Saturday, December 22, 2012

ሰበር ዜና – መንግሥት የፓትርያሪክ ምርጫውን የሚከታተል ባለሥልጣን መደበ

ሐራ ዘተዋሕዶ
  • ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ የመንግሥቱን ባለሥልጣን በግልጽ ተቃውመውታል
  • የአስመራጭ ኮሚቴውን መቋቋም የተቃወሙ አባቶች በከባድ ጫና ሥር ወድቀዋል
  • የኮሚቴው አባል አቡነ ቄርሎስ ‹‹አልሠራም፤ አላምንበትም›› በሚል ራሳቸውን አግልለዋል
  • የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ አቡነ ሕዝቅኤል ‹‹መግለጫ አልሰጥም›› በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል
  • ምእመኑ ተቃውሞውን በየአጥቢያው እንዲጀምር ጥሪ ተላልፏል
ከቀን ወደ ቀን፣ ጥቂት በጥቂት ከቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አመራር ለሰላምና አንድነት ጥያቄው የማይናወጥ ድጋፍ ከመስጠት አልፈው አቋማቸውን በግልጽ መናገር የጀመሩ ብፁዓን አባቶች እየጨመሩ ነው፡፡ የሰላም አምላክ ከአቋማቸው አያናውጽብን፤ አንደበታቸውን አይለውጥብን ! ! !
በቀዳሚው ዘገባዎቻችን የጠቀስናቸው ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በአቋማቸው እንደ ጸኑ ከመኾናቸውም ባሻገር በትላንትናው ምሽት ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የዕርቀ ሰላም ልኡኩን በመወከል በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ያስተላለፉትን የጋራ አቋም እንደሚደግፉ አስታውቀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ÷ ‹‹የላክናቸው ሳይመለሱ በመልእክቱ (በላክንበት ጉዳይ ላይ) ውሳኔ አናሳልፍ›› እያሉ ቢሟገቱም ተንኮል በተሞላበት ስሌት የአስመራጭ ኮሚቴው አባል ተደርገው መመረጣቸው አስገራሚ ነበር፡፡ በዛሬው ዕለት እኚህ አንጋፋ ብፁዕ አባት÷ ‹‹በሂደቱ አላምንበትም፤ በኮሚቴውም አልሠራም›› በማለት ግልጽ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኮሚቴው መቋቋም ውሳኔ በተላለፈበት የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ላይ፣‹‹የልዩነት ሐሳቤ በቃለ ጉባኤ ይስፈር›› ያሉት ብፁዕነታቸው የኮሚቴው አባል ኾነው የተመረጡበትን ደብዳቤም ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልኾኑና እንዳልተቀበሉም ተዘግቧል፡፡ ሌሎቹ አባላትስ ይከተሏቸው ይኾን?
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ
ሰውን እንደ ጊዜ ግብሩ ማመስገን የተገባ ነው፡፡ በሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲ እና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ትላንት ምሽት ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ እንደተናገሩት÷ በጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ የተወሰነው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ ረቂቅ አቅርቦ ለመወያየትና ለማጸደቅ እንጂ የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ለማቋቋም አይደለም፡፡ ‹‹ውሳኔው አዲስ ሐሳብ ነው፤ የዕርቁን ሂደት እንዳያበላሸው፣ እንዳያሰናክለው ስጋት አለኝ፤›› ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሰፋ ያለ ሥራ ከማከናወን እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡
አሁንም እንላለን÷ ሰውን እንደ ጊዜ ግብሩ ማመስገን መልካም ነው፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው በተቋቋመበት ዕለት ‹‹ከአስመራጭ ኮሚቴው በፊት ዕርቁ ይቅደም፤ የጥሩን የሎሳንጀለስ የሰላም ጉባኤ ውጤት እንጠብቅ›› በማለት ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ እና ከብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ጋራ ምልአተ ጉባኤውን ሲሞግቱ የዋሉት የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ሌላው የሰላም አርበኛ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው ቅዱስ ሲኖዶሱ አስመራጭ ኮሚቴ በማቋቋም ያስተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ለብዙኀን መገናኛ መግለጫ እንዲሰጡ የተላለፈላቸውን ትእዛዝ አልቀበልም ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለት መንግሥት በይፋ በመደበው አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጭምር ቢታዘዙም፣ ከማዘዝም አልፎ ቢያስፈራሯቸውም ብፁዕነታቸው÷‹‹ምልአተ ጉባኤው ተሰብስቦ መግለጫ ስጥ ሲለኝ እንጂ አንተ ስላልኸኝ አልሰጥም›› በማለት የጽናታቸውን ልክና ዳርቻ አሳይተዋል፡፡ ግና÷ ማግባባቱ፣ ጫናው ዛሬ ቀን ተመድበው ከመጡት ባለሥልጣን ከፍ ያለ ሥልጣን ባላቸው ሌላ ባለሥልጣንም ይቀጥላል በመባሉና ብፁዕነታቸውን በዚያው ባሉበት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ይኹን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ውጭ ወደ መንግሥት አካል ተጠርተው ከግራ ከቀኝ የማጨናነቁ ዘመቻ በመቀጠሉ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሲሉ በወሰዱት አቋም ጽናትን እንዲሰጣቸው እንለምንላቸዋለን፡፡
