ከፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.
ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ
“ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” ብለው አንድነታችንን የሚያጠናክር ንግግር
ሲናገሩ የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ጥቅም በሚገባ እንደ ገለጹት ተረድተናል።
ቀጥለውም ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ መውሰድ ይቻላል! ነገር ግን ከኢትዮጵያዊ ልብ
ኢትዮጵያ ዘላለም አትወጣም ትኖራለች! ብለው የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ጥቅም
ደግመው አጉልተውታል።
ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ተምሳሌት እንደመሆኗ በብዙ ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ
ኢትዮጵያ ልዩ ቦታ አላት። ኢትዮጵያውያን ብዙ ላናውቅና ላንረዳ እንችላለን እንጂ፣
ከኢትዮጵያ ከኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያዊኒዝም አስተሳሰብና ፍልስፍና ተወልዷል።1
ኢትዮጵያኒዝም የተፈጠረው በኃይማኖትና በፖለቲካ ከጭቆና ውስጥ የነበሩ የጥቁር ዘር
ባላቸው ሰዎች ነው። አፈጣጠሩ አፍሪቃ ለአፍሪቃኖች ትገባለች የሚለውን የፓናፍሪካ
ፍልስፍና አስቀድሞ በመጀመሪያ የገለፀ ነው። ሲጠነሰስ ጀምሮ መንፈሳዊነትን ከሰው ልጆች
ነፃነት ጋር አጣምሮ አቀናጅቶ አስተባብሮ የተፈጠረ ፍልስፍና ነው።2
ኢትዮጵያኒዝም በስፋት የተጀመረው 1660 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን ከ1776 ከአሜሪካ የነፃነት
ትግል በኋላ እያየለ መጣ። አፍሪቃ/አሜሪቃኖች በአሜሪካ ነፃነት በተፈጠረው ለቀቅ ያለ
ሁኔታ በመጠቀም ኢትዮጵያኒዝምን ፈጠሩ። በ1808 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ
ቤ/ክ በአሜሪካ አቋቋሙ።3 በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና በዓለም
ተስፋፋ። የሚገርመው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም የታወቀ ፍልስፍና ሆኖ አልገባም።
ትልቁ ጥያቄ አሁን ኢትዮጵያኖች እንዴት ይህን ፍልስፍና ያዩታል? የሚለው ነው። ስለ
ሐገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ ይጠቅማል ብለው ይሄን ፍልስፍና መመርመርና መወያየት
ቢችሉ ጥሩ ነው የሚል አስተያየት አለን። እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ቀላል የምንቆጥረው
ኢትዮጵያዊነት በኢትዮጵያኒዝም መልክ በሌሎች ሕዝቦች ዘንድ ያለውን አዎንታዊ
ተጽእኖ ብንረዳው የበለጠ ኢትዮጵያዊነታችንን ለማጠናከር ሊረዳንም ይችል ነበር።4
የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናን ያስፋፉት እነማን ናቸው?
ኢትዮጵያኒዝምን በመጀመሪያ ያስፋፉት በ19ኛው ክፍለ ዘመን በመንፈሳዊ ዓለም
የተሰማሩት በአሜሪካና በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ቄሶች ናቸው።
በመሠረቱ ዘረኝነት በፖለቲካና በኢኮኖሚ ዓለማዊ ዙሪያ ላይ ብቻ ሳይሆን በጥቁሮች
መንፈሳዊ ዓለም ላይም ከባድ ጫና ነበረው። በሃይማኖት ሳይቀር ጥቁርን እንደ ሰይጣን ነጭን
