“በኔ የምርጫ ወረዳ ውስጥ ማናባቱ ነው ሊወዳደደር የሚከጅለው!” እስከማለት የደረሱም አሉ፡፡ አስተያየታቸውም ሆነ አመለካከታቸው የደጅአዝማችነት ነው፡፡ በኔ ደጅ ድርሽ ትሉና አለቃችሁም የሚል ጩኸትና ቡራ ከረዩ አለበት፡፡ በዚያም ላይ ድምጽን እንደቀድሞዎቹ የመሬት ከበርቴዎች ለብቻቸው ለመቀራመትና “የተከበሩ አቶ እከሌ ወይም ፕሮፌሰር እከሌ ወይም ዶክተር እከሌ” ለመባል ብቻ ነው የሚፈልጉት፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በዛ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ የገለልተኛነት ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም መያዝ ችለዋል፡፡ ይህ ትልቅ አርምጃ ነው፡፡ እስከምናውቀው ድረስ የተቃዋሚውን ጎራ ፖለቲከኞች ቢያንስ ስድስት አጀንዳዎች በጋራ ያስማሙአቸዋል፡፡ ይኼ የምርጫ ቦርድ የገለልተኛነት ጉዳይ፤ የመገናኛ ብዙኃኑም የገለልተኛነትና የሕዝባዊነቱን ጉዳይ በተመለከተ፣ የፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊቱና የደህንነቱም ሕዝባዊነትና ገለልተኛነት፤ ስለፖለቲካ እስረኞች በግፍ መታሰር ጉዳይ፣ በገዢው ፓርቲ ብቸኛ ውሳኔ እየወጡ ስላሉት አፋኝ ሕጎችና መመሪያዎች፤ (ለምሳሌ ስለፕሬስ ሕጉ፣ ስለመያዶችና ስለሽብርተኝነት፣ እንዲሁም ስለመሬት ይዞታ የወጡት አዋጆች) በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ፣ በንግዱ ማሕበረሰብና በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ባለው ኢ-ፍትሐዊ የግብር አጣጣልና የኑሮ ውድነት ላይ አጀንዳ ቀርፀው ለመሥራት ይችላሉ፡፡
ከዚህ በፊት የነበሩት ስለምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ጥያቄዎች ምርጫው ከተካኼደ በኋላ ወይም “ምርጫው ተጭበርብሯል” የሚል ስሞታ መደመጥ ሲጀምር ነው፡፡ ከላይ እንዳልነው፣ በተቃዋሚዎቹ ቀድመው ችግሮች ላይ መንቃት በመጀመራቸው የተሰማንን ደስታ መሸሸግ አንፈልግም፡፡ ምክንያቱም በሰላማዊ ትግል ወቅት ትልቁ ስልት ቀድሞ ችግሮችን መለየትና ችግሮቹንም ነጥሎ መሣሪያ ማድረግ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ Counter Reaction ማለትም ይኼው ነው፡፡ ከኮሚቴና ከግብረ-ሃይልም ባለፈ ሕዝባዊነትን የተላበሰና ተዓማኒነት ያለው ሰላማዊ ትግል እንደሚያድረጉት ተስፋ አለን፡፡ በተለይም ፖለቲካ ውስጣዊ አሠላለፍንም ማሳመር ነውና፣ ፓርቲዎቹ በተናጠል የአባላቶቻቸውን አቋምና ውስጣዊ ድጋፍ ቀድመው ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደማናየው “ነገራችን ሁሉ የንቧይ ካብ-የእንቧይ ካብ” እንዳይሆን መሥራት አለባቸው፡፡
ስጋታችን ግልጽ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ብሔራዊ ምርጫዎች ዋዜማና ማግሥትም የነበሩት ከባድ ፈተናዎች በሁለት የተከፈሉ ነበሩ፡፡ አንደኛው ሰበብ፣ የፓርቲዎቹ ውስጣዊ ነውጥ ውስጥ መግባት ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃም የሚመጣው ውጫዊ የሆነውን ጫና ለመቋቋም አለመቻላቸው ነው፡፡ ውጫዊዎቹ ግፊቶች ከገዢው ፓርቲና ከሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም ከዲያስፎራው በኩል የሚመጡ ናቸው፡፡ ገዢው ፓርቲ ልዩ ልዩ ማዳከሚያዎችን እንደሚጠቀም ያደባባይ ሚስጢር ስለሆነ ወደሌሎቹ እንለፍ፡፡ ከሌሎች ተቃዋሚዎችም ጋር የሚስተሳስሯቸው ጉዳዮች ይልቅ የሚያለያዩዋቸው በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ሆኖም፣ በጋራ ከሚያስማሟቸው ነገሮች ይልቅ የሚያለያዩዋቸውን ጉዳዮችን ማራገቡ የማን ስራ እንደሆነም እናውቀዋለን፡፡ በብዛት ስልጣናቸውን የሙጥኝ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ ጉምቱ መሪዎች ትግባር መሆኑን መናገር ያስፈልጋል፡፡
መንግስታዊዎቹም ሆኑ የግሎቹ የመገናኛ ብዙኃን ከዚህ አልፈህ አትሂድ ወይም እዚህ ድረስ ብቻ አስብ እየተባሉም እንደሚሠሩ እሙን ነው፡፡ ስለሆነም፣ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓት ለመገንባት ካስፈለገ፣ በመጀመሪያ ዲሞክራሲውን ሊሸከሙ የሚችል ትከሻና አደረጃጀት ያላቸው ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ (ታዲያን፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎቹንም ጨምሮ ነው፡፡) የማዘጋጀቱ ሥራ ከምርጫ ቦርድ መጀመሩም እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡ ከዚያም ወደሌሎቹ ተቋማት እንደሚንሰራፋ ጥርጥር የለንም፡፡ በተለይም፣ የመገናኛ ብዙኃኑን ገለልተኝነት በተመለከተና የፖሊስና የፀጥታው እንዲሁም የሠራዊቱንም ገለልተኝነት በተመለከተ አሌ የማይባል የጋራ አጀንዳ ቀርፆ መንቀሳቀስ ያዋጣል፡፡ ካለፉት ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫዎች ብዙ ተመክሮዎችን ማግኘታችን መካድ የለበትም፡፡ ስሕተቶቹን አርሞ፣ ጥንካሬዎቹንም ጠብቆ መዝለቅ ከፓርቲዎቹ ይጠበቃል፡፡ በተለይም ከተቃዋሚዎቹ በኩል የግድ ያስፈልጋል፡፡
ሕዝቡ ተቃዋሚዎችን “ወይ ተባበሩ፣ ወይ ተሰባበሩ” (Make or Break) እያለ ነው፡፡ አንዳንዶች አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠትም ከፍተኛ ሙከራ እያደረጉ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ በብሔር የተደራጁትም ሆኑ በሕብረ-ብሔራዊነት የተሰለፉት የፖለቲካ ቡድኖች ከመቼውም ጊዜ በላይ የሕዝቡን ጥሪ ባግባቡ ለመመለስ መሽቀዳደም ቢኖርባቸውም ቅሉ፤ አንዳንዶቹ ላይ የሚታየው ያፈጀና ያረጀ አካሄድ ውሎ አድሮ መጋለጡ አይቀርም፡፡ በዚህ ጽኹፍም ውስጥ የተወሰኑትን የሀገር ውስጥ ፓርቲዎች የገጠሟቸውን ፈተናዎች ለሕዝቡ በወቅቱ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ መረጃዎቹ በጣም ቁጥብና የተጀመሩትን ጥረቶች እንዲያግዙ በማሰብ ጥቅል እንዲሆኑ ማድረጋችንን እንድታውቁት እንፈልጋለን፡፡ በተለይም፣ በጎ ፈቃዳቸውን ያሳዩትን አስማሚዎች/አደራዳሪ ሽማግሌዎችና ቅንነት ያሳዩትንም ፓርቲዎች በዚህ አጋጣሚ ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሕዝብ በወቅቱ ማግኘት ያለበትን መረጃ ለማቀበል ስንል መጠነኛ ጥቆማ ብቻ እንሰጣለን፡፡ ወደፊት ፓርቲዎቹ በጋራ በሚያወጡት መግለጫም ላይ ሙሉውን ሃተታ ለማግኘት እንደምንችል ተስፋ አለን፡፡
