የተስፈኞች የሰሞኑ ጫጫታና እንደምታው (ዶ/ር አሸናፊ ጐሳዬ)
July 17, 2015
የአገራችንን ፖለቲካ በቅርብ የምትከታተሉ ሰሞኑን ለነጻነት የሚደረገውን ጉዞ ለማዳከም የተከፈተውን ዘመቻ እና የዘንድሮውን አገር አቀፍ የምርጫ ውጤት ተከትሎ ብዙ አዳዲስ የሚመስሉ ነገር ግን የጠበቅናቸው ክስተቶች እንዳስተዋላችሁ እገምታለሁ። ከእነዚህ ውስጥ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፦
1. ወያኔ/ኢሕአዴግ 100% አሸንፌአለሁ በማለት ከእንግዲህ በምርጫ የሚመጣ የፖለቲካ ለውጥም ሆነ ለይስሙላ የነበረው የመድብለ ፓርቲ ስርአት እንዳበቃለት አሁንም በድጋሚ ማረጋገጡ፤
2. በሰላማዊ ትግል ወያኔ/ኢሕአዴግን አሸንፈን የስርአት ለውጥ እናመጣለን ብለው በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች የምርጫውን ኢፍትሀዊነት በየመግለጫቸው ከማውገዝ ያለፈ የተሰረቀባቸውን የህዝብ ድምፅ ለማስመለስም ሆነ እጩዎችቸውንና አባሎቻቸውን በጠራራ ፀሀይ የገደሉ በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ህዝብ ቀስቅሰው አደባባይ ውጥተው ድምጻቸውን እንኳን ማሰማት ሳይችሉ መቅረታቸው፤
3. ወያኔ/ኢሕአዴግን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ማስወገድ እንደማይቻል ካወቅን ቆይተናል የሚሉ ኃይሎች ደግሞ ወያኔን በሚገባው ቋንቋ ለማነጋገርና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ዝግጅታችንን ጨርሰን የነጻነት ጉዞ ፊሽካ ነፍተን ጀምረናልና ነጻነት ናፋቂዎች ሁሉ ተቀላቀሉን ሲሉ ማውጃቸው እና
4. አላማው ከላይ በቁጥር ሁለትና ሶስት ከተጠቀሱት ኃይሎች የተለየ ወገን ደግሞ በቅርቡ የትጥቅ ትግሉን አስመልክቶ የከፈተው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት የሳበና ህዝብን እያነጋገረ መሆኑ ናቸው። በዚህ አጭር ጽሁፍ እነዚህን ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በጥልቀት ለመዳሰስ ስለማይቻልና ምናልባትም ብዙዎች በተራ ቁጥር አራት የጠቀስኩትን ኃይል ማንነትና ድብቅ አላማ እንዲሁም በቅርቡ የትጥቅ ትግሉን አስመልክቶ የከፈተውን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በተመለከተ ጥያቄዎች ሊኖራቸው ስለሚችል የታዘብኩትን ባካፍልና በዚህ ጉዳይ ላይ በግልጽ መወያየት ብንጀምር ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ያግዛል ብዬ ስላመንኩ ነው።
ባለፉት አምስት ዓመታት የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ለምን በሚግባቡባቸው ጉዳዮች ተባብረው በመስራት ውጤታማ ለመሆን አልቻሉም ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ብዙ ጊዜዬን አጥፍቻለሁ። ችግሩ የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት፣ በዘር በቋንቋ መከፋፈላችን፣ ታሪካችን ጥሎብን ያለፈው ጠባሳ ወይስ የወያኔ ጥንካሬ ይሆን ለሚለው ጥያቄዬ መልስ ለማግኘት ብዙ ሞክሬአለሁ።
የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ሳልሆን እዚህ ሲያትል ውስጥ ከሚገኙ አክቲቪስቶች ጋር ሆነን በፈጠርነው ሕዝባዊ ፎረም አማካይነት በብዙ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ተካፍያልሁ መርቻለሁ፣ ከአብዛኛዎቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች፣ የሲቪክ ማህበራት ሀላፊዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ለመወያየትም እድሉን አግኝቻለሁ። የተቻለኝን ያህል ስለ አገሬ ፖለቲካ እከታተላለሁ አነባለሁ። በዚህ ጽሁፌ የማቀርበው ትዝብት ከዚህ ሁሉ የመነጨ ነው።
ትዝብት አንድ
