Thursday, December 13, 2012

የግፍ ጽዋ ሞልቶ ሲፈስ


 

ዓለማችን ላይ በዘመናት ብዙ ጥሩ እና መጥፎ መሪዎች ተነስተው አልፈዋል። እንደ ሂትለር፣ሙሶሊኒ፤ ኢዲ አሚን፤ ቢን ላደን የመሳሰሉት በመላው ዓለም ላይ የሚታወቁት በጨካኝነታቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰዎችን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ በማጥፋታቸው ነው። ለምሳሌ አብዛኛው የጀርመን ሕዝብ ሂትለርንም ሆነ በሱ ዘመን የነበሩ ባለሥልጣኖች ምንም የሠሩት ጥሩ ነገር እንኳ ቢኖር፤ በሠሩት ሥራ ስለሚያፍሩ ስለ እነርሱ ማውራትም ሆነ ምንም እንዲነገር አይፈልጉም። በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ ሥራ በመሥራታቸው እንደ እነ ማሕተመ ጋንዲ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ኬኔዲ የመሳሰሉት ስማቸው ከሀገራቸው አልፎ በመላው ዓለም ላይ እስከዛሬ ድረስ ተደጋግሞ ይነሳል።
መቸም በሁሉም ዘመን የሚነሱ መሪዎች ጥሩም መጥፎም ሠርተው እንደሚያልፉ የታወቀ ነው። ነገር ግን መታየት ያለበት በሥልጣን ዘመናቸው ከፈፀሙት ጥሩው ወይስ መጥፎው ይበዛል ተብሎ መገምገም ይኖርበታል። ከዐፄ ኃ/ሥላሴ ጀምሮ እንኳ ሀገሪቱን የመሩትን ስናይ፤ ለንጉሡ ከሥልጣን መውደቅ መነሻ የሆነው የኑሮ ውድነት፣ የሀገሪቷ ወደ ኋላ መቅረት፣ በመጨረሻም የወሎ ድርቅ ነበር። ታዲያ በዚያ ለውጥ ሰሞን ዐፄ ኃ/ሥላሴ ፈሪሀ እግዚአብሔር ስለነበራቸው የተሰለፈ ሁሉ ይታሰር፣ ይጨፍጨፍ፣ይገደል አላሉም። ሌላው ቢቀር ከየክፍለ ጦሩ ተወክለው የመጡትን በኋላም ደርግ ተብለው የዘውዱን አገዛዝ ገልብጠው ሥልጣኑን የወሰዱትን ወታደሮች መጥፎ ዓላማ አስቀድመው ያወቁት አንዳንድ
ሚኒስትሮቻቸው እርምጃ እንዲወሰድ ቢጠይቁም ንጉሡ አልፈለጉም። ንጉሡ ምክሩን ተቀብለው ቢሆን ኖሮ ምናልባት አሁን የደረስንበት ሁኔታ ላይ ባልደረስን ነበር። ነገር ግን እሳቸውን ከሥልጣን አውርደው ለሰፊው ሕዝብ ነው የመጣንልህ ያሉት ወታደሮች ብዙም ሳይቆዩ ከንጉሡ አንስቶ ለሀገራችን ትልልቅ ሥራ የሠሩ ባለሥልጣናትን በአንዲት ምሽት ከገደሉ በኋላ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በቀይ ሽብር ስም ፈጅተዋል። በደርግ ጊዜ ብዙ ሥራ የተሠራ ቢሆንም ገና ሥልጣን በኃይል ከያዙበት ቀን አንስቶ የገደሉት የሰው ብዛት፣ ከየመንገዱ ታፍሶ እና ተወስዶ ወንበዴዎችንና ሱማሌን ሲዋጉ የረገፉት ወገኖቻችን፣ እንዲሁም ደርግ የ10ኛውን ኢሠፓ ምስረታ ለማክበር በሚጥበት ወቅት በቸልተኝነት በሚልዮን
የሚቆጠር ዜጎች በረሃብ ሲረግፉ ፤ የእነዚህ ወገኖች ሁሉ ደም ጩኽት ከመቃብር ዓለም ሆኖ ሲያስተጋባና እንዲሁም እነዚያን የወለዱ እናቶችና አባቶች ዕንባ ከመንበረ ጸባዖት ሲደርስ፤ የግፍ ጽዋ ሲሞላ፤ እነዚህ የተናቁ ወንበዴዎች ነገር ግን እነሱ እንዳሉት <<ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ>> ብለው በራሳቸው እንደተመኩት ሳይሆን፤ ማንም አይነቀንቀኝም፣ ግማሽ ሚሊዮን ጦር አለኝ ብሎ የተመካው ደርግ ብትንትኑ ወጥቶ ወያኔዎች ሥልጣኑን ለመያዝ ችለዋል።
2
ወያኔና አቶ መለስ
የትግራይ አርነት ነፃ አውጭ ግንባር ከኤርትራ ወንበዴዎች ጋር በመተባበር ደርግን ጥለው ሀገሪቱን ሲቆጣጣሩ በተረጋጋ ሁኔታ እየመራን እንቆያለን ብለው ስላልተማመኑ ይመስላል፤ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ያካሄዱት ንብረትና ቁሳቁሶችን ከመሐል ሀገር ወደ ሰሜን ማሻገር ነበር። ለዚህም ነበር በእነዚያ መጀመሪያ ዓመታት አንዲት የቡና ፍሬ ምድ የማያበቅለው ኤርትራ፤ በዓለም ላይ ቡና በብዛት ከሚልኩ ሀገሮች አንዷ ለመሆን የበቃችው። እነዚህ ምንም ዓይነት ይሉኝታ የሌላቸው ፍጥረቶች ከንብረት መዝረፍና ማሸሽ ባሻገር ሌላው የሀገሪቱን ጎሣዎች ከምንም ቁጥር ባለማስገባት በእብሪት ሰውን ሲከፋፍሉ፣ ሲገድሉ፣ሲያሳድዱ ቆይተው በመጨረሻም በወያኔዎችና በኤርትራ መካከል ግጭት ተፈጥሮ ከሰባ ሺህ በላይ የሚሆኑ
ዜጎች ሕይወታቸው ሊጠፋ ችሏል። የወያኔ መንግሥት ደርግን ገልብጦ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሰው በደል እና ለቀጣይ ዘመናት የጣለው ጠንቅ መለኪያ የሌለው ነው። ከጫካ ይዘው የመጡትን በዘር የተመሠረተ አስተዳደርና የብቀላ መንፈስ እስከ አሁን ለ21 ዓመታት እያካሄዱት ነው። እነዚህ ዘረኛ ወያኔዎች ከዚህ ቀደም ከተነሱ መሪዎች የተለዩ በተንኮልና በጭካኔ ተወዳዳሪ የሌላቸው ናቸው። እነዚህ በጎጠኝነት ስሜት የታወሩ የዘሩት የዘር ክፍፍል መርዛምነቱ ሁሉን በክሎ ብዙ ሰው በወጥመዱ ውስጥ ጥሏል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲመራው የሚፈልገው ከየትኛውም ጎሣ ይሁን ብቻ ሀገሩን የሚወድ፣ ሕዝቡን የማይንቅ፣የማይበድል ነው።
ወያኔ ይህ መርዛም አመራሩን እንዲሁም የትግራይ ዘር አገዛዝን በሀገሪቱ ላይ የበለጠ ለማጠንከር ካወጣው ዘዴ አንዱ ቤተ ክርስቲያንን ተጠቅሞ ዓላማውን ማስፋፋትና ራሷንም ማዳከም ስለሆነ በወቅቱ የነበሩትን ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ደርግ የሾማቸው በትክክለኛው መንገድ አይደለም እያስባለ አሳድሞ፤ አቡነ መርቆሬዎስን ከሥልጣን እንዲወርዱ ካደረገ በኋላ፤ አቡነ ጳውሎስን ወደ አዲስ አበባ አምጥቶ ፓትርያርክ እንዲሆኑ አደረገ። ይህን የታዘቡት አለቃ አያሌው ነፍሳቸውን ይማረውና በአንድ ክብረ በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እናንት የአሁኑ ገዥዎች <<እግዚአብሔር ትዝብት ላይ ሊጥላችሁ ቤተ መንግሥቱንና ቤተ ክህነቱን ሰጥቷችኋል>> ነበር ያሉት። ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ውስጥ
የመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት በተለይ ሀገር ከለማበት ይልቅ የወደመበትና ብዙ ግፍ የተሠራበት ነው።
በመቀጠልም የሚከተለው ትውልድ በቀላሉ ከፍሎ የማይጨርሰው ገንዘብ በመበደር እንዲሁም በዕርዳታ በተገኘ ገንዘብ ህንፃዎች ተገንብተዋል፤ መንገዶች ተሠርተዋል። የኑሮ ውድነትም ከሀገሪቱ ኤኮኖሚ አኳያ ከመቸውም በላይ ንል። ለስሙ የተለያየ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ ይባል እንጂ፤ ሀገሪቷ የምትመራው በአንድ ወያኔ ፓርቲ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በአለፈው ምርጫ በዓለም ላይ ሆኖ የማያውቅ 99% ድምፅ በማግኘት ወያኔ ማሸነፉን እናስታውሳለን። በ1997 ምርጫ ጊዜም ሕዝቡ ቅንጅትን ደግፎ በወጣ ጊዜ ወያኔ የወሰደውን ጨካኝ እርምጃ ስላየ፤ ለውጥ ለማምጣት ለመታገል ቅስሙ ስለተሰበረ፤ ወደ እግዚአብሔር ዞሮ ከዚህ አውጣን እያለ ሲማፀን ከመኖር ሌላ አማራጭ አልነበረውም።
የሆነ ሆኖ እነዚህ ሁለት ሰዎች (አባ ጳውሎስና አቶ መለስ) በየፊናቸው ሕዝብን ሲያሳዝኑ፣ ሲያስለቅሱ፣ከሥራ ሲያፈናቅሉ፣ ሲያስርቡ፣ ሲያስጠሙ፣ ሲገድሉ፣ በዘር ሲከፋፍሉ ከ20 ዓመታት በላይ ቆይተው፤በመጨረሻ አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል እንደሚባለው ከዓለም ተገልለው፣ ርቀው ከሚኖሩት የዋልድባ አባቶች ጋር መጣላት ደረጃ ደረሱ። እነዚህንም አባቶች ከመዝለፍ አልፈው አለምንም በደል ይዘው፣አስረው ሲያንገላቱ፤ ባህታውያኑም የኢትዮጵያ አምላክ ሆይ እስከመቼ ዝም ትላለህ ብለው በጮኹ ጊዜ፤ ጸሎታቸው በውኑ ከመንበረ ጸባዖት የደረሰ ይመስላል እነዚህ ሁለት መሪዎች በተቀራራቢ ጊዜያት ሞቱ። የታላቁ የእግዚአብሔር የቁጣው ሰይፍ በእነዚህ ሰዎች ላይ ጥይት ሳይተኮስ በመጨረሻ ቀሰፋቸው።
ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ወደ ሌሎች የጸሎት ቤቶች ስንሄድ የጠየቅነው፤
አቤቱ እስከመቼ ዝም ትላለህ ከነዚህን ግፈኞች እጅ አታወጣንም ወይም አታስወግድልንም እንጂ ልባቸውን
አራራልን፤ አስተዋይ አእምሮን ስጣቸው ብለን አልነበረም። ነገር ግን ሁላችን ተስፋ በቆረጥን ጊዜና፤
የግፍ ጽዋ ሲሞላ፤ በራሱ ሰዓት የእርሱ ድንቅ ሥራ ይገለጥ ዘንድ፤ እንዲሁም ሕዝቡ እንዳይጎዳበት
አንድ ጥይት ሳይተኮስ ከላይ የነበሩትን ሁለቱ ሰዎች ከዚህ ዓለም አሰናበታቸው። የአምላካችን የቁጣ
ሰይፍ በዚህ ብቻ አይቆምም ነገር ግን ሌሎችም በዚህ ምስኪን ሕዝብ ላይ በደልና ግፍ የፈጸሙ ሁሉ ገና
ይቀጣሉ።
እነዚህን ሁሉት ሰዎች የሆነ ፓርቲ ተመስርቶ ወይም አንድ ሆድ የባሰው ያልታወቀ ሰው ተኩሶ
ቢገድላቸው ኖሮ፤ እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያው ጤዛ ነሽ እንደሚባለው ሕዝብን ለማሰቃየት ለመምታት
ተዘጋጅቶ የሚገኝው የደኅንነትና የመለስ አንጋቾች፤ ገዳዮቹን ለማግኘትና ለማጣራት ሲባል የሚታፈሰውና
የሚታሰረው ሰው ብዛት ምን ያህል እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ነገር ግን እግዚአብሔር ሁል ጊዜ
ሕዝቡ እንዳይጎዳ ስለሚፈልግ ነገሮችን የሚሠራበት የራሱ ጊዜ እና መንገድ አለው።
ባለፈው አቶ መለስ ሞተ በተባለ ሰሞን በየፌስ ቡክ እና ድኅረ ገጾች ላይ ሞቱን አስመልክቶ የሀዘንም፣
የሠራውን በደሎች እንዲሁም ደግሞ ዓይን ያወጡ የሙገሳ መልእክቶችን አንብበናል። የሀዘን መልእክት
አስመልክቶ ከመንገድ ተዳዳሪዎች አንስቶ እስከ ሴተኛ አዳሪዎች የሰጡትንም አስተያየት በቴሌቪዝን
ተመልክተናል፤ እንዲሁም መንግሥት ለድርጅቶች ሠራተኞች ለሐዘን እንዲወጡ ያስተላለፈውንም ጥብቅ
4
ትዕዛዞችን አንብበናል። ለሐዘን እንዲወጣ የተገደደው ሕዝብ ቢበዛም ሌሎች ደግሞ ሙት ወቃሽ መሆን
አያስፈልግም በማለት ከልብ ያዘኑ ሀገር ቤት ብቻ ሳይሆን በውጭ ያሉም አሳይተዋል። ታዲያ ላለፉት ሃያ
አንድ ዓመታት ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ከእነዚህ ሰው በላ ዘረኛ ወያኔዎች እባክህ ነፃ አውጣን ብሎ
ሲያለቅስ፣ ሲማፀን ኖሮ፤ በደል ሲፈጽም የነበረው መሪ ከላይ ሲመታ ጸሎታች ደረሰ ብሎ ምስጋና
ማቅረብ ሲገባው፤ ጭራሽ የደረሰበትን በደል ረስቶ ይሁን ወይም ተገዶ፤ እኔ ሞቼ እሱ በኖረ እና
ሌሎችም የመሳሰሉትን አስተያየቶች ስሰማ፤ የእሥራኤል ሕዝቦች ከግብጽ ምድር በሙሴ መሪነት
ያወጣቸውን አምላክ ረስተው የጥጃ ምስል አቁመው እየሰገዱ ጭራሹን የግብጽ ባርነት ይሻለናል ብለው
በማጉረምረማቸው ለዘመናት በበረሃ ሲንከራተቱ እንደኖሩ፤ እኛም ደግሞ መልሰን በዚህ ግፈኛና ዘረኛ
አስተዳዳር እንድንቀጥል የእግዚአብሔርን ቁጣ ሊያስከትል ይችል ይሆናል ብዬ ሰጋሁ። በርግጥ እነዚህ
ሰዎች ለሠሩት በደልና ግፍ ንሥሐ ሳይገቡ መጠራታቸው እጅግ አሳዛኝ ነው።
ማዘኑስ ይሁን ይባል፤ ግን ጥቂት ካየናቸው ፎቶግራፎች መካካል አንዳንዶች የሬሳው ሣጥን ከተቀመጠበት