ያም ሆኖ፣ በተወሰኑት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አካባቢ ከባድ የአመለካከት ችግሮች እንዳሉ ልንገልፅ እንወዳለን፡፡ ዋና ዋናዎቹም ችግሮች የሚከተለት ናቸው፡፡ አንደኛ፣ የድምፅ ከበርቴነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ ስሜት በብዙዎቹ ላይ ከ1980ዎቹ ጀምሮ የሚታይ አስተሳሰብ ነው፡፡ በተለይም፣ በብሔር በተደራጁት የፓርቲ አመራሮች አካባቢ በጣም ይንፀባረቃል፡፡ ላለፉት አስራ ስምንት አመታት ካለነሱም ሌላ ወኪል መሪዎቹ በሚወዳደሩበት አካባቢ/ወረዳ የሌለ ይመስል በየምርጫው ወቅት ከረቫታቸውን አስረው የሚታበዩት ብዙ ናቸው፡፡ ይባስ ብሎም፣ “በኔ የምርጫ ወረዳ ውስጥ ማናባቱ ነው ሊወዳደደር የሚከጅለው!” እስከማለትም የደረሱ አሉ፡፡ አስተያየታቸውም ሆነ አመለካከታቸው የደጅአዝማችነት ነው፡፡ በኔ ደጅ ድርሽ ትሉና አለቃችሁም የሚል ጩኸትና ቡራ ከረዩ አለበት፡፡ በዚያም ላይ ድምጽን እንደቀድሞዎቹ የመሬት ከበርቴዎች ለብቻቸው ለመቀራመትና “የተከበሩ አቶ እከሌ ወይም ፕሮፌሰር እከሌ ወይም ዶክተር እከሌ” ለመባል ብቻ ነው የሚፈልጉት፡፡ ሕዝቡ ላለፉት 18 ዓመታት የተካሄዱትን ነገሮች ልብ ብሎ ያጤናቸው መሆኑን አንኳን አያገናዝቡትም፡፡
በገዢው ፓርቲም አካባቢ ያለው ሕመም ይኼው ነው፡፡ በቅርቡ ነው የአቶ መለሠ ዜናዊ ምትክ ማን መሆን እንዳለባቸው የታወቀው፡፡ አለበለዚያ፣ አቶ መለሠ በጥርስ ብቻ ሳይሆን በድዳቸውም ጭምር በወረዳቸው እንደፈለጉ እንዲመረጡ ልዩ መብት የተሰጣቸው ነበር እሚመስለው፡፡ በተቃዋሚውም አካባቢ ያው ነው፡፡ ከኛ ወዲያ ላሳር የሚሉት ናቸው የሚበዙት፡፡ የመተካካት ፈሩን ከቶም አልጀመሩትም፡፡ ሊጀምሩትም ያሰቡት በቁጥር ከእጅ ጣት አይበልጡም፡፡ ወደፊትም ቢሆን በጥርሳቸውም ሆነ በጥፍራቸው፣ የሕዝቡን የተባበሩ ጥሪ ከመቦጫጨቅ የሚመለሱ አይደሉም፡፡ የእነርሱን የድምጽ ከበርቴነት ማን ወንድ ነው የሚፈታተናት? ምናባቱስ ቆርጦት፡፡ ስለሆነም የሕዝቡን የተባበሩ ወይም ተሰባበሩ ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ የሚያሰኛቸው ይኼ “የድምፅ ከበርቴነት” አጉል አምልኮ መሆኑን ልንናገር እንወዳለን፡፡
በሁለተኛ ደረጃም፣ የፓርቲ መሪዎች ስልጣን ባለቤትነትና የፈላጭ ቆራጭነቱ ችግር መኖሩን ሕዝቡ እንዲያውቅ ማድረግ ይገባል፡፡ ብዙዎቹ እንቀዳሚዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ስልጣናቸው ለዕድሜ ልክ ከሰማየ-ሰማያት የተሰጣቸው አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡ ሥዩመ-እግዚአብሔር የሆኑ ያህል የሚሰማቸው ጥቂቶች አደሉም፡፡ የትም-ፍጪው ሥልጣኑን አምጭው የሚል አባዜና ዛር ሰፍሮባቸዋል፡፡ ለዚህም ነው፣ “ሕብረት፣ ቅንጅት፣ መድረክ፣ ትብብር፣ ወይም ውህደት” ሲባሉ እንባ የሚተናነቃቸው፡፡ ገና ለገና በአዲሱ ድርጅት ውስጥ ኃላፊነት አላገኝም ብለው ስለሚያስቡ/ ስለሚያምኑ ጥረቶችን ያደናቅፋሉ፡፡ ደግሞም፣ በርካታ የማስተጓጎያ ሸፍጦችን ያለመታከት ይሰራሉ፡፡ እውነታው ይኼ ነው፡፡ ባይሆን ኖሮ፣ ከ2004 ዓ.ም ወዲህ እንኳን ተጀምረው የነበሩት የውህደት እና/ወይም የትብብር ሙከራዎች ለምን ከሸፉ? የሚያውቅ ያውቀዋል፤ ግና ለሕዝቡ ቀቢጸ ተስፋ ከሚመግቡት ይልቅ እውነቱን ግልጽ ልናደርገው እንወዳለን፡፡ “ሥልጣናችንን እናጣለን!” የሚሉ ወገኖች ጥረቱን ስላደናቀፉት ነው፡፡ ብሎም አከሸፉት፡፡ ይኼው ነው ሀቁ!
በሦስተኛ ደረጃ የሚስተዋለውን የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ችግር እናንሳ፡፡ ይህ ችግር በዋናነት ጊዜውን ያለመረዳት ችግር ነው፡፡ ጊዜው እንደተረዳነው ከሆነ የብሔረተኝነትና የጎሰኝነት ዘመን አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ብዙዎቹ የፓርቲ አመራሮች ይኼንን ያከተመ ዘመን በቅጡ አልተረዱትም፡፡ ሊረዱትም አይፈልጉም፡፡ ምክንያቱም ስልጣናችንን ያሳጣናል ብለው ስለሚሰጉና ያንንም ላለማጣት ሲሉ ነው፡፡ እርግጡን ለመናገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔረተኝነት ችግር ማክተሙን የሚያሳዩ ሦስት ምልክቶች እንጠቅሳለን፡፡ የመጀመሪያዎቹ ምልክት የ1997ቱና የ2002ቱ ምርጫዎች ውጤት ነው፡፡ በነዚህ ምርጫዎች በድምር/በጅምላው ከብሔር ድርጅቶቹ ይልቅ ሕብረ-ብሔራዊዎቹ ቅንጅትና መድረክ ከፍተኛ ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በጠራራ ፀሐይ እንደተዘረፈ በሚታወቀው የ1997ቱም ምርጫ ሆነ በወከባና በሸፍጥ በተጠናቀቀው የ2002ቱ ምርጫዎች እንደታየው ከሆነ የብሔር ፓርቲዎች ከንግዲህ ወዲያ “ጤናችሁን ይስጣችሁ!” ወይም በኦሮሚኛ “ፈያ ደይ!” ተብለዋል፡፡ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ሁለተኛው ምልክት ደግሞ፣ ብዙ ጊዜ በጽንፈኝነት የሚታሙት ፓርቲዎች ከሕብረብሔር ድርጅቶቸ ጋር ለመሥራት ያሳዩት ተነሳሽነት ነው፡፡ ኦፍዴን-ከቀድሞው ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ መጣጥፎች እንደምንረዳው ከሆነ፣ ብሔረተኛነቱን ሊያነሳ አፍታ ብቻ ነው የቀረው፡፡ ይበል የሚያሰኝ እርምጃ ነው፡፡ በውጭም የኦነግ አመራር ያሳየው ሆደ ሰፊነት በቀላሉ የሚታይ ምልክት አይደለም፡፡ የአረናም ቢሆን የሚያስመሰግን ምልክት ነው፡፡
በሦስተኛ ደረጃም የምንጠቅሰው ምልክት የእስልምና ተከታይ ወንድሞቻችና እህቶቻችንን የብሔረተኛነትን ግንብ ተሻግሮ የመነሳት ምልክት ነው፡፡ ትልቅ ምልክት ነው፡፡ ሰው በግል መብቱ ከመጡበት የብሔርና የጎጥ አጥር እንደማይከልለው ማሳየት ችሏል፡፡ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ የብሔር ፖለቲካን መቅኖ ያሳጣ ተግባር ነው፡፡ ትልቅ ማነቃቂያ ደወል ነው - ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለተቃዋሚዎቹ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከታዩት የትግል ስልቶችም ሁሉ በይዘቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከአርባ አምስት አመታት ወዲህ፣ የብሔረተኝነት አደጋን ተሻግሮ ወደሰውነት ደረጃ የደረሰ ትግል ከተባለም በዋናነት መጠቀስ እንደሚችል እንተማመናለን፡፡
ልናጠቃልል ነው፡፡ ተቃዋሚዎችን የሚያስተሳስሯቸውን ጉዳዮች ጠቅሰናል፡፡ የምርጫ ቦርድ ጉዳይ፣ የገለልተኛና ፍትሐዊ መገናኛ ብዙኃንና የፖሊስና ፀጥታ እንዲሁም የመከላለያ ሠራዊቱ ገለልተኛነት ጉዳዮች፣ ብሎም እየወጡ ያሉት ሕጎችና ደንቦችን በተመለከተ መተባበር እንደሚችሉ ጠቁመናል፡፡ በአንጻሩም፣ የድምፅ ከበርቴነት አስተሳሰብ፣ የሥልጣን አባዜና የፈላጭ ቆራጭነት አመለካከቶች እንዲሁም ለፖለቲካው አሰላለፍ የሚያዋጣውን የአደረጃጀትና የአሰላለፍ ችግሮች ጠቁመናል፡፡ በእነዚህም ችግሮች ላይ ብርቱ እርምትና ማስተካከያዎች ካልተወሰዱ ገዢው ፓርቲ እንደሚዝተው ቀጣዮቹም የምርጫ ዘመኖች ያለውጤት ይጠናቀቁ የሆናል፡፡ “ዲሞክራሲ! የሕግ የበላይነት! ነፃነት!” እያለ የሚጮኸውም ሕዝባችን ሮሮና ዋይታ እንደሚቀጥል ጥርጥር የለንም፡፡ ጊዜው አሁን ነው፤ በምርጫ ቦርድ ጉዳይ የተጀመረው ሕብረትና ትብብር ወደላቀ ደረጃ እንዲያድግ የሁሉም ዜጎች የጋለ ፍላጎት ነው፡፡ (መልካሙን ሁሉ እንመኝላችኋለን!)
No comments:
Post a Comment