰላምና አንድነት ጉባኤውን በተጨማሪ ሽማግሌዎች የማጠናከር አማራጭ ተይዟል
በመጪው ሳምንት ሰኞ፣ ጥር 6 ቀን 2003 ዓ.ም፣ ለዕርቀ ሰላም ልኡካኑ ሪፖርትና ተጓዳኝ ሐሳቦች ቅድሚያ በመስጠት የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብስባ÷ በአወዛጋቢ ውሳኔ የተቋቋመው የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ሥራውን እንዲጀምር የታዘዘበትን የማሳሰቢያ ደብዳቤ ሊሽረው እንደሚችል ተጠቆመ፡፡
የማሳሰቢያ ደብዳቤው የተጻፈው በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ ነው፤ በይዘቱም እስከ ጥር 30 ቀን ድረስ ከአምስት ያላነሱ ከሦስት ያልበለጡ የፓትርያሪክ ዕጩዎችን እንዲያቀርቡ የተሠየሙት የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተገኝተው ሥራ እንዲጀምሩ የሚያሳስብ ነው፡፡
የመንበረ ፓትርያሪኩን አስፈጻሚ አካል ብቻ የመምራት ሓላፊነት ያለባቸው የጠ/ቤ/ክህነቱ ዋ/ሥ/አስኪያጅ÷ ይህን ዐይነቱን ማሳሰቢያ መስጠት ‹‹የማይመለከታቸውና ያለሥልጣናቸው የገቡበት ነው›› ብለዋል ኮሚቴው በቅ/ሲኖዶሱ የተሠየመበት የቀደመው ደብዳቤ ተፈርሞ የወጣው በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ፊርማ እንደነበር የሚያስታውሱ ወገኖች፡፡
ይኸው የማሳሰቢያ ደብዳቤ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ወይም በቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ተፈርሞ አለመውጣቱ አስመራጭ ኮሚቴው ከመሠየሙም አስቀድሞ በመጠናከር ላይ የሚገኘውን ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚሉ ወገኖች ተቃውሞ/ትኩረት ለመቀነስ፣ በአመዛኙ ግን ዐቃቤ መንበሩና ብፁዕ ዋና ጸሐፊው በጉዳዩ ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት አቋም ለመያዛቸው በአስረጅነት ተዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል የምልአተ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ ለጥር 6 ቀን በተጠራበት ኹኔታ አስመራጭ ኮሚቴው ጥር 8 ቀን ሥራውን እንዲጀምር መታዘዙ የቅ/ሲኖዶሱ የውሳኔ አሰጣጥና አፈጻጸም ‹‹የዕርቀ ሰላም ጉባኤው ከፓትርያሪክ ምርጫው ተለያይቶ መታየት አለበት፤ ዕርቀ ሰላሙ በአቡነ ጳውሎስ ጊዜ የተጀመረ ነውና ይቀጥል፤ የፓትርያሪክ ምርጫውም ጎን ለጎን መካሄድ ይኖርበታል›› የሚል አቋም በያዙ በቁጥር ያነሱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተጽዕኖ ሥር ለመውደቁ ማሳያ ለመኾኑ የሚስማሙ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እሊህ አባቶች (አንዱ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ናቸው) ባገኙት መድረክ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ከማስተማር፣ ከመጸለይ ይልቅ ‹‹እንደ አቡነ ጳውሎስ ያለ አባት አናገኝም፤ ግን ጸዋሚ፣ ተሐራሚ፣ ሰጋጅ፣ ጸሎተኛ አባት እንዲሰጠን ጸልዩ›› ማለታቸውን አጠንክረው መያዛቸው ተዘግቧል፡፡
በአንጻሩ ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚሉና ቁጥራቸው በየጊዜው የሚጨምረው ብዙኀኑ ብፁዓን አባቶች ከወዲሁ የተለያዩ ማስፈራሪያዎች፣ ዛቻዎች፣ ጫናዎች የሚደርስባቸው መኾኑ ሲታይና ሲሰማ ተመሳሳይ ጥሪ በማስተጋባት ላይ የሚገኘው አገልጋይና ምእመን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከጎናቸው እንዲቆም የሚያስፈልግበት ቀናት እንዲኾን አድርጎታል፡፡
የሰላምና አንድነት ጉባኤው እገዳና ወከባ ስለደረሰባቸው ልኡካኑ፣ የአገር ቤቱ የዕርቀ ሰላም ልኡካን ስለተቃወሙት መግለጫው ማብራሪያ እንደሚሰጥ ተጠብቆ የነበረ ቢኾንም የተጠበቀው አልኾነም፡፡ በአስቸኳዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ÷ የሰላምና አንድነት ጉባኤውን እንደ አዲስ በሚዋቀር አደራዳሪ አካል ለመተካት ቢታሰብም ከዚህ ይልቅ ጉባኤው ተደማጭነት ባላቸው የአገር ሽምግሌዎች ቡድን የተመረጡ አባላት ማጠናከር በውጭ ባሉትም ብፁዓን አባቶች ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ እንደማይቀር ተገምቷል፡፡ ከአገር ሽማግሌዎቹ መካከል እንደ ራስ መንገሻ ሥዩም፣ ፊታውራሪ ዘውዱ አስፋው እና አቶ አምኃ ወልዴ ያሉት ስማቸው ተጠቅሷል፡፡
በአስቸኳዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ለሚሳተፉት የቅ/ሲኖዶስ አባላት በጽ/ቤቱ የሚደረገው ጥሪ ተጠናቆ ተሳታፊዎቹ ወደ አዲስ አበባ – መንበረ ፓትርያሪኩ በመግባት ላይ ሲኾኑ በውጭ አህጉረ ስብከት ከሚገኙ ዐሥር ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ከግማሽ በላይ ለስብሰባው እንደሚደርሱ ተገልጧል፡፡ በስብሰባው ታኅሣሥ 8 ቀን የጸደቀው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ አንዳንድ አንቀጾች የሚነሣባቸው ጥያቄዎች/ተቃውሞዎች፣ ሕገ ደንቡ የጸደቀበት የስብሰባ ሥነ ሥርዐት እንዲሁም ከሕገ ደንቡ መጽደቅ በፊት ታኅሣሥ 6 ቀን በአወዛጋቢ ውሳኔ የተሠየመውየስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ቀጣይነት በከፍተኛ ደረጃ ሊያከራክር እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
No comments:
Post a Comment