እነደ መልዓክ ማየት የተለመደ የነጭ ቄሶች እምነትና ተግባር ነበር።
ገጽ 2 የ8
በመሠረቱ ነፃነት የሚፈልጉ የጥቁር ቄሶች ሁለት ችግሮች ገጠሟቸው፤ የነጭ ቄሶች ሲሰብኩ
ጥቁርን እንደ ሉሲፈር (ሰይጣን) ስለሚቆጥሩ የነሱ ቄስ ሆኖ ማገልገል በራሳቸው በጥቁሮች
ላይ መንፈሳዊ ኩነናን እንደ መቀበል መስሎ ስለ ታያቸው መቀበል አልዋጥላቸው አለ።
በሁለተኛ ደረጃ የነጭ ቄሶች ለጥቁር ቄሶች ምንም ቢሆን ያመራር ተግባር እንዳያገኙ
ከለከሏቸው። ሌላው በጣም ያማረራቸው ደግሞ የነጭ ቄሶች ሲሰብኩ የጥቁር ቄሶች ቀና
ብለው ወደ ላይ አምላክን ከማየት ወደ ታች አንገታቸውን ደፍተው ቁልቁል እንዲያዩ
አምላክን አሻቅበው እንዳያዩ የነጭ ቄሶች እንዳገዷቸው እንደሳፈሯቸውና እንደ ጨቆኗቸው
ይናገራሉ። ጭቆናው እየቀጠለ በሄደ ቁጥር ነጮች በሚቆጣጠሯቸው ቤተክርስቲያን መቀጠል
እንዳንገፈገፋቸው ይናገራሉ። በአንድ በኩል ቤተክ/ያን እንዲቀይሩ ጥያቄ ያቀርባሉ፤
ካልተቀየረ ግን ሌላ ቤተክ/ ለማቋቋም አቋም ይወስዳሉ። ያቀረቡት ጥያቄ ሙሉ የመንፈሳዊ
ነፃነት ማግኘት እንደ ምዕመናን ወደ እግዚአብሔርና ወደ ክርስቶስ ካላንዳች ዘረኝነትና
አድልዎ የሚያገናኝ ሃይማኖትና ቤተክ/ ፈለጉ። የነጮች ቤተክ/ ይህንን ጥያቄያቸውን
ሊያሟሉ አልቻሉም፤ ስለዚህ አዲስ ቤተክ/ ማቋቋም ወይም የነበረውን ቤተክ/ መቀየር
ፈለጉ፤ እናም በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ስሟ የተጠቀሰው ኢትዮጵያ ስለ ሆነች የኢትዮጵያ
ቤተክ/ እያሉ ማቋቋም ፈለጉ። ኢትዮጵያ የጥቁር ሐገር በመሆኗ ሌላው ደግሞ በመጽሐፍ
ቅዱስ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ስለሚል ያለምንም መድልዎና
ዘረኝነት ወደ እግዚአብሔር እምታገናኘን ቤተክ/ ናት ብለው ኢትዮጵያኒዝምን አቋቋሙ።5
ኢትዮጵያኒዝምን ያዩት እንደ መንፈሳዊ ጎዳና ከእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር በቀጥታ
መንገድ ከፋች፤ ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ የጥቁር ሐገር ሆና እራሷን ማስተዳደር የቻለች
ታላቅና ክቡር እንዲሁም የራሳችው ሐገርና እንደ አለኝታ በመቁጠር ነበር
የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና በመንፈሳዊ ትግል የጀመሩት፤ ያነፁትና የገነቡት።6
የሚገርመው የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና መንፈሳዊ መሠረት ይኑረው እንጂ ለተጨቆኑት
የዓለም ሰዎች ሁሉም መመሪያ አድርገው ነው የመሠቱት። ከመንፈሳዊ መሠረቱ ወደ
ዓለማዊ ጭቆናዎችን ለመቋቋም የኢትዮጵያኒዝም የሚከተሉትን ስምንት ባሕሪያት
ያጠቃልላል፤
1. መንፈሳዊ ነፃነት
2. በራስ መተማመን
3. ለራስ ክብር
4. እራስን መቻል
5. የውጭ ጭቆናን መቋቋም
6. መንፈሳዊ ነፃነት ከዓለማዊ ነፃነት ጋር ማጋራት አብሮ እንዲሔድ ማድረግ
7. የተጨቆኑ ሰዎች በጋራ መተባበር
8. ሰብአዊነት፣ መረዳዳትና እርስበርስ መተሳሰብ።
እነዚህ ስምንት ታላላቅ ፅንሰ ሀሳቦች የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና የሚያራምዱና በኋላ
ደግሞ ኢትዮጵያኒዝምን ተከትሎ የመጣውን ፓንኣፍሪካኒዝምን ለአፍሪቃ ነፃነት አንድነት
ሕድስና ስር መሠረት የሰጡ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ፅንሰ ሀሳቦች ናቸው። የኢትዮጵያ
ነፃነትም ጠቅሟል።7
ገጽ 3 የ8
እንግዲህ ኢትዮጵያኒዝም በ16ኛው ክፍለ ዘመን ተጀምሮ 18ኛው ክፍለ ዘመንን ተደግፎ
እሰከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የቆየ ፍልስፍና ነው።8
ኣሁንም ቢሆን የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ታቦይ ኢምቤኪ እንደሚሉት
የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና አሁን ላለንበት ዘመን ያስፈልጋል ይላሉ።9 እናም የኢትዮጵያ
ቤተክርስትያኖችም በደቡብ አፍሪቃ በአሜሪካና በካሪቢያን ሀገሮች አሉ፤ አሁንም ቢሆን
እነዚህ ቤተክርስትያኖች ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተጨመማሪ ያላለቀውን የነፃነት ትግል
የገለፁ ናቸው። ኢትዮጵያኒዝም በዓለም መድረክ ያመጣቸው ለውጦች በደቡብ አፍሪቃ
የአፍሪቃን ናሽናል ኮንግሬስ ያቋቋሙት በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ቤተክ/ ቄሶች ናቸው፤
እናም የመጀመሪያው የአፍሪቃ ናሽናል ኮንግሬስ ፕሬዝዳንት ጆን ላንጋቢሌሌ ዱቤ
በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናቸውና አቋማችው ታስረው ከተፈቱ በኋላ የአፍሪቃ ናሽናል
ኮንግሬስ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።10 የስማቸው ቅፅል ግልፅ ኢትዮጵያዊ ሁልጊዜ አደጋ ላይ
ያሉ ይሏቸው ነበር፤ እናም ነጮቹ 1906 የኢትዮጵያኒዝምን ፕሮፖጋንዳ አንቋሽሸው
ኢትዮጵያኒስትን ማሰርና አልፎ አልፎም መግደል ጀመሩ። ቀጥለውም የኢትዮጵያኒዝም
እንቅስቃሴን እንደ አደጋና እንደ ረብሻ አሰራጭ ቆጥረው የወታደር ኃይላቸውን አሳደጉ።
የዙሉ እንቅስቃሴ 1906 ቀጥሎም ባንባታ በሌሎችም አካባቢዎች ያፓርታይድ ተቃውሞ
እንቅስቃሴ ተጀመረ። እንቅስቃሴውውንም ያስጀመሩት እንዲሁም ይመሩት የነበሩት
ኢትዮጵያኒዝሞች ነበሩ።
እንዲሁም በተለያዩ የአፍሪቃ ሐገሮች በእንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ፖርቱጋል፣ በቅኝ ግዛት
ተገዝተው የነበሩ በኢትዮጵያኒዝም በመጠቀም ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር በማገናኘት ከቅኝ
አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ተጠቅመውበታል።
ራስተፈሪያኒዝንም የፈለቀው ኢትዮጵያኒዝም በሚለው ፍልስፍና ነው።
አፍሪቃ ለአፍሪቃዊያን የሚለው አስተሳስብ የመጣው ኢትዮጵያኒዝም በሚለው ፍልስፍና
ነው።
ቅኝ ግዛትን በመቃወም እነፕሬዝዳንት ጆሞ ኬኒያታ ሳይቀሩ በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና
እሰከ 1960 ዓ.ም ድረስ ተጠቅመውበታል።
በተለያየ መንገድ ቢገለፅም የተለያዩ ሰዎች በተለያየ መንገድ ቢጠቀሙበትም መሠረታቸው
ኢትዮጵያኒዝም እንደ ሆነና አፍሪቃን ሙሉ ከቅኝ ግዛት ለማውጣት እንደ ችቦ መብራት
እነደ ተጠቀሙብት ጥርጥር የለውም። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያኒዝም የኢትዮጵያ ሚና
በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ምንድነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።
በመጀመሪያ ኢትዮጵያን የኢትዮጵያኒዝም መሠረት አድርጎ ሲፀነስ ሐገሪቷ ልዩ ቦታ እንደ
ተሰጣት ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ኢትዮጵያ መንፈሳዊ ምግብ ለዓለም የሰጠች
