ሃገራችን ሩብ ምዕተ-ዓመት በቆየችበት ህወሃት-መር የጎጠኝነት ፖለቲካ እንደ አማራው ግራ የተጋባ ህዝብ/ልሂቅ የለም፡፡አማራው ከጎጥ ፖለቲካው ጋር መላመዱ አልሆን ብሎት እስካሁን በገዛ ሃገሩ እንደ መፃተኛ ሆኗል፡፡በጎጥ መደራጀቱ እንደ የማይገለጥ ምስጢር የሆነበት የአማራ ልሂቅ መገፋት ገፍቶት የመሰረተው መአድ የተባለው ፓርቲ ግማሽ ጎኑ አፍታም ሳይቆይ ወደ ህብረብሄራዊ ፓርቲነት ሲቀየር መቀየሩን ያልወደደው ቅሪቱ መአድ እንደ ሲኒ ውሃ እያደር ተመናምኖ ወዳለመኖር የተጠጋ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ መአድ የተባለው ፓርቲ መኢአድ ወደሚባል ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ የተቀየረው መለስ ዜናዊ አማራውን የሚያሳድድበትን በትር፣የሚያሳርድበትን ቢለዋ ወደ ሰገባው ሳይመልስ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው አማራው በጎጥ መደራጀቱን ስለማያውቅበት ነው፡፡ይህ የዘመኑን ፋሽን ያለመከተል የአማራው ግርታ ያደረሰበት ጉዳት መጠነ ሰፊ ነው፡፡
አማራን ሁሉ ባላንጣ አድርገው የሚያስቡ ኦነጋዊ የኦሮሞ ብሄርተኞች የአማራ ልሂቃንን ለዘውግ ፖለቲካ ባይትዋርነት “አማራው የብሄር ፖለቲካው አልገባ ብሎት ሲደናገር ሩብ ምዕተ አመት ሞላው፤ይህ ለኦሮሞ መልም ነው” ሲሉ በመሳለቅ ይገልፁታል፡፡እነዚህ ቡድኖች አማራው ሲሞትም፣ሲፈናቀልም፣ሲንጓጠጥም ሲገደለም ዝም ማለቱ ብቻ ይስማማቸዋል፡፡አማራው መናገር ሲጀምር ኦነጋዊ የኦሮሞ ብሄርተኞች እና ህወሃታዊ ትግራዊያን የሚናገረው ሁሉ ያስበረግጋቸዋል፡፡አማራው በዘውጉ የሚደርስበትን ሁሉ ችሎ የለመደውን ኢትዮጵያዊነት ሲያጠብቅ በኢትዮጵያዊነት ስም ፍላጎቱን በብሄረሰቦች ላይ የሚጭን ጨቋኝ ሲሉ ኢትዮጵያን በማለቱ በድንጋይ መወገር የሚገባው ሃጢያተኛ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ እነሱው በየደረሱበት በሚሰኩት የአማራ ጥላቻ ሳቢያ በአማራነቱ መሞቱ ተሰምቶት ኢትዮጵያዊነቱን ሳይጥል አማራነቱ እያስገደለው እንደሆነ ከተናገረ ደግሞ በጭብላምነት ያብጠለጠሉታል፡፡ አማራውም ይጥለው ዘንድ የማይችለውን ኢትዮጵያዊነት በደሙ ውስጥ ይዞ የተጋረጠበትን የህልውና አደጋም ለመከላከል ቢጣጣርም አማራነቱን ማጠባበቁ ከኢትዮጵያዊነቱ የሚጋጭ እየመሰለው በፈራተባ ውስጥ ይኖራል፡፡
የአማራው ዘመን አመጣሹን የጎጥ ፖለቲካ ፋሽን ተረድቶ ራሱን ከዘመኑ ጋር ማራመድ አለመቻሉ(በባላንጣዎቹ ንግግር “ግራ መጋባት”) ቋጥኝ የሚያክል ፈተና ያንዣበበትን የአማራውን ህዝብ ያለጠበቃ አስቀርቷል፡፡የጎጥ ፖለቲካውን መላመድ ድሮ ቀርቶ ዛሬ ያልሆነላቸው የአማራ ምሁራን በአማራ ብሄርተኝነት መስመር ተሰልፈው ሌሎች እንደሚያደርጉት ለህዝባቸው መሞገት አለመቻላቸው ለኦነግ ግርፍ የኦሮሞ ብሄርተኞች እና ህወሃት ቀመስ ትግራዊያን የአባት ገዳይን በግላጭ እንደማግኘት ያለ ሰርግ እና ምላሽ ነበር፡፡ሆኖም በአማራው ላይ የሚወርደው ዱላ የተኛ ቀርቶ ሙት የሚቀሰቅስ እየሆነ ሲመጣ ዛሬ ላይ የአማራ ምሁራንም ከእንቅልፋቸው መንቃት ጀመሩ፡፡ይህ ደግሞ ለኦነጋዊ የኦሮሞ ብሄርተኞች እና ለህወሃቶች መልካም አዝማሚያ አይደለም፡፡ ለእነሱ መልካም የሚሆነው ባፈው ሃያ ሰባት አመት እንደሆነው አማራው ከሞት በበረታ ዝምታ ውስጥ ሆኖ ግድያውንም፣መንጓጠጡንም፣መፈናቀሉንም፣መገደሉንም አጎንብሶ ሲቀበልነው፡፡
