ዋዜማ ራዲዮ- የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሕዳሴው ግድቡ ዉሀ የሚተኛበትን ሰፊ ቦታ ከደን ነጻ እንዲያደርግ 2 ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን የተሰጠው ከዓመታት በፊት ነበር፡፡ አሁን ግን ገንዘቡ ሳይባክንብኝ አልቀረም እያለ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ የተከፈለው ከመንግሥት አሠራር ውጭ ፣ ያለምንም መደበኛ ውል፣ ሥራው ተሠርቶ እንደተፈጸመ ተደርጎ መቶ እጅ ክፍያን በመፈጸም ነው፡፡
ሜቴክ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ግን ሥራው መስተጓጎል ገጥሞታል፡፡ ገንዘቡን ጠፍቶበታል፡፡
ፕሮጀክቱ የሚጠይቀው የሰው ኃይል እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ ሁኔታ መሠራት ቢኖርበትም ሜቴክ በወቅቱ ያዘጋጀውን ጨረታ በመሰረዝ የቀድሞው የሕወሓት ታጋዮች መቋቋሚያ እንዲሆናቸው በሚል ሥራውን ያለጨረታ አሳልፎ ሰጥቷቸው ነበር፡፡
ኾኖም ነባር ታጋዮች ለተሰጠው እድል አመስግነው ሥራውን በወቅቱ የተረከቡ ቢሆንም የስራውን ስፋት ከግምት በማስገባት ለሌላ ሦስተኛ አካል ‹‹ሰብ ኮንትራት›› መስጠት እንዳለባቸው ከስምምነት ደርሰው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በግምት ከአዲስ አበባ እስከ ዝዋይ ያክላል የሚባለውን ይህን ሰፊ በደን የተሸፈነ ቦታ መመንጠር የሚችሉ በሺ ለሚቆጠሩ የተደራጁ ወጣቶች ሥራውን በስምምነት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ስምምነቱም ወጣቶቹ እንዴትም ብለው ምንጠራውን በብቃት እንዲወጡና ክፍያ ሲፈጸም ግን ሰባ በመቶውን ለነባር ታጋዮች እንዲያካፍሉ የሚል ነው፡፡
ይህን ስምምነት ተከትሎ በሺ የሚቆጠሩና ራሳቸውን በ72 ማኅበራት ያደራጁ ወጣቶች ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘምተው ነበር፡፡ መቶ ሚሊዮን ብር ለሥራ ማስኬጃ ቅድመ ክፍያ የተቀበሉት እነዚህ ወጣቶቹ በከፍተኛ ሞራልና ተስፋ ወደ ስፍራው በመዝመት፣ ከአጎራባች አካባቢዎችና በተለይም ከጎጃም የጉልበት ሠራተኞችን በገፍ በመመልመል የዛፍ ቆረጣውን ሥራ ጀምረውት ነበር፡፡
‹‹በባህላዊ መንገድ ዛፎቹን መመንጠር የጀመርነው ዘመናዊ መጋዞች ከአየር ንብረቱ ጋር ስላልተጣጣሙልን ነው›› ይላል በዚህ ሥራ ተሠማርተው ከነበሩ ማኅበራት የአንዱ አስተናባሪ ለዋዜማ ሲናገር፡፡ ‹‹እውነት ለመናገር የገንዘቡን ትልቅነት እንጂ የሥራው ስፋት ሳንረዳ ነበር የገባንበት›› የሚለው ይኸው ወጣት በእድሜ ልክ የማያገኙትን ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ውሎና አዳራችንን ጫካ ውስጥ በቀለሷቸው ድንኳኖች ለማድረግ ተገደው እንደነበር ያስታውሳል፡፡
1500 ኪሎ ሜትር እስኩዌር እንደሚሸፍን የሚነገረው ይህ ደን ግድቡ ካለበት ወደ ኃላ በትንሹ 200 ኪሎ ሜትር ይሸሻል፡፡
በስድስት ወራት ብቻ 56ሺ ሄክታር ደን ጨፍጭፈን ከጨረስን በኃላ በስምምነታችን መሠረት ሁለተኛ ዙር ክፍያ ስንጠይቅ ‹‹አትቸኩሉ›› ተባልን የሚለው ይህ ወጣት የመጀመርያ ክፍያውን በዋናነት ለቁሳቁስ መግዣና ለዕለት ቀለብ ስላዋልነው ሁለተኛውን ክፍያ በጉጉት ለመጠበቅ ተገደን ነበር ይላል፡፡
‹‹ቀላል ሥራ አልነበረም፡፡ 12ሺ የጉልበት ሠራተኞች ተሳትፈውበታል፡፡ ዛፎችን ለመገንደስ ትልልቅ መጋዞች ሊቋቋሙት ባለመቻላቸው በሺ የሚቆጠሩ መጥረቢያዎች ከተገዙ በኋላ በሰው ጉልበት ነበር ሥራው ያሠራነው፡፡ 12ሺ የጉልበት ሠራተኞች ቁርስ ምሳና እራት እንዲሁም የበረሀ ድንኳን ማቅረብ፣ ሕክምናና ሌሎች ፋሲሊቲዎችን መስጠት የኛ ድርሻ ነበር፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ሂደት ሰዎች ሞተውብናል፤ እባብ የነደፋቸው የጉልበት ሠራተኞች፣ ወንዝ የወሰዳቸው ዛፍ ቆራጮች አሉ፡፡›› ሲል ፈተናው እንዴት አስቸጋሪ እንደነበር ለዋዜማ ተናግሯል፡፡
ቃል የተገባልን ክፍያ በጣም ሲዘገይብን ግን እኛን ከቀጠሩን ታጋዮች ጋር ሆነን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በደብዳቤና በአካል መጠየቅ ጀመርን ሲል ሂደቱን ያስረዳል፡፡
‹‹በመጨረሻም ከጄኔራል ክንፈ ጋር ቀጠሮ ተይዞልን መነጋገር ስንጀምር ገንዘቡ ለሌላ አጣዳፊ ነገር ውሎ ሊሆን ስለሚችል ያንን እስካጣራ እናንተ ሥራችሁን ቀጥሉ እንዳሏቸው ይናገራል፡፡ ሥራችንን ምን ይዘን እንደምንቀጥል አልገባንም ነበር ይላል፡፡
ከዚያ በኋላ በነበሩ ተከታታይ ስብሰባዎች ግን ነገሮች እየተበላሹ እንደመጡና ነባር ታጋዮችና ጄኔራሉ ሊግባቡ አለመቻላቸውን ያብራራል፡፡
‹‹ለዚህ ሥራ ተብሎ 2 ቢሊዮን ብር ለሜቴክ እንደተከፈለው እናውቅ ነበር፤ ብሩ ግን ሳይባክንባቸው እንዳልቀረም›› የሚለው ይኸው ወጣት ‹‹ምክንያቱም የሜቴክ ሰዎች ሲነግሩን ብሩ እኮ የለም፣ ከየት ነው የሚከፈላችሁ? ይሉን ነበር፤ እኛ ግን አላመናቸውም ነበር›› ይላል፡፡
‹‹እንዲህ አይነት ትልቅ ብር ባከነ ሲባል ለማመን አስቸጋሪ ነበር››
ነገሮች እየተካረሩ እንደመጡ ሲያስረዳም፣ ‹‹እኔ ማኅበሩን በመወከል አልፎ አልፎ ስብሰባዎቹ ላይ እገኝ ነበር፡፡ በትግርኛ ኃይለቃል ሲለዋወጡ እንሰማለን፡፡ በተለይም በአንድ ወቅት የጄኔራሉ የቅርብ ቤተሰብ ነው የሚባል የቀድሞ ታጋይ ‹‹የዕድል ጉዳይ ሆኖ ነው አንተ እዚህ ወንበር ላይ፣ እኔ ዊልቸር ላይ የተመጥነው›› ብሏቸው ስብሰባ ረግጦ እንደወጣ አልተመለሰም ይላል፡፡
ጄኔራሉም ከዚያ በኋላ ስሜታዊ በመሆን ‹‹ይሄ አገራዊ ፕሮጀክት ነው፣ ገንዘብ ገንዘብ አትበሉ፤ እኛ ጨረታ ማውጣት አቅቶን አይደለም፤ እናንተን እናግዝ ብለን ነው የሰጠናችሁ›› ሲሉ መናገራቸውን ያብራራል፡፡
በጄኔራሉ ተስፋ የቆረጡት ታጋዮች ፖስታ ቤት ቅጥር ግቢ ወደሚገኘው የዶክተር ደብረጽዮን ቢሮ በቀጥታ በመግባት መፍትሄ እንዲፈልጉላቸው ጠይቀዋቸው ‹‹ክንፈን አናግሬው እኔ ራሴ መልስ ይዤላችሁ እመጣለሁ፣ በጭራሽ አታስቡ›› ብለው በእርግጠኝነት መልሰዋቸው ነበር ይላል፡፡ ሆኖም ዶክተሩ ቃላቸውን ባለመጠበቃቸው የኛ ተወካዮች አቶ አስመላሽ ጋር በመሄድ እንዲያሸማግሏቸው ተማጽነው ይህም ውጤት ሳያስገኝ ቀርቷል፡፡
ይህን የሰሙት ጄኔራሉ የኛን ተወካዮቹን ለመጨረሻ ጊዜ አስጠርተው፣ ‹‹ስማችንን በየቢሮው እየሄዳችሁ ታጠፋላችሁ፣ ነገሩን በእልህ ለመጨረስ ካሰባችሁ እኛ እንብሳለን›› በማለት እንዳስፈራሯቸው ይናገራል፡፡
ከዚህ የተራዘመ ሂደት በኋላ ብዙዎቹ ተስፋ ቆርጠው ነገሩን እርግፍ አድርገው የተዉ ሲሆን 12 የሚሆኑ ማኅበራት ግን እውቅ ጠበቆችን በመያዝ ፍርድ ቤት ክስ መመስረታቸውን ይኸው ወጣት ይናገራል፡፡ ሌሎች ማኅበራት መክሰስ ያልፈለጉት በሌላ ሳይሆን ፍርሃት ስላደረባቸው ነው ይላል፡፡ ‹‹ሜቴክን ከሰን የት እንደርሳለን›› ያሉ ነበሩ፡፡ የመጣው ይምጣ ብለው የከሰሱም ነበሩ ይላል፡፡
ወደ ፍርድ ቤት ከሄዱት ማኅበራት የተወሰኑት ጉዳዩን እንዲይዙላቸው እውቅ ጠበቆችን መቅጠራቸውንና ከነዚህም መሐል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአቃቢ ሕግ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ እሸቱ ወልሰማያትና ቀድሞ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩም ይገኙበታል ይላል፡፡
ኾኖም የፍርድ ሂደቱ ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደ ሲሆን ዳኞች ጉዳዩ እያሰጋቸው ነው መሰለኝ ቶሎ ቶሎ ይለዋወጡ ነበር ብሏል፡፡
አንዱ በፍርድ ቤት ጉዳዩን አከራካሪ ያደረገው ለማኅበራቱ መከፈል ያለበት የምንጣሮ ሥራ የቦታ ስፋት መለካት ያለበት በጂፒኤስ ነው ወይስ በሜትር የሚለው ሲሆን ሜቴክ በጂፒኤስ ይለካልኝ ሲል ማኅበራቱ በሜትር ነው መለካት ያለበት የተስማማነውም በዚህ መንገድ ነው ብለው ተከራክረዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም የመሬቱ አቀማመጥ ወጣ ገባ ስለሚበዛው በጂፒኤስ ቦታውን መለካት አካባቢው ጠፍጣፋና ሜዳማ እንደሆነ ታሳቢ እንደሚያደርግና የምንጣሮውን ልፋት ግምት ውስጥ የማይከት ያደርገዋል ባይ ናቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያዋ ዳኛ የኢትዮጰያ ካርታ ሥራዎች ድርጅት ሞያዊ አስተያየት እንዲልክ በማዘዛቸው የከሳሽ ጠበቆች ቦታው በሜትር መለካት እንዳለበት የሚያስረዳ ደብዳቤ ከዚሁ መሥራያ ቤት አምጥተው ለውሳኔ ቀጠሮ ሊሰጥ ሲል የሜቴክ ጠበቆች ከተመሳሳይ መሥሪያ ቤት ቦታው በጂፒኤስ መለካት እነዳለበት የሚያስረዳ ሌላ ተጻራሪ ደብዳቤ አጽፈው በማምጣት መቻላቸው ፍርድ ቤቱን አስገርሟል፡፡ ሁለቱም ደብዳቤዎች የተፈረመባቸው በተመሳሳይ ሰው መሆኑም ሌላ አግራሞትን ፈጥሯል፡፡
ችሎቱን የምታስችለው ዳኛ በጉዳዩ በመደመም ችሎቱን ድንገት በትና የወጣች ሲሆን ከዚህ ዕለት ጀምሮም ችሎቱን የሚያስችሉት ዳኛ መቀየራቸው ተነግሯል፡፡ ዳኛዋ ከዚህ ውሳኔ ያደረሳቸው ምናልባት ቀደም ብለው የሜቴክ ኃላፊዎች መጥተው እንዲመሰክሩ የሚለው ትእዛዝ ሊከበርላቸው ስላልቻለ ሊሆን ይችላል፡፡
እኚህ ዳኛ ለማኅበራቱ የሚያደላ ውሳኔ ሊወስኑ ይችላሉ በሚል ለውሳኔ ቀጠሮ ከመሰጠታቸው ቀደም ብሎ የሜቴክ ጠበቆች ‹‹የኛ ሠራተኞች ጉዳይ የሚታየው በጦር ፍርድ ቤት ነው›› የሚል ነገር ለችሎቱ ማሰማታቸው ዳኛውን ሳያስቀይማቸው እንዳልቀረም ይገመታል፡፡
ሜቴክ በኮንትራት ለሚሰጣቸው ሥራዎች በጊዜውና ተገቢውን ክፍያ መክፈል ባለመቻሉ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይቀርቡበታል፡፡
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ በስተምዕራብ 600 ኪሎ ሜትር በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ፣ ያዩ ወረዳ የድንጋይ ከሰል እያወጣ መሸጡ የሕዝብ ቅሬታን በመፍጠሩ በተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄን አስነስቶ ነበር፡፡
በሌላ ዜና የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን መስርተው ለስምንት ዓመታት ያስተዳደሩት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኜው ሰሞኑን የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ሳምንታዊው የቢዝነስ ጋዜጣ ፎርቹን ዘግቧል፡፡
No comments:
Post a Comment