መሆኑ ምንም የሚያሻማ ነገር የለውም። ዛሬ ቁሳቁሳዊ እርዳታ ከሚሰጡት እንደ አሜሪካ
ካሉ ሀገሮች ይልቅ ኢትዮጵያ መንፈሳዊ የነፃነት ምግብ ለዓለም የሰጠች ታለቅ ሐገር መሆኗ
ጥርጥር የለውም። እንግዲህ ኢትዮጵያን ሊጎዷትና ሊገድሏት ያሰቡ ሐገሮች ግለሰቦች
እንዲሁም ቡድኖች ማወቅ የሚገቧቸው ነገሮች ቢከሷትም በታሪኳ ቢፈርዱም ብትሞትም
ዘላለም የምትኖር ሐገር ናት።
ሁላችንም ቢሆን ይህችን ሀገር እንዲህ ያለ የተጨቆነውን ዓለም በሙሉ ያከበረውን መንፈሳዊ
ስጦታ ያበረከተች ሐገር አሳልፈው የሰጡንን አባቶቻችንና እናቶቻችንን ማክበር እንጂ በውጭ
ገጽ 4 የ8
ሐገር ፕሮፖጋንዳና በማናውቀው ሥልጣኔ ባልገባንና ባልተረዳነው ተውጠን ይህችን ሐገር
መናቅ ትልቅ ስሕትተ ነው።
በተጨማሪም ኢትዮጵያኒዝም የተመሠረተው በክርስትና ሃይማኖት ላይ የነጭ ቄሶች
ዘረኝነትን በማስፋፋት የእግዚአብሔርን መልክ በነጭ ቅልፅ በመግለፅ ሌሎችን በማግለልና
መጠቀሚያ ብቻ በማድረግ እንደማይቻል በመቃወም ነበር። የእስልምና ሃይማኖትን
በኢትዮጵያኒዝም አመለካከት ስናየው ተቃውሞ በተነሳበት ጊዜና ምዕመናኑ ስደት
ባጋጠማቸው ወቅት የኢትዮጵያ ድጋፍ ትልቅ ልዩነት እንዳመጣ ታሪክ ይመሰክራል።11
ኢትዮጵያ ለሙስሊሞች ያደረገችው ድጋፍ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና
ይገልፃል።
ከእኛ ምን ይጠበቃል?
በመጀመሪያ ይህንን ታሪክና ፍልስፍና ማወቅ ይገባናል።
ይህንን ታሪክና ፍልስፍናን መሰረት አድርገን ዘመናዊነትን ለመገንባት ዝግጁ መሆን
ያሰፈልጋል።
ከውጭ የተለያዩ ሀሳቦችን እየኮረጅን ሐገራችን የፈጠረችውን ፍልስፍና ማንቋሸሽና ታሪኳን
መወንጀል አላግባብ መፍረድ አይገባም።
መጠየቅ ያለብን የራሳችን ሐገር ምን ፈጠረች፣ ለምን በዓለም ዙሪያ ያሉ ሐገሮች እንደዚህ
ተማሩባት አከበሯት ብለን በትሕትና ሐገራችንን አክብረን ያለባትን የተወሳሰቡ ችግሮችን
አጥንተን ተወያይተን ተባብረን አንድ መንገድ ፈጥረን በሐገሪቷ ባህል መሰረት ካላንዳች
ኩረጃ ታላቋን ኢትዮጵያ መፍጠር እንችላለን።
መደምደሚያ ሃሳብ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ለአዲስ ብሔራዊ ውይይት
አሁን አዲስ የብሔራዊ ውይይት ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። ስለ ሐገራችን ነባራዊ ሁኔታ
በሰለጠነ አስተሳሰብ መወያየትና ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል።
ለውጥ መጣ በተባለበት ዘመን ማለትም ባለፉት ዓርባ አመታት ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ
የውይይት መድረክ ነበር ማለት ያስቸግራል። ከእንግዲህ ወዲህ ግን ይህ የብሔራዊ ውይይት
መድረክ መፈጠር አለበት።
ኢትዮጵያ የት ነው ያለችው፣ ወደ የት ነው ምትሔደው? ያለችበት ጎዳና ትክክል ነው ወይስ
አይደለም በሚሉ ሀሳቦች ላይ በጋራ በመወያየት ስምምነት ላይ በመድረስ በኢትዮጵያኒዝም
በመጠቀም አሁን ሐገራችን ካለችበት ውስብስብ ችግር መውጣት እንችላለን።
ባጠቃላይ ከእንግዲህ ወዲህ ለውይይት የሚጠቅሙን ኢትዮጵያ በንፅህናዋ የተበጀውን ፣
በመንፈሳዊ ኃይል የተመራውን የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ተጠቅመን ትልቅ እንደ
ነበረች እንደ ገና ትልቅ ለማድረግ ተሳስበን ተደማምጠን በታላቅ ትሕትና በኢትዮጵያዊ
ጨዋነት እንገንባት።
ሁሉ ነገር ከሃገራችን ስለ ተፈጠረ ለሌሎች ምሳሌ ስለ ሆንን ሃገራችን ወደ ፊት እንድትሄድ
ጠንክረን እንሥራ።
ከእርስዎ አመራር ምን ይጠበቃል?
ገጽ 5 የ8
ሌሎች ሃገራት በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ተጠቅመው ነጻ የወጡና ሃገራቸውን ወደ ተሻለ
መንገድ የመሩት በእኛ ኢትዮጵያዊነት ጥንካሬ እና የደረሱብንን የተለያዩ ተግዳሮቶች
ተቋቁመን በነፃነት መኖር በመቻላችን ነው።
አሁን ሃገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት በዘር፤ በኃይማኖት እና በጎሳ
ተከፋፍሎ ሕዝቡን በቋንቋ እና በክልል አዋቅሮ በመግዛት፤ ከኢትዮጵያዊነት በፊት ለጎሳ
ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ በሥራ ምክንያት ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስና ሥራ
እንዳይሠራ አድርጓል።
ሕገ መንግሥቱ በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በክልል መንግሥት አደረጃጀት የተመሠረተ
ስለሆነ ሕዝቡ ከሃገሩ ይልቅ ቅድሚያ ለብሔሩ እና ለክልሉ እንዲሰጥ አድርጎታል። ይህ
የክልል አደረጃጀት እስካልተስተካከለ ድረስ አሁን ሃገራችን ከገባችበት ውጥንቅጥ ችግር
ውስጥ መውጣት አትችልም።
ሃገራችን ከገባችበት ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ችግር ልትወጣ የምትችለው የክልል አወቃቀር
ተስተካክሎ ዜጋው ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት የመዘዋወር፤ የመሥራት፣ የመማርና የመኖር
መብቱ ተጠብቆ ሊያስኬድ የሚቻለው ለኢትዮጵያዊነት ቅድሚያ የሚሰጥ ሕገ መንግሥት
ሲኖር እንደሆነ እሙን ነውና ሕገ መንግሥቱ መሻሻያ ቢደረግበትና ቢስተካከል ለሃገራችን
ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል።
ሃገራችን ኢትዮጵያ ለውጪው ዓለም በተለይም ለተጨቆኑ ሕዝቦች ራሷ ተቸግራ እና የደም
ዋጋ በመገበር የሰጠችው መንፈሳዊ ፀጋ ቀላል የሚባል አይደለም፣ ከራሷ አልፋ ለተጨቆኑ
ሕዝቦች ሁሉ ምሳሌ እና አርዓያ የሆነች ሕገራችንን ችግሮቿን እና እንከኖቿን እኛ ልጆቿ
በሰለጠነ እና በሰከነ መንገድ በመነጋገር በመደማመጥና በመከባበር ልንፈታና አሁን
ካለችበት ወደ ተሻለች ኢትዮጵያ ልናሸጋግራት ይገባል።
የሃገራችን የትኛውም ዓይነት ችግር መፈታት ያለበት በራሷ ልጆች መሆን አለበት! በፖለቲካ
አመለካከት እና አመከንዮ ባንግባባም እንኳ ለሃገራችን እና ለሕዝቧ ቅድሚያ በመስጠት
ወደ መፍትሔ መንገድ መምጣት እንችላለን።
እርስዎ የጀመሩት ኢትዮጵያዊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአራቱ አቅጣጫ አስተጋብቷል!
ሕዝቡም ሲናፍቀው የነበረ ዓቢይ ጉዳይ ነውና ተቀባይነትዎ ጨምሯል! ይጨምራልም።
አሁን የተጀመረውን ኢትዮጵያዊነት መነቃቃት ወደ ተሻለ እና ከፍ ወደሚል ደረጃ
ለማድረስ እርስዎ ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት እና አሁን ካለንበት
የብሔር እና የሃይማኖት ችግር ወጥተን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ተከብሮ የሚኖርበትን
ዕድል ለመፍጠር ሁላችንም በጋራ የምንሠራበት ዕድል መፈጠር ይኖርበታል።
አሁን ከሚታየው ተስፋ እና ጅማሮ በመነሳት ሃገራችን ወደ ቀድሞ ክብር እና ዝናዋ
የምትመለስበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።
በእርስዎ አመራር የሚከተሉት ዋና ዋና ተግባሮች እንዲከናወኑ በትሕትና እናመለክታለን፤
1ኛ/ የኢትዮጵያኒዝም መንፈስ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪቃና በዓለም አቀፍ ደረጃ
እንዲሰራጭ፤ እንዲዘረጋና እንዲዳብር ማድረግ፤
2ኛ/ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሙሉ መሻሻል እንዲያስገኝ መለወጥ ከሚገባቸው ብዙ
ጉዳዮች አንዳንዶቹን እንጠቁማለን፤
ገጽ 6 የ8
የክልል አስተዳደር ኢጣልያኖች ኢትዮጵውያንን መግዛት የሚቻለው በመከፋፈል ነው
በማለት የዘረጉት አስቀያሚ ሥልት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከዚህ መላቀቅ አለባት። በዘር፤
በኃይማኖት፤ በቋንቋ የኢትዮጵያን ሕዝብ መከፋፈል እንደ ሀጢአት የሚቆጠር በመሆኑ
ሐገራችን በክፍለ፟ ሐገር እንድትደራጅ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሃገራችንን ረጅም ታሪክ፤ ጥበብና ዕውቀት በሚያጎላ
መንፈስ እንዲስፋፋ ይሁን። በተለይ ሰንደቅ ዓላማው ኣረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ቀለማት ብቻ
የሚታይበት ሆኖ መንግሥት በተቀየረ ቁጥር ሊለዋወጥ አይገባም። በአፍሪቃ አፍሪቃውያን
የፈጠሩት ፊደል ግዕዝ ብቻ ነው። ስለዚህ በዚህ ታሪካዊ ፊደል መጠቀም ሲገባን በሌሎች
ባእድ ቋንቋዎች ፊደሎች ለምሳሌ በላቲን መጠቀም ተገቢ አይደለም።12, 13 ከኢትዮጵያ
አካባቢ እንደዚሁም የመላ አፍሪቃ አንድነት በጣም አስፈላጊ ነው። በእዚህ ጉዳይ ላይ
ኢትዮጵያ ልዩ ሚና እንዳላት መገንዘብ ያስፈልጋል። ይኸውም በዓለም ሕዝብ ከ1829 እስከ
1929 ድረስ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጊዜ የነበረ መሆኑ በዓለም ተሰራጭቷል።
በኢትዮጵያ ስም ሁለት ማኒፌስቶዎች (መመሪያዎች) በ1829 ዓ.ም. በአሜሪካ፤ በ1896
በደቡብ አፍሪቃ፤ ከአድዋ ጦርነት ድል በኋላ ተሰራጭተዋል። አፍሪቃ በሙሉ በኢትዮጵያ
ስም የሚታወቅበት ጊዜም እንደ ነበረ ማስተዋል ይገባል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ያከናወነችውን
አሁንም እንድትቀጥልበት ያስፈልጋል። ይህም ታሪካዊ መሠረታችን ነው። ከእዚህ ቀደም
የነበረው የእርስ በርስ መፈራረጅ፤ የመለያየትና ችግር ሲያጋጥም ወደ ጦርነት ከማዘንበልና
በውጭ ሃገሮች መሣሪያ ከመጠቀም፤ ወደ መወያየት፤ መግባባትና መመካከር ባሕል
መለወጥ ይጠቅማል። የኢትዮጵያን ችግር በኢትዮጵያውያን መፍትሔ ማስወገድ ይገባል።
በውጭ እጅ ላይ መተማመን መክፋፈል ያስከትላል። የመንግሥቱ አወቃቀር ግልጥነት፤
የወስጥ ቁጥጥር፤ ውጤታማነት የሚያሰፍን ሊሆን ይገባዋል። የመንግሥት ሠራተኞችና
ባለሥልጣኖችም ሊመደቡ የሚገባው በተገቢ መስፈርት ብቁነታቸው ብቻ ሳይሆን ተደጋጋሚ
ሥልጠናም እየተከናወነላቸው በቂ ቅልጥፍናና ከሙስና የተላቀቀ አገልግሎት እንዲያበረክቱ
ማድረግ ያስፈልጋል። የበላይ አመራሩ የጊዜ ገደብ ይወሰን።
3ኛ/ ኢትዮጵያ ካለችበት ቀውጢ ጊዜ ተላቅቃ አስተማማኝ ወደ ሆነ ጎዳና እንድትገባ ሁሉም
ማለት የፖለቲካ፤ የማሕበረ ሰብዓዊ፤ የመንፈሳዊ፤ ወዘተ ድርጅቶች የሚሳተፉበት
የሽግግር ሒደት ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ።
የእርስዎንም የአስተዳደር ዘመን እስክ መጨረሻው ለሃገር የሚበጅ ውጤታማ እንዲሆን
እንመኛለን። ኣገርን በጎሳ መከፋፈል ኢትዮጵያን ሰማንያ ቦታ መከፋፈል ነው።
በኢትዮጵያዊነቱ ተከባብሮ መኖር የማይችል ሕዝብ በየቤተሰቡ መንግሥት ፈጥሮ መኖር
ኣይችልም። ለኣፍሪቃውያን መከታና ኣለኝታ ሆኖ የቆየው ኢትዮጵያዊነት ኣፍሪቃ ኣንድ
ኣገር ሆና መብቷ በዓለም ደረጃ እስኪመለስ ከመንደርና ጎሳ ኣስተሳሰብ መላቀቅ ይገባናል።
ከታላቅ አክብሮት ጋር!
እግዚአብሔር ሃገራችንን ይባርክ!!
1 ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ
2 ፕሮፌሰር ሲሳይ አሰፋ
3 ፕሮፌሰር ብርሃኑ መንግስቱ
4 ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ
5 ዶ/ር ኣበራ ሞላ
6 ዶ/ር ወርቁ አበራ
7 ዶ/ር ጌታቸው ተመስገን
ገጽ 7 የ8
8 ዶ/ር አበባ ደግፌ
9 ዶ/ር እጀቡሽ አርጋው
10 ወ/ሮ ጽጌረዳ ሙሉጌታ
11 የተከበሩ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ
12 አቶ ምንተስኖት መንገሻ
አቶ ሰይፉ ኣዳነች ብሻው
13 አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሄር
አቶ ኪዳኔ አለማየሁ
14 አቶ እርቅርማሪያም ደረስ
አቶ ተፈራወርቅ አሰፋ
አቶ ይልማ ዘሪሁን አቶ ይርጋለም ጎበዜ
15 አቶ ከድር ሰይድ አቶ መሸሻ ካሳ
16 አቶ ኤሊያስ ማሞ
17 አቶ ብርሃኑ ገመቹ
18 ወ/ሮ አስቴር ኃይሌ
19 አቶ በቀለ ተገኝ
20 አቶ አብርሃም ቀጀላ
21 አቶ ግርማ ካሳ
ዋቢ
1. Ethiopianism, http://www.druglibrary.net/olsen/RASTAFARI/campbell.html2. ETHIOPIANISM IN PAN-AFRICAN PERSPECTIVE, 1880-1920, https://www.upjournals.co.za/index.php/SHE/article/view/85
3. Abyssinian Baptist Church, New York City (1808- ) http://www.blackpast.org/aah/abyssinian-baptist-church-1808
4. Ethiopianism in African Christianity, https://repository.up.ac.za/bitstream/handle/2263/21579/011_Chapter10_p258- 277.pdf?sequence=12 5. Ethiopianism and African Nationalism in South Africa before 1937, https://www.persee.fr/doc/cea_0008-0055_1986_num_26_104_1689
6. Ethiopianism, http://www.blackpast.org/gah/ethiopianism
7. Ethiopianism and the Independent Church Movement, http://www.worldhistory.biz/sundries/4707
8-ethiopianism-and-the-independent-churchmovement.html 8. Ethiopianism, https://www.britannica.com/topic/Ethiopianism
9. Ethiopianism a symbol of resistance to injustice, http://www.aau.edu.et/blog/ethiopianism-a-symbol-of-resistance-to-injustice-thabo-mbeki/
10. John Dube, http://www.anc.org.za/content/john-dube ገጽ 8 የ8
11. Ethiopian Muslims History, http://www.selamta.net/ethiopian%20muslims%20history.htm
12. http://www.ethiomedia.com/1000dir/oromigna-be-amara-kilil-be-geez-fiddelendiset.pdf
13. http://www.ethiomedia.com/1000dir/open-letter-to-president-lemma-megersa.pdf8
No comments:
Post a Comment