ይህ ሁለት ጥቅም አለው፡፡ አንደኛው አማራው “በሰራው ታሪካዊ ወንጀል” የሚሸማቀቅ በደለኛ እንጅ ስልጣን የሚጋራ የፖለቲካ ሃይል አለመሆኑ ለኦሮሞ ብሄርተኛ ሁለተኛውን ግዙፍ ዘውግ ከስልጣን ተገዳዳሪነት ይቀንስለታል፡፡ ሁለተኛው ጥቅም በታሪክ በድሎናል የሚሉትን ህዝብ በማሸማቀቅ የሚያገኙት ስሜት በቀለኝነት የሚጋልበውን የስነ-ልቦና ቀውሳቸውን ተንፈስ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ አሁን አሁን ከበደል ብዛት የተነሳ እያቆጠቆጠ ያለውን የአማራ ብሄርተኝነት አይወዱትም፡፡ ምክንያቱም የአማራው ብሄርተኝነት ካቆጠቆጠ አማራው ያለ ስራው የተለጠፈበትን የበደለኝነት ተረክ የሚያፈርስ መልስ መስጠት ይጀምራል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አማራውን ጭራቅ አድርገው የሚያቀርቡበትን ተረክ ብቻቸውን እያወሩ፣ያወሩትም እንደእውነት እየተቆጠረ ወደስልጣን ማዝም አይቻልም፡፡አማራውን የማይስተሰረይ ሃጢያት የሰራ በደለኛ አድርጎ ማሸማቀቅም አይቻልም፡፡ ስለዚህ አማራው በደሉ እንዲሰማው አይፈለግም! በአይን የሚታየውን በአማራ ህዝብ ላይ ያንዣበበ አደጋም ሆነ በዚህ ህዝብ ላይ በወያኔ እና ኦነግ የተደረገውን ግፍ አንስቶ የሚሞግት አማራም ሆነ ሌላ የሰው ዘር አይፈለግም፡፡
ከወያኔ ወደ ስልጣን መምጣት ወዲህ በአማራ ህዝብ ላይ በርካታ በደል የተፈፀመ፣አሁንም ይህ ህዝብ በሃገሪቱ ባሉ የዘውግ ፖለቲከኞች ሁሉ በክፉ አይን የመታየት ፈተና ውስጥ ያለ ቢሆንም የአማራ ምሁራን እና ልሂቃን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነታቸውን የሚቀማቸው የሚመስላቸውን የአማራ ብሄርተኝነት መልበስ አይፈልጉም፡፡በአንፃሩ የወጡበት ህዝብ ያለበት ፈተናም ያሳስባቸዋል፡፡ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነታቸውን ሳይጥሉ ስለ አማራው ህዝብ እንግልትም ይሟገታሉ፡፡የአማራ ህዝብ ሁሉ ባላንጋራቸው የሚመስላቸው ኦነጋዊ የኦሮሞ ብሄርተኞች ደግሞ መለስ ዜናዊ እንዳደረገው የአማራን ህዝብ ያለ አንዳች ጠበቃ መቅጣት ስለሚፈልጉ ይህን ነገር አምርረው ይጠላሉ፡፡ኢትዮጵያዊነትን ሳይጥል የአማራ ህዝብ ለምን በገዛ ሃገሩ እንዲህ ይደረጋል የሚል የሚል የአማራ ልሂቅ ሲገጥማቸው ሌባ እጅ ከፍንጅ እንደያዘ ሰው ባለድልነት ይሰማቸዋል፡፡
