Saturday, February 22, 2020
ለክቡር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አዲስ አበበ፤ ኢትዮጵያ፤ ዛሬም አሰብን እንላለን! በያዕቆብ ኃይለ ማርያም
የአድህሮትና የክፍፍል በአንድ ጎራ፤ የነጻነትና የአንድነት ኃይሎች በሌላው ጎራ፤ ሰቅዞ፤ በያዛቸው ትግል ዉስጥ ሆነው፤በሚፋለሙበት በዚህ ተስፋ ሰጪ ወቅት፤የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዛሬ ማንሳት፤ዋናው የተጀመረዉ በጎ እንቅስቃሴ፤ ማዘናጋት እንዳይሆን የሚሰጉ ሰዎች ይኖራሉ። ሆኖም የአሰብ ባለቤትነት ጥያቄ የአገር ሕልዉናና ልማት ጥያቄ አንዱ አካል እንደመሆኑ መጠን፤ዛሬ በተከሰተዉ ብዙ ተስፋ ከጫረዉ የዲሞክራሲና የአንድነት እንቅስቃሴ ጋር ተደምሮ ገና በጥዋት መነሳት ያለበት ጉዳይ ነዉ። የአሰብን ጥያቄ ግዙፍነት ተረድተዉ አዲሶቹ የኢትዮጵያ መሪዎች በቅድሚያ አጀንዳቸዉ ዉስጥ እንዲያካትቱት በአክብሮት ለማሳሰብ ነዉ። ዛሬ የተነሱት የኢትዮጵያ መሪዎች የኢትዮጵያን ጥቅሞችና መብቶች የሚያስከብሩ ናቸዉ የሚል ፍንጭ ስለአየን ግዳዩን እንድናነሳ ቀሰቀሰን። ኤርትራ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ተገንጥላ፤ የኢትዮጵያን ሉዐላዊ ግዛት የነበረችዉን አሰብን ስትይዝ፤አሰብ በታሪክ፤በሕግና በስነመንግሥት እሳቤ የኤርትራ አካል እንዳልነበረች ለማስረዳት ኢትዮጵያዉያን ምሑራን ያልፈነቀሉት ድንጋይ፤ ያልማሱት ስር አልነበረም። በወቅቱ አሰብ የኢትዮጵያ ግዛት ለመሆኗ ለማስረዳት ያህል ኢትዮጵያዊ ጉዳይ አልነበረም። የአገሪቱ ፕሬዚደንት የነበሩት መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ የኢሓደግ ባለሥልጣናት አቶ መለስ ዜናዊ፤ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና አቶ በረከት ስመዖን ከመንገዳቸዉ ወጥተዉ፤ አሰብ የኤርትራ ግዛት ነች፤ኢትዮጵያ በአሰብ ላይ ምንም መብት የላትም ሲሉ መስክረዋል። ይኸ ስም ማጥፋት ሳይሆን በሰነድ ሊረጋገጥ የሚችል ጉዳይ ነዉ። እ.አ.አ. በ2000 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል በተደረገዉ አላስፈላጊና ትርጉም የለሽ ጦርነት በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት እንደሚደመደም ግምት ተወስዶ ስለነነበረ፤ ጦርነቱ አልቆ ወደ ድርድር በሚኬድበት ጊዜ ለኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ግበዐት የሚሆኑ፤ በሕግና በታሪክ የተደገፉ ሃሳቦች፤ ምሁራን በተለያዩ ሚዲያ አቅርበዉ ነበር። ጦርነቱ እንደተጠበቀዉ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ሲደመደም ኢሕአደግ ከመነሻዉ፤ኤርትራን ለማስገንጠል በብዙ የደከሙት የኢትዮጵያ ጠላት የአልጄሪያዉ ፕሬዚደንት ቡተፍሊካን አስታራቂ እንዲሆኑ ጠየቀ። ቡተፍሊካም አቶ ኢሳያስን ና አቶ መለስን አጨባብጠው ዉዝግቡ ዓለም ሁሉ እምነቱ ወደጣለበት ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (International Court of Justice) ከመውሰድ ፈንታ በገንዘብ በተገዙ ግለሰቦች እንዲዳኝ የድንበር ኮሚሽኑ ጉዳይ ወደዚያ ተመራ። እዚህ ላይ አንድ አስገራሚ ምናልባትም በአገር ክሕደት ወንጀል የሚያስጠይቅ በደል መጠቀስ አለበት። የድንበር ኮሚሽኑ ዳኞች የቀረበላቸውን ማስረጃዎች ተንተርሰዉ ጾረና የኢትዮጵያ ግዛት መሆኗን ዉሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ በኢትዮጵያ መንግሥት ተእዛዝ ኢትዮጵያን የወከሉ ጠበቆች፣ “የለም ተሳስታችኋል፤ ጾረና የኤርትራ ግዛት ነዉ” ብለዉ በመከራከራቸዉ ዳኞቹ ምርጫ በማጣት ጾረናን ወደ ኤርትራ አካለሉት።በታሪክና በሕግ ሥነ መንግሥት የተካኑ ኢትዮጵያዉያን አገልግሎታቸዉን በነጻ እንደሚለግሱ ቢረጋገጥም፤ ኢሕአደግ ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪካዊና ወቅታዊ ግንኙነት ምንም ዕዉቀት የሌላቸዉ ዳኞች በዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ተቀጥረዉ፤ ጉዳዩ ወደነዚህ ዳኞች ችሎት ተመራ።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment