Wednesday, February 27, 2013

አንድ አስተያየት፤ ህውሀት ተኮር | አቤ ቶኪቻው

Gudu Kassa
ሞት ይርሳኝ እና የህውሃት ወዳጆቼን እንኳን ለየካቲት 11 አደረሳችሁ ሳልላቸው የካቲት 21 ሊሆን አይደል እንዴ!? በሉ አሁንም የካቲት ራሱ ሳይወጣ “እንኳ አብፃኩም” ልበል። እኔ የምለው ይሄ ስንተኛ አመት ነው ማለት ነው… በዛ ሰሞን ስታትስቲክስ መስሪያ ቤት ስሰራ አንድ አባት ዕድሜያቸውን ስጠይቃቸው…” አይ ልጄ የእኔ እድሜ ሩቅ ነው… ቢጠሩትም አይሰማ!” እንዳሉኝ አይነት ህውሀትም እድሜው በጣም እየራቀ ሄዷል። በዚህ ቢጠሩት በማይሰማ ሩቅ ዕድሜ ምን ያህል ስራ እና ምን ያህል ሴራ እንዳከናወነ ግምገማው ይቁጠረው።

በበኩሌ የህውሃትን እምቢ ባይነት እና ታጋይነት አደንቃለሁ። አንድ ማህበረሰብ ጭቆና አለብኝ ብሎ ካመነ፤ እና ተዉኝ አትጨቁኑኝ ቢል የሚሰማው ካጣ “ዘራፍ” ብሎ ማምረሩ የአባት ነው። ችግሩ አትጨቁኑኝ ብሎ ዘራፍ ያለው መልሶ ጨቋኝ ሲሆን ነው እንጂ!
ይህው ዛሬም የደርግ ስርአት ህውሃትን እንደፈጠረው ሁሉ፤ የኢህአዴግ/ ደርግ ስርአት ደግሞ፤ አርበኞች ግንባርን፣ ኦነግን፣ ኦብነግን፣ ደህሚትን እና የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሀይልን ፈጥሯል። ሁሉም በየ አቅጣጫው ነፍጥ አንግበው “ና በለው… ና!” እያሉ ከግዙፉ የኢህአዴግ ሰራዊት ጋር እየተፋለሙ እንደሆነ በተለያየ ግዜ እየሰማን ነው።
ባለፈው ጊዜ በአዲስ አበባ የመከላከያ ቀን ተብሎ ሲቀወጥ የመንግስት ባለስልጣኖች የሀገር ውስጡም የውጪውም ነፍጠኛ ለመመከት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ሲያሳዩን ነበር። ይሄንኑ ነገር ደርግ ሲያደርገው ነበር። አምባገነኖች መኮራረጅ በጣም እንደሚያስደስታቸው የሚያውቁት ይሄኔ ነው። ኢህአዴግ ደርግን ስታብጠለጥል ላያት እርሱ የነካውን የምትነካ በሄደበት መንገድ የማትራመድ ትመስላለች ግን ልክ ደርግ የሚያደርገውን ስታደርግ ሲመለከቱ አምባገነኖች ለመኮራረጅ የሚጨክን አንጀት እንደሌላቸው ይረዳሉ።
ታድያ ዛሬም ርስ በርሳችን ልንታኮስ ማዶ ለማዶ ተፋጠናል። ህውሀት አርባ አመት ሊሞላት ሁለት አመት ብቻ ቀርቷታል። በእውነቱ ቢያንስ የእርስ በርስ ጦርነትን ታሪክ ማድረግ ከተሳናት ህውሀት አርባ አመቷን ከምታከብር አርባዋ ቢወጣ ይሻላታል።
ለማንኛውም በዚህ አጋጣሚ አንድ አስተያየት እሰጣለሁ። … ህውሃት ብቻ ሳትሆን በጥቅሉ ኢህአዴግ ራሷ ዝም ብላ ዕድሜዋን እና አበሳችንን ከምታስቆጥረን እርሷ የመጣችብትን መንገድ ዳግም እንዳይኖር ብትተጋ ለሁላችንም ጥሩ ነው!
እኔ የምለው ወዳጆቼ… ሰላም ናችሁ ወይ! የኔ ነገር ሰላምም አላልኳችሁኮ!
ይመቻችሁ!
 
staff reporter | February 27, 2013 at 7:28 am | Categories: AMHARIC NEWS | URL: http://wp.me/p2gxmh-1tJ
 


Comment

No comments:

Post a Comment