ፊት ለፊት ሲሰግዱ ታይተዋል። ይህ ፍጹም አስፀያፊ፣ ቆሻሻ የሆነ ምግባር መወገዝ ያለበት ነው።
እንዲህ ዓይነት ርካሽ ባሕርይ የእግዚአብሔር ቁጣ የሚቀሰቅስ ነው። አንድ የፈላስፎች አባባል አለ
<<አንድ ሕዝብ የሚገባውን መሪ ያገኛል>> ይላሉ። ታዲያ አሁንም ይህ ሕዝብ ይህን የመሰለ መሪ
የለም፤ እሱ ያቀዳቸውን ከግቡ እናደርሳል፣ ወያኔ ይኑርልን የሚሉ አስተያየቶችን ስሰማ ይህ ሕዝብ
በእውኑ ጨካኝ አረመኔ መሪ ነው የሚወደው ወይስ DIMENTIA (የመርሳት በሽታ) እንደያዘው ሰው
ላላፉት ዓመታት የደረሰበትንና የተፈፀመውን በደል ረስቷል ማለት ነው ብዬ ራሴን ጠየኩት። በጣም
የሚገርመው ብዙዎች ራሳችንን ስለምንወድና ስለምንፈራ፤ ሀገራችንን ከእነዚህ የቀን ጅቦች ነፃ ለማውጣት
መታገል ሳይሆን፤ ሌሎች መስዋዕትነት ከፍለው ለውጥ እንዲያመጡልን የምንፈልግ ነን። ሌላው ቢቀር
እንኳ የሚታገሉትን በገንዘብም ይሁን በሞራል መደገፍ ሲጠበቅብን፤ ነገር ግን ሌሎች በአደባባይ ፊት
ለፊት መለስን የተቃወሙትን እንደ እነ አበበ ገላውን፣ ታማኝንና ሌሎችንም ፀረ ኢትዮጵያ እንደሆኑ
አድርገው ሲያወግዙና፣ ሲኮንኑ ማየት ምን ያህል፣ አሳፋሪና ይሉኝታ ቢሶች የሚያብል ነው።
አንዳንዶች የጎጠኝነት ስሜት የተፀናወታቸው ደግሞ አባይን የደፈረ ጀግና፣ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አፍሪቃ
ጭምር መሪ አጣች እያሉ ዓይናቸውን በጨው አጥበው መልሰው እኛኑ በዚህ በተረገመ ሰው ሥርዓት
ውስጥ ያለፍነውን ሰዎች ሊነግሩን፣ ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። አባይን ለመገንባት ጀማሪው የደርግ
መንግሥት ነው። ያንን ለማድረግ መጀመሪያ ያደረገው የባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ በመሥራት የአየር
ኃይልን ወደዚያ በማቋቋም ግብጽ በሱዳን በኩል ልትወር ብትፈልግ ከዚያ በቀላሉ ለማጥቃት ነበር።
ከዚያም በራሽያኖች የተሰራው እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ የሚመታ የሚሳየል ማወንጨፊያና
5
እንዲሁም የበለስ ፕሮጄክት ተብሎ ከኢጣሊያኖች ጋራ ሲሠራ የነበረው የእርሻ ልማት በኋላ ወያኔዎችና
ሻቢያ ሲገቡ ያወደሙት ለዚሁ ዓላማ ነበር። ይሁን እንጂ በመሀሉ የደርግ መንግሥት በመውደቁ
የታቀደው ከግቡ ሳይደርስ ቀረ። አሁን ግን የግብጽ አለመረጋጋት በፈጠረው አጋጣሚ፤ ግድቡ እንዲሠራ
መጀመሩ የሚያስመሰግን ቢሆንም ነገር ግን አባይን የደፈረ ተብሎ ተጋኖ መወራቱ አሳፋሪ ነው።
ሌላው ደግሞ ሁላችን እንደምናውቀው በአንድ ወቅት አቶ መለስ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ እምነት
እንደሌለው የተናገረው መሆኑ እየታወቀ፤ ነገር ግን ከዚህ ሰው ፎቶግራፍ ጎን <<እግዚአብሔር ሆይ
ኢትዮጵያ የሃይማኖት፣ የዘር፣ የብሄረሰቦች፣ የፍቅር ልዩነት እንዳይፈጠር አደራ ብያለሁኝ>> የሚል
ሳይ፤ ይህን የጻፉ ሰዎች ሕዝቡ እንደነሱ ቂል መስሏቸዋል ወይም ደግሞ ጸሐፊዎቹ የአእምሮ
ዝግምተኝነት አለባቸው ብሎ ለመናገር ያስደፍራል። ጭራሽ አንዳንዶች ደግሞ <<በሞተ ሰው የሚደሰት
ሰይጣን ብቻ ነው>> ብለው ስዕል መለጠፋቸውን አይተናል። እንደ ፈላስፎች አነጋገር ከሆነ <<ጓደኛህን
ንገረኝና ስለ አንተ እነግርሃለው>> ይላሉ። ይህ ማለት በሌላ አነጋገር ሰይጣናዊ ተግባር ሲፈፅም የኖረ
ሰውን የሚያደንቅ፣ የሚያመሰግንና የክፉን ሰው ሥራ ጥሩ አድርጎ የሚክብ፤ የሌሎችን ሥቃይ ካለምንም
የሚቆጥር ሰው ነው፤ የሰይጣን አሽክላ ተብሎ ሊጠራ የሚገባው። ሰው ጥሩ ላደረገ ሳይገደድ ዕንባውን
ያፈሳል ነገር ግን ብዙ ጭቆናና በደል ሲፈጽምበት ለኖረ መሪ ካላዘንክለት፣ ካላላቀስክለት ብሎ መናገር
ግን ለሌላ ሰው ሥቃይና መከራ ግድ የማይሰጠው፤ ልበ ደንዳና፣ አእምሮ ቢስ ተብሎ ሊጠራ ይገባዋል።
አንዳንዶች የጊዜው ጥቅመኞች አለምንም ይሉኝታ ለወያኔ ቋሚ ጠበቃ ቢሆኑ እና ቢከራከሩ አያስደንቅም።
ለምሳሌ ቀሲስ ቸርነት ኃ/ሥላሴ የተባለ የአቶ መለስን ሞት አስመልክቶ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ተገኝቶ ያደረገውን ንግግር ላየ የመጨረሻ አሳፋሪ ነው። ይህ ቄስ ስለ
አምባገነኑ መሪ ሲናገር << መለስ እውነት ነው፣ መለስ አባታችን አልሞተም፤ ጀግና ነው ለሀገሩ
አንድነት የታገለ ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችን ለእንዲህ ዓይነቱ ጀግና ነው መሸለም ያለባት ወዘተ>> እያለ
ሲደሰኩር ተደምጧል።
በመጀመሪያ የክርስትና እምነት በአጠቃላይ የሚያስተምረን፤ ሰዎች ስንባል ደካማዎች እንደሆንና
እንደምንሳሳት ነገር ግን በንስሐ ደግሞ ከሠራነው በደል ይቅር እንደምንባል ነው። ነገር ግን ምንም ስሕተት
የማይገኝበት ፍፁም የሆነው እውነት የተባለ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ ይህ ቄስ ነኝ ባይ ከየት
ያገኘውን ትምህርት ነው አፉን ሞልቶ አቶ መለስ እውነት ነው ብሎ ያስተማረው?
በሁለተኛ ደረጃ <<አቶ መለስ ለሀገሩ አንድነት የታገለ ነው>> ሲል የኤርትራ ሀገር እንድትገነጠል
እንዲሁም የአሰብ ወደብን አስረክቦ ኢትዮጵያ ያለ ወደብ ያስቀረ ማን ነው? በየትኛው ዘመነ መንግሥት
6
ነው ማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ራሱን በራሱ ችሎ መገንጠል ይችላል ተብሎ በሕገ መንግሥቱ
የሰፈረው?
