Tuesday, February 19, 2013

የሠራዊቱ ቀንና የሠራዊቱ ክብር

 

                      

ሰሞኑን የመከላከያ ሰራዊት ቀን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡ “የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን” ተብሎ በመንግስት ዕውቂያ መጀመሩም መልካም ጀምር ነው፡፡ ነገር ግን፣ ከ1983 ዓ.ም በፊት ኢትዮጵያ ምንም የመከላከያ ሠራዊት እንዳልነበራት አድርጎ የማቅረብ ችግሮች በመገናኛ ብዙኃኑም ሆነ በመከላከያ ሠራዊቱ ቃል-አቀባዮች ዘንድ ይንጸባረቃል፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ እንዲያማ ከሆነ፣ የአህመድ ግራኝን ወረራ ማን መከተው? ከደቡብ ተነስቶ ወደመሃል አገርና ወደሰሜን ይገሰግስ የነበረውን የሉባዎቸ ጦር ማን ተዋካው? የኦቶማን ቱርክን፣ የግብጹን ፓሻህ እና የመሃዲስቶቹን ጦር ማነው መክቶ የመለሰው? ኧረ ማንን ሊዋጋ ነው ጄኔራል ናፒዬር ከህንድ ድረስ የመጣው? ማነው የመተማውን ውጊያ የተፋለመው? መነውስ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ወድ የሌለውንፀ ድል አድዋ ላይ የተቀዳጀው? ለመሆኑ ማነው የፋሺስቶችን ግፍና መርዝ ጋዝ ተቋቁሞ ሀገሩን ነፃ ያወጣው? ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም በፊት የመከላከያ ሠራዊት ካልነበራት ወያኔና ሻዕቢያ አዲስ አበባንና አስመራን ለመያዝ ለምን አስራ ሰባት ዓመታት ፈጀባቸው? መልሡ ቀላል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስለነበራት ነው፡፡
ኢትዮጵያ እንኳን በ20ኛው ክፍለ ዘመንና ጥንትም ሠራዊት ነበራት፡፡ በ1983 ዓ.ም ወያኔ/ኢሕአዲግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ አራት መቶ ዓመት በፊት የነበረውን የኢትዮጵያ ሠራዊት አውድ፣ አባ ባሕርይ እንዲህ ሲሉ ዘግበውታል፡፡ በ1583 ዓ.ም ሙልአታ የተባለው የቢፎሌ ልጅ፤ ዘጠነኛው ሉባ ሆኖ ተሾመ፡፡ የዚያን ጊዜ፣ ጦርነቱ የመሬት ወረራ፣ የሰው ምርኮና የወደደውን ደግሞ በጉዲፈቻና በሞጋሳ መቀበል ብቻ አልነበረም፡፡ “የቁንዳላ ጦርነትም” ተካሄደ፡፡ ይህም የቁንዳላ ጦርነት ጎጃምን፣ ሸዋንና ዳሞትን በእጅጉ ጎዳቸው፡፡ ወደምዕራብ አቅጣጫም ተስፋፍቶ ከፍተኛ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከተለ፡፡ ከአርባ አምስት ዓመታት በፊት ከተደረገው አህመድ ግራኝ ካስከተለው ቀውስ የማይተናነስ ቀውስ ተከተለ፡፡ በዚህ ወቅት ንጉሡ ሠርፀ ድንግል ሠራዊቱን ይዞ አንዴ ደቡብ አንዴ ሠሜን ሲራወጥ ነበር፡፡ ሉባ ሙልአታ የተመከተው በራስ ወልደ ክርስቶስ በቤጌምድር ላይ ነበር፡፡ በተረፈ ግን ደል ወደ ሉባ ሙልአታና ወደርሱ ጦር ያጋደለ ነበር፡፡
የዚህ ጊዜ ታዲያ በዘመኑ የነበረውና የነሉባ ሙልአታን ወረራና የንጉሥ ሠርፀ ድንግልን በአራቱም አቅጣጫ የሚራወጥበትን ችግር ምክንያት ለመረዳት የፈለገው አባ ባሕርይ ሊጽፍ ሲነሳ እንዲህ ብሎ ጠየቀ፡፡ “በአፎ ይመውአነ ሙልአታ እንዘ ብዙኃን ወብዙኅ ንዋየ ጸብዕነግ (ማለትም፣ እንዴት ነው የሙልአታ ጦር እኛ (የክርስቲያኖቹ ጦር አባላት) ብዙ ሆነን ሳለ፣ የጦር መሣሪያችንም ብዙ ሆኖ ሳለ የተሸነፍነው?)” ሲል አደገኛውን ጥያቄ ከ400 ዓመታት በፊት ይጠይቃል፡፡ መልሱንም ለመስጠት አይዘገይም፤ ለዚህ ዋናው ምክንያት “የክርስቲያኖቹ ደንብ” እና የሕብረተሰቡን አደረጃጀት አብራርቶ ይገልጥልናል፡፡ “ከአሥሩ ደንብ ውስጥ አንዱ ብቻ ነው ተዋጊ ሆኖ የሚወጣው፡፡ ዘጠኙ ደንብ በቀጥታ ከጋሻ ጃግሬነትና ከውትድርና ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤” ሲል ያትታል፡፡ አንፃሩ ግን፣ “በሙልአታ የሚመራው ወራሪ ኃይል ከሕዝቡ አብላጫው (ከግማሽ በላይ) የሚሆነው ተዋጊ ስለሆነ ነው፤” ሲል ያጠቃልላል፡፡
አባ ባሕርይ እንዳተተው የክርስቲያኑ ጦር የተደራጀባቸው ዐስሩ ደንቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡ አንደኛ፤ መነኮሳት ናቸው፡፡ እነዚህም ቁጥራቸው ብዙ ነበር፡፡ ዋና ተግባራቸውም ጸሎት ማድረግ ስለሆነ ዘመቻ አይወጡም፡፡ ሁለተኛ፤ ደባትር ናቸው፡፡ እነዚህም ሥራቸው በማኅሌትና በዝማሬ እግዚአብሔርን ማመስገን ስለሆነ ዘመቻ አይወጡም፡፡ ሦስተኛ፤ ዣን ሐፀናና ዣን ማሰሬዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ዋና ሥራቸው ወንበርተኞች/የወረዳ ወይም የቀበሌ ካድሬዎችና የቀላድ ጣዮች ስለሆኑ ዘመቻ አይወጡም፡፡ አራተኛ፤ የሴት ወይዛዝርት ደጋፊዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ወይዘሮዎችን ማጀብ ስለሆነ ሥራቸው ለዘመቻ አይወጡም ነበር፡፡ አምስተኛዎቹ ደንበኞችም፤ ሽማግሎች ናቸው፡፡ እነዚህም “ወባዜ” ይባሉ ነበር፡፡ ዋና ሥራቸው ርስት ማካፈል ብቻ ስለነበረ፤ ወደዘመቻ አይወጡም ነበር፡፡ ስድስተኛ፣ አራሾች ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ከእርሻ በስተቀር ሌላ ሥራ አያውቁም ነበር፡፡ ሰባተኛ፤ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ መሸጥና መለወጥ እንጂ ውጊያን ስለማያውቁ ዘመቻ አይወጡም ነበር፡፡ ስምንተኛ፤ የእጅ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ በሽመና፣ በቀጥቃጭነትና በአንጥረኝነት እንዲሁም በልዩ ልዩ ሥራዎች ይሰማራሉ እንጂ ወደዘመቻ አይሄዱም ነበር፡፡ ዘጠነኛው ረድፍ ላይ ያሉት ደንበኞች ደግሞ፤ የኪነት ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ በአዝማሪነትና በአመሸታ ቤት ይሆናሉ እንጂ ወደዘመቻ ለውጊያ አይሄዱም ነበር፡፡ዐሥረኞቹና የመጨረሻዎቹ፣ ጋሻ ጃግሬ የሚባሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ወታደሮች ናቸው፡፡ ዋና ሥራቸውም ውጊያ ነበር፡፡ ይህም የመጨረሻው ደንብ ቁጥሩ አነስተኛ ስለነበረ፤ “ጠፍአት ሀገርነ (አገራችን ጠፋች)” በማለት አባ ባሕርይ ይደመድማል፡፡