ከላይ በተራ ቁጥር አራት የጠቀስኩት ኃይል በአንድ ድርጅት ጥላ ስር የተሰባሰበ ሳይሆን በሁሉም የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ያለ ነው። ሆኖም ይህ ኃይል ድብቅ ዓላማ አለው። ብዙ ጊዜ የዚህ ዓላማ አራማጆች የተቀላቀሉት ድርጅት የቆሙለትን አላማ የማያሳካ መስሎ በታያቸው ቁጥር እና አመራሩን እነሱ ካልተቆጣጠሩት የሚወስዱት እርምጃ ሁሌም አፍራሽና አደገኛ ነው። አንድም ድረጅቱን አዳክመው ያፈርሱታል አልያም መሰሎቻቸውን ይዘው በመውጣት አላማቸውን ለማሳካት ይሞክራሉ። ቅንጅትን ጨምሮ ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው ድርጅቶች ለውድቀታቸው ምክንያቶች ከወ ያኔ ይልቅ እነዚህ ኃይሎች መሆናቸው ቢታወቅም ይህን በይፋ ስላልተነጋገርንበትና መፍትሄ በጊዜ ስላልሰጠነው ደግመን ደጋግመን እዛው ወጥመድ ውስጥ ስንወድቅ እንገኛለን። መቼ ይሆን “ዓላማችሁ ገብቶናል በቃችሁ” የምንላቸው?
ትዝብት ሁለት
የዚህ ዓላማ አራማጆች ከማንም በላይ የወያኔ ጠላት ናቸው። ብዙ ጊዜ የነዚህን አፍራሽ ኃይሎች ድርጊት ያስተዋሉ ወገኖች፣ ወያኔ ወደ ተቃዋሚ ድርጅቶች አስርጎ ያስገባቸው ናቸው ብለው iske meterater yigersalu ይጠራጠራሉ። ጥርጣሬአቸው እውነት ቢመስልም ሀቁ ግን ሌላ ነው። እንዲያውም ወያኔንና የትግራይን ህዝብ መለየት እስከሚያቅታቸው ድረስ የወያኔን አምባገነንነት፣ ዘረኝነትና አድሎአዊ አገዛዝ ለማጋለጥ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ወያኔን ለመቃወም በተጠሩ ዝግጅቶች ሁሉ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሲሆኑ ገንዘባቸውንና ጊዜአቸውን ለመሰዋትም ወደኋላ አይሉም።
ትዝብት ሶስት
እነዚህ ኃይሎች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነትና ሉአላዊነት መቆማቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ችግሩ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከነሱ ባላነሰ እንደሚወዱ መረዳት አለመቻላቸውና በተለይ የብሄር ጥያቄ የሚያነሱና በዚያ መሰረት የተደራጁ ወገኖች ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዳይቻል ዋነኛ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸው ነው። በነሱ እምነት በአገራችን የመደብ እንጂ የብሄር ጭቆና መቼም ኖሮ አያውቅም። የኢትዮጵያን አንድነት ለማምጣት በተደረጉ ጦርነቶች ወገኖቻችን አልቀዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በባርነት እንዲያገለግሉ ሆነዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል ወይም ተወርሷል፣ ስለሆነም ወደድንም ጠላንም እንደምንኮራባቸው ታሪኮች ሁሉ ይህም ያገራችን ታሪክ ነውና ተመዝግቦ ለትውልድ ይተላለፍ የሚሉትን ወገኖች በኢትዮጵያ ጠላትነት ለመፈረጅ ለአፍታም አያቅማሙም።
ትዝብት አራት
የዚህ ዓላማ አራማጆች የትግል ስልት ምርጫ የላቸውም። ወያኔ የሚወድቀው በምርጫ፣ በህዝብ አመጽ ወይም በትጥቅ ትግል ቢሆን ግድ የላቸውም። ወያኔን የሚጥለው ኃይል ከኬንያ፣ ከሱዳን፣ ከሱማሌ ወይም ከኤርትራ ቢነሳ ጉዳያቸው አይደለም። ዋንው ቁም ነገር ወያኔ ወድቆ ያ በሚስጥር የያዙት ዓላማቸው መሳካቱ ብቻ ነው። ታዲያ ሰሞኑን ከኤርትራ ተነስተን ተከዜን አቋርጠን አገራችንና ህዝባችንን ከወያኔ አምባገነናዊ አገዛዝ ነጻ የማውጣት ጉዞአችንን ጀምረናል በሚሉት ኃይሎችና በህዝብ ተሳትፎ የቆመውንና አማራጭ የመረጃ ምንጭ የሆነው ሚዲያ ላይ ኃይለኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ የከፈቱት ለምንድነው? ከተወሰነው የአገራችን ክፍል ወጣቶች መጥተው እነዚህን የነጻነት ታጋዮች እንድይቀላቀሉ የሚማጸኑትስ ለምን ይሆን?
ትዝብት አምስት
እኔን ጨምሮ ብዙዎች ተመልሰን ወደ ጦርነት መግባታችንና ወንድማማቾች ሊገዳደሉ መሆኑን ስናስብ እናዝናለን። ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ስለማንችል ስጋታችንም በዛው ልክ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን የሰላሙ ሁሉ በር ተዘግቶ ወደዚህ አማራጭ ተገደን እየገባን እንደሆነም እንረዳለን፣ ህይወታቸውን ለአገራችን ነጻነት ለመስጠት የቆረጡትን
ጀግኖቻችንን እናከብራለን መልካሙን ሁሉ እንዲገጥማቸውም እንመኛለን። በተቃራኒው እኔ እንደምገምተው አፍራሽ ኃይሎቹ ይኸ ሁሉ ጫጫታ የሚያበዙትና አቧራ የሚያስነሱት ይህ የነጻነት ኃይል ከተሳካለት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የቆሙለትን አላማ ገድሎ እንደሚቀብረው ስለሚያውቁ ነው። የነጻነቱ ኃይል በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ አንዳርጋቸው ጽጌ ራዕይ የታነጸ፣ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ወጣቶች የተሰባሰቡበት እና ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መመስረት እንደሚፈልግም ጠንቅቀው ይረዳሉ።
ውድ አንባቢያን
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ እነዚህ ኃይሎች ሁለት ገጽታ አላቸው። የመጀመሪያዎቹ ብዙ ተከታይ ያላቸው ሲሆኑ ዋና ዓላማቸው ያለውን የአንድ ብሄር የበላይነትን አስወግዶ በሌላ መተካት ነው። ይህን አላማቸውን ይፋ አውጥተው በዚያ ዙሪያ ተደራጅተው መታገል እንደማያዋጣቸው በሚገባ ስለሚረዱ የተለያዩ ጭንብሎችን አጥልቀው አፍራሽ ተልኮአቸውን ሲፈጽሙ ይስተዋላሉ። ሁለተኞቹ ደግሞ ዓለም የምትሽከረከረው በእነሱ ዙሪያ ብቻ የሚመስላቸው ግለሰቦች ሲሆኑ እነሱ ያልመሩት ድርጅት ወይም ትግል ውጤታማ ሲሆን ማየት ሞታቸው ስለሆነ ያንን ለማጨናገፍ የማይገቡበት የለም።
እነዚህ ኃይሎች ናቸው እንግዲህ ግንባር ፈጥረው የነጻነት ጉዞውን ለማደናቀፍ ሌት ከቀን የሚሰሩት። ለዚህም ነው እንግዲህ በቅርቡ በነጻነት ታጋዮች እቅስቃሴ ላይ ተልካሻ ምክንያቶቻቸውን በመደርደርና የአዞ እንባቸውን በመርጨት ነጻነት ናፋቂው ህዝብ በጥርጣሬ እንዲመለከተው ለማድረግ የሚሞክሩትና በሁላችንም ጥረት በየጊዜው እየጠነከረ የመጣውን የመረጃ ምንጫችንን ጥላሸት በመቀባት ለማጥፋት ከወያኔ ባልተናነሰ ጦርነት የከፈቱበት።
በግልጽ ተነጋግረን እነዚህ አፍራሽ ኃይሎች ያጠለቋቸውን ጭንብሎች እስወልቀን ካላጋለጥናቸው አንድም አፍራሽ ተልእኮአቸውን እንዲቀጥሉ ፈቅደን የወያኔን ዘላለማዊነት እናረጋግጣለን አለያም ለአገር ከፋፋዮችና ገንጣዮች መንገዱን ከፍተን ቁራሽ ቁራሻችንን ይዘን እንበታተናለን።
No comments:
Post a Comment