ሦስተኛ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ላለ እምነት ለሌለው፣ የስንት ኢትዮጵያውያን ደም በእጁ ላለ፤ አልፎ
ተርፎ አብረውት ስንት ትግል ያሳለፉትን የገደለ (http://www.youtube.com/watch?v=Bao416_t3vs
እንዲሁም ከጅምሩ አንስቶ የቤተ ክርስቲያናችንን ሕልውናዋን ሊያጠፋ ለተነሳ አረመኔ አትሸልምም።
እንግዲህ ከዚህ ቄስ ባይ ነኝ ንግግር እንደምንረዳው ይህ ሰው ለእምነቱ የቆመ ሳይሆን ለወያኔ ያደረና
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክል እንደሆነ ነው። እንዲህ ዓይነት አስመሳይ ቄሶች የወያኔ ምልምል
ለመሆናቸውና ዓላማቸው ቤተ ክርስቲያናችንን ለማጥፋት እንደሆነ አረጋዊ በርሄ የጻፉትን ስናነብ፤
በእርግጥ ይህ አፈ ጮሌ ቄስ አንዱ ምልምል ዘረኛ ነው ብንል ስሕተት አይሆንም። ወያኔ ቤተ
ክርስቲያናችን ለማፍረስ ከሚጠቀምባቸው ዘዴ አንዱ እንዲህ ዓይነት መርዘኛ የሆኑ እምነተ ቢስና
አስመሳይ ቄሶች በአደባባይ እንዲህ ዓይነት አሳፋሪና አስጸያፊ ንግግር ከእምነታችን ውጭ እንዲናገሩና፤
ተከታይ ምዕመናኖች እንዲያፍሩ አልፎም ተርፎም በብስጭት ወደ ሌላ እምነት እንዲሄዱ ለማድረግ ነው።
በዚህ የተነሣ የእነዚህ ወያኔ ካድሬዎች ዋና ዓላማ የኦርቶዶክስ እምነት እንዲዳከም ለማድረግ ስለሆነ፤
ምዕመናን ከእነዚህ ካድሬዎች መርዘኛ ከፋፋይ ተልዕኮ ሊጠነቀቁና መሠሪ ዓላማቸውን ሊያከሽፉ ይገባል።
ታዲያ እንደዚህ ዓይነቱ ለስሙ ቀሚስና ቆብ ያጠለቀ ይሉኝታ የሌለው ስለ ወያኔ በአደባባይ ቢሰብክ
ምንም አያስደንቅም። ይሁን እንጂ በተለይ የቤተ ክርስቲያንም ሆነ የሀገር ጠባቂ የዓለሙ ሁሉ ገዢ
የሆነው ታላቁ እግዚአብሔር እያለ፤በስመ ዘማሪነት ብቻ ተነስቶ ኢትዮጵያ ጨለመባት ብሎ የዘመረው
ሀብታሙ ሽብሩ የተባለ አሳፋሪና አጨብጫቢ የመሳሰሉትን ሳይ ደግሞ ነፍሴ ምን ያህል እንደምትፀየፋቸው
ለመግለጽ ቃላቶች ያጥሩኛል።
ትክክለኛ መንፈሳዊ የሆነ ሰው፣ አባት ማንንም ሳይፈራ በዘመን እንደ ቀደሙ አባቶቻችን መንጋዎቹን
ሁሉንም በእኩል ዓይን ሊያይና እውነቱን ሊመሰክር ይገባዋል። አባቶች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ክርስቲያን
እውነትን እውነት፤ ሐሰትን ሐሰት እንድንል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል። ለምሳሌ በ1953
የእነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ጊዜ፤ አቡነ ባስልዮስ በክብር ዘበኛና በጦር
ሠራዊት መካካል የነበረውን ተኩስ ለማስቆም የክብር ዘበኛን በማውገዝ ግጭቱ እንዲቆም አድርገው ነበር።
ይሁን እንጂ ጦር ሠራዊቱ አጋጣሚውን በመጠቀም ክብር ዘበኞችን ማንገላታት ሲጀምሩ፤ የክብር
ዘበኛዎቹ ሚስቶች ወደ አቡነ ባስልዮስ በመሔድ፤ እርስዎ እንዳይዋጉ ገዝተው ነው ባሎቻችን እየተንገላቱ
ያሉት በማለት አቤት ብለው ነበር። ስለዚህ ግዝቱን ያንሱ ወይ አንድ ነገር ያድርጉ ሲሏቸው፤
ፓትርያርኩ ወደ ንጉሡ ዐፄ ኃ/ሥላሴ በመሔድ ጦር ሠራዊቱ ሕገ ወጥ ጥቃታቸውን እንዲያቆሙ ለጦር
7
ሠራዊቱ ይንገቸው ብለው ሲጠይቁ፤ ንጉሡ ብዙም ፍላጎት ስላላሳዩ፤ ፓትርያርኩም ይህንን ካላደረጉ
ሥልጣኑን አልፈልግም ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳሜ እሄዳለው በማለታቸው የነበረው ግጭት እንዲቆም
አድርገዋል። እኝህን የመሰሉ አባት ነው ቤተ ክርስቲያናችንና ሀገራችን የምትፈልገው።
ከእነዚህ ጎጠኞች ባሻገር አንዳንድ የአፍሪቃ መሪዎች በቀብሩ ሥርዓት ላይ ስለ መለስ መሪነት ሲያወድሱ
ተደምጠዋል። የአይጥ ምስክ ድንቢጥ እንደሚባለው፤ እነዚህ የእርሱ ቢጤ አምባገነኖችና ነፍሰ ገዳዮች
የሚሰጡት ምስክርነት ከንቱ ነው። የምዕራቡም ዓለም መሪዎችም ቢሆኑ ዓላማቸውን ሲያራምድ የኖረ
በመሆኑ ተጠቀሙበት እንጂ፤ ግብጽ ላይ እንደተፈጠረው ችግር ቢፈጠር እንደ ሙባረክ በል ሥልጣንህን
አስረክብ ከማለት የማይመለሱ መሆናቸውን ማንም የሚዘነጋው አይመስለኝም።
በጣም የሚገርመው መለስ ሥልጣን ከወጣበት ጊዜ አስንቶ ካደረጋቸው በጣም በጥቂቱ፦
1ኛ/ኤርትራ እንድትገነጠል ሲያደርግ በወቅቱ ከአደራዳሪዎች መካካል አንዱ የሆነው የአሜሪካው ተወካይ ሄርማን
ኮኽን አሰብ ወደ ኢትዮጵያ መሆን አለባት ሲል ያልፈለገው አቶ መለስ ነበር። ድሮም ከባንዳ ልጅ ምን ይጠበቃል።
2ኛ/ከዚያም በመቀጠል ከዚህ ቀደም እንግሊዞች ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የጠነሰሱት ተንኮልንና ያልቻሉትን
ፖሊሲ ይህ የባንዳ ልጅ ሀገራችንን ሊበታትንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠፋ የሚፈቅድ አንቀጽ በሕገ
መንግሥቱ በማስገባት መንገድ መክፈቱ።
3ኛ/ የዘረኝነት አመራር በሃገሪቷ ላይ መጀመሩ
4ኛ/ ብዙዎችን የንግድና ኢንዱስትሪ ኤፈርት በሚባለው የፓርቲው ድርጅትና እና በስግብግብ ሚስቱ ወ/ሮ
አዜብ መስፍን ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ማድረጉ።
5ኛ/ የሀገሪቷን ምርጥ ባላሙያዎች ከሀገር እንዲሰደዱ ማድረጉ
6ኛ/ በ1997ቱ ምርጫ ጊዜ ምርጫውን በማጭበርበር ለመቆየት ሲል የብዙዎቹን ሕይወት ማጥፋቱ
እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ በእስር ቤት እንዲገላቱ ማድረጉ
7ኛ/ ሀገራችን በዲሞክራሲ የምትመራ ነች እያለ ነገር ግን ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን በእስር
ቤት በማጎርና ከሀገር ሲያሳድድ የኖረ በመሆኑ
8ኛ/ ብዙ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ቁልፍ የሆኑ የሥልጣን ቦታዎችን በወያኔዎች እንዲያዙ ማድረግና
የፓርቲ አባላት ያልሆኑ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ዕድገት እንዳይኖራቸው ማድረጉ
9ኛ/ ሕዝብን ሲንቅ ሲያንቋሽሽ፤ ስንቶች የወደቁለትን ባናዲራ ጨርቅ እያለ ሲያጥላላ የኖረ
10ኛ/ በክርስቲያኖችና እስልምና እምነት ተከታዮች መካካል ግጭት እንዲፈጠርና የሰው ነፍስ እንዲጠፋ ያደረገ
11ኛ/ ከደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ሰዎች ከሌላ ጎሣ የመጡ ተብለው እንዲፈናቀሉ ከበስተኋላ ሆኖ ሲሠራ የነበረ፤
8
12ኛ/ የሀገሪቷን ለም የሆኑ ቦታዎች ለውጭ ዜጎች በጣም በርካሽ ዋጋ የቸረቸረ።
ታዲያ ይህን ሁሉ ግፍ የፈጸመ ነፍሰ ገዳይ፣ አንድ ላይ አብሮ የኖረን ሕዝብ በዘር የከፋፈለ፣ ሀገር
እንድትፈራርስ መሠረት የጣለ፤ እንዴት ሆኖ ነው ታላቁ መሪ ተብሎ የተደነቀው?
