Wednesday, January 16, 2013

መነኮሳቱ እና ቀሳውስቱ ምን እየሰሩ ነው ? የፓትርያሪኮቹ አቋም ምን ይመስላል ?


በወቅታዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የቅ/ሲኖዶሱ አባላት አቋም ምን ይመስላል?
  • ‹‹ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› የሚሉ አባቶች በአቋም ተጠናክረዋል፤ በቁጥር ጨምረዋል
  • የምልአተ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ ዛሬ ከቀትር በኋላ ውይይቱን ይቀጥላል
አቋም መያዝ የመራጭ (ምርጫ ያለው) ግለሰብ ወይም ቡድን መብት ነው፡፡ ከምን አንጻር ወይም ለምን ዓላማ ከሚለው በመነሣት አቋሙን ማሔስ ወይም መተንተን ደግሞ የወደረኞች፣ የተገዳዳሪዎች፣ የተሟጋቾች፣ የተበላላጮች ጠባይዕ ከእነርሱም አልፎ የተመልካቾች መብትና ነጻነት ነው፡፡
በተነሣንበት ርእሰ ጉዳይ÷ ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ቅድሚያ የሚሰጡ አባቶችና ወገኖች ለአቋማቸው ሥልጡንና ሥዩም (entitled) ቢኾኑም ‹‹ከምርጫው ይልቅ ለሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተን የልዩነቱን ምዕራፍ እንዝጋ፤ የዕርቀ ሰላም ሂደቱን ፍጻሜ እንጠብቅ፤ ውጤቱን እንይ፤ ለውጤቱም እንሥራ›› የሚሉ አባቶችና ወገኖች የያዙትን አቋምና የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ ‹‹የብዙኀን ዐምባገነንት ነው፤ የሥልጣን ጥማትና የተቃዋሚ ፖሊቲከኞች ሽፋን ነው›› ብለው ሊተቹ ይችላሉ፡፡ እኒህም እነኛን ‹‹ዕርቅንና ሰላምን የጠሉ፣ ሥልጣን የሚወዱ፣ ለመንግሥት ተጽዕኖ ያደሩ›› ቢሏቸው ያው ትችት ነው፡፡ ግና ቁምነገሩ የታሪክ ስሕተቶችን ከማረም፣ ለዘመኑን ለመጪው ትውልድ ጠንካራ ቤተ ክርስቲያንን ከማቆየት አንጻር የሚበጀው የቱ ነው የሚለውን በትክክልና በአግባቡ መመለስ ነው፡፡
ሐራውያን እይታ ‹‹ከምርጫው ይልቅ ለሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተን የልዩነቱን ምዕራፍ እንዝጋ፤ የዕርቀ ሰላም ሂደቱን ፍጻሜ እንጠብቅ፤ ውጤቱን እንይ፤ ለውጤቱም እንሥራ›› የሚለው አቋም የብዙኀን አቋም ነው፡፡ መሠረቱ በደልን እየተዉ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አንድነት፣ መንፈሳዊ ሕይወትና ተቋማዊ ጥንካሬ መጨነቅ ነውና ‹‹ከብዙኀን ዐምባገነንነት›› ሊመነጭ አይችልም፡፡ ከተባለም እንደ ነገሩ አግባብነት የአንዱ ሰው (የጥቂቶች) ስለ ብዙኀን ‹መሞት›፣ ለብዙኀን ፍላጎት መገዛት ክርስቶሳዊነት (ዮሐ.18÷14) ነውና የሚነቀፍ አይኾንም፡፡ እውነታው÷ በአቋማቸው ያጽናቸው ከቁጥርም አያጉድላቸው እንጂ ‹‹ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› የሚሉ አባቶች በአቋም ተጠናክረዋል፤ በቁጥርም መጨመራቸው ነው፡፡
አሁን ጎልተው የወጡና ከሞላ ጎደል በሁለት ተጠቃለው ሊወሰዱ የሚችሉ ወቅታዊ አጀንዳዎች አሉ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የቅ/ሲኖዶሱ አባላት ከሰጡት አስተያየትና ካንጸባረቁት አቋም በመነሣት ሐራውያን ምንጮች ባካሄዱት የአቋም ማመዛዘን (በሂደት ሊታይ የሚችለው የአቋም ሽግሽግ የሚጠበቅ ኾኖ) ይህ ጽሑፍ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በአባላቱ ዘንድ የሚታየውን አሰላለፍ/አቅዋም እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፡፡
1) ለፓትርያሪክ ምርጫው የዕርቀ ሰላሙን ውጤት መጠበቅ አያስፈልገንም፤ የዕርቀ ሰላም ሂደቱ ከፓትርያሪክ ምርጫው ጎን ለጎን ሊካሄድ ይችላል፤
  • ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል (በአሁኑ ወቅት ለፓትርያሪክ ምርጫው ቅድሚያ ሰጥቶ ከመሥራት አኳያ በግልጽም በስውርም ከሚከናወኑት ተግባራት ሁሉ ጋራ ተያይዞ ስማቸው የሚነሣ አባት ናቸው፤ ‹‹ባለራእይና ዘመናዊ አባት ናቸው›› የሚሏቸው ቀራቢዎቻቸው ፍላጎት እንደሌላቸው ቢናገሩም ሌሎች ወገኖች በቢሯቸው አካባቢ የሚታየውን የብዙዎች ወጣ ገባ ማለትና በተለያዩ መድረኰች የሚያደርጓቸውን ንቁ ተሳትፎ በማገናዘብ የምርጫ ዘመቻ መሰል ነገር መጀመራቸውን ይናገራሉ)
  • ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
    ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
  • ብፁዕ አቡነ አብርሃም (የሰላም ድርድሩ/ንግግሩ ከፓትርያሪክ ምርጫው ጋራ ግንኙነት የለውም፤ ሁለቱ አቋሞች አይጫረቱም/አይነጻጸሩም/፤ ድርድራችንም ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋራ ብቻ መኾን ይገባዋል በሚለው አቋማቸው እና በሰላምና አንድነት ጉባኤው ላይ በሚሰነዝሯቸው ሒሶች ይታወቃሉ)
  • ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ (ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ የሚሉ አባቶችን በሃይለ ቃል በማሸማቀቅና ከምርጫው አኳያ የሚከናወኑ ተግባራት እንዲፋጠኑ እየሠሩ ናቸው፤ ለረጅም ጊዜ በቆዩበት ሀገረ ስብከት አጥጋቢ ተግባር ባለማከናወናቸው ብቻ ሳይኾን በችግሮች አፈታታቸው የሚተቿቸው ቀራቢዎቻቸው ለፓትርያሪክነት በዕጩነት እንደሚቀርቡ ከዚህም በላይ ቀጣዩ ፓትርያሪክ ሊኾኑ እንደሚችሉ በመስማታቸው ብቻ እንኳ ይሣቀቃሉ)
  • ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ (በአስመራጭ ኮሚቴው አባላት አሠያየም ዋነኛ ሚና ተጫውተዋል)
  • ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ (ዕርቀ ሰላሙ ሢመተ ጵጵስናቸውን ጥያቄ ውስጥ እንዳያያስገባው ይሰጋሉ)
  • ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ
  • ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ
  • ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም
  • ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ (አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን እንዲጀምር ማሳሰቢያ የተሰጠበትን ደብዳቤ የፈረሙ፣ ከሰሞኑም የ6ው ፓትርያሪክ ምርጫ በአጭር ጊዜ እንዲካሄድ እየተደረገ ለሚገኘው እንቅስቃሴ አስተዳደራዊ ድጋፍ እየሰጡ የሚገኙ ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ (ቀደም ባሉት ዓመታት ለአራተኛው ፓትርያሪክ በጻፉት ደብዳቤ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ሲባል ‹‹ብዙ ነገር እንዲታገሡ›› ተማፅነዋቸው ነበር፡፡ አሁን በያዙት አቋም ደግሞ የውጭዎቹን አባቶች ‹‹ሰላም አይፈልጉም፤ ፖሊቲከኞች ናቸው፤ ወደ ምርጫው እንግባ›› የሚል አቋም ይዘዋል፤ ኾኖም በአስመራጭ ኮሚቴ አባልነታቸው ላይ ያላቸው አቋም ብዙም አስተማማኝ አይደለም፡፡)
2) ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት የዕርቀ ሰላሙን ፍጻሜ ማየት፣ ውጤቱን መጠበቅ፣ ለውጤታማነቱም መሥራት ይገባናል፡፡ አጋጣሚው ካለፈው ተምረንና በታሪክ ማኅደር አስቀምጠን ለዘመናችንና ለቀጣዩ ትውልድ በአስተዳደር የተከፋፈለች ሳይኾን አንዲት ቤተ ክርስቲያንን የምናስረክብበት ነው፡፡ ይህን ሳናደርግ ወደ ፓትርያሪክ ምርጫ የምንገባውና ፓትርያሪክ የምንሾመው ለማን ነው? የቤተ ክርስቲያን መከፋፈል የከፋ ይኾናል፤
  • ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ (በአሜሪካ ተልእኳቸው የሰላምና አንድነት ጉባኤውን መግለጫ በመቃወም በዕርቀ ሰላም ልኡካኑ መካከል‹‹የተቃውሞ መግለጫ እንስጥ፤ የለም! አገር ቤት እስክንገባ እንቆይ›› የሚል ክርክር በተነሣበት ወቅት በንቡረ እድ ኤልያስ የተሞከረውን የዕርቀ ሰላም ልኡካኑን በአቋም የመከፋፈል ተንኰል በመቋቋም የልኡኩን አንድነት ያስጠበቁ ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ (ከዕርቀ ሰላም ልኡካኑ አባላት መካከል በልዩ ኹኔታ ጫና እየተደረገባቸው የሚገኙ፣ በዛሬው የአስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባም ሕመማቸው እስኪቀሰቀስ ድረስ አበክረው ለዕርቀ ሰላሙ ሲናገሩ የዋሉ ናቸው)
    አቡነ ቀውስጦስ
    አቡነ ቀውስጦስ
  • ብፁዕ አቡነ ገሪማ (ለዕርቀ ሰላም ጉባኤው ወደ አሜሪካ ተልከው አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን በዚያው ኾነው በሰሙ ጊዜ እንባቸውን ማፍሰሳቸው ይነገራል)
  • ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ (‹‹የላኳቸው ሳይመለሱ በመልእክቱ ላይ አልወስንም›› በሚለው ዝነኛ ንግግራቸው አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን የተቃወሙ፣ የኮሚቴው አባል ኾነው መምረጣቸውንም ያልተቀበሉ አባት ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘኢየሩሳሌም (በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት እያሉ ዕርቀ ሰላምን አስመልክቶ ለአቡነ ጳውሎስ ደብዳቤ የጻፉ፣ ከዕርቀ ሰላም ሐሳብ አመንጪዎች መካከል ስማቸው የሚጠቀስ አባት ናቸው፡፡ ለፓትርያሪክ ምርጫው በዕጩነት እንዲቀርቡ –በቀጥተኛ አነጋገር ቀጣዩ ፓትርያሪክ እንዲኾኑ – የመንግሥትና እንደ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ያሉት አባቶች ግልጽ ድጋፍ ያላቸው ቢኾኑም ስለእርሳቸው አቋም በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፤ ሌሎች አባቶች ብፁዕነታቸው አሜሪካዊ ዜግነት መያዛቸውንና ዕድሜያቸውን በመጥቀስ – በአንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 4 ከ50 ያላነሰ ከ70 ያልበለጠ ስለሚል – ዕጩነታቸውን ይቃወማሉ)
  • ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ (በዕርቀ ሰላሙ ላይ ግልጽ አቋም እንዲያዝ ያሳሰቡ ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ (‹‹እግዚአብሔርን ዕድሜ እለምነዋለኹ፣ ቤተ ክርስቲያን አንድ ኾና እስከማይ፤ ከዚያ በኋላ መኖርን አልሻም›› በሚል ተምኔታቸው ይታወቃሉ፡፡
  • ብፁዕ አቡነ ሉቃስ (‹‹ለዘመኑና ለተከታዩ ትውልድ የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን አናወርስም፤ ሰላምን ለማምጣት መታገሥ ይገባናል›› በሚለው ንግግራቸው ይታወቃሉ፡፡ በታኅሣሡ ስብሰባ የዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜ ሳይታይ የአስመራጭ ኮሚቴውን መሠየም ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ጋራ በጽኑ ተቃውመዋል፤ በመጨረሻም ከስብሰባው ሂደት ራሳቸውን አግልለዋል፤ በዚህም ሳቢያ በአንዳንድ ጳጳሳት በግልጽ ተዘልፈዋል)
     ብፁዕ አቡነ ሉቃስ
    ብፁዕ አቡነ ሉቃስ
  • ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ (ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ ይሰጥ በሚለው አቋማቸው አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን ተቃውመዋል፤ በአባልነት መመረጣቸውንም አልተቀበሉትም)
  • ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል (በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነታቸው ባላቸው ሓላፊነት ዕርቀ ሰላሙ ከፓትርያሪክ ምርጫው በትይዩ/በተጓዳኝ እንደሚካሄድ ቢገልጹም በታኅሣሡ ስብሰባ የዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜና ውጤት ዕድል እንዲሰጠው፣ በአንድነትም ወደ ምርጫው እንዲገባ ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ ጋራ በጽኑ ተከራክረዋል፤ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን በግልጽ ተቃውመዋል)
  • ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ (ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት የዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜ እንዲታይ፣ ምርጫው በተረጋጋ መንፈስና በአንድነት ለቤተ ክርስቲያን የሚኾናትን ደገኛ አባት በመምረጥ እንዲካሄድ የሚያሳስቡ አባት ናቸው፤ ከዚህ በቀር ‹‹አላሿሹምም›› በሚለው አነጋገራቸው የሚታወቁ ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (በውጭ ያሉት አባቶች ለፓትርያሪክ ምርጫው የሚያስፈልጉ በመኾኑ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ መስጠት፣ ውጤቱን መጠበቅና ለውጤቱም መሥራት እንደሚገባ ያሳሰቡ፣ ወትዋቾችን የገሠጹና ያባረሩ አባት ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ዳንኤል (በውጭ ያሉት አባቶች ለፓትርያሪክ ምርጫው የሚያስፈልጉ በመኾኑ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ መስጠት፣ ውጤቱን መጠበቅና ለውጤቱም መሥራት እንደሚገባ ያሳሰቡ፣ ወትዋቾችንና የሥልጣን ጥመኞችን ጭምር የገሠጹ ‹እንጃልህ› ያሉ አባት ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል (የቅ/ሲኖዶሱ አስመራጭ ኮሚቴ የመሠየም አጀንዳ ያልተመከረበት መኾኑን፣ ኮሚቴው እንዲሠየም መወሰኑም የዕርቅና ሰላም ጉባኤውን ሂደት የሚያስተጓጉል በመኾኑ ከተጨማሪ ርምጃ መቆጠብ እንደሚገባ በሚዲያ በግልጽ አሳስበዋል)
  • ብፁዕ አቡነ ቶማስ (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ የሚለውን አቋም በግልጽ የሚያስተጋቡ አባት ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ
  • ብፁዕ አቡነ ኄኖክ
  • ብፁዕ አቡነ እንድርያስ
3) አቋማቸው ለጊዜው አልተገለጸም፤ አይታወቅም፡፡ በስብሰባዎች ላይም በተሳትፎ ብዙም አይታወቁም፡፡ ከሁለቱ አቋሞች ወደ አንዱ በተለይም ለዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜ ቅድሚያ ከመስጠት አኳያ አቋም እንደሚይዙ ወይም አቋማቸውን ግልጽ እንደሚያደርጉ ተስፋ ይደረጋል፡፡
  • ብፁዕ አቡነ ስምዖን
  • ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ (ከአኗኗራቸው፣ ከልምዳቸውና ከትምህርት ዝግጅታቸው አኳያ በቀጣዩ ፓትርያሪክ ምርጫ በዕጩነት እንደሚታሰቡ ይነገርላቸዋል)
  • ብፁዕ አቡነ ዮናስ
  • ብፁዕ አቡነ ያሬድ
  • ብፁዕ አቡነ ሰላማ
  • ብፁዕ አቡነ ኤልያስ
  • ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ
  • ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም
  • ብፁዕ አቡነ በርቶሎሜዎስ
  • ብፁዕ አቡነ ማርቆስ
  • ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘካናዳ
maleda times | January 15, 2013 at 2:32 pm | Categories: AMHARIC NEWS | URL: http://wp.me/p2gxmh-1ky
Comment  

          

No comments:

Post a Comment