ከ1583 እስከ 2005ዓ.ም ድረስ ቢያንስ አራት መቶ ሃያ ሁለት (422) ዓመታት ያህል ተቆጥረዋል፡፡ ያም ሆኖ፣ ኢትዮጵያ ካሳለፈችውና ካደረገቻቸው መራራ የነፃነትና የሉዓላዊነት ትግሎች አንጻር ገና “ብቁና ንቁ የመከላከያ ሠራዊት” አላደራጀችም፡፡ ቀድሞም ሆነ አሁን የመከላከያ ሠራዊቱ በግለሰቦች ጥላ ሥር ነው ያለው፡፡ ያኔም “የራሶችና የደጃዝማቾች ጦር” ነበር፤ አሁንም በዚያው መንገድ ላይ እየተጓዘ ነው፡፡ ያኔም ሆነ አሁን፣ ራስ አመልማሎች፣ ራስ ወልደ ክርስቶሶች፣ ራስ አሊዎች፣ ደጃች ውቤዎች፣ ደጃች ካሳዎች፣ ፊታውራሪ መሸሻዎችና ፊታውሪ አሰጌዎች አሉ፡፡ ጦሩ/ሠራዊቱ ገና የኢትዮጵያ ጦር ሆኖ አልቆመም፡፡ አሁን የምናየው፣ የሕወሃት/ወያኔ ጦር፤ የብአዴን/ኢሕአዲግ ጦር፤ የአሕዲድ/ኢሕአዲግ ጦር የሚባለውን ከራሶችና ከደጃዝማቾች ወደ ፓርቲ-ራስነትና ደጃዝማችነት የተለወጠውን ነው፡፡ ማለባበስ አንፈልግም፡፡ ሀቁን አውቀን ወደፊት ልንራመድ ይገባናል፡፡
ይሄው ጦር በሰሜን፣ በምስራቅና በምዕራብ በኩል ደሙን እያፈሰሰ ሳለ፤ ለምን በግለሰብ “ራዕይ” ላይ ተንጠልጠል እንደተባለም አልታየንም፡፡ ጦሩ፣ አሁንም ቢሆን ቅድመ 1983 ዓ.ም በነበረው ቅርጹና መልኩ እንዲደራጅና እንዲሄድ የመፈለግ ዝንባሌ አለ፡፡ ይህም ዝንባሌ በሠራዊቱ አባላትና መኮንኖች የተመከረበት ሳይሆን በፖለቲከኞቹ የተጫነበት ነው፡፡ በጥቂት የፓርቲን ጥቅምና የሀገርን ጥቅም በሚያቀላቅሉ ወገኖች የተደረገ ረብ-የለሽ ተግባር ነው፡፡ ይሄውም ተግባር የሚገለጥባቸው ወሳኝ ነጥቦች አሉ፡፡ በዋናነት ሥስት ናቸው፡፡ አንደኛ፤ ከፍተኛውን የወታደራዊ ሥልጣን የመቆጣጠር አባዜ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ከሙሉ ኮሎኔል በላይ ባለው የወታደራዊ ማዕረግ አሰጣጥ ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ ከብርጋዴር ጄነራል ማዕረግ ጀምሮ የሚፈቀደው ለሥርዓቱ ታማኝ መሆናቸው ለተረጋገጠላቸው ሰዎች እንጂ (በአገልግሎት ወይም በጀብዱ አፈጻጸም) የሚሰጥ አይደለም፡፡ በዚህም መስፈርት መሠረት ካየነው አብዛኛውን ቦታ የተቆጣጠሩት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ከአንድ ፓርቲ የመጡና የሥርዓቱ ታማኞች ሆነው እናገኛቿቸዋለን፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው፣ በፓርቲ ስም የተደራጁ ራሶች፣ ደጃዝማቾችና ፊትአውራሪዎች የማዘጋጀት አዝማሚያ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃም የሚነሳው ነጥብ፣ ስለሠራዊቱ “ሁሉንም ልቆጣጠር፣ ሁሉንም ልሽጥ-ልሸቅጥ” የሚለው አባዜ ነው፡፡ ይህም ከላይ ከጠቀስነው ከፍተኛውን ወታደራዊ ሥልጣን ከያዙት የአንድ ፓርቲ/ራስና ደጃዝማቾች የግል ጥቅምና ፍላጎት ጋር የተሣሰረ አደጋ ነው፡፡ በቀጥታ ከገንዘብና ከጥቅም ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ብዙዎቹ ግዙፍ የመዋለ-ንዋይና የቴክኖሎጂ አቅምን ይዘው የተደራጁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመከላከያ ብረታ-ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን፣ የላሊበላ ኮንስትራክሽንን መውሰድ እንችላለን፡፡ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የምዕዋለ-ንዋይ አላቸው፡፡ ሆኖም ግን ከፍተኛ አመራራቸው ከቅድመ 1983 ዓ.ም በፊት ከነበረው መንፈስ ብዙም የራቀ አይደለም፡፡ የአንድ ቡድን የበላይነት ጎልቶ ይታይበታል፡፡ ከጥበቃ እስከ ባለሙያና የመምሪያ ኃላፊዎች ድረስ የአንድ ቡድን/ፓርቲ የጎላ ቁጥጥርና ርብርብ ይንፀባረቅበታል፡፡ ለምን ኢትዮጵያዊ እንዲሆን አይደረግም? ለምንስ የአንድ ቡድን/ፓርቲ ቀልብና መንፈሥ ብቻ እንዲንጸባረቅበት ተፈለገ? ለመሆኑ የእስራኤልን ወይም የግብጽን መከላከያ ሞዴል አድርጎ መነሳቱ ባልከፋ፡፡ ነገር ግን፣ ለምን እንደስራኤልና እንደግብጽ ሀገራዊ ቅርጽና መልክ እንዲኖረውስ አልተደረገም? መልሱ ቀላል ነው፡፡ የራሶችና የደጃዝማቾች መንፈስ ዛሬም ስላለ ነው፡፡ ሁሉም በየፊናው “ዘመናዊ ፊታውራሪ” ለመሆን ቋምጧል፡፡
ወደሦስተኛው ችግር እንለፍ፤ ይሄውም ከጦሩ/ከሠራዊቱ አባላት ክብር፣ መብትና ጥቅም ጋር የሚነሳ ነው፡፡ መከላከያው ከፍተኛ የሆነ የጥቅምና የመብት አለመከበር ችግሮች አሉበት፡፡ ብዙኃኑ የመከላከያው ሠራዊት ወታደራዊ አባላት ክፍያ የሚያተጋ አይደለም፡፡ ሌላውን ትተነው እንኳን የመሥመራዊ መኮንኖች (ከም/መ/አለቃ እስከ ሻምበል ያሉት) ደሞዝ ከ2300.00 ብር ያነሰ ነው፡፡ የአንድ ኮሎኔልም ደሞዝ ቢሆን እምብዛም ነው፡፡ ኧረ! ከእጅ-ወዳፍ ነው ቢባልም ማጋነን አይሆንም፡፡ ስለሆነም፣ የሠራዊቱ አባላት ከፍተኛ የሆነ የጥቅም አለመከበር ችግር አለባቸው፡፡ ጥቅማቸው ባለመከበሩም፣ ከፍተኛ የሆነ የመብትና የክብር ጥያቄዎችን በየስብሰባዎቹ ላይ እንደሚያነሡም ይታወቃል፤ ከፍተኛ አመራሮች የሚሠጡት መልስ ግን አጭር ነው፡፡ “መንግሥት በጀት የለውም!” የሚል ነው፡፡ ይህ በርግጥ አሳማኝ አይደለም፡፡ ምክንያቱም፣ ሠራዊቱ ካለበት ኃላፊነትና ካለበት የሀገርን ሉዓላዊነት የማስከበር አደራ አንጻር ዝቅተኛ ነው፡፡ በተለይም፣ ለነፍሱ ሳይቀር ሳይሳሳ ለሚያደርገው ተጋድሎው የሕይወትም ሆነ የአካል መጥፋትና መጉደል ዋስትናና መድን (Inesurance) የሌለው ምስኪን መሆኑን ለሚያውቅ ሰው ምን ያህል የሠራዊቱ-ክብር፣ መብትና ጥቅም እንዳልተከበረ ይረዳል፡፡
ሌላም ተያያዥ ችግር አለ፡፡ ይኼውም በሠራዊቱ ውስጥ ካሉት የተማሩ ሙያተኞች ጥቅምና መብት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህንን ሃሳብ በምሳሌ ማስረዳቱ ያዋጣል፡፡ አንድ የማስተርስ ዲግሪ ያለው የትኛውም የመከላከያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለ ባለሙያ የሚከፈለው ደሞዝ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የደሞዝ ስኬል መሠረት ነው፡፡ የቤት አበልም አለው፡፡ በአጠቃላይ አንድ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለ የሲቪል ባለሙያ የሚከፈለው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለ ማንኛውም የማስተርስ ዲግሪ ምሩቅ የሚከፈለውን ደሞዝ ነው፡፡ ነገር ግን፣ አንድ የመከላከያ የኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠራ መሳሳይ የት/ት ደረጃ ያለው ባለሙያ ከዚህ በጣም ያነሰ ክፍያ ነው ያለው፡፡ ለምን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ በወሰነው መሠረት እንደማይከፈላቸው የተብራራ ነገር የለም፡፡ ዋናው ምክንያት ግን፣ “የከፍተኛ መኮንኖች ደሞዝ ስንት ነው?” የሚለው ነው፡፡ እጅግ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ በተለይም በፋይናንሻል ተቋማት (በባንኮች፣ በኢንሹራንስ ተቋማት)፣ በግንባታ ድርጅቶችና በመንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ያሉ ኃላፊዎች ከሚከፈላቸው ጋር ካነጻጸርነው እጅግ አናሳ ነው፡፡
ይህንንም ጉዳይ በምሳሌ ብናወሳው ሳይሻል አይርም፡፡ አንድ የግል ባንክ ውስጥ የሚሠራና በሥሩ አራት መቶ ሃምሳ የማይሆኑ ሰራተኞችን የሚመራ የባንክ ሥራ-አስፈጻሚ ከሠላሳ ሺህ ብር በላይ ይከፈለዋል፡፡ በዚያ ላይ ቢያንስ ሁለት መኪናዎችና የቤት አበል፣ እንዲሁም የተለያዩ ጥቅማ-ጥቅሞች አሉት፡፡ ይህ ሰው ልጆቹን የተሻለ ትምህርት ቤት ልኮ ያስተምራል፡፡ ዘመዶቹ ሲመጡ የቻለውን ያህል የሚረዳበት ገንዘብም አለው፡፡ መስረቅም ሆነ ሙስና ውስጥ መግባቱ (ዓመል ካልሆነበት በስተቀር) እምብዛም አያስፈልገውም፡፡ አንድ የዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሠራም የብሔራዊ ድርጅት ሥራ-አስኪያጅ ከሠላሳ ሺህ ብር በላይ የከፈለዋል፡፡ እንደባንኩ ሥራ-አስፈጻሚ ሁሉ፣ የመኪና፣ የቤትና የተለያዩ ጥቅማ-ጥቅሞች አሉት፡፡ ልጆቹን የተሻለ ትምህርት ቤት ማስተማርም ሆነ ለወደፊቱ መጦሪያውን ማስቀመጥ/መቆጠብ ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ የአንድ የዕዝ ኃላፊ የሆነ ጄኔራል ክፍያ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ እርግጥ ነው የቤት፣ የመኪናና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ቢኖሩትም ቅሉ፤ ደሞዙ የባንኩን ወይም የመንግሥታዊ የልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሠራውን ሰው ደሞዝ አንድ ስድስተኛ (1/6) ገደማ ቢሆን ነው፡፡
ይህ ደሞዝና የገቢ ምንጭ አንድን የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የሚያተጋው አይደለም፡፡ ምናልባትም ለመርኅ መከበርም በጽናት እንዲቆም ላያደርገው ይችል ይሆናል፡፡ ስለሆነም፣ ስልጣኑም ሆነ ከስልጣኑ የሚገኘው ጥቅም “የዛፍ ላይ ዕንቅልፍ” ከመተኛት ብዙም የተለየ አይሆንም፡፡ ደንበኛ እንቅልፍ ለመተኛት ደግሞ የአንዱ ቡድን/ፓርቲ አባል መሆን የግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ፣ በፖለቲካ ታማኝነት የሚሰጠው ከብ/ጄነራል በላይ ያሉትን ማዕረጎች ማሰብ ቀርቶ ማለምም አይቻልም፡፡ በዚህ መስመርና በዚህ ታማኝነት የሚመጡ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ደግሞ እንደምን አድርገው የመከላከያው ውስጥ ያሉትን የሠራዊቱ አባላትና ሙያተኞች መብትና ጥቅም ሊያስከብሩ እንደሚችሉ መሰቡ ራሱ ከባድ ችግር አለው፡፡ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖቹ ተጠሪነታቸው ለሾማቸው አካል እንጂ ለሚመሩት ሠራዊትና ሙያተኞች አለመሆኑ ስለሚያመዝን ነው፡፡ ስለሆነም፣ አንድ የማስተርስ ዲግሪ ያለው መቶ አለቃ የሚከፈለው ክፍያ፤ ከሲቪሉ ጋር ተመሳሳይ ሥራ እያከናወነ ከሙያውና ከትምህርቱ ጋር የማይመጣጠን ነው፡፡ “ለምን ሆነ?” የሚል ካለ መልሱ ቀላል ነው፡፡ የመከላከያ የደሞዝ እርክን ማሻሻያ የሚያስፈልገው ስለሆነ ነው፡፡ (መዘንጋት አልነበረበትም፤ ግን ተዘንግቷል፡፡)
ይህንን ሁሉ ያተትነው የመከላከያ ሠራዊቱ ከተከናነበው የቡድናዊነት ስሜት ወጥቶ እንደምን የሀገራዊ/ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት መሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ ስሊያሳስበን ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ከአራት መቶ ሃያ ዓመታት በኃላ የወራሪዎች ችግር ከውስጥም ከውጭም ተጋርጦባታል፡፡ ያለምንም ጥርጥር ችግሩ የፖለቲካና የሥልጣን ችግር እንደሆነም እናውቃለን፡፡ በኦጋዴንም ሆነ በጋምቤላና በባሌ እንዲሁም በትግራይና በጎንደር አካባቢ ያሉት ቡድኖች የሥልጣን ትግል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን መካድ አያሻም፡፡ በተለይም፤ ከኤርትራና ከሶማሊያ በኩል ያለውን ችግር በቁርጠኝነት የሚመክት ደንበኛ መከላከያ ሠራዊት እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡ ስለሆነም፣ እንደግብጽ ጦር የተሽከርካሪዎች መለዋወጫና አንዲት ካይሮ አጠገብ ያለች የ25 ሰዎች መኖሪያ የምትሆን ደሴት ልቆጣጠር የሚል ቀቢጸ-ተስፋውን ትቶ ሀገራዊ ኃላፊነቱንና ሉዓላዊነትን የሚያስቀድም የመከላከያ ሠራዊት እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡ መከላከያ ሠራዊቱ አይዘመን፣ ወይም ደግሞ ራሱን አይቻል አላልንም፤ አንልምም፡፡ ኢትዮጵያንም ከግብርና-መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ አሻሸጋግራት አላልንም፤ አንልምም፡፡ ነገር ግን፣ ቅድሚያ ሰጥቶ ሠራዊቱን ኢትዮጵያዊ መልክና ቁመና ይስጠው፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርና የሕዝብ አለኝታ እንጂ፣ የአንድ ወይም የጥቂቶች ፖለቲካዊ አጀንዳና ድርጅት ደጋፊ መልክ እንዲኖረው ማድረግ አይገባም፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ ከክልላዊነት ስሜቱ ወጥቶ የብሔራዊነት ስሜትንም እንዲላበስ ሊከበሩለት የሚገቡ የክብር፣ የመብትና የጥቅም ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መከናወን አለባቸው፡፡ አሁኑኑ፣ በአፋጣኝ የመከላከያ ሠራዊቱን ከፍተኛ አመራር በኢትዮጵያዊነት መርኆና የብሔራዊ ስሜት አብነትን ባረጋገጡ ኃላፊዎች መተካት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ የጋራ ቤታችንን ኢትዮጵያን የሚጠብቀውና ለነፃነቷ የሚጋደለው ከተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሆኖ ሳለ፣ እነዚህን ሙሉ-ለሙሉ የማይወክል አመራር ቆም ብሎ ማሰብ ይጠበቅበታል፡፡ ሰባ በመቶ (70%) የሚሆነው የመላከያ ሠራዊት እስከ አፍንጫው ታጥቆ፣ አንድ ክልል ላይ ብቻ ለምን እንደተከማቸም ሊመረመር ይገባዋል፡፡ መከላከያው ራሱን እንዲመረምር ጊዜውም ዕድሉም አለውና ፋታ ወስዶ ይመርምር፡፡
ከዚህ በተረፈ፣ እንኳንም የመከላከያ ሠራዊቱን ቀን ለማክበር ጅማሮው መታየቱ መልካም ነው፡፡ ሆኖም፣ በአምስቱም ዕዞችና በየክፍለ ጦሮቹ ብቻ በሚደረግ የወታደራዊ ትርኢትና ኤግዚቢሽን ብቻ ከሚወሰን በተለያዩ ክፍለ ጦሮችና ዕዞች አማካይነት በሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮችም ታጅቦ ቢቀርብ መልካም ነው እንላለን፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የመከላከያ ሠራዊቱ አባላትንም ሆነ የሕዝቡን ተሳትፎ ለማግኘት ያስችላል፡፡ በ1950 ዓ.ም ጀምሮ ይደረግ የነበረውና ቀዳሚው “የመከላከያ ሰራዊት ቀን” እንዴት ይደረግ እንደነበርም ታሪክን መርምሮ መነሳቱ ያዋጣል፡፡ እነዚህን “የመከላከያ ሠራዊት ቀን” አከባበሮች በተመለከተ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይልም ሆነ የክብር ዘበኛ ተቋማት እያንዳንዳቸው ከዐሥር በላይ የክብረ በዓሉን አስመልከቶ ዘጋቢ መጽሔቶችን አሳትመው ነበር፡፡ ስለሆነም፣ ታሪክን አጥንቶና መርምሮ ከታሪክ መማርና የተሻለ ለመሥራት መሞከርም ይገባል፡፡ (በቸር ያቆየን!)
maleda times | February 17, 2013 at 9:45 pm | Categories: AMHARIC NEWS | URL: http://wp.me/s2gxmh-5563
Unsubscribe or change your email settings at Manage Subscriptions.
Trouble clicking? Copy and paste this URL into your browser:
http://www.maledatimes.com/2013/02/17/5563/

No comments:

Post a Comment