አባ ጳውሎስ
የዐፄ ኃ/ሥላሴ መንግሥት በደርግ ወታደሮች ሲገለበጥ በወቅቱ የነበሩት ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ነበሩ።
ደርግም ሥልጣኑን እንደያዘ በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የውሽት ክስ በመመሥረት እና በማሳጣት ከሥልጣን
አውርዶ ወደ ወኅኒ አወረዳቸው። በዚያ ወቅት እሳቸው በእስር ላይ እያሉ አቡነ ተ/ሃይማኖት ሦስተኛው
ፓትርያርክ ሆነው በ1967 እንዲሾሙ አደረገ። እንግዲህ ይህ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ መሾም
የሚለው ስሕተት በዚያ ጊዜ ተጀመረ ማለት ነው። ፓትርያርኩም በእስር ላይ ስለነበሩ በመጨረሻ ደርግ
ምን እንደሚያደርጋቸው ግራ ስለገባው በ1971 ዓም በግፍ እኝህን አባት አንቆ ገድሏቸዋል። ነገር ግን
ደርግ እኝህን አባት ሲያስር፤ በወቅቱ ከነበሩት የሲኖዶስ አባላት አባቶች መካከል አንዳንዶች፤ ደርግ
በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የወሰደውን እርምጃ እንደግፋለን ብለው በመጻፍ ፈንታ፤ ልክ እንደ ግብጽ ቤተ
ክርስቲያን ሲኖዶስ፤ አንዋር ሳዳት አቡነ ሺኖዳን አስሮ ሌላ ፓትርያርክ ሹሙ ሲላቸው፤ በሕይወት እያሉ
ሌላ ሰው አንሾምም ብለው በሲኖዶስ ለረጅም ጊዜ ሲተዳደሩ ቆይተው አንዋር ሳዳት ሲሞት አቡነ ሺኖዳ
ወደ ሥልጣን እንደተመለሱ ሁሉ፤ የእኛም አባቶች እንደዚያ ቢያደርጉ ኖሮ ሥርዓት ባልተፋለሰና፤ አቡነ
ቴዎፍሎስም ባልተገደሉ ነበር። አቡነ ተ/ሃይማኖትም ሦስትኛው ፓትርያርክ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን ሲመሩ
ቆይተው በመጨረሻ ሲያርፉ አቡነ መርቆሬዎስ አራተኛው ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ።
በዚህ መሐከል ደርግ ተንኮታኩቶ ሲወድቅ ወያኔ ሥልጣን እንደያዘ ያተኮረው የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን
ላይ ነው። በወቅቱ በመንበሩ ላይ የነበሩትን አቡነ መርቆሬዋስን የደርግ ሹም ናቸው በማለት ከሥልጣን
እንዲነሱ በእጅ አዙር በመገፋፋት ወይም በማስተባባር ግፊት ስላበዛባቸው፣ በመጨረሻም በሕመም የተነሣ
ለመሥራት አልቻልኩም ብለው ሥልጣኑን ለቀው ከቆዩ በኋላ ከሀገር ወጥተው ተሰደው ወደ አሜሪካ ገቡ።
ደርግ ሥልጣን በያዘ ጊዜ አስሯቸው ከነበሩት ጳጳሳት መካከል አንዱ የሆኑት አባ ጳውሎስ ከተፈቱ በኋላ
ወደ አሜሪካ በመሔድ ምዕምናን እያስተማሩ እያገለገሉ ነበር። እኝህ ሰው በሎስ አንጀለስ ለተከፈለችው
የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምክንያት ሲሆኑ፤ ከተከፈሉት አንዷ የድንግል ማርያም
ምዕመናን የራሳቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ገዝተው ለማስመረቅ የተለያዩ እንግዶች እንዲገኙ የግብዣው
ጥሪ የላኩት አባ ጳውሎስ ነበሩ። ይሁን እንጂ በዓሉ ሊከበር ጥቂት ጊዜ ሲቀረው ወያኔ ሥልጣን ስለያዘ
አባ ጳውሎስ ማንንም ሳያማክሩና ሳይነግሩ ፕሮግራሙን ትተው ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ሄዱ። እዚያ
9
ሰንብተው ከተመለሱ በኋላ በሎስ አንጀለስ አካባቢ የሚኖሩትን አባላት የሆኑትንም ሆነ ያልሆኑትን ሁሉ
የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ምዕመናንን በቤተ ክርስቲያኗ ሰብስበው የቪዲዮ ቀራጭ በግላቸው አዘጋጅተው
ለተሰበሰበው ምዕመናን ንግግር ሲያደርጉ፤ <<እስከዛሬ ድረስ የበኩር ቋንቋ የሆነውን የትግርኛ ቋንቋ ትቼ
በአማርኛ በማስተማሬ አዝናለው>> ብለው ሲናገሩ፤ አባላቱም ከዚህ በፊት ያልነበረ እንዲህ ዓይነት
የሚከፋፋል ቃል ለምን ይናገራሉ በማለት አቋርጧቸዋል። ከዚያ ቀን በኋላ በሎስ አንጀለስ አካባቢ
የሚኖሩትን የትግራይ ሰዎች አቡነ አረጋዊ የሚባል በትግርኛ ግልጋሎት የሚፈፀምበት ቤተ ክርስቲያን
ከፈቱ። እንግዲህ በውጭው ዓለም አባ ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያናችን በዘር ላይ እንድትከፈል በመጀመር
ግንባር ቀደም ሆኑ ማለት ነው። አባ ጳውሎስ ድንገት አዲስ አበባ ደርሰው ከመጡ በኋላ የትግርኛ ቋንቋ
ተናጋሪዎች ቤተ ክርስቲያን እንዲከፈቱ በግልጽ መንገዱን ቢከፍቱም፤ ሁኔታዎች እስኪመቻቹ ውስጥ
ውስጡን ከወያኔ ጋራ ይሠሩ እንደነበር ከአድራጎታቸው መገመት አያዳግትም።
ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ቀሲስ አስተርአየ <<የነ ፋሌቅ ወጥመድ>> በሚል ርዕስ ከዶ/ር አረጋዊ የዶክትሬት
ምረቃ ጽሑፍ ላይ፤ ወያኔ ከጫካ ጀምሮ እንዴት አድርጎ የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን እንደሚያዳክም፣
እንደሚያጠፋና፤ የእዚህ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ዋና ጠንሳሾች እነ ስብሐት ነጋና ገብረ ኪዳን ደስታ
እንደሆኑ ግልጽ አድርገው ጽፈውታል። ቀሲስ አስተርአየ ተርጉመው የጠቀሱትን መልሼ እዚህ ላይ ማሳየት
እፈልጋለው << … ቤተ ክርስቲያን ለረዥም ዘመናት በሕዝቡ አዕምሮ ላይ ስትቀርፅ የኖረችውን ብሄራዊ
የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከትግራይ ሕዝብ አዕምሮ ጠራራጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ
ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው። …የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን
ጠቅላላ መዋቅራዊ አስተዳደር በትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ባለሟሎች መተካትና በቤተ ክርስቲያኒቷ
አካባቢ የትግርኛ ቋንቋ እንዲሰፍን ማድረግ ነው።>> ታዲያ አባ ጳውሎስ ባለፉት 20 ዓመታት ቤተ
ክርስቲያኒቱ ላይ የፈጸሙትን ካየን አንዱ ምልምል ናቸው ብንል ስሕተት አይሆንም። አባ ጳውሎስም
ሥራቸውን አስቀድመው በአሜሪካ ስለጀመሩና ለወያኔ ስላስመሰከሩ፤ ደርግ በወደቀ ጊዜ በግርግሩ መሐል
ወደ አዲስ አበባ መጥተው የመንበረ ጵጵስናውን በቀላሉ ለመያዝ ችለዋል።
አባ ጳውሎስ መንበሩን ከያዙ ጀምሮ የፈጸሟቸው በደሎች ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሲሆኑ፤ ልክ ከላይ
እንደጠቀስኩት ወያኔ ከጫካ ጀምሮ የዘረጋውን ተንኮል ተግባራዊ ለማድረግ፤ በየአድባራቱ የሚሾሟቸው
አብዛኛዎቹ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች የመሳሰሉት የትግሬ ዝርያ ያላቸው እንዲሆኑ
አድርገዋል። በእሳቸውም ዙርያ ከወንድማቸው አንስቶ የእሳቸው ዘር በሆኑ የተከበቡ ሲሆን፤ እነዚህ
ሰዎች ፓትርያርኩን በመተማመን ሌሎች ጳጳሳት ላይ የሚያሳዩት ንቀት፣ስድብ አልበቃ ብሏቸው ቤታቸውን
10
እየሰበሩ በመግባት እስከ መደብደብ መድረሳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። እንዲህ ዓይነት አስፀያፊ
ቆሻሻ ተግባር እንኳን ከቤተ ክርስቲያን አካባቢ ቀርቶ ከአንድ ጥሩ ኢትዮጵያዊ የማይጠበቅ ነው።
በተጨማሪም እንደ ሀገራችን ባሕል ሰው ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ደውሎ አስታርቁኝ፣ አማልዱኝን ካለ
አባቶች በሁኔታው ገብተው ለማስታረቅ ይሞክሩ ነበር። ነገር ግን በአንድ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች
ረብሸው ፖሊስ ሲያሳድዳቸው ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ገብተው አስጥሉን ባሉ ጊዜ አሳልፈው
ለወያኔ ወታደሮች ሰጥተዋቸዋል። እኝህ ሰው እንደ ዓለማዊ መሪም ባሕታዊውን በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ
ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት ያስገደሉት ሳያንሳቸው፤ እሳቸው ሾመው የላኩትን አለቃ አንቀበልም
በማለታቸው በልደታ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን ላይ ፖሊስ አዘመቱባቸው። በዚያም የተነሣ የቤተ
ክርስቲያን አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ ተቋረጠ። አባ ጳውሎስ በዚህ ብቻ አላቆሙም ነገር ግን ሌሎች
የሚጠሏቸውን ሰዎች እንደ ዓለማዊ መሪ የሚበቀሉና የሚያሳድዱ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ወይም
ቀኖናን ከምንም ያልቆጠሩ፤ ለሥጋዊ ተድላ ያመዘኑና ምግባራቸውና ባህሪያቸው መንፈሳዊ ስላልሆነ፤
ከመኖሪያቸው ሲወጡ ልክ እንደ አንድ አምባገነን መሪ ጥይት በማይበሳው መኪና የሚጓዙ ነበሩ።
በዚህ የተነሳ አባ ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያናች ታሪክ ሆኖ የማያውቀውን በየሄዱበት ጫማ፣እንቁላልና
ድንጋይ እየተወረወረባቸው እሳቸው ተዋርደው ቤተ ክርስቲያንን መሳቂያና መሳለቂያ አድርገዋታል።
በንብረትና ገንዘብ ዘረፋውም ከአንድ የሃይማኖት አባት በማይጠበቅ ሁኔታ ራሳቸውን አስገመቱ። ለዚህ
ሁሉ ውርደት የተዳረጉት ከላይ በፈጸሟቸው ተግባራት ሆኖ ሳለ፤ እሳቸው ግን በአንድ ወቅት ሕዝቡ
የጠላኝ ትግሬ በመሆኔ ነው ብለው ጥፋታቸውን ለመሸፈን ሞክረዋል። ረስተውት ነው እንጂ የኢትዮጵያ
ሕዝብ ለ1600 ዓመታት ጆሮአቸውን ቢቆርጧቸው አማርኛ ወይ ግዕዝ በማይሰሙ ግብጻውያን ይመራ
እንደነበር እንዴት እንደዘነጉት የሚገርም ነው። ታዲያ ከዚህ እንደምንረዳው ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት
ጥሩ አባት ሁሉን በእኩል የሚያይ፤ ሕይወቱ ሌሎችን የሚያስተምር እንጂ ዘሩ ምን እንደሆነ ግድ
እንደማይሰጣቸው ነው።
በመጨረሻም መንግሥት ካልጠፋ ቦታ ሄዶ ለዘመናት ተከብሮ ከኖረው የዋልድባ ገዳም አጠገብ የስኳር
ፋብሪካ እሠራለሁ ብሎ የገዳሙ ባሕታውያንና አባቶች በመቃወማቸው በፖሊሶች ተደበደቡ። ፓትርያርኩም
በገንዘብ ሊደልሏቸው ሞከሩ ግን አልሆነም። የእነዚያ አባቶች ጸሎት የደረሰ ይመስላል ላለፉት 21
ዓመታት ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን ሲበድሉ፤ እንዲሁም ሕዝብንና ሲያስለቅሱ ኖረው መለስ እያለ ማንም
አይነካኝም እያሉ ከተማመኑበት ሰው ጋር ተከታትለው በድንገት ሞቱ። እንደ ሃይማኖታቸው
በእግዚአብሔር ቢታመኑ ግን አይሻልም ነበርን? አባ ጳውሎስ በሞቱ ሰሞን በየድኅረ ገጾች ላይና በፌስ
11
ቡክ ሌሎችም ላይ ያየነው ከሠሩት ደግ ሥራ ወይም አስተዋፅዖ ይልቅ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን እንዴት
በድለዋት እንደሄዱና ይህች ቤተ ክርስቲያን ከእኝህ ሰው የተበላሸ አመራር እፎይ እንዳለች ነው።
አንዳንዶች ደግሞ ምንም በደል ቢያደርጉም ይቅር ማለት ነው በማለት ሐዘናቸውን ገልፀዋል። በአንጻሩ
ደግሞ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ ሲያርፉ ግን በሁሉም ድኅረ ገጾች ላይ የተነበበው
ግን አንድ ዓይነት የሀዘን መልዕክት ነበር።ይህ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሚሾመው ፓትርያርክ
ዘር ግንድ ስሜት እንደማይሰጠው፤ ነገር ግን ምግባሩ ጥሩ የሆነና መንጋዎቹን የሚጠብቅ አባትን
እንደሚፈልግ ነው።
ባለፈው ነሐሴ 2004 መጨረሻ ላይ ዓቃቤ መንበር የነሆኑት አቡነ ናትናኤል <<…ቤተ ክርስቲያኒቷ
ሁለንተናዊ ዕድገት ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት የሚበጅ ተተኪ አባት (ፓትርያርክ) ለቤተ ክርስቲያኗ
እግዚአብሔር ባወቀ መርጦ እንዲያስቀምጥ……ከጳጉሜ 1 ቀን 2004 እስከ መስከረም 10 ቀን 2005
ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን አውጀዋል።>> ሐሳቡ በቅንነት እስከሆነ ድረስ በጣም
አስፈላጊ ነው። ይህ ምስኪን ሕዝብም አዋጁን ሰምቶ ሱባኤውን በጾምና በጸሎት አሳልፏል። ይሁን እንጂ
እያፈተለኩ ከሚወጡት ወሬዎች እንደተረዳነው፤ ወያኔ መጀመሪያ ላይ ሲገቡ በነበረው ግርግር ያደረገው
ማጭበርበር አንሶ አሁንም የወያኔን ዓላማ ያራምዱልኛል ብሎ የሚያሰባቸውን ፓትርያርክ ነው በመንበሩ
ላይ እንዲቀመጡ የሚፈልገው። በጥቅምት ወር አካባቢ ላይ የተሰማው ጭምጭምታ ወያኔ እንዲመረጡ
ያሰባቸው ሰዎች አቡነ ማትያስ ወይም አቡነ ጎርጎርዮስ የተባሉትን ወይም የአባ ጳውሎስ ቀኝ እጅ
ከነበሩት ዋነኛው አቡነ ገሪማ መሆኑን ተደምጧል። እንዲሁም ዐቃቤ መንበር የሆኑት አቡነ ናትናኤል
ደግሞ በስደት የሚገኙትን ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስን ማነጋገራቸው ሲታወስ፤ ባለፈው ሳምንት የወቅቱ
የኢትዮጵያ ፕሬዜዳንት ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ሀገር ተመልሰው ሥልጣኑን እንዲረከቡ ከጋበዙ በኋላ
ወዲያው ውሎ ሳያድር ደግሞ ጥሪውን ማንሳታቸውን ተናግረዋል። መጀመሪያ ላይም ከብፁዕ አቡነ
መርቆሬዎስ ጋር ንግግር የጀመሩት አቡነ ናትናኤልም መንግሥት በቤተ ክህነቱ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ
መግባት የለበትም በማለት የፕሬዜዳንቱን ጥሪ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል። በእርግጥ ፓትርያርኩን
ለማስቀመጥ በሚደረገው ምርጫ ላይ መንግሥት ጣልቃ ካልገባ ምናልባት ሁኔታዎች ሊስተካከሉ ይችሉ
ይሆናል። ይሁን እንጂ ካለፉት ዘመናት ልምድ እስከምናውቀው ድረስ መንግሥት በቤተ ክርስቲያን
አስተዳደር ውስጥ ያልገባበት ጊዜ የለም። አሁንም በመንበሩ ላይ የሚቀመጠው አባት የወያኔንን ዓላማ
የሚያራምድ ሳይሆን፤ ከእምነቱና ዕውቀት ባሻገር ሁሉን በእኩል ዐይን የሚመለከትና ለቤተ ክርስቲያን
ዕድገት ደከመኝ ታከተኝ ሳይል የሚሠራ መሆን ይኖርበታል። እንዲሁም ምዕመናን ደግሞ እኔ የጳውሎስ
ወይም የአጵሎስ ሳይሉ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ተከትሎ በመንበሩ ላይ በመንፈስ ቅዱስ ተሾሞ
12
ለተቀመጠው መታዘዝ ይኖርባቸዋል። አሁንም የሚሾመው ፓትርያርክ በመንግሥት ትዕዛዝ ከሆነ፤ የወያኔ
መንግሥት ሲወድቅ የተሾመው ፓትርያርክ ከሥልጣን ይወርዳል አልፎም ተርፎም ለስደት ተዳርጎ ሌላ
ሦስተኛ ሲኖዶስ ሊቋቋም ይችል ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ብፁዓን አባቶች እንዲሁም ምዕመናን
ምርጫው በሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲፈጸምና የተበላሸው ሥርዓት እንዲስተካከል የማድረግ ኃላፊነት
አለባቸው። አባ ጳውሎስ በሕይወት በነበሩ ጊዜ በውጭ ሀገር በስደት ካለው ሲኖዶስ ጋራ ስብሰባ መካሄዱ
ይታወሳል። ነገር ግን ወደ የትም እንደማያደርስ የታወቀ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ቤተ ክርስቲያንን ከሁለት
የከፈለና ምዕመናን የጎሪጥ እንዲተያዩ ያደረገ ስለሆነ፤ ይህ አሁን ያለው አጋጣሚ ተጠቅሞ ቤተ
ክርስቲያንን ወደ አንድነት ለማምጣት ሁሉም አባቶች፣ ካህናት እንዲሁም ምዕመናን ከልባቸው ሊጥሩ
ይገባል።
እዚህ ላይ የወያኔ ዓላማ ምን እንደሆነ ከዶ/ር አረጋዊ በርሔ ጽሁፍ ተረድተናል ማለትም ቤተ
ክርስቲያንን የሚያዳክምና የሚያጠፋ ማለት ነው። ታዲያ እንዴት አድርገን ነው በራሳችን ላይ አጥፊ
ሲሾምብን ዝም ብለን ለዚህ አረመኔ መንግሥት የምንታዘዘው? ቤተ ክርስቲያናችንን የመጠበቅ መስዋዕትነት
የሚከፈለው መቼ ነው? ይህን አጋጣሚ በዝምታ ካለፍንና መንግሥት አሁንም ጣልቃ ገብቶ የሚረብሽ
ከሆነ፤ እንደ እነ አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤል የመሳሰሉ የጣሊያንን ጥይት ሳይፈሩ ስለ እውነት፣
ስለ ሃይማኖታቸውና ሀገራቸው ተናግረው መስዋዕትነት የተቀበሉ አባቶችን የመሰሉ በቤተ ክርስቲያናችን
የሚፈጠሩት መቼ ነው ብለን እንዳናዝን እፈራለው። የአጤ ምኒልክ የክተት አዋጅ <<ሀገርህን የሚወር፣
ሃይማኖትህን የሚለውጥ ጠላት መጥቶብሃል፤ ተነስ ተከተለኝ ነበር።>> አሁን ደግሞ የሁላችንም አዋጅ
መሆን ያለበት፤ ወገኔ ሆይ ከዚች ምድር ላይ የተፈለፈሉ በሥልጣን ላይ ያሉ ሃይማኖትህን ሊያጠፉ፣
ሀገርህን ሊያፈራርሱ ሲያሴሩ ውለው አድረዋልና በቃ ተነሥ ነው መሆን ያለበት።
መደምደሚያ
ከላይ እንዳየነው ባለፉት 21 ዓመታት ወያኔ በሀገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ያደረሰውን ጥፋቶች
ጠቅለል ባለ መልኩ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ታዲያ አክሱም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና
የተጫወተችና ከዚያችም ክፍለ ሀገር እንደ ዐፄ ካሌብ፣ ቅዱስ ያሬድ፣ ዐፄ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ አባ ነጋ
ሌሎችም በታሪካችን ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉ ከወጡባት ምድር፤ ወያኔ የተባሉ ከአንድ መንደር
የመጡ ሀገር አፍራሾች፣ ዘረኞች፣ ዓይን ያወጡ ዘራፊዎችና ይሉኝታ ቢሶች እንዴት ሊፈጠሩ እንደቻሉ
የሚገርም ነው። እነዚህ ወያኔዎች የሚያካሄዱት የሀገር ንብረትና ገንዘብ ዘረፋ፣ የግል ሀብትን በማካበት
ላይ የሚደረገው ዐይን ያወጣ ዝርፊያ እና ይኽን ጥቅም ለማስጠበቅ ሀገሪቷ ላይ የዘረጉት የከፋፍለህ
13
ግዛው ቆሻሻ አመራር አሳፋሪ ነው። በስደት ያለው አቶ አርአያ ወልዱ ኢየሩሳሌም አርአያ በሚል በብዕር
ስም በተከታታይ በሚጽፋቸው ጽሑፎች ላይ ያለውን የፖለቲካ ሽኩቻና ምዝበራ እያጋለጠና እያስገነዘበን
ይገኛል። ባለፈውም <<ከፖለቲካው ፍጥጫ ጀርባ>> ብሎ የጻፈውን ማንበብ ጥሩ ግንዛቤን ይሰጣል
(http://www.ethiomedia.com/assert/behind_the_scene.pdf )።
ወያኔዎች እንዴት አድርገው ሀገሪቷን በዘረኝነት መንፈስ እንደከፋፈሉና ያለምንም ይሉኝታና ዕፍረት መጥፎ
ሥራቸው እንደ ታላቅ ጀብዱ ለሕዝብ ለማሳየት ለሆዳቸው በተገዙ ወይም በዚህ አገዛዝ የተጠቀሙትን
መሣሪያ በማድረግ ኅብረተሰቡን እንደከፋፈሉትና በሕዝብ መካካል ያለውን መፋቀር እንዳጠፉት በዓይናችን
እያየነው ያለ ሂደት ነው። እንዲሁም ደግሞ አንዳንድ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የሚሠራውን ግፍ እያዩ፤
ነገር ግን ሥልጣን ከትግሬ ዘር ውጭ መውጣት የለበትም በማለት በጭፍን የሚደግፉ በታሪክ ወደፊት
ከመወቀስ አይድኑም። ለጊዜው የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ የያዘው ሰው የትግሬ ተወላጅ ባይሆንም
ደኅንነቱንና ጦር ኃይሉንም ተቆጣጥረነዋል፤ የሚያሰጋን ነገር የለም በሚል ትዕቢት የሚመኩም ሊጠነቀቁ
ይገባል። ምክኒያቱም ነገሮችም እኛ ብቻ እንደምናስበው ስለማይሄዱ ። ደግሞም ብልጥነት ሁልጊዜ ደግሞ
አያዋጥም። አንድ አባባል አለን <<ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው>> ማለትም ሌላውን ዘር እናጠቃለን
ብለን ተንኮል ስንሸርብ፣ ሕዝብ ስናሳድድ ስናሰቃይ፤ በፈጠርነው የተንኮል አሠራር እኛው ራሳችን
ተመልሰን የራሱ ሰለባ እንዳንሆን ያሰጋል።
እንደ ስብሐት ነጋ ደግሞ ያለ የሽማግሌ ቀላል፤ ወደፊት ምን ያስከትላል ብሎ ባለማሰብ አማራንና
ኦርቶዶክስን ሰብረነዋል ብሎ በአደባባይ ሲናገር ስንሰማ፤ የወያኔን መርዝ ዓላማ በግልጽ እንድንረዳው
ከዚህ የበለጠ ምስክር አያስፈልገንም። እንዲህ ዓይነት በዘር ላይ የተመሠረተ ጥላቻን ይዘው ተነስተው
ብዙ ጥፋት ያደረሱ ለምሳሌ ያህል በሩዋንዳ በዩጎዝላቪያ ታይተዋል ነገር ግን መጨረሻቸው አላማረም።
እዚህ ላይ አንድ መገንዘብ ያለብን ነገር ምናልባት በስመ ትግሬነት ብቻ የወያኔን መንግሥት ወይም ደግሞ
የስብሐት ነጋን ሐሳብ የሚደግፉ፤ የእምነታቸው ሕልውና በአንጻሩ ደግሞ ፈተና ላይ መሆኑን መዘንጋት
የለባቸው። ይህ ስብሐት የሰጠው ዓይነት አስተያየቶች አብሮ ለብዙ ዘመናት የኖረን ሕዝብ የሚከፋፍልና
የሚያቃቅር ነው። በመጽሐፈ ሲራክ ላይ እግዚአብሔር አምላክ 6 ነገሮችን አይወድም ነገር ግን
ሰባተኛውን ነፍሱ አጥብቃ ትፀየፋለች፤ ይኽውም <<በወንድማማቾች መካከል ፀብን የሚዘራ>> ይላል።
ስለዚህ ይህን ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ስብሐት ነጋም ሆነ የእሱ ፓርቲ ከአእምሮአቸው አውጥተው ወደ ፍቅር
ወደ አንድነት እንዲመጡ፤ ልቡናቸው ይመለስ ዘንድ ልንጸልይ ይገባል ምክንያቱም ክርስትና የፍቅር
እምነት ነውና።
14
በቅርቡም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ የተረከቡት አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ በሚቀጥሉት ዓመታት ሟቹ
አቶ መለስ የጀመሩትን ዕቅድ ብቻ ሳይሆን የተነፈሱትንም አየር ነው የምተነፍሰው ብለው ሲናገሩ መስማቱ
የሰውየውን የፖሊቲካ ብስለት ገና ከመጀመሪያው እንድንጠራጠርና፤ ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም
የሚለውን የሀገራችን አባባል እንድናስብ አድርጎናል። አሁን እሳቸው በሚመሩበት ዘመን ለሚፈጠሩት
ችግሮች ተጠያቂው አቶ ኃ/ማርያም እንጂ ከመቃብር ዓለም አቶ መለስ አይደለም። አስተዋይ የሆነ መሪ
የሚያደርገው ከዚህ በፊት የተደረጉ ስህተቶች በማስተካካል አስተዳደርን ያሻሽላል፣ በደል ተፈፀመ ሲባል
እንዲጣራና አስፈላጊ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል እንጂ ምንም አልለወጥም ብሎ መናገር አሳዛኝ ነው።
በቅርብ ጊዜ ባልና ሚስት ዕርቃነ ሥጋቸውን በአደባባይ እየታየ እንዲፈጽሙ የተደረገውን ላየና ለሰማ
በእውነቱ ይህ ዓይነት ባሕርይ ኢትዮጵያውያን ከየት እንዳመጡት የሚያሳዝን ነው። ሉሉ ከበደ የጻፉትን
ማንበብ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል http://www.ethiomedia.com/assert/yewenjelegnochu_mengist.pdf
ይህ የአቶ ኃ/ማርያም ግትር አባባል የሮብዓምን ታሪክ እንዳስታውስ አደረገኝ።
ንጉሥ ሰለሞን ሞቶ ሮብዓም በነገሠ ጊዜ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ወደ እርሱ መጥተው አባትህ ቀንበር
አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር
አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት። እርሱም ሂዱ፥ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ
ተመለሱአላቸው። ሕዝቡም ከሄዱ በኋላ ንጉሡ ሮብዓም ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ
ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ።
እነርሱም። ለዚህ ሕዝብ አሁን ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው፥
በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል ብለው ተናገሩት።እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ
ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። እርሱም አባትህ የጫኑብንን ቀንበር
አቃልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው። ከእርሱም ጋር
ያደጉት ብላቴኖች። አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፥ አንተ ግን አቃልልልን ለሚሉህ ሕዝብ። ታናሺቱ ጣቴ
ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች። አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ
እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት።
ንጉሡም በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን
ወደ ሮብዓም መጡ። ንጉሡም ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው።
እንደ ብላቴኖችም ምክር። አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤
አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ ብሎ ተናገራቸው። እስራኤልም ሁሉ
ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ ለንጉሡ። በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ
ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ፥ ወደ ድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ፥ አሁን ቤትህን ተመልከት
ብለው መለሱለት። እስራኤልም ወደ ድንኳኖቻቸው ሄዱ። (መጽ ነገ ቀዳ ም 12፦4)
ሙሉ ታሪኩን ስናነብ በንጉሥ ሮብዓም እብሪት ጥጋብ ብዙም ሳይቆይ እስራኤል ከሁለት እንደተከፈለች
ከዚህ አሳዝኝ ታሪክ እንማራለን። ስለዚህ አቶ ኃ/ማርያም በሥልጣን ላይ በሚቆዩበት የሚቀጥሉት ጥቂት
ዓመታት የተበላሸውን ሊያስተካክሉ፣ የተጣመመውን ሊያቃኑ፣ በግዞትና በእስር አለ አግባብ
የሚንገላቱትን ጉዳያቸውን ሊመለከቱና ነፃ ሊያወጧቸው፤ እንዲሁም ይህች ጥንታዊ ሀገራችን አንድነቷ
ተጠብቆ ሕዝቦቿም በፍጹም ዲሞክራሲና ፍትሕ ሊመሩ የሕሊና እና ኢትዮጵያዊ ግዴታ አለባቸው።
በቤተ ክህነቱም ቢሆን ወደፊት በመንበሩ የሚቀመጠው ፓትርያርክ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ተከትሎ መሰየም
ሲኖርበት፤ በአጠቃላይ በአገልግሎት ከድቁና አንስቶ እስከ ላይ ፕትርክናው ድረስ የተሾሙ ካህናት
15
ሕይወታቸውን እንደ ቅዱስ መጽሐፉ ትዕዛዝ ሊያስተካክሉና፤ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በቅንነት ሊወጡ
ይገባል። አንድ ካህን ሥልጣነ ክህነት ሲቀበል መሥዋዕትነት ድረስ የመቀበል መከራ እንደሚደርስበት
ማወቅ አለበት። ለምሳሌ ከሐዋርያቱ አንዱ የሆነው ይሁዳን ለመተካት ከዮሴፍና ማትያስ አንዱን
ለመምረጥ ዕጣ አውጥተው ነበር። የሐዋርያት ሥራ (ምዕራፍ 1፤26) እንደሚለውም በማትያስ ላይ ዕጣ
ወደቀበት/ወጣበት እንጂ ወጣለት አይልም ምክኒያቱም የተመረጠበት ዓላማ መስዋዕትነት የሚቀበልበት
ነገር ግን ዋጋው በዚያኛው ዓለም የሚያገኘው ስለ ነበረ ነው። ስለዚህ መንፈሳዊ ሥልጣን ለመቀበል
ስንዘጋጅ ታዲያ በትክክል መንፈሳዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣትና መስዋዕትነት ለመቀበል ዝግጁ ነን ወይ
ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል። ከላይ እንደገለጽኩት ባለፈው አባ ጳውሎስን ለማስመረጥ የተደረገው
ዐይነት ማጭበርበር እንዳይደገም፤ በተለይም ደግሞ የወያኔን ዓላማ አሁን በደንብ ስላወቅን፤ ቅዱስ
ሲኖዶስ አለምንም መንግሥት ተጽዕኖ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መንገድ መንበሩን ማስከበር
ይኖርበታል። በመንበሩ ላይ የሚቀመጠውም ፓትርያርክም ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖታችን የምትስፋፋበትን፤
ፍትህና ርትዕ በሀገሪቱ ላይ እንዲሰፍን የሚችለውን ማድረግ ይጠበቅበታል።
በአጠቃላይ በአመራር ላይ ያሉም ይሁኑ ወይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህች ጥንታዊ ሀገራችን አንድነቷ
ተጠብቆ፣ ሕዝቦቿ ተከባብረው በአንድነት በፍቅር እንዲኖሩ ሊታገል ይገባዋል። ፍቅርና ቅንነት ካለ ይህች
ሀገራችን ከእኛ አልፎ ለሌሎች ሀገሮች ትተርፋለች። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለቂም በቀል የፈጠነ አይደለም፤
የሆኖ ሆኖ ያለው ስሕተትና አሳፋሪ ተግባሮች ግን ካልተስተካከሉ ጥፋትን ያስከትላል። ለምሳሌ ባለፈው
ሉሉ ከበደ ወደፊት ምን ማድረግ እንደሚገባ <<ህልሜ ቅዥት ባይሆን>> ሲሉ የጻፉት ጥሩ ማሳሰቢያ
ነው። (http://www.ethiomedia.com/assert/hilme_qzhett_baihon.pdf)
አለበለዚያ ግን የግፍ ጽዋ ሲሞላ እግዚአብሔር ሰው ሊገምት እና ሊያስብ በማይችለው ሁኔታ ነገሮችን
ይለዋውጣል። አምላካችን እንደ እኛ ቶሎ ቸኩሎ የሚበቀል ስላልሆነ ለንስሐ ጊዜ ይሰጣል። አሁንም ያሉ
መሪዎች በትዕቢት ተወጥረው፣ አምላክነቱን ንቀው፣ ሕዝብ መበደልን ከቀጠሉ፤ አወዳደቃቸው
ከትላንትናዎቹ ባልተሻለ ሁኔታ ይሆናል። የሞቱትም ሆነ አሁን በሕይወት ያሉት የሠሩት በደል ወደፊት
ሲወጣ፤ ይህ ሙት ወቃሽ አታድርገኝ ብሎ እንባውን ያፈሰሰላቸው ሕዝብ ምን ነክቶኝ ነበር ብሎ ራሱን
የሚወቅስበት ጊዜ ይመጣል። አሁንም ሁላችንም መከፋፈሉን፣ መጠላለፉን፣ ጎጠኝነቱን፣ በጎሪጥ
መተያየቱን ትተን በአንድነት ሆነን እግዚአብሔር አምላክ ሆይ ሕዝብህንና ይህቺን ቅድስት ሀገር ጠብቅ
ብለን ልንጸልይ ይገባል።
ይደነቃል ፍርዱ
 

staff reporter | December 12, 2012 at 7:32 pm | Categories: AMHARIC NEWS | URL: http://wp.me/p2gxmh-1bY
CommentSee all comments

             


No comments:

Post a Comment