Saturday, July 11, 2015

የመከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ ጦር ሰራዊት አባላት ሆይ! የምትሞቱት ለማን ነው?” ከአርበኞች ግንቦት 7

“የመከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ ጦር ሰራዊት አባላት ሆይ! የምትሞቱት ለማን ነው?” ከአርበኞች ግንቦት 7

በዚህ ሳምንት ከተከናወኑት አበይት ጉዳዮች አንዱ፤ የአርበኞች ግንቦት 7 ጦር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መጀመሩ ነው። የአርበኞቹ እንቅስቃሴ በሰሜን ትግራይ ተጀምሯል። ከዚያም አልፎ ሌላው ግንባር ወደ ወልቃይት ጠገዴ ዘልቆ በመግባት፤ የወያኔ ወታደሮችን እየደመሰሰ መሆኑን ከስፍራው የሚደርሱን ዜናዎች አረጋግጠዋል።

ከአርበኞች ግንቦት 7 ህዝብ ግንኙነት “የመከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ ጦር ሰራዊት አባላት ሆይ! የምትሞቱት ለማን ነው?” በማለት ከዚህ የሚከተለውን መግለጫ ይፋ አድርጓል።

አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ በረሃ ወርዶ ነፍጥ በማንሳት ወደ ጦርት የገባው ተገዶ ነው፡፡ ያስገደደውም ተፋላሚው ቡድን አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የህዝባዊ ሓርነት ትግራይ አገዛዝ ነው፡፡ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ አገዛዝ ምን፣ ምን አይነት ግፍ እና በደል እያደረሰ እንደሚገኝና ምን አይነት መንግስታዊ ስርዓት እያራመደ እንዳለ ለእናንተ ለመከላከያ፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለልዩ ኃይልና ለሚሊሻ ጦር ሰራዊት አባላት መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ምክንያቱም እናንተም የአገዛዙ የግፍ ሰለባ ሌላኛው አካል ስለሆናችሁና ፍዳውን እያየ ከሚገኘው ህዝብ አብራክ ስለተከፈላችሁ የህዝቡ ብሶት ብሶታችሁ ስለሆነ ነው፡፡
welkayt-294x300
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የሚዋጋው በጉልበት ስልጣን ይዞ በመንግስትነት ስም ኢትዮጵያን እያዋረደ፣ ህዝቧን እየገደለ እያስገደለ፣ እያሰረ፣ እያሰደደ፣ እያስራበ እና እያሳረዘ የሚገኘውን ህወሓት የሚሰኝ ዘረኛ ቡድን በኃይል ደምስሶ ህዝቡን ብቸኛው ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ለማድረግ በማለም ነው፡፡ አርበኞች ግንቦት 7 ህወሓትን በጥይት በመደብደብ ገድሎ ጉድጓዱን አርቆ በመቆፈር ከቀበረው በኋላ የሽግግሩን ሂደት ከማገዝና የህዝቡ የስልጣን ባለቤትነት በተግባር እንዲረጋገጥ ከማድረግ ውጭ በምርጫ ተወዳድሮ የመንግስት ስልጣን የመያዝ ዓላማ ፈፅሞ የለውም፡፡ አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞካራሲ ንቅናቄ ስልጣን የህዝብ እና የህዝብ ብቻ አንዲሆን አንጂ አምርሮ የሚታገለው መንግስት የመሆን ምኞት ኖሮት አይደለም፡፡ በታሪክ እስካሁን ከተደረጉት የነፃነት ትግሎች የአርበኞች ግንቦት ሰባትን ትግል ልዩ የሚያደርገው አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ይሄ ነው፡፡
እኛም እናውቃለን፣ የኢትዮጵያ ህዝብም ያውቃል፣ እናንተም ታውቃላችሁ የአገሪቱን ሀብት እየዘረፉ በብልፅግና ላይ ብልፅግና እየተጎናፀፉ፣ ከመኪና መኪና እያማረጡ፣ በዲዛይነር የተሰራ ሱፍና ከረባት እየለበሱ፣ ጮማ እየቆረጡ ዊስኪ እየተራጩ፣ የተንደላቀቀ የቤተ መንግስት ህይወት የሚመሩት የህወሓት ባለስልጣናት ወደ ስልጣን ሲመጡ ምንም የከፈሉት ዋጋ የለም በድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ልጅ ደም እንጂ፡፡ አሁንም ስልጣናቸውን ማስቀጠል የሚፈልጉት የደሃውን ህዝብ ልጅ ለጦርነት በማሰለፍ በእሱ ደም እንጂ እነሱና ዘመድ አዝማዶቻቸው ምንም የሚከፍሉት ዋጋ አይኖርም፡፡
መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ሆይ! በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሞትክ፣ በሶማሊያ ጦርነት ሞትክ፣ ኦጋዴን፣ ጋምቤላ፣ ሚዛን ቴፒ፣ አርማጭሆ… ላይ ደጋግመህ ሞትክ አሁን ደግሞ ትግራይ ክልል ውስጥ እየሞትክ ትገኛለህ፡፡ በአንተ ክቡር ህይወት፣ በአንተ ደምና አጥንት፣ በአንተ ታሪክ… ሊወድቅ የዘመመው የህወሓቶች የስልጣን ደሳሳ ጎጆ ለጊዜውም ቢሆን ተደግፎ ቆሞ አየህ እንጂ ለአንተ፣ ለቤተሰብህ፣ ለአገርህ ኢትዮጵያ፣ ለበቀልክበት ህዝብ ምን አተረፍክ? ባንተ ሞት እነማን ሹመትና ሽልማት እንዳገኙ ኑሯቸው እንደ ተቃና አንተው ራስህ ጠንቅቀህ ታውቀዋለህ፡፡ የምትሞተው አንተ፤ የምትዋረደው አገርህ ኢትዮጵያ፤ የሚረገጠው የወለደህ ህዝብ፤ የምትሞትለት መልሶ እየገደለህ የሚገኘው አንተው ራስህን ነው፡፡
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የጀመረው ጦርነት የጥቃት ስልቱን እየቀያየረ ከህወሓት አድማስ ረቀቅና ወሰብሰብ ባለ መልኩ በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘናት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን ፍልሚያው አንደኛው ጭቆናን ለማስወገድ ሌላኛው ጭቆናን ለማስቀጠል ሲባል ጎራ ለይተው በተሰለፉ ሁለት ጭቁን ወንድምአማች ኢትዮጵያዊያን መካከል መሆኑ ግን አርበኞች ግንቦት ሰባትን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ በመሆኑም ህወሓት በእናንተ ሞት ነግሶ ለመኖር አስታጥቆ ለእርድ ያሰለፋችሁ የመከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ ጦር ሰራዊት አባላት የታጠቃችሁትን ጦር መሳሪያ አፈሙዝ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የእናንተ ጠላት ወደሆነው ህወሓት እንድታዞሩ አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ አለበለዚያ ግን የምትከፍሉት ዋጋ ከመቸውም ጊዜ በላይ በእጅጉ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ ጦርነቱ በጣም ፈታኝ፣ ይህ ነው ተብሎ በቃላት ሊገለፅ የማይችል ዋጋ የሚያስከፍል፣ እስካሁን በተለያዩ ቦታዎችና ወቅቶች ሲደረግ ከነበረው የጎሬላ ውጊያ የተለየ የረቀቁ የውጊያ ስልቶችን የሚከተል መሆኑን ቃፍታ መሲን፣ ኮርጃሙስ፣ ማይ ሰገል፣ በዋል፣ ጓንጋ አሳግላ እና ማይ እምቧ ላይ በተደረገው ጦርነት በየዋህነት ተማግደው የተረፉ ጓዶቻችሁ ካሉ ጠይቃችሁ እውነታውን ማረጋገጥ ትችላላችሁ፡፡
ህወሓት የኢትዮጵያ ህዝብ በጠቅላላ አንቅሮ የተፋው የበሰበሰ ስርዓት መሆኑንም እንድታስታውሱ አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባችኋል፡፡
ዘረኛው የህወሓት ቡድን ያቋቋመው መንግስት በቅርቡ ብትንትኑ መውጣቱ አይቀርም የእናንተ ለስልጣኑ መጠበቂያ አሽከርነት ያቆማችሁ የመከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ ሰራዊት አባላት ከንቱ ሞት ግን አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄን ከወዲሁ በእጅጉ ያሳስበዋል ያሳዝነዋልም፡፡ ዘላለማዊ ክብር ለጀግኖች ሰማዕታት ድል ለአርበኞች ግንቦት 7 ጀግኖች ሞት ለዘረኛውና ፋሽስቱ ወያኔ!

No comments:

Post a Comment