መንግሥት ‹‹ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ›› በሚል ከፍተኛ ባለሥልጣኑን የመደበው ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው፡፡ ባለሥልጣኑ አቶ ትእዛዙ ደሳለኝ የሚባሉ ሲኾኑ የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ይኹንና አቶ ትእዛዙ በዛሬው የመንበረ ፓትርያሪክ ውሏቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ለማግባባት ያደረጉት ጥረት የሠመረላቸው አይመስልም፤ ‹‹ዕርቀ ሰላሙ በምርጫው ሂደት አይሰናከልም፤ ወደፊትም ሊካሄድ የሚችል ነው፤›› ቢሉም የሰማቸው ባለመኖሩ ይህንኑ ለበላይ አካል አስታውቀዋል ተብሏል፡፡ የእርሳቸውን ሪፖርት ተከትሎ ከእርሳቸው ከፍ ያሉ ባለሥልጣን በአቋማቸው የጸኑትን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዛሬውኑ ማምሻውን ወይ ባሉበት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አልያም ወደ ውጭ አስጠርቶ የማወያየት፣ የማስፈራራት፣ የማስጠንቀቅ አካሄድ ሳይኖር እንደማይቀር ተገምቷል፡፡
የመንግሥትን ፍላጎት÷ በ‹‹ፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ››፣ በዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ምክንያት የለሽ አመጣጥ፣ ከዚያም በኋላ የዕጣውን አሠራር በምርጫ ሥርዐት ባስቀየሩት የተደራጁ ሊቃነ ጳጳሳት ቡድናዊ ቅስቀሳ፣ በቀጭኗ ሽቦ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስ እንዲተላለፍ በተደረገ ትእዛዝ ዐቃቤ መንበሩ በሌሉበት የፓትርያሪክ ምርጫ ሕጉን አቻኩሎ በማስፈረምና በማጽደቅ አስመራጭ ኮሚቴው በተፋጠነ ኹኔታ እንዲሠየም ባደረጉት ‹‹ተኳሽና አስተኳሽ›› ጳጳሳት ስልታዊ ዘመቻ አይተናልና፤ አረጋግጠናልና አያስገርምም፤ አያስደነቅም፡፡ አስገራሚው፣ አስደማሚው ጉዳይ ለእኚህ ባለሥልጣን÷ ‹‹መረጃ በመስጠት ያግዛሉ፤ ከአባቶች ጋራ ያቀራርባሉ፤›› በሚል የተመደቡት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች እና የማኅበረ ቅዱሳን ተወካዮች ነገረ ሥራ ነው፤ በተለይ የ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› ተብዬዎቹ ጥቂት ‹መለካውያን› አመራሮች ! ! !
‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም፤ ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› በሚለው መልእክቶቹ እና ርእሰ አንቀጾቹ የምናውቀው የማኅበረ ቅዱሳን ጥቂት አመራር÷ ‹‹ቅድሚያ ለምርጫው›› በማለት የወሰደው የአቋም ለውጥ ‹‹ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማስፈጸም›› በሚል በተመደቡት የመንግሥት ባለሥልጣን ዘንድ ሳይቀር ክፉኛ ትዝብት ውስጥ ጥሎታል፤ ‹‹በጳጳሳት ላይ እንዴት ቁማር ይጫወታል !!›› ያሉት አቶ ትእዛዙ÷ ‹‹ዕርቁ ይቅደም እያለ እንዴት ደግሞ ከመንግሥት ጋራ ይሠራል›› እያሉ ሲያሙት መደመጣቸው ተነግሯል፡፡ ሌላው የአስመራጭ ኮሚቴው አባል ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስም በአቋማቸው ስለጸኑት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለተመደቡት የመንግሥት ባለሥልጣን ሲናገሩ ‹‹እኛ ሥራችንን በአግባቡ እየሠራን ነው፤ የሚያስቸግሩኝ ማኅበረ ቅዱሳን በገንዘብ የገዛቸው ጳጳሳት ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
አጀብ ነው!! አቡነ ጢሞቴዎስን እንዲህ ያናገራቸው ምርጫውን ለማስፈጸም ያላቸው ችኮላና ዝንባሌ (ጽነት) ይኾናል፡፡ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንና ምቀኛ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ ደስ አይበላቸውና ማኅበሩስ በገንዘብ የሚገዛቸው ጳጳሳት የሉም፤ አልነበሩም፤ አይኖሩም፤ በገንዘብ የሚገዙ ጳጳሳትም ሊኖሩ አይገባም፡፡ ነገር ግን÷ ነገር ግን በማኅበሩ ጥቂት አመራሮች ውሳኔ በተደረሰበት ውሳኔአቋሙ እንዲህ ‹‹180 ዲግሪ ይታጠፋል›› ብለው የገመቱ ብፁዓን አባቶች አልነበሩምና ለተነበበባቸው ስሜት ‹‹አዘኑ›› የሚለው ቃል አይገልጸውም፡፡ በጭራሽ ! ! !
ብፁዓን አባቶች የማኅበሩን ብዙኀን አመራርና አስፈጻሚ እንዲሁም መላውን አባላት በማይወክለው በጥቂት አመራሮች ‹መለካዊነት› በተላለፈው ውሳኔ ቢያዝኑም ርእዩን፣ ተልእኮውንና ዓላማውን በቅጡ ያውቃሉና፣ በየአህጉረ ስብከታቸው ገና ታሪክ ለትውልድ የሚዘክራቸውን አያሌ ገድሎች የፈጸሙትንና በመፈጸም ላይ የሚገኙትን አባሎቹን አይዘነጉምና በ‹መለካውያኑ› አመራሮች ተስፋ ይቆርጣሉ ተብሎ አይታመንም፡፡
እነኾ÷ በሀገር ውስጥም በባሕር ማዶ የሚገኙ አባላቱ ለመላው ምእመን በተላለፈው ጥሪ መሠረት ‹‹ከኮምፒውተር ጀርባ›› እና በስልክ በሚደረግ የኢንተርኔት ተቃውሞ መልክ ለመስጠት በመጪው እሑድ፣ ቅዳሴ ካለቀ በኋላ በየአጥቢያቸው እንደሚሰበሰቡ፣ ሐዘናቸውንና መከፋታቸውን እንዲሁም በውሳኔው ማዘናቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንደሚገልጹ ይጠበቃል። ከወዲሁም በስልክና በአካል እየተገኘ ብስጭቱን ለሚቀርባቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በመግለጽ ላይ የሚገኘው አገልጋይና ምእመን ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡
‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› በሚለው አቋማቸው ከፊት መሥመር ከተሰለፉት ብፁዓን አባቶች አንዱ የተናገሩትም ምእመኑ በፌስቡክና በጡመራ መድረኮች እያሳየው ለሚገኘው የመንፈስና የተግባር ተናሥኦት ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ ነው – ‹‹ከዕርቀ ሰላሙ በፊት አስመራጭ ኮሚቴው መቋቋሙን አንደግፍም የሚል የምእመኑ ፔቲሽን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መምጣት አለበት፤ እኛ ደግሞ እርሱን በሥራ አስፈጻሚው ላይ አቅርበን እናየዋለን፡፡››
ለሁሉም ግን የተቃውሞ መግለጫውንና የጥያቄ ማቅረቢያውን እንቅስቃሴ በሓላፊነት የሚያስተባብር፣ እኔ ባይና ተጠያቂ የአደባባይ አካል ቢቋቋም የሚል ምክርም አለና ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ ከጡመራ መድረኮችና ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ባሻገር በማንኛውም ደረጃ ሊቋቋም የሚችለው ይህ አካል አሁን በተለያየ መንገድ የተጀመረው ቅስቀሳ በሚገባ ወደ አገልጋዩና ምእመኑ እንዲዘልቅ፣ የቅስቀሳ መልእክቱ ወደ አገልጋዩና ምእመኑ ከዘለቀ በኋላም የሚጨበጥ የተደራጀ ኀይል ኾኖ ተፈላጊውን በጎና ጠንካራ ተጽዕኖ በከፍተኛ አመራሩ ላይ ለማሳደር እንደሚያስችል ይታመናል፡፡ ይታሰብበት ! ! !
በእሑድ ሰንበት የመጀመሪያ ቀን መሰባሰባችን÷ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት የሚያፋጥን፣ ቤተ ክርስቲያን ከፓርቲ አባላትና ከመንግሥት አላስፈላጊ ተጽዕኖ ነጻ እንድትወጣ፣ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸመው ሁሉ ምእመናንና ካህናትን የሚያሳምን፣ የሚያሳትፍ እንዲኾን እንጠይቅ፤ እንወያይ፤ አቋም እንያዝ፤ እንጸልይ ! ! !
staff reporter | December 21, 2012 at 2:51 pm | Categories: AMHARIC NEWS | URL: http://wp.me/p2gxmh-1ep

No comments:

Post a Comment