ማሳሰቢያ፦ ይህ ጽሑፍ በየሳምንቱ ለሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ማክሰኞ ጃኑዋሪ 21/2013 የተጻፈ ነው። በዚያው መንፈስ እንዲነበብ ይሁን።)
(ኤፍሬም እሸቴ - READ IN PDF)፦ ከዚህ በፊት አንዲት ተውሼ ለራሴ ያሻሻልኳትን ግጥም ነግሬያችሁ ነበር። የግጥሟ ባለቤት የአብዬ መንግሥቱ ለማ አባት የኔታ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ ናቸው። መጽሐፋቸው በድጋሚ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለታተመ ምራቁን የዋጠ፣ ታሪክ የሚወድ፣ ማንነቱን የሚፈልግ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊያነበው የሚገባ “ባዮግራፊ” ነው። አገር ቤት የሚሄድ የአሜሪካ ነዋሪ ባገኘኹ ቁጥር “ይኼንን መጽሐፍ ሳትገዛ/ዢ እንዳትመጣ/ጪ” እላለኹ። አንዴ ያነበበው መድገሙ እንደማይቀር እርግጠኛ ነኝ።
እናም የኔታ ኃይሉ በየት/ቤቱ (ማለት በየቆሎ ት/ቤቱ) ዕውቀት ፍለጋ ሲዞሩ ኖረው በመጨረሻም አዲስ አበባ ይመጣሉ። ከአገራቸው ዕውቀትና ፊደል ብለው ወጥተው “በየሰዉ አገር ሲንከራተቱ” ከቤተሰባቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ተቋርጦ ኖሮ ናፍቆት ልባቸውን አጠፋቸው። ለሰላምታው ብቻ በሚመጣው በሚሔደው ሰው ሰላምታ ሲልኩ፤ ሰላምታ ሲቀበሉ ይኖሩ ያዙ። እናም በአንዱ ዕለት ናፍቆታቸውን በግጥም (የአማርኛ ጉባዔ ቃና ትመስላለች) እንዲህ ብለው አሉ።
ተደርጎ ያውቃል ወይ እንዲህ ያል ሥርዓት፣
እግር አዲሳባ ልቡና መቄት።
በዚህች ግጥም ውስጥ “መቄት” የተባለችው የአካባቢ ስም (የየኔታ ኃይሉ አገር) መሆኗን ብቻ ላስታውስ። በቃሌ ስለማውቃት እኔም እንደርሳቸው አገሬ ሲናፍቀኝ ወይም እንደበቀደሙ ሰኞ፣ ብሔራዊ ቡድናችን ከዛምቢያ ጋር እንደተጫወተባት ዕለት፣ ያለች ቀን ስታጋጥመኝና “በዚህን ሰዓት ምነው አገሬ በነበርኩ” በምልባቸው ወቅቶች በየኔታ ለማ ኃይሉ ግጥም እቆዝማለዅ።
|
"የኔታ ለማ ኃይሉ" by Afewerk Tekle
|
“ተደርጎ ያውቃል ወይ እንዲህ ያል ሥርዓት፣
እግሬ ባሕር ማዶ ልቤ አገር ቤት።” እያልኩ።
በዚህች ዕለተ ሰኞ በአሜሪካ፣ ያውም እኔ በምኖርበት በዲሲ-ሜትሮ (ዲሲና አካባቢው) ታላቅ የበዓል ቀን ነው። ያውም በየአራት ዓመቱ የሚመጣ። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቃለ መሐላቸውን ለሁለተኛ ጊዜ የሚፈጽሙበት ቀን። በዚያው ሰዓት ደግሞ (በእኛ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ጀምሮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ከዛምቢያ ጋር ያደርጋል። እውነት እንነጋገር ካላችሁ ቃለ መሐላውም ሆነ ሥርዓቱ ምንም ቁብ አልሰጠኝም ነበር። ይኼንን ለማየት ከስንት ዓለም ሰው በሚመጣበት በዓል እኔ ደግሞ አገር ቆርጬ በልቤ ደቡብ አፍሪካ ገብቻለኹ። አሁን እኔ የት ነው ያለኹት? የት ነው የምኖረው? ከዚህ በፊት“የአሜሪካ ኑሮ በኢትዮጵያ አዕምሮ” ያልኩትን ጽሑፌን ካስታወሳችሁ እኔ እርሱን ሆኜ ነበር። በአሜሪካ እየኖርኩ ልቤ ግን ኢትዮጵያ። እኔ ብቻ እንዳልነበርኩ መረጃና ማስረጃ ባልሰበስብም (ይቺ የዘመኑ አባባል ደስ ብላኛለች - በውነት) ብዙ ኢትዮጵያውያንም እንደኔው እንደነበሩ እርግጠኛ ነኝ። አንድ አብነት አለኝ።
እሑድ ለሰኞ አጥቢያ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ ጠዋት ጀምሮ፣ ጆሮዬን ሸገር ኤፍ.ኤም ጣቢያ ላይ ተክዬ እያዳመጥኩ ነበር። ከዚያም አንድ የዲሲ ሰው (ፋሲል የተባሉ) ደወሉ። ስልኩን ማግኘት እንዳስቸገራቸው፣ ብዙ እንደሞከሩ ከተናገሩና ሁለት ሦስት ስልኮች እንዲያዘጋጁ ከመከሩ በኋላ ጨዋታውን በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን፣ ሸገርንም እንደሚያዳምጡ ሲናገሩ “አኻ፣ ለካስ እኔ ብቻ አይደለኹም እንቅልፍ ያጣኹት” ብዬ ተጽናናኹ።
እውነትም በየዓለሙ እንደጨው የተበተነች አዳሜ-ኢትዮጵያዊ ሁላ እንቅልፏንም ቀልቧንም አጥታ ኳስ ኳስ ስትል መሰንበቷን ፌስቡክና ትዊተር ይመሰክራሉ። ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ እንወጣለን እንጂ ኢትዮጵያ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ልብ ወጥታ አታውቅም። እደግመዋለዅ። እኛ ከአገር እንወጣለን እንጂ አገራችን ከውስጣችን-ከልባችን ወጥታ አታውቅም። በደቡብ አፍሪካ የታየው ምስክር ነው። “ኢታርዕየኒ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ - የኢትዮጵያን ጥፋት አታሳየኝ” እንዲል ጸሎተኛው።
ይህ ጽሑፍ ማክሰኞ (January 21/2013) ማታ እንደመጻፉ አሁንም የጨዋታው ‘ሙድ’ አልለቀቀኝም። አሁንም ውስጤ አንዳች መግነጢሳዊ በሆነ ስሜት እንደተሟሟቀ ነው። በመጀመሪያ ጨዋታ እኩል እንደወጣን ሳይሆን የውድድሩን የመጨረሻ ጨዋታ እንዳሸነፍን ዓይነት ስሜት ነው ያለኝ። አገር ቤት ያሉ ወዳጆቼ ስሜቱ በየቦታው ተመሳሳይ ለመሆኑ ከተማቸውን እማኝ እያደረጉ ነግረውኛል። ግን ስሜታችን ምንድነው? ስሜቱን በአገርኛ ምሳሌ ላስቀምጠው ካልኩኝ የማገኝለት ትርጉም ልጁ ለቁምነገር የበቃለት ወላጅ የሚሰማው ዓይነት ክብርና ስሜት ነው። “አኮሩን” የሚል ዓይነት። የሁሉም አገር ተመልካች ስፖርትን በዚህ መንፈስ ለመመልከቱ እርግጠኛ አይደለሁም። እኛ ግን ከስፖርቱ የምንፈልገው በሌላው ያጣነውን ክብር፣ ተሰሚነት፣ ተደማጭነት፣ መታየት እና እንደ አገር ያለንን ማንነት ማሳየት ሳይሆን አይቀርም።
