Thursday, August 16, 2018

ለማ መገርሳ እና ፖል ካጋሜ በጨረፍታ (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)



Lemma Megersa
ሩዋንዳ በምሰራቅ አፍሪካ የምትገኝ ትንሽ አገር ስትሆን በ1994 እንደ አ.አ ከደረሰበት የሁቱና ቱትስ  እልቂት አገግማ ዛሬ ሰላማዊ አገር ሆናለች፡፡ የሩዋንዳ የዘር ፍጅት የሰው ልጅ አረሚያዊ ማነቱን ያሳየበት አንዱ የታሪክ ክስተት ነበር፡፡ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች  ሁቱና ቱትስ በዘውግ ተቧድነው አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚደርሱ ዜጎቻቸውን ያጡበት ክስተት ዋናው ምክንያት የዘርን ጥላቻ በሚሰብኩ የፖለቲካ ሊህቃን ምክንያት ነው፡፡
በሩዋንዳ በ1994 ከተፈጸመው የዘር ፍጅት በፊት የሩዋዳ ዜጎች በቋንቋ አንድ ቢሆኑም በብሔር ተከፋፍለው  በዘውግ መታወቂያ ደብተር ላይ ቱትሲ፣ ሁቱ እና ትዋ በሚል የዘር መታወቂያ ካርዶች ልዩነታቸው ገዝፎ ነበር፡፡ ጭካኔ በተሞላበት የዘር ፍጅት መታወቂያቸው ላይ የተጻፈው የብሔር ማንነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ከዘር ፍጅቱ በኋላ የፖል ካጋሜ ስልጣን መያዝ ተከትሎ የብሔርና እና የኃይማኖት ማነትን የሚገልጽ ስያሜ በመታወቂያቸው ላይ እንደዳይሰፍር ተደረገ፡፡ ዛሬ በሩዋዳ ውስጥ ቱቲስ እና ሁቱ የሚል መከፋፈል እንደነውር የሚቆጠር ሆኗል፡፡ ዜጎች በችሎታቸው ብቻ የሚለኩበት ስርዓት በመፈጠሩ ፖል ካጋሜ ሀገሪቱን እያዘመናት ይገኛል፡፡
ከሩዋንዳ የዘር ፍጅት ትምህርት የቀሰሙት እንደ ታንዛንያ ያሉ ሀገራት በዜጎቻቸው መታወቂያ ላይ ምንም ዓይነት የኃይማኖትና የብሔረ ማንነትና የሚገልጽ ቃላት እንደይኖሩ በማድረግ ከ120 በላይ ያሉ ብሔሮች በሰላም ለማስተዳደር ችለዋል፡፡
የህወኃት ወራሹ ስርዓት በ1983 ስልጣን ከጋዛ በኋላ የብሔር ጥላቻን የሚፈጥሩ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ፣ በብሔር ስም ህዝቡን በመከፋፈል በርካታ የጎሳ ግጭት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ ዘረኞች መሰረተ-ቢስ በሆነ ጥላቻና በራስ ወዳድ ማነታቸው ምክንያት ህዝቡን በዘር እያቧደኑ በሚፈጠረው ግጭት የስልጣን እድሚያቸውን ለማራዘም ብዙ ጥረዋል፡፡ ይህም ይሳካላቸው ዘንድ በመታወቂያቸው ላይ የብሔር እና የኃይማኖት ማንነታቸንን በግዴታ ጭነውብን ለ27 ዓመታት ለጎሪጥ ስንተያይ፣ ስንጋጭ፣ ስንጋደል፣ ስንሰደድ ቆይተናል፡፡
ፖል ካጋሜ በሩዋንዳ ላይ ከተፈጠረው እልቂት ተምሮ ከዘር ፍጅቱ በፊት የነበረውን የብሔር ማንነት አጥፍቶ አንድነት የሰፈነባት ሩዋንዳን ሲመሰረት ብልሁ፣ ወጣቱ መሪ ለማ መገርሳ ደግሞ ያንዣበበውን የብሔር ግጭት ተረድቶ የዘር ፍጅቱን በማስቀረት አገሪቱን ከዶ/ር አብይ አህመድ ጋር ሊታደጓት እየታተሩ ነው፡፡
አሁን ለሚታየው የለውጥ ሂደት ጠንሳሽ እና ፊታውራሪ የሆነው የቁርጥ ቀን ኢትዮጵያዊ  ለማ መገርሳ በአገሪቱ ያንዣበበውን አደጋ በመረዳት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ሀገሪቱን እየታደጋት ይገኛል፡፡ ለማ መገርሳ  ከወሰዳቸው በርካታ እርምጃዎች አንዱ የብሔር ማንነትን በዜጎች መታወቂያ ላይ ፍቆ በኢትዮጵያ ዜግነት መተካቱ ነው፡፡የቆራጥ መሪያችንን የለማ መገርሳን አርያን በመከተከል ለሌሎችም የክልል ርእሰ-መስተዳደር ከዜጎቻቸውን መታወቂያ ላይ ከብሔር ማንነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነት በማስፈር በአንድነታችን ጉዞ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የህወኃት ወራሹ ስርዓት ባለሟልና ተቆርቋሪ ነን የሚሉ የሰርኣቱ አጋፋሪዎች ከጎሳ ድርጅት ይልቅ በአስተሳሰብ ልዩነትን ያማከለ የፖለቲካ ድርጅት መሰረት ላይ ማንነታቸውን እንዲገነቡ እና የጎሳ ፖለቲካ እና የብሔር ቡድነኝነት ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ከመተማመነን ይልቅ መጠራጠርን ከሰላም ይልቅ ግጭትን፣ ከፍቅረ ይልቅ ጸብን የሚያራግብ እንደሆነ ከበቂው የታሪክ መዛግብት ትምህርት ቢቀስሙ መልካም ነው ፡፡

ኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጥቅም ለአሁኗና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ



ከፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. 
ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ 
“ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” ብለው አንድነታችንን የሚያጠናክር ንግግር ሲናገሩ የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ጥቅም በሚገባ እንደ ገለጹት ተረድተናል። ቀጥለውም ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ መውሰድ ይቻላል! ነገር ግን ከኢትዮጵያዊ ልብ ኢትዮጵያ ዘላለም አትወጣም ትኖራለች! ብለው የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ጥቅም ደግመው አጉልተውታል። ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ተምሳሌት እንደመሆኗ በብዙ ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ኢትዮጵያ ልዩ ቦታ አላት። ኢትዮጵያውያን ብዙ ላናውቅና ላንረዳ እንችላለን እንጂ፣ ከኢትዮጵያ ከኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያዊኒዝም አስተሳሰብና ፍልስፍና ተወልዷል።1 ኢትዮጵያኒዝም የተፈጠረው በኃይማኖትና በፖለቲካ ከጭቆና ውስጥ የነበሩ የጥቁር ዘር ባላቸው ሰዎች ነው። አፈጣጠሩ አፍሪቃ ለአፍሪቃኖች ትገባለች የሚለውን የፓናፍሪካ ፍልስፍና አስቀድሞ በመጀመሪያ የገለፀ ነው። ሲጠነሰስ ጀምሮ መንፈሳዊነትን ከሰው ልጆች ነፃነት ጋር አጣምሮ አቀናጅቶ አስተባብሮ የተፈጠረ ፍልስፍና ነው።2 ኢትዮጵያኒዝም በስፋት የተጀመረው 1660 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን ከ1776 ከአሜሪካ የነፃነት ትግል በኋላ እያየለ መጣ። አፍሪቃ/አሜሪቃኖች በአሜሪካ ነፃነት በተፈጠረው ለቀቅ ያለ ሁኔታ በመጠቀም ኢትዮጵያኒዝምን ፈጠሩ። በ1808 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ቤ/ክ በአሜሪካ አቋቋሙ።3 በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና በዓለም ተስፋፋ። የሚገርመው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም የታወቀ ፍልስፍና ሆኖ አልገባም። ትልቁ ጥያቄ አሁን ኢትዮጵያኖች እንዴት ይህን ፍልስፍና ያዩታል? የሚለው ነው። ስለ ሐገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ ይጠቅማል ብለው ይሄን ፍልስፍና መመርመርና መወያየት ቢችሉ ጥሩ ነው የሚል አስተያየት አለን። እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ቀላል የምንቆጥረው ኢትዮጵያዊነት በኢትዮጵያኒዝም መልክ በሌሎች ሕዝቦች ዘንድ ያለውን አዎንታዊ ተጽእኖ ብንረዳው የበለጠ ኢትዮጵያዊነታችንን ለማጠናከር ሊረዳንም ይችል ነበር።4 የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናን ያስፋፉት እነማን ናቸው? ኢትዮጵያኒዝምን በመጀመሪያ ያስፋፉት በ19ኛው ክፍለ ዘመን በመንፈሳዊ ዓለም የተሰማሩት በአሜሪካና በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ቄሶች ናቸው። በመሠረቱ ዘረኝነት በፖለቲካና በኢኮኖሚ ዓለማዊ ዙሪያ ላይ ብቻ ሳይሆን በጥቁሮች መንፈሳዊ ዓለም ላይም ከባድ ጫና ነበረው። በሃይማኖት ሳይቀር ጥቁርን እንደ ሰይጣን ነጭን እነደ መልዓክ ማየት የተለመደ የነጭ ቄሶች እምነትና ተግባር ነበር። ገጽ 2 የ8 በመሠረቱ ነፃነት የሚፈልጉ የጥቁር ቄሶች ሁለት ችግሮች ገጠሟቸው፤ የነጭ ቄሶች ሲሰብኩ ጥቁርን እንደ ሉሲፈር (ሰይጣን) ስለሚቆጥሩ የነሱ ቄስ ሆኖ ማገልገል በራሳቸው በጥቁሮች ላይ መንፈሳዊ ኩነናን እንደ መቀበል መስሎ ስለ ታያቸው መቀበል አልዋጥላቸው አለ። በሁለተኛ ደረጃ የነጭ ቄሶች ለጥቁር ቄሶች ምንም ቢሆን ያመራር ተግባር እንዳያገኙ ከለከሏቸው። ሌላው በጣም ያማረራቸው ደግሞ የነጭ ቄሶች ሲሰብኩ የጥቁር ቄሶች ቀና ብለው ወደ ላይ አምላክን ከማየት ወደ ታች አንገታቸውን ደፍተው ቁልቁል እንዲያዩ አምላክን አሻቅበው እንዳያዩ የነጭ ቄሶች እንዳገዷቸው እንደሳፈሯቸውና እንደ ጨቆኗቸው ይናገራሉ። ጭቆናው እየቀጠለ በሄደ ቁጥር ነጮች በሚቆጣጠሯቸው ቤተክርስቲያን መቀጠል እንዳንገፈገፋቸው ይናገራሉ። በአንድ በኩል ቤተክ/ያን እንዲቀይሩ ጥያቄ ያቀርባሉ፤ ካልተቀየረ ግን ሌላ ቤተክ/ ለማቋቋም አቋም ይወስዳሉ። ያቀረቡት ጥያቄ ሙሉ የመንፈሳዊ ነፃነት ማግኘት እንደ ምዕመናን ወደ እግዚአብሔርና ወደ ክርስቶስ ካላንዳች ዘረኝነትና አድልዎ የሚያገናኝ ሃይማኖትና ቤተክ/ ፈለጉ። የነጮች ቤተክ/ ይህንን ጥያቄያቸውን ሊያሟሉ አልቻሉም፤ ስለዚህ አዲስ ቤተክ/ ማቋቋም ወይም የነበረውን ቤተክ/ መቀየር ፈለጉ፤ እናም በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ስሟ የተጠቀሰው ኢትዮጵያ ስለ ሆነች የኢትዮጵያ ቤተክ/ እያሉ ማቋቋም ፈለጉ። ኢትዮጵያ የጥቁር ሐገር በመሆኗ ሌላው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ስለሚል ያለምንም መድልዎና ዘረኝነት ወደ እግዚአብሔር እምታገናኘን ቤተክ/ ናት ብለው ኢትዮጵያኒዝምን አቋቋሙ።5 ኢትዮጵያኒዝምን ያዩት እንደ መንፈሳዊ ጎዳና ከእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር በቀጥታ መንገድ ከፋች፤ ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ የጥቁር ሐገር ሆና እራሷን ማስተዳደር የቻለች ታላቅና ክቡር እንዲሁም የራሳችው ሐገርና እንደ አለኝታ በመቁጠር ነበር የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና በመንፈሳዊ ትግል የጀመሩት፤ ያነፁትና የገነቡት።6 የሚገርመው የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና መንፈሳዊ መሠረት ይኑረው እንጂ ለተጨቆኑት የዓለም ሰዎች ሁሉም መመሪያ አድርገው ነው የመሠቱት። ከመንፈሳዊ መሠረቱ ወደ ዓለማዊ ጭቆናዎችን ለመቋቋም የኢትዮጵያኒዝም የሚከተሉትን ስምንት ባሕሪያት ያጠቃልላል፤ 1. መንፈሳዊ ነፃነት 2. በራስ መተማመን 3. ለራስ ክብር 4. እራስን መቻል 5. የውጭ ጭቆናን መቋቋም 6. መንፈሳዊ ነፃነት ከዓለማዊ ነፃነት ጋር ማጋራት አብሮ እንዲሔድ ማድረግ 7. የተጨቆኑ ሰዎች በጋራ መተባበር 8. ሰብአዊነት፣ መረዳዳትና እርስበርስ መተሳሰብ። እነዚህ ስምንት ታላላቅ ፅንሰ ሀሳቦች የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና የሚያራምዱና በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያኒዝምን ተከትሎ የመጣውን ፓንኣፍሪካኒዝምን ለአፍሪቃ ነፃነት አንድነት ሕድስና ስር መሠረት የሰጡ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ፅንሰ ሀሳቦች ናቸው። የኢትዮጵያ ነፃነትም ጠቅሟል።7 ገጽ 3 የ8 እንግዲህ ኢትዮጵያኒዝም በ16ኛው ክፍለ ዘመን ተጀምሮ 18ኛው ክፍለ ዘመንን ተደግፎ እሰከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የቆየ ፍልስፍና ነው።8 ኣሁንም ቢሆን የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ታቦይ ኢምቤኪ እንደሚሉት የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና አሁን ላለንበት ዘመን ያስፈልጋል ይላሉ።9 እናም የኢትዮጵያ ቤተክርስትያኖችም በደቡብ አፍሪቃ በአሜሪካና በካሪቢያን ሀገሮች አሉ፤ አሁንም ቢሆን እነዚህ ቤተክርስትያኖች ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተጨመማሪ ያላለቀውን የነፃነት ትግል የገለፁ ናቸው። ኢትዮጵያኒዝም በዓለም መድረክ ያመጣቸው ለውጦች በደቡብ አፍሪቃ የአፍሪቃን ናሽናል ኮንግሬስ ያቋቋሙት በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ቤተክ/ ቄሶች ናቸው፤ እናም የመጀመሪያው የአፍሪቃ ናሽናል ኮንግሬስ ፕሬዝዳንት ጆን ላንጋቢሌሌ ዱቤ በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናቸውና አቋማችው ታስረው ከተፈቱ በኋላ የአፍሪቃ ናሽናል ኮንግሬስ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።10 የስማቸው ቅፅል ግልፅ ኢትዮጵያዊ ሁልጊዜ አደጋ ላይ ያሉ ይሏቸው ነበር፤ እናም ነጮቹ 1906 የኢትዮጵያኒዝምን ፕሮፖጋንዳ አንቋሽሸው ኢትዮጵያኒስትን ማሰርና አልፎ አልፎም መግደል ጀመሩ። ቀጥለውም የኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴን እንደ አደጋና እንደ ረብሻ አሰራጭ ቆጥረው የወታደር ኃይላቸውን አሳደጉ። የዙሉ እንቅስቃሴ 1906 ቀጥሎም ባንባታ በሌሎችም አካባቢዎች ያፓርታይድ ተቃውሞ እንቅስቃሴ ተጀመረ። እንቅስቃሴውውንም ያስጀመሩት እንዲሁም ይመሩት የነበሩት ኢትዮጵያኒዝሞች ነበሩ። እንዲሁም በተለያዩ የአፍሪቃ ሐገሮች በእንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ፖርቱጋል፣ በቅኝ ግዛት ተገዝተው የነበሩ በኢትዮጵያኒዝም በመጠቀም ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር በማገናኘት ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ተጠቅመውበታል። ራስተፈሪያኒዝንም የፈለቀው ኢትዮጵያኒዝም በሚለው ፍልስፍና ነው። አፍሪቃ ለአፍሪቃዊያን የሚለው አስተሳስብ የመጣው ኢትዮጵያኒዝም በሚለው ፍልስፍና ነው። ቅኝ ግዛትን በመቃወም እነፕሬዝዳንት ጆሞ ኬኒያታ ሳይቀሩ በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና እሰከ 1960 ዓ.ም ድረስ ተጠቅመውበታል። በተለያየ መንገድ ቢገለፅም የተለያዩ ሰዎች በተለያየ መንገድ ቢጠቀሙበትም መሠረታቸው ኢትዮጵያኒዝም እንደ ሆነና አፍሪቃን ሙሉ ከቅኝ ግዛት ለማውጣት እንደ ችቦ መብራት እነደ ተጠቀሙብት ጥርጥር የለውም። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያኒዝም የኢትዮጵያ ሚና በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ምንድነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። በመጀመሪያ ኢትዮጵያን የኢትዮጵያኒዝም መሠረት አድርጎ ሲፀነስ ሐገሪቷ ልዩ ቦታ እንደ ተሰጣት ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ኢትዮጵያ መንፈሳዊ ምግብ ለዓለም የሰጠች መሆኑ ምንም የሚያሻማ ነገር የለውም። ዛሬ ቁሳቁሳዊ እርዳታ ከሚሰጡት እንደ አሜሪካ ካሉ ሀገሮች ይልቅ ኢትዮጵያ መንፈሳዊ የነፃነት ምግብ ለዓለም የሰጠች ታለቅ ሐገር መሆኗ ጥርጥር የለውም። እንግዲህ ኢትዮጵያን ሊጎዷትና ሊገድሏት ያሰቡ ሐገሮች ግለሰቦች እንዲሁም ቡድኖች ማወቅ የሚገቧቸው ነገሮች ቢከሷትም በታሪኳ ቢፈርዱም ብትሞትም ዘላለም የምትኖር ሐገር ናት። ሁላችንም ቢሆን ይህችን ሀገር እንዲህ ያለ የተጨቆነውን ዓለም በሙሉ ያከበረውን መንፈሳዊ ስጦታ ያበረከተች ሐገር አሳልፈው የሰጡንን አባቶቻችንና እናቶቻችንን ማክበር እንጂ በውጭ ገጽ 4 የ8 ሐገር ፕሮፖጋንዳና በማናውቀው ሥልጣኔ ባልገባንና ባልተረዳነው ተውጠን ይህችን ሐገር መናቅ ትልቅ ስሕትተ ነው። በተጨማሪም ኢትዮጵያኒዝም የተመሠረተው በክርስትና ሃይማኖት ላይ የነጭ ቄሶች ዘረኝነትን በማስፋፋት የእግዚአብሔርን መልክ በነጭ ቅልፅ በመግለፅ ሌሎችን በማግለልና መጠቀሚያ ብቻ በማድረግ እንደማይቻል በመቃወም ነበር። የእስልምና ሃይማኖትን በኢትዮጵያኒዝም አመለካከት ስናየው ተቃውሞ በተነሳበት ጊዜና ምዕመናኑ ስደት ባጋጠማቸው ወቅት የኢትዮጵያ ድጋፍ ትልቅ ልዩነት እንዳመጣ ታሪክ ይመሰክራል።11 ኢትዮጵያ ለሙስሊሞች ያደረገችው ድጋፍ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ይገልፃል። ከእኛ ምን ይጠበቃል? በመጀመሪያ ይህንን ታሪክና ፍልስፍና ማወቅ ይገባናል። ይህንን ታሪክና ፍልስፍናን መሰረት አድርገን ዘመናዊነትን ለመገንባት ዝግጁ መሆን ያሰፈልጋል። ከውጭ የተለያዩ ሀሳቦችን እየኮረጅን ሐገራችን የፈጠረችውን ፍልስፍና ማንቋሸሽና ታሪኳን መወንጀል አላግባብ መፍረድ አይገባም። መጠየቅ ያለብን የራሳችን ሐገር ምን ፈጠረች፣ ለምን በዓለም ዙሪያ ያሉ ሐገሮች እንደዚህ ተማሩባት አከበሯት ብለን በትሕትና ሐገራችንን አክብረን ያለባትን የተወሳሰቡ ችግሮችን አጥንተን ተወያይተን ተባብረን አንድ መንገድ ፈጥረን በሐገሪቷ ባህል መሰረት ካላንዳች ኩረጃ ታላቋን ኢትዮጵያ መፍጠር እንችላለን። መደምደሚያ ሃሳብ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ለአዲስ ብሔራዊ ውይይት አሁን አዲስ የብሔራዊ ውይይት ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። ስለ ሐገራችን ነባራዊ ሁኔታ በሰለጠነ አስተሳሰብ መወያየትና ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል። ለውጥ መጣ በተባለበት ዘመን ማለትም ባለፉት ዓርባ አመታት ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ነበር ማለት ያስቸግራል። ከእንግዲህ ወዲህ ግን ይህ የብሔራዊ ውይይት መድረክ መፈጠር አለበት። ኢትዮጵያ የት ነው ያለችው፣ ወደ የት ነው ምትሔደው? ያለችበት ጎዳና ትክክል ነው ወይስ አይደለም በሚሉ ሀሳቦች ላይ በጋራ በመወያየት ስምምነት ላይ በመድረስ በኢትዮጵያኒዝም በመጠቀም አሁን ሐገራችን ካለችበት ውስብስብ ችግር መውጣት እንችላለን። ባጠቃላይ ከእንግዲህ ወዲህ ለውይይት የሚጠቅሙን ኢትዮጵያ በንፅህናዋ የተበጀውን ፣ በመንፈሳዊ ኃይል የተመራውን የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ተጠቅመን ትልቅ እንደ ነበረች እንደ ገና ትልቅ ለማድረግ ተሳስበን ተደማምጠን በታላቅ ትሕትና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንገንባት። ሁሉ ነገር ከሃገራችን ስለ ተፈጠረ ለሌሎች ምሳሌ ስለ ሆንን ሃገራችን ወደ ፊት እንድትሄድ ጠንክረን እንሥራ። ከእርስዎ አመራር ምን ይጠበቃል? ገጽ 5 የ8 ሌሎች ሃገራት በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ተጠቅመው ነጻ የወጡና ሃገራቸውን ወደ ተሻለ መንገድ የመሩት በእኛ ኢትዮጵያዊነት ጥንካሬ እና የደረሱብንን የተለያዩ ተግዳሮቶች ተቋቁመን በነፃነት መኖር በመቻላችን ነው። አሁን ሃገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት በዘር፤ በኃይማኖት እና በጎሳ ተከፋፍሎ ሕዝቡን በቋንቋ እና በክልል አዋቅሮ በመግዛት፤ ከኢትዮጵያዊነት በፊት ለጎሳ ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ በሥራ ምክንያት ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስና ሥራ እንዳይሠራ አድርጓል። ሕገ መንግሥቱ በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በክልል መንግሥት አደረጃጀት የተመሠረተ ስለሆነ ሕዝቡ ከሃገሩ ይልቅ ቅድሚያ ለብሔሩ እና ለክልሉ እንዲሰጥ አድርጎታል። ይህ የክልል አደረጃጀት እስካልተስተካከለ ድረስ አሁን ሃገራችን ከገባችበት ውጥንቅጥ ችግር ውስጥ መውጣት አትችልም። ሃገራችን ከገባችበት ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ችግር ልትወጣ የምትችለው የክልል አወቃቀር ተስተካክሎ ዜጋው ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት የመዘዋወር፤ የመሥራት፣ የመማርና የመኖር መብቱ ተጠብቆ ሊያስኬድ የሚቻለው ለኢትዮጵያዊነት ቅድሚያ የሚሰጥ ሕገ መንግሥት ሲኖር እንደሆነ እሙን ነውና ሕገ መንግሥቱ መሻሻያ ቢደረግበትና ቢስተካከል ለሃገራችን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል። ሃገራችን ኢትዮጵያ ለውጪው ዓለም በተለይም ለተጨቆኑ ሕዝቦች ራሷ ተቸግራ እና የደም ዋጋ በመገበር የሰጠችው መንፈሳዊ ፀጋ ቀላል የሚባል አይደለም፣ ከራሷ አልፋ ለተጨቆኑ ሕዝቦች ሁሉ ምሳሌ እና አርዓያ የሆነች ሕገራችንን ችግሮቿን እና እንከኖቿን እኛ ልጆቿ በሰለጠነ እና በሰከነ መንገድ በመነጋገር በመደማመጥና በመከባበር ልንፈታና አሁን ካለችበት ወደ ተሻለች ኢትዮጵያ ልናሸጋግራት ይገባል። የሃገራችን የትኛውም ዓይነት ችግር መፈታት ያለበት በራሷ ልጆች መሆን አለበት! በፖለቲካ አመለካከት እና አመከንዮ ባንግባባም እንኳ ለሃገራችን እና ለሕዝቧ ቅድሚያ በመስጠት ወደ መፍትሔ መንገድ መምጣት እንችላለን። እርስዎ የጀመሩት ኢትዮጵያዊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአራቱ አቅጣጫ አስተጋብቷል! ሕዝቡም ሲናፍቀው የነበረ ዓቢይ ጉዳይ ነውና ተቀባይነትዎ ጨምሯል! ይጨምራልም። አሁን የተጀመረውን ኢትዮጵያዊነት መነቃቃት ወደ ተሻለ እና ከፍ ወደሚል ደረጃ ለማድረስ እርስዎ ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት እና አሁን ካለንበት የብሔር እና የሃይማኖት ችግር ወጥተን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ተከብሮ የሚኖርበትን ዕድል ለመፍጠር ሁላችንም በጋራ የምንሠራበት ዕድል መፈጠር ይኖርበታል። አሁን ከሚታየው ተስፋ እና ጅማሮ በመነሳት ሃገራችን ወደ ቀድሞ ክብር እና ዝናዋ የምትመለስበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም። በእርስዎ አመራር የሚከተሉት ዋና ዋና ተግባሮች እንዲከናወኑ በትሕትና እናመለክታለን፤ 1ኛ/ የኢትዮጵያኒዝም መንፈስ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪቃና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጭ፤ እንዲዘረጋና እንዲዳብር ማድረግ፤ 2ኛ/ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሙሉ መሻሻል እንዲያስገኝ መለወጥ ከሚገባቸው ብዙ ጉዳዮች አንዳንዶቹን እንጠቁማለን፤ ገጽ 6 የ8 የክልል አስተዳደር ኢጣልያኖች ኢትዮጵውያንን መግዛት የሚቻለው በመከፋፈል ነው በማለት የዘረጉት አስቀያሚ ሥልት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከዚህ መላቀቅ አለባት። በዘር፤ በኃይማኖት፤ በቋንቋ የኢትዮጵያን ሕዝብ መከፋፈል እንደ ሀጢአት የሚቆጠር በመሆኑ ሐገራችን በክፍለ፟ ሐገር እንድትደራጅ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሃገራችንን ረጅም ታሪክ፤ ጥበብና ዕውቀት በሚያጎላ መንፈስ እንዲስፋፋ ይሁን። በተለይ ሰንደቅ ዓላማው ኣረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ቀለማት ብቻ የሚታይበት ሆኖ መንግሥት በተቀየረ ቁጥር ሊለዋወጥ አይገባም። በአፍሪቃ አፍሪቃውያን የፈጠሩት ፊደል ግዕዝ ብቻ ነው። ስለዚህ በዚህ ታሪካዊ ፊደል መጠቀም ሲገባን በሌሎች ባእድ ቋንቋዎች ፊደሎች ለምሳሌ በላቲን መጠቀም ተገቢ አይደለም።12, 13 ከኢትዮጵያ አካባቢ እንደዚሁም የመላ አፍሪቃ አንድነት በጣም አስፈላጊ ነው። በእዚህ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ልዩ ሚና እንዳላት መገንዘብ ያስፈልጋል። ይኸውም በዓለም ሕዝብ ከ1829 እስከ 1929 ድረስ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጊዜ የነበረ መሆኑ በዓለም ተሰራጭቷል። በኢትዮጵያ ስም ሁለት ማኒፌስቶዎች (መመሪያዎች) በ1829 ዓ.ም. በአሜሪካ፤ በ1896 በደቡብ አፍሪቃ፤ ከአድዋ ጦርነት ድል በኋላ ተሰራጭተዋል። አፍሪቃ በሙሉ በኢትዮጵያ ስም የሚታወቅበት ጊዜም እንደ ነበረ ማስተዋል ይገባል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ያከናወነችውን አሁንም እንድትቀጥልበት ያስፈልጋል። ይህም ታሪካዊ መሠረታችን ነው። ከእዚህ ቀደም የነበረው የእርስ በርስ መፈራረጅ፤ የመለያየትና ችግር ሲያጋጥም ወደ ጦርነት ከማዘንበልና በውጭ ሃገሮች መሣሪያ ከመጠቀም፤ ወደ መወያየት፤ መግባባትና መመካከር ባሕል መለወጥ ይጠቅማል። የኢትዮጵያን ችግር በኢትዮጵያውያን መፍትሔ ማስወገድ ይገባል። በውጭ እጅ ላይ መተማመን መክፋፈል ያስከትላል። የመንግሥቱ አወቃቀር ግልጥነት፤ የወስጥ ቁጥጥር፤ ውጤታማነት የሚያሰፍን ሊሆን ይገባዋል። የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣኖችም ሊመደቡ የሚገባው በተገቢ መስፈርት ብቁነታቸው ብቻ ሳይሆን ተደጋጋሚ ሥልጠናም እየተከናወነላቸው በቂ ቅልጥፍናና ከሙስና የተላቀቀ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ማድረግ ያስፈልጋል። የበላይ አመራሩ የጊዜ ገደብ ይወሰን። 3ኛ/ ኢትዮጵያ ካለችበት ቀውጢ ጊዜ ተላቅቃ አስተማማኝ ወደ ሆነ ጎዳና እንድትገባ ሁሉም ማለት የፖለቲካ፤ የማሕበረ ሰብዓዊ፤ የመንፈሳዊ፤ ወዘተ ድርጅቶች የሚሳተፉበት የሽግግር ሒደት ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ። የእርስዎንም የአስተዳደር ዘመን እስክ መጨረሻው ለሃገር የሚበጅ ውጤታማ እንዲሆን እንመኛለን። ኣገርን በጎሳ መከፋፈል ኢትዮጵያን ሰማንያ ቦታ መከፋፈል ነው። በኢትዮጵያዊነቱ ተከባብሮ መኖር የማይችል ሕዝብ በየቤተሰቡ መንግሥት ፈጥሮ መኖር ኣይችልም። ለኣፍሪቃውያን መከታና ኣለኝታ ሆኖ የቆየው ኢትዮጵያዊነት ኣፍሪቃ ኣንድ ኣገር ሆና መብቷ በዓለም ደረጃ እስኪመለስ ከመንደርና ጎሳ ኣስተሳሰብ መላቀቅ ይገባናል። ከታላቅ አክብሮት ጋር! እግዚአብሔር ሃገራችንን ይባርክ!! 
1 ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ 
2 ፕሮፌሰር ሲሳይ አሰፋ 
3 ፕሮፌሰር ብርሃኑ መንግስቱ 
4 ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ 
5 ዶ/ር ኣበራ ሞላ 
6 ዶ/ር ወርቁ አበራ 
7 ዶ/ር ጌታቸው ተመስገን ገጽ 7 የ8 
8 ዶ/ር አበባ ደግፌ 
9 ዶ/ር እጀቡሽ አርጋው 
10 ወ/ሮ ጽጌረዳ ሙሉጌታ
11 የተከበሩ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ 
12 አቶ ምንተስኖት መንገሻ  አቶ ሰይፉ ኣዳነች ብሻው
13 አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሄር  አቶ ኪዳኔ አለማየሁ
14 አቶ እርቅርማሪያም ደረስ  አቶ ተፈራወርቅ አሰፋ  አቶ ይልማ ዘሪሁን  አቶ ይርጋለም ጎበዜ 
15 አቶ ከድር ሰይድ  አቶ መሸሻ ካሳ 
16 አቶ ኤሊያስ ማሞ 
17 አቶ ብርሃኑ ገመቹ 
18 ወ/ሮ አስቴር ኃይሌ 
19 አቶ በቀለ ተገኝ 
20 አቶ አብርሃም ቀጀላ 
21 አቶ ግርማ ካሳ 
ዋቢ 1. Ethiopianism, http://www.druglibrary.net/olsen/RASTAFARI/campbell.html
2. ETHIOPIANISM IN PAN-AFRICAN PERSPECTIVE, 1880-1920, https://www.upjournals.co.za/index.php/SHE/article/view/85
3. Abyssinian Baptist Church, New York City (1808- ) http://www.blackpast.org/aah/abyssinian-baptist-church-1808
4. Ethiopianism in African Christianity, https://repository.up.ac.za/bitstream/handle/2263/21579/011_Chapter10_p258- 277.pdf?sequence=12 5. Ethiopianism and African Nationalism in South Africa before 1937, https://www.persee.fr/doc/cea_0008-0055_1986_num_26_104_1689
6. Ethiopianism, http://www.blackpast.org/gah/ethiopianism
 7. Ethiopianism and the Independent Church Movement, http://www.worldhistory.biz/sundries/4707
8-ethiopianism-and-the-independent-churchmovement.html 8. Ethiopianism, https://www.britannica.com/topic/Ethiopianism
9. Ethiopianism a symbol of resistance to injustice, http://www.aau.edu.et/blog/ethiopianism-a-symbol-of-resistance-to-injustice-thabo-mbeki/
10. John Dube, http://www.anc.org.za/content/john-dube ገጽ 8 የ8
11. Ethiopian Muslims History, http://www.selamta.net/ethiopian%20muslims%20history.htm
12. http://www.ethiomedia.com/1000dir/oromigna-be-amara-kilil-be-geez-fiddelendiset.pdf
 13. http://www.ethiomedia.com/1000dir/open-letter-to-president-lemma-megersa.pdf8

ክስተቱ የቀድሞ የህወሓት ታጋዮችን አስቆጥቷል



ዋዜማ ራዲዮ- የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሕዳሴው ግድቡ ዉሀ የሚተኛበትን ሰፊ ቦታ ከደን ነጻ እንዲያደርግ 2 ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን የተሰጠው ከዓመታት በፊት ነበር፡፡ አሁን ግን ገንዘቡ ሳይባክንብኝ አልