Tuesday, May 26, 2015

መጀገን- በምርጫ ቀን

(ሀብታሙ ስዩም እንደ ጻፈው)

ከወረቀቱ አናት ላይ እንዲህ ተጽፏል፡፡‹‹ለመምረጥ በሚፈልጉት ፓርቲ ምልክት ፊት ለፊት የ ‹ኤክስ› ምልክት ያድርጉ፡፡››በወረቀቱ ላይ የተደረደሩ ፓርቲዎችን ስምና ምልክታቸውን በቀስታ ቃኘ፡፡በመጀመሪያው ረድፍ አመልካች ጣት፣ሁለት ጣት ፣አምስት ጣት ….በሌላኛው ረድፍ ፈረስ፣ንብ፣አበባ …አየ፡፡አገጩን ተደግፎ ፈገግ አለ፡፡ፊት ለፊት በሚተያዩት ምልክቶች መካከል ሳይቀር ፍጥጫ ያለ መሰለው፡፡አመልካቹ ጣት ሰጋሩን ፈረስ ቀጭን ትዕዛዝ ለመስጠት የተቀሰረ አይነት ነው፡፡ሁለት እግሮቹ አየር ላይ ሁለት እግሮቹ ምድር ላይ ያለው ፈረስ ደግሞ እንጃልህ እያለ እየጎፈላ ነው፡፡ ሁለቱ ጣቶች ንቧን ይዘው ሊያልዘምዟት የቋመጡ እንደሆኑ ያሳብቅባቸዋል፡፡ንቧ  በሚጠጋ ጣት ላይ ነዝናዥ እሾኋን ለመቀብቀብ እንደ ቆረጠች አይነት ተነፋፍታለች፡፡ አምስቱ ጣቶች አበባዋን ለመቀንጠስ የሆነ አጋጣሚ ብቻ የሚፈልጉ አይነት ናቸው፡፡የአበባዋ መዝመም በጣቶቹ ውስጥ ላለመግባት እንደመሸሽ አይነት ሆነበት፡፡
‹‹ወንድሜ ቶሎ ምረጥና ቦታ ልቀቅ እንጂ ብዙ መራጮች እኮ እየጠበቁ ነው፡፡›› የሚል ድምጽ በሚስጢር ድምጽ መስጫዋ ጠባብ ክፍል የጨርቅ ግድግዳ አልፎ ተሰማው፡፡ከያዘው የሃሳብ መዋለል ራሱን አነቃና እስኪርቢቶውን አቀባበለ፡፡
‹‹ማንን ልምረጥ?›› ለራሱ አንሾካሾከ፡፡እናቱ ትዝ አሉት፡፡የብዙ አማራጮች ንግስት የተለዩ ፍልስፍናዎች ግምጃ ቤት የሆኑት እናቱ ያወሩት መሰለው፡፡
‹‹እኔ በበኩሌ አባ ዮሴፍን ብትመርጣቸው ደስ ይለኛል፡፡››
‹ማናቸው አባ ዮሴፍ›
‹‹እኚህ ከዳቦ ቤቱ ጎን ባለው ቤት ውስጥ የሚኖሩት ሰውዬ ናቸዋ፡፡››
‹‹እንዴት ነው የትምህርት ደረጃቸው?››
‹‹መቸም ከአባዱላ አያንሱም››
‹‹ከህዝብ ጋር ለመጮህ ዝግጁ ናቸው?››
‹‹ሚሰማቸው ከተገኘ!››
‹‹ለምንድነው እሳቸውን እንድመርጥ የፈለግሽው?››
‹‹እንጃ እንዴው ሳያቸው አንጀቴን ይበሉኛል፡፡ጡሮታ ከወጡ በኃላ እንቅልፍ ያላቸውም አሉ፡፡››
‹‹እና ፓርላማ እንዲገቡ የምመርጣቸው እንዲንቀለፉ ነው?››
‹‹መቸም ከዚህ የተለየ ሲያደርግ ያየነው የፓርላማ አባል የለም፡፡››
አባዮሴፍን የማይመርጥበት ምክንያት ምልክታቸውን ሳላልወደደው ነው፡፡የአባ ዮሴፍ የምርጫ ምልክት ሰባት ቁጥር ነው፡፡የመንግስት ደጋፊዎች ለምን ሰባት ቁጥርን ተጠቀምክ ሲሏቸው ‹‹ደደቢት በረሃ የገቡትን የመጀመሪያ ሰባት ታጋዮች ለማሰብ ነው ይላሉ፡፡የመንግስት ጠላቶችን በሚያገኙ ጊዜ ታሪኩን ይቀይሩታል ‹የጀግኖች ስብስብ የሆነውን ግንቦት 7ን› ለማስታወስ ነው ብለው ይሸውዳሉ፡፡እንደ እማየ ያሉትን ከቤተመንግስት  ይልቅ የቤተ ክርስቲየን ጉዳይ የሚመስጣቸውን ሰዎች ሲያገኙ ደግሞ‹ ወር በገባ በሰባት የሚውሉት ስላሶች ከጎኔ ናቸው ለማለት ነው››  ብለው አንጀት ይበላሉ፡፡
እሱ ግን ሰባት ያለበት ነገር በጤና ተጠናቆ ስለማያውቅ አልራራላቸውም፡፡ማስረጃ አቅርብ ቢባል 67ን ይጠቅሳል- ወጣት እንደ ስጦ አስፓልት  የሸፈነበትን ዓመት፡፡77ን ያነሳል- ርሃብ  እንደ ቄጠማ ትውልድ የረመረመበት አመትን፡፡87ን ያስታውሳል- አጎቱ ከነ መፈክሩ ስድስት ኪሎ በር ላይ የተደፋበትን፡፡97ን ይጠቅሳል – እሱና ወዳጆቹ ደዴሳ የከረሙበትን፡፡ዘንድሮ ደግሞ—-እንጃ እንግዲህ፡፡ብቻ ላይመርጣቸው ምሏል፡፡
አሁንም ወረቀቱ ላይ እንዳቀረቀረ ነው፡፡እስኪርቢቶውን በጣቶቹ መሃል ያሽከረክራል፡፡የምርጫ አስተባባሪው ድምጽ በድጋሚ አባነነው፡፡
‹‹ኧረ ወንድሜ ፈጠን በልና ጨርስ፡፡ብዙ ሰው እኮ አንተን ነው የሚጠብቅ፡፡››
‹‹እሺ ትንሽ ታገሰኝ…››መልሶ የምርጫ ምልክቶችን ይመረምር ገባ፡፡
‹‹ማንን ልምረጥ ?›› የእናቱ ድምጽ በድጋሚ  መጣበት፡፡
‹‹ኢህአዴግን ብትመርጥ ይሻላል፡፡››
‹አብደሻል?››
‹‹ባብድ በምን እድሌ ! ዘንድሮ እብድ እና ሰካራም ብቻ አይደል የልቡን እንዲናገር የተፈቀደለት›
‹‹ለምንድነው ኢህአዴግን የምመርጠው…?››
‹‹መረጥከውም አልመረጥከውም ጎረምሳው መንግስት ምርጫውን ማሸነፉ አይቀርም፡፡አንተ ባትመርጠው አንዳች ነገር አይጎድልበትም፡፡እንደሚባለው በየምርጫ ጣቢያው ስውር ካሜራ ካለው  ደግሞ ይሄ ውሳኔህ ኮንደሚኒየም አልባ እና ምልምል ሽብርተኛ ያደርግሃል፡፡ለበለጠ ጦስ እራስን ከማመቻቸት ‹ደስ ይበላችሁ ያው መረጥኳችሁ ብሎ ማለፍ ይሻላል፡፡እነሱ እቴ ከስልጣን ወንበር ጋር አብረው ተሰፍተው እንኳን ህዝብ ቸሩ መድሃኒያለም ሰቅስቆ የሚያነሳቸውም አይመስሉም፡፡››
‹‹እማዬ ምርጫ ጣቢያ ውስጥ ካሜራ የለም፡፡››
‹‹አትሞኝ ልጄ፡፡በሁሉም ቦታ የስለላ መሳሪያ አላቸው ፡፡ሌላው ይቅር በስልክ ምትነጋገረውን ሁሉ ጠልፈው ያዳምጣሉ፡፡ይሄን ያልኩት ካለ ማስረጃ አይደለም፡፡ባለፈው እንጀራ እየጋገርኩ ከማስረክበው ነጋዴ ጋር በስልክ እያወራሁ ነበር፡፡100 እንጀራ በ3 ብር ሂሳብ ስንት ይሆናል የሚለውን ለማስላት ያ እንከፍ ነጋዴ ግማሽ ሰዓት ፈጀበት፡፡በመሃል ሲያዳምጠን የነበረው ሰላይ ተናደደ መሰል ከየት ገባ ሳንለው በዝምታው መሃል ጥልቅ ብሎ  ‹‹አንት ደነዝ ማባዛት ሳትችል ነውንዴ ብር የምትቆጥር›› ብሎ ልብሱ እንዳይቀር አድርጎ ሞለ ጨው፡፡››
ኢህአዴግን እንዳይመርጥ የወሰነበትን ምክንያት ብዙ ነው፡፡በዚህ ሰው ጭንቅላት ውስጥ ኢህአዴግ የሚለው ቃል ከታላላቅ ስድቦች ጋር ይመሳሰልበታል፡፡በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛው ከስድቦች ሁሉ ትልቁ ‹ባለጌ› የሚለው ነው ብሎት ነበር፡፡እንደ ጓደኛው አነጋገር ባለጌ የሚለው ቃል ውስጥ የማይወድቅ መጥፎ ድርጊት የለም፡፡ሌብነት ‹ባለጌነት› ነው፡፡ሰካራምነት ‹ባለጌነት› ነው፡፡ነውረኝነት ‹ባለጌነት› ነው፡፡ሆዳምነት፣ጨካኝነት ፣አይረቤነት ባለጌነት ነው፡፡ታሪክ አዋራጅነት፣ትውልድ ሻጭነት፣ህልም አምካኝነት ‹ባለጌነት› ነው፡፡ከብዙ አመታት በኃላ ባለጌ የሚለውን ስድብ የሚበልጥ ስድብ እንደተፈጠረ ይሄ ሰው ያምናል፡፡ያም ስም ‹ኢህአዴግ› የሚለው ቃል ነው፡፡
ኢህአዴግን ለመምረጥ የማይፈልገው ለዚሁ ነው፡፡ቢሆንም እናቱ ያሉትን ስጋት መርሳት አይቻልም፡፡ካቀረቀረበት ቀና ብሎ ዙሪያውን ቀኘ ከጠባቧ የድምጽ መስጃ ጣሪያ ላይ ካሜራ መኖር አለመኖሩን አረጋገጠ፡፡ካሜራ የለም፡፡ስለሆነም ኢህአዴግን ባለመመረጥ ውሳኔው ጸንቶ ወደ ሌሎቹ ምልክቶች አቀረቀረ፡፡
የስኪርቢቶውን ክዳን እያኘከ በዝምታ ቆየ፡፡የቱን ፓርቲ እንደሚመርጥ ግራ ገባው፡፡የእናቱ ድምጽ ዳግም ተመለሰ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ህዝቦች መጽናኛ ፓርቲን ምረጥ፡፡በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ስልጣን ከያዝን የመጀመሪው ስራችን የቀድሞ ባለ ስልጣናትን ልብሳቸውን አስውቆ አርባ መግረፍ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡››
‹‹እነሱን አልመርጣቸውም…››
‹‹ለምን?››
‹‹ ሬድዋን ሁሴንን ማን ራቁቱን ያያል፡፡ለብሶም ይዘገንነኛል፡፡››
‹‹እሺ የኢትዮጵያ ህዝቦች ምኞት ህብረትን ምረጥ፡፡የሀገሪቱ ችግር የጓድ መንግስቱ አለመኖር ስለሆነ እሳቸው እንዲመለሱ እናደርጋለን ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ፡፡››
‹‹እነሱንም አልመርጣቸውም፡፡››
‹‹ምን አጠፉ?››
‹‹መንግስቱ ሃ/ማሪያም እኮ አሁንም ስልጣን ላይ አለ፡፡ትንሽ ቁመትና ሞኝነት ጨመረ እንጂ ››
‹‹ምን ደህና ደህና ሰዎችን ለቃቅሞ እስር ቤት ከትቶብን አኮ ነው ለምርጫ የተቸገርነው፡፡የዘንድሮው ምርጫ እኮ መካሄድ የነበረበት ቃሊቲና ዝዋይ ነበር፡፡ባዶ የዕጣ ጥቅሎችን በትሪ ላይ እያንጓለሉ ‹‹በሉ አንዱን ምረጡ›› አይነት ጨዋታ ሆነብን እኮ፡፡ለምን የሰገሌ ህዝቦች ነጻ አውጪ ፓርቲን አትመርጥም…››
‹‹ደግሞ እሱ የትኛው ፓርቲ ነው?››
‹‹ይሄ ካሸነፍኩ የሰገሌ ህዝቦችን ከመላ ሃገሪቱ እገነጥላለሁ ያለው ነዋ፡፡››
‹‹እሱን ታዲያ በቦክስ መገንጠል እንጂ የምናባቱ ድምጽ መስጠት ነው፡፡እስቲ ወንድ የሆነ ይገነጠላታል፡፡ከሚስቱ የተኮራረፈ ሁሉ መኝታ ቤቴን ይዤ እገነጠላለሁ ሊል ምንም አልቀረውም እኮ፡፡ ሌሎች ነፍስ ያላቸው ፓርቲዎች የሉም?››
የእናቱ መልስ አይጠፋውም -አሉ፡፡ግን ቢያሸንፉም አያሸንፉም፡፡እንቅልፋሙን ፓርላማ እንቅልፍ የሚነሱ ጥሩ ምሁራን ነበሩ፡፡የተናገሩት አድማጭን ሚያሳድግ የሚሰነዝሩት ተመልካችን የሚያነቃ ጎበዝ ሊቆች ነበሩ፡፡ህዝብ በጅምላ እንዳልመከነ የሚያሳዩ ናሙናዎች አሉ፡፡ሁለት አይነት ሰዎች አሉ፡፡አንደኞቹ ከሚበልጣቸው ሊቆች  ጋር እየዋሉ እራሳቸውን ለመስተካከል የሚጥሩ፡፡ሁለተኞቹ የሚበልጣቸውን ሊቅ አሰደድደው ‹እኔ ነኝ የቀረኋችሁ ሊቅ !›የሚሉ፡፡መንግስት ከሁለተኛው ይመደባል፡፡ባለው ሃቅም ልሂቃኑ ከአጠገቡ እንዳይቀመጡ ይተጋል፡፡የምርጫ ወቅት ይሄ የመንግስት ኢያጎአዊ ጠባይ የሚገለጥበት ነው፡፡ሚሊየን ሰው ልሂቃኑን ይምረጥ ቢሊየን አውጥቶ ድምጻቸውን ይዘርፋል፡፡
‹‹እንደዚህ ከሆነ ለምን እመርጣለሁ!›› አለ በድንገት፡፡
‹‹ድምጼ የማይቆጠር -ሃሳቤ የማይከበር ከሆነ ለምን እመርጣለሁ?››
‹‹ለአለም በሚያሳዩት የሳውቅዮሽ አውጫጭኝ መሃል ለምን እዳክራለሁ?››
‹‹በባሩድና በሚታጠን በድንጋይ በሚከበብ ወር መሃል ስለምን እቆማለሁ?››
የድምጽ መስጫ ወረቀቱን አጣጥፎ በኪሱ ከተተ፡፡እስኪርቢቶውን በደረት ኪሱ ውስጥ አስገባ፡፡ከተከለለው ጠባብ የድንኳን ክፍል ሊወጣ ተሰናዳ፡፡
የእናቱ ድምጽ መጣበት
‹‹ሊቢያ ላይ የተሰውት ወጣቶች ገዳዮቻቸውን አሳፍረው ሞሞታቸውን ሰማሁ ልበል?››
‹‹አዎ እማዬ አለም እያወራበት ነው፡፡በሞት አፋፍ ላይ ሆነው ሁሉ ጠላቶቻቸው ይፈልጉት የነበረውን ፍርሃት እና ለቅሶ እና መሰበር ሳያሳዩ ማለፋቸው ብዙ ሰውን አስገርሟል፡፡››
‹‹ አየህ ቶሎ አልተገለጠልንም እንጂ – ጀግንነት ጠላትህ ከሚፈልገው ተቃራኒ ቆሞ በማሳየትም ይገለጣል፡፡አቀርቅር በሚባልበት ሰዓት ቀና ማለት ጀግንነት ነው፡፡ዝምበል በተባልክበት ሰዓት መናገር ጀግንነት ነው፡፡ቁም በተባልክበት ሰዓት መራመድ ጀግንነት ነው፡፡እርምህን አውጣ በተባልክበት ሰዓት ተስፋህን ማሳደግ ጀግንነት ነው፡፡ትልቁ ሞት ሳይሞክሩ መሞት ነው፡፡››
የድምጽ መስጫ ወረቀቱን ከኪሱ አወጣ፡፡እስኪርቢቶውን ከደረት ኪሱ መዘዘ፡፡በምልክቶቹ ላይ አይኑን አበረረ፡፡ከሆነ ምልክት ፊት ለፊት ባለው ሳጥን ውስጥ የኤክስ ምልክት አደረገ፡፡
ምልክቱን ከገዥው ፓርቲ ምልክት ፊት ለፊት አለማድረጉን ያውቃል፡፡
ባለጉም ሃሳቦች ከመሰረቷቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፊት ለፊት አለማድረጉን ያውቃል፡፡
ሲረገጡ መሬት ይዘው የሚነሱ ሊሂቃን እና ተስፋዎች የተሰባጠረው ፓርቲ ፊትለፊት ምልክት ማድረጉን ብቻ አረጋጧል፡፡የድምጽ ወረቀቱን አጣጥፎ ፈንጠር ብሎ በሚገኘው ሳጥን ውስጥ ጨመረው፡፡በር ላይ ከምርጫ አስተባባሪዎች አንዱ ‹በሰላም ነው ብዙ ጊዜ ፈጀብህ እኮ ….›› ሲል ስሞታ አቀረበበት፡፡
‹‹አንዳንዴ ለመጀገን ጊዜ ይፈጃል›› ብሎት ከምርጫ ጣቢያው ራቀ፡፡

No comments:

Post a Comment