ከእግር ኳሱ ዛሬ የምንፈልገው ክብር ለብዙ ዓመታት በአትሌቲክሱ ስንፈልገውና ስናገኘው የኖርነው ነው። የአገራችን መሥሪያ ቤቶች፣ ባለሥልጣኖችና የሕዝብ ግንኙነት ተቋማት በሙሉ ተደማምረው ሊያመጡ የማይቻላቸውን አገር የማስተዋወቅ ሥራ አትሌቲክሱና አትሌቶቻችን ሲሠሩ ኖረዋል። እግረ መንገዱን አትሌቶቹ ራሳቸውን ቢጠቅሙም አገራቸውም ከዚህ እስከዚህ የማይባል ትልቅ ጥቅም አግኝታበታለች።
እግር ኳሱም በዚሁ መስመር መራመድ ጀምሯል። እውነተኛ ሕዳሴ ይሉኻል ይህ ነው። የእግር ኳሳችን ከወደቀበት አመድ ላይ ተነስቶ፣ አቧራውን አራግፎ፣ ዕንባውን አብሶ፣ ሐፍረቱን ውጦ እና ጠንክሮ ሠርቶ ለዚህ ክብር መብቃት ታላቅ የሕዳሴ ትርጉም ነው። ሕዳሴና ትንሣኤ ማለት ይህ ነው። ሕዳሴ በመፈክር፣ በዘፈን ብዛትና በፐርሰንት ጋጋታ የሚመጣ ሳይሆን እንዲህ አፈር ግጦ ሰርቶ፣ ተባብሮ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ በመደማመጥ የሚገኝ ውጤት ነው። በዚህ ረገድ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም ሊመሰገን ይገባዋል። ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚጓዝ እርግጠኛ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ያሳዩት ቀናነት እና ስሕተቶችን ለማስተካከል የወሰዱት እርምጃ በግሌ አስደስቶኛል። (ለምሳሌ በሽልማት ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት የዘጉበትን ቀና ውሳኔ ይመለከቷል)።
ሕዳሴዎች ሁል ጊዜም በዕውቀት ነው የሚመሩት። በየትኛውም ዓለም የነበሩ ሕዳሴዎች የተመሩት በአዋቂዎች፣ በተገቢ ሰዎች፣ በአዕምሮ ነበር። ውጤቱም እስካሁን ይታያል። ብዙ አገሮችን ከድንቁርና ጨለማ አውጥቶ በሥልጣኔ ብርሃን የመራቸው ይኸው አማናዊ ሕዳሴ (እውነተኛ ሕዳሴ) ነው። እንግዲህ ይህ እውነተኛ ሕዳሴ አንድ ጊዜ ታይተው ከሚጠፉት፣ በመፈክር ብዛት፣ በዕውቀት ጉድለት ከሚመሩት ሕዳሴ መሰል “ደቦዎች” ይለያል። ደቦዎቹ ወጥነት፣ ተከታታይነት፣ መለኪያ የሌላቸው ግርግሮች ስለሆኑ በዚያ ወቅት ላሉ መንግሥታት ካልሆነ ለሕዝቡም ለአገርም ዘላቂ ፋይዳ የላቸውም።
ሕዳሴ ሕዝብን ከማሳወቅ፣ አዕምሮውን ለሕዳሴው ከማዘጋጀት ይጀምራል። ሕዳሴዎች የሚወለዱት ከብዕር ጫፍ እንጂ ከጠመንጃ አፍ አይደለም። በርግጥ ዕውቀት እንዲስፋፋም ሆነ እንዲከስም ጠመንጃዎች ትልቅ ጉልበት አላቸው። ያም ዕውቀት ትክክለኛና ጤናማ ዕውቀት መሆን አለበት። ከፕሮፓጋንዳ የተለየ፣ እውነትን በመፈለግ ላይ የተመሠረተ ዕውቀት። ከምዕራቡ ዓለም ልንማረው የሚገባ ነገር ካለ አንዱ ይህ መሆን አለበት። እኛም ብንሆን ዕውቀት ለመገብየት የምንሰንፍ ሕዝቦች አይደለንም። ለዚህም ብዙ አሻራዎች አሉን። ታዲያ ሕዳሴዎቻችን ሳይወለዱ እንዲጨነግፉ ያደረጋቸውን ሾተላይ መፈለግ ይኖርብናል።
ዕውቀት የሕዳሴ ምንጭ ነው አልን እንጂ ሁሉም አዋቂ ሕዳሴ የሚፈነጥቅ ነው አላልንም። ከዚህ በፊት በአንድ ጽሑፌ እንዳልኩት ዕውቀታቸውን ለጊዜያዊ ጥቅም ማግኛ የሚያደርጉ “የንጉሥ አጫዋቾች” ብዙ ናቸው። ሌላው ቀርቶ ባላቸው ዕውቀት የሚገነዘቡትን ብርሃን እና ጨለማ ለጥቅማቸው በማድላት ብርሃኑን ጨለማ፣ ጨለማውን ብርሃን፣ መልአኩን ሰይጣን፣ ሰይጣኑን መልአክ ብለው ከማቅረብ ወደ ኋላ የማይሉ ናቸው። አንድ አፍሪካዊ ፀሐፊ እንዳለው እንዲህ ዓይነት “ሰበነክ ሊቃውንት” (intellectual prostitutes) ዕውቀቱ ሳያንሳቸው ሕዳሴዎችን በመግደል ላይ የተሠማሩ ናቸው። ገዢዎች ደግሞ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ይወዳሉ። ይጠቀሙባቸዋል። መድኃኒቱ ሰዎቹ ወደልባቸው እንዲመለሱ መጠበቅ ሳይሆን አዕምሯችንን እንዳይበክሉ መጠበቅ ነው።
እንግዲህ ሕዳሴ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ “የሬዲዮ ቃል” መሆኑ ካልቀረ አማናዊ ማስረጃ ማድረግ የሚያስፈልገን ስፖርቱን ነው። እግር ኳሳችን በደቦ የሚመራ ሳይሆን ደህና ባለ-አዕምሮ እንደያዘው ያስታውቃል። ዛሬ ያደነቅናቸው ተጫዋቾቻችን በአንድ ጊዜ የተገኙ ሳይሆኑ በብዙ ችግር አልፈው ነው የመጡት። “ሮም በአንድ ሌሊት አልተፈጠረችም” እንደሚባለው ይህ ቡድን በአንድ ጥረትና ምኞት የተወለደ ሳይሆን ቀስ በቀስ እያደገ የመጣና ለውጤት መብቃት የቻለ ነው።
ከዚህም ጋር ሕዝቡ ለቡድኑ ያሳየው ድጋፍ እጅግ የሚያስመካ ነው። ያውም ውጤታማ ድጋፍ። ጥሩ ነገር መመኘትና ጥሩ ነገርን መደገፍ ይለያያል። ሕዝቡ እግር ኳስ ይወዳል፤ ጥሩ ብሔራዊ ቡድንም ይፈልጋል፤ መፈለግ ብቻ ሳይሆን ከአገር ቤት እስከ ደቡብ አፍሪካ ያለው ኢትዮጵያዊ የሚታይና የሚጨበጥ ሥራ ሠርቷል። መፈለግ ከማድረግ ጋር ሲቆራኙ ማለት ይኸው ነው። አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አይችሉም ለሚሉን ተግባራዊ ምላሽ ነው። “ይበል” ብለናል። እንዲህ እየተባበርን፣ የአገራችንን ትንሣኤ ማቅረብ ከቻልን በዓለም መድረክ ፊት ዳግም ቀና ብለን መራመድ የምንችል እንሆናለን። ደግሞም አይቀርም።
ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ራስ ራሷን የሚደቃት ቢበዛም ኢትዮጵያዊነት እንዳልደከመች፣ እንደማትደክም፣ እንደማትከስም ለማየት ስለረዳን ደስታችን እጥፍ ድርብ ነው።
ይቆየን - ያቆየን
No comments:
Post a Comment