Saturday, August 31, 2013

ወያኔ የ1997ን በማስታወስ አፋርታምነቱን ሲደግም ከአዲስ አበባ


 በ97 ምርጫ ወቅት ቅንጅት በመስቀል አደባባይ ሕዝባዊ ጥሪ ሲያስተላልፍ አብል አልከፈለም፤ ቲሸርት አልሰጠም፤ ምሳ አላዘጋጀም፤ የላብ ማድረቂያና የፍልውሃ ብሎ በጀት አልተመነም፡፡ ኑ ውጡ እንውጣና ለዴሞክራሲ እንዝፈን፡፡ የፖለቲካ ዲስኩር ሳይደረግ፤ መፈክር ሳይሰማ፤ ሚያዝያ 30 በመስቀል አደባባይ ተገናኝተን አንዳችም ፖለቲካዊ ዲስኩር ሳይደረግ ዝም ብለን ለዴሞክራሲ፤ ለሰብአዊ መብት፤ ለፍትሕ መረጋገጥ፤ ለመጪው ምርጫ የሕዝብ ድምጽ መከበር እንዝፈን ተብሎ ሕዝቡ ሲጠራ ከሩቅም ከውጭም መልእክቱ ኑ ብቻ ነበር፡፡ ይህን የሰማው ወያኔ ልዋረድ ነው ብሎ ደንግጦና በርግጎ፤ ፈርቶና ተርበትብቶ፤ መግቢያ መውጫው ግራ ሆኖበት ለሚያዝያ 29 ጥሪ አስተላለፈ፡፡

የቀን ወጪ መደበ፤ ትራንስፖርት ከየአቅጣጫው መድቦ፤ ቲሸርት አድሎ ለቁርስ ሳንድዊች መግዣ በጥሬው ሰጥቶ፤ ከሰልፍ መልስ ለድካም ማካካሻ በነፍስ ወከፍ 50 ብር መድቦ፤ ለላብ ማጽጃ የፍልውሃ ሌላ ተጨማሪ ክፍያ ሰጥቶ በየቀበሌው፤ በየዞን አመራሮቹ፤ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡ መልእክቱ ለሁሉም ይድረስ፤ ፓርቲያችሁ ኢህአዴግ የተሰነዘረበትን የውርደት ጅራፍ አብረን እንድንከላከል፤ የተቃጣብንን የስልጣን ገፈፋ አብረን እንድንመክት፤ ቅንጅት የሚባል ጣውንታችንን አብረን እንድንዋጋው አስፈላጊውን ትራንስፖርትና ወጪ ለየአንዳንዳችሁ የመደበ ስለሆነ ለቁም ተዝካሬ እንድትደርሱልኝ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህን ለማድረግ ትብብር የነፈገ ነጋዴው ከሱቁና ከንግድ ፈቃዱ ጋር ተማሪው ከትምህርት ቤቱ ጋር ጎዳና ተዳደሪም ተንደላቆ ከሚተኛባቸው የጎዳና አስፋልቶች ጋር የመንግስት ሰራተኛም ከደምወዝና ቅጥሩ ጋር ይሰናበት ለዚህ ኢህአዴግን አድን ሰልፍ ካልወጣ መገናኘት ህልም ነውና!፡፡ በማለት ተጣራ፡፡
     ነገ ከማልቀስ ጥሪውን በአዎንታዊ መልኩ መመለስ አለ ሁሉም 29ን ለወጪው፤ ለ50 ብሩ፤ ለቲሸርቱ፤ ለስራ፤ ለትምህርት፤ ለንግድ ፈቃዱ፤ ማዳኛና ማግኛ 30ን ለዴሞክራሲዬ ፤ ለሰብአዊ መብቴ፤ ለፍትሕ መረጋገጥ፤ ለነጻነቴ ለመቆም ብሎ አቀደ በ29 በተደረገው የትእዛዝና የዛቻ ሰልፍ፤ ዋ እቴ!፤ ነፍሳቸውን ይማረውና መለስ በተኩራራና በተረጋገጠ ሰሜት ይህን ጎርፍ ያየ ምርጫ ይሰረቃል ሊል አይችልም፡፡ ዛሬ ሕዝቡ አረጋገጠልን ፍላጎቱን፤ ምርጫዬ ኢህአዴግ ነው አለ ሲሉ፤ ሕላዊም በተሸከርካሪ ወንበሩ ላይ ሆኖ ቦታ አልበቃ አለው፤ ድል ታየኝ ብሎ ተኮፈሰ፡፡ በረከትም እንግዲህ ቅንጅት እርሙና ያውጣ አንድ ወንበር አይገኝም ብሎ ተወራረደ፤ እርግጥ እርታታው ሲታወቅ ግን ማፈር ቀለቡ ነውና ውርርዱን አልከፈለም፡፡ አፋርታም አይደል ድሮስ! ሚያዝያ 30 ያን ጎርፍ የተባለውን ሱናሚ ሲያደርገው፤ ሕዝቡ በራሱ ፍላጎትና በግል ትርንስፖርቱ፤ አደባባዩን ጠጠር መጣያ ሲያሳጣው እነ እንቶኔ የት ይግቡ፡፡
      እኛው ነፍሳቸውን ይማረውና እኛው ሰውዬ መላ ሲጠፋቸው ሰማይ ሲደፋባቸው ‹‹ያልኩት፤ ቃል የገባሁት ሁሉ ፉርሽ ሆኗል፤ ፎገርኳችሁ! ብለው ጣት እቆርጣለሁ፤ አስረለሁ ማለት ጀመሩ ብቻ ሁሉም ነገር ጨዋታ ፈረሰ…. ሆነ አሁን ደግሞ ተቃዋሚዎች ሕዝቡን ና እንነጋገርና ውሳኔህን አስተላልፍ ብለው ሲጠሩና፤ ወያኔ ኢህአዴግም፤ አዝማሚያውን በየቦታው በሰገሰጋቸው ሰላዮቹና አገልጋዮቹ ሲያጣራ ሕዝቡ ለተቃዋሚዎች ጥሪ ምላሹን ለመስጠት መዘጋጀቱን ሲያረጋግጥ፤ አርብ እለት ነሐሴ 24 ቀን፤ በየወረዳውና ቀበሌው ነዋሪውን ሰብስቦ፤ ካድሬዎቹን አሰልፎ መመርያ ሰጠ፡፡ መመርያውም እንዲህ ይላል---
1. ማንኛውም ነዋሪ በዚህ ሰልፍ መሳተፍ አለበት፤ ያን ካላደረገ የሽብርተኛ ተባባሪ ነው
2. ለመጓጓዣ ትራንስፖርት በየወረዳው ተመድቧልና በእግር ማንም ወደ መስቀል አደባባይ መግባት ስለማይችል በሚቀርበው ትራንስፖርት መጠቀም ግዴታ ነው
3. በአውቶቡሱና በመሰል ትራንስፖርት ላይ ያልተገኘና በስም መዝገቡ ላይ መገኘቱ ካልተረጋገጠ ስራ ያለው በስራው፤ ተማሪው በትምህርት እድሉ፤ ነጋዴው በንግድ ፈቃዱ እንደፈረደ እንዲያውቀው፡፡
4. በምንም መልኩ ከዚህ መቅረት ማለት ዘላቂ ቸግር ውስጥ መግባት ስለሆነ አስቡበት ተብሎ ስብሰባው ከምሽቱ 3 ሰአት ላይ ተጠናቋል፡፡ . ይህ ሁሉ ማስፈራሪያ፤ ይህ ሁሉ ዛቻ ያለበት የሰልፍ ጥሪ እንዴት ሆኖ ነው ሕዝቡ ሰልፍ ወጣ የሚያሰኘው፡፡ . መቼ ነው ወያኔ ከማስመሰል ተግባሩ የሚለያየው . አይ አቶ ሃይለማርያም ምነው ጃል የማይሆን ትምህርት ቀሰሙ ያውም በወረደና በተዋረደ መልኩ፡፡ ያሳዝናል፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ተቃዋሚው ባገኘው አጋጣሚና በኢንተርኔት ቀኑን አሳውቆ ጥሪ አስተላለፈ፡፡
ኑ አብረን ለኢህአዴግ ስህተቱን በመንገር እንዲያርም፤ ለሕዝብ ድምጽ እንዲገዛ፤ የግፍ እጁን እንዲሰበስብ፤ ማን አለብኝ ባይነቱን ትቶ ሕዝብን እንዲያከብር፤ ሕገመንግስቱን በሚጥመውና በሚጠቅመው ብቻ ሳይሆን ሳይሸራርፍ እንዲያከብረውና ለዚህም ከማንም ቀድሞ እንዲገኝ፤ ባሻው ማሰርና የፈጠራ ማስረጃ በማስደመጥ አሰልቺነቱን እንዲያቆም፤ ፍትሕን ፍትሃዊ በሆነው እውነታው፤ ሰብአዊ መብትን ከራሱ አሳልፎ ለመላው የሰው ልጅ እንዲጠቅም፤የአገልጋዮቹ አመልካች ጣት ወገን ላይ ጥይት ለማርከፍከፍ ሳይሆን ወንጀለኛንና ሕገወጥን ለመጠቆሚያ፤ በስልጣኑ አለአግባብ ከመባለግም አልፎ ለጋጠ ወጥ ድርጊት እንዳይሆን፤ ገዢው መንግስት ከመግዛት ወደ ማስተዳደር እንዲለወጥ፤ ወዘተ….. እንዲውሉ በአንድነት እንቁም ብሎ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ሕዝቡም ነሐሴ 26ን የነጻነቴ ቀን ብሎ በማስታወሻው፤ በሕሊናው፤ መዝግቦ ቀኑን ሲጠብቅ፤ ወያኔ በድንገት ከእንቅልፉ ነቃና በአዲስ አበባና በአካባቢው ያሉትን የወረዳ ነዋሪዎች በአስቀመጣቸው ጀሌ የወረዳ ሹማምንቶች፤ በሰገሰጋቸው ካድሬዎች፤ ባሕሪው በሆነው ማስፈራራት ለስብሰባ ጠራ፡፡ መመርያ ሰጠ፡፡ ዋ ብሎ ዛቻውን ደረደረ፡፡
       በገዢው ከሚቀርበው ትራንስፖርት ውጪ ማንም በእግሩም ሆነ በግል ትራንስፖርት ጨርሶ ወደ መስቀል አደባባይ መግባት ክልክል ነው አለ፡፡ ይህም ማለት ተቃዋሚ የጠራው ሰልፍ ላይ ለመካፈል ማንም ወደ መስቀል አደባባይ በእግር አይገባም ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ እንግባ አትገቡም በሚል በሚነሳ አተካሮ ወያኔ ኢህአዴግ የተቃዋሚ አባላትንና ደጋፊዎችን ሊደበድብ፤ ሊገል፤ ሰብስቦ ሊያስር፤ ማቀዱን አረጋገጠ፡፡ እዚህ ላይ ወያኔ ፈርቶ በማስፈራራት ባህሉ አሁንም ሕዝብ ዳግም ከተቃዋሚ ጋር እንዳይሰለፍ ማዘዣውን እያስተለካለፈና መንገዱንም እየዘጋ ነው፡፡ (ይሆን መስሎት) ያንንም እምቢ ለነጻነቴ ብሎ የተቃዋሚውን ሰልፍ፤ ሰልፌ ነው ብሎ ቢወጣ በከተማው የሚበትናቸው ‹‹ፖሊስ›› መሰል ጀሌና አገልጋዮቹ፤ በፖሊስ ልብስ ተጨንብለው ያን የግፍ እርምጃቸውን ሊወስዱ እንዲችሉ የተዘረጋ ዘዴ ነው፡፡ ሃገርን በጉልበቴ በመጠቀም እገዛለሁ፤ ያለ መንግስት ነኝ ባይ ቡድን፤ ለዚህ በምንም መመዘኛ መንግስት ሊያሰኘው በማይችል ተግባር ላይ መሰልፍን የመሰለ የወረደ፤ ያዘቀጠ፤ ምንም ነገር የለም፡፡ ያሳዝናል፡፡ ምን ቢደረግ፤ ምንም ቢዶለት ቀኑ መቆረጡ አይቀሬ ነውና የመጠየቂያ ወንጀላችሁን ባታበዙት ይሻላል፡፡ ያለው እኩይ ተግባራችሁ በቂ ነውና!
staff reporter | August 31, 2013 at 12:57 am | URL: http://wp.me/p2gxmh-2bM
Comment   See all comments

No comments:

Post a Comment