ለአማራ ልሂቃን/ምሁራን ኢትዮጵያዊነት የክብር ልብስ እንጅ ጭንብል አይደለም!ኢትዮጵያዊነት ጭንብላችን ቢሆን ኖሮ በአማራ ህዝብ ላይ ከመለስ ዜናዊ እስከ ጃዋር መሃመድ ነጋሪት ጎሳሚነት የደረሰው በደል ጭንብል ቀርቶ ቆዳ የሚያስወልቅ ክፉ ነውና “ጭንብል” ወርውሮ ጎጠኛ መሆን አስቸጋሪ ሆኖ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በአማራ ህዝብ/ልሂቅ/ምሁር ዘንድ በደም ውስጥ የሚሮጥ ልክፍት እንጅ ጭንቅላት ላይ ለይምሰል ሸብ የሚደረግ ቡቱቶ ጨንብል አይደለም፡፡የአማራ ልሂቃንን በጭንብላምነት የሚከሱ የኦሮሞ ብሄርተኞች ኢትዮጵያ እንደኩንታል አናታቸው ላይ ተጭና የምትከብዳቸው ሸክማቸው እንደሆነች የፈረንጅ ጋዜጠኛ እጅ እየመቱ የሚምሉ፣ ኦሮሚያ የምትባል ሃገር ናፍቆተኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁሉም እንደነሱ ይመስላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ማለት ትርጉም ስለማይሰጣቸው ሁሉም እንደእነሱ ኢትዮጵያን በጭንብሉ፤መንደሩን ሃገር አሳክሎ በልቡ ተሸክሞ የሚጓዝ የማነስ ልክፍተኛ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ የሌለ ጭንብል ይፈልጋሉ፡፡
ለማንኛውም እነሱ ጭንብል የሚሉት ነገር ለአማራው ማን እንደጣለበት የማያውቀው፣በደሉን እንኳን እንዳይቆጥር የሚያደርግ ኢትዮጵያን የሚያስብለው ከደሙ ጋር በመላ ሰውነቱ የሚዞር ልክፍቱ እንጅ አናቱ ላይ የተንከረፈፈ ጭንብሉ አይደለም፡፡ይህ ልክፍቱ ነው ኢትዮጵያን ካለ ጋር ሁሉ የሚያዛምደው፡፡አማራው ኢትዮጵያን ይላል ማለት ግን ስሟ በተጠራበት ልገኝ በሚልላት ሃገሩ አማራነቱ ወንጀል ሆኖ ሲያስገድለው ዘላለም የማይገባው ነፈዝ ነው ማለት አይደለም፡፡ኢትዮጵያዊ ሆኖም በአማራነቴ አትግደሉኝ ማለትን የሚከለክል ፍርደ-ገምድል ህግ የለም! “ኢትዮጵያዊ ነኝ ካልክ አማራ ነህ ብየ ስገድልህ አመጣጤ አይግባህ” የሚባል አካሄድ ድሮ ቀርቷል፡፡ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን ሰው አማራ ነህ ብሎ ገድሎ ያስገደለህን ምክንያት ስሙን አትጥራ ማለት የሞኝ ብልጠት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን ሰው አማራ ነህ ብሎ የሚያስገድለው አባዜ ሁለቱንም የመጥላቱ በሽታ መሆኑን ማን ያጣዋል?
ለማንኛውም አማራው አጠለቀው የተባለው የኢትዮጵያዊነት ጭንብል የኢትዮጵያዊነቱን ከፍታም ሳይለቅ በአማራነቱ ሚመጣበትን ፍላፃም ለመከላከልም የመሞከሩ የሚዛናዊነቱ ምልክት ነው፡፡ አማራውን ኢትዮጵያዊ ነኝ በል እያሉ ግን በአማራነቱ የሚገድሉት አዳኞች ደግሞ ይህን አይወዱምና ኢትዮጵያዊነት ከአማራው ላይ እንደማይወልቅም፣ ጭምብል እንዳልሆነም እያወቁ “ጭንብልህን አውልቅ” ይላሉ፡፡ አይሆንም እንጅ አማራው ችሎ ኢትዮጵያዊነቱን እንደተንከረፈፈ ጭንብል ቢያወልቅ ለኢትዮጵያ መልካም አይሆንም፡፡ አማራው ኢትዮጵያዊነቱን አወለቀ ማለት ትልቁ የኢትዮጵያ አእማድ ፈረሰ ማለት ነው፡፡ ይሄኔ ኢትዮጵያዊነት በአማራነት ይተካል፤ከተተካ ደግሞ የጎጥ ፖለቲካ መለያ የሆነው “ሁሉ ኬኛ” የሚባለው አባዜ አማራውንም ይዋሃደውና የቱ የአማራ የቱ የኦሮሞ ግዛት እንደሆነ የመነጋገሪያ ፋታ የለም! ያኔ መናጋገሪያው ጡጫ ይሆናል፡፡አንዴ ወደ ቁልቁለት ከተወረደ ደግሞ ጡጫ የማይጨብጥ እጅ ያለው የለም፤በአንድ እጅ አስር ጡጫ የሚጨብጥ ባለ ዘጠኝ ሱሪም የለም!
No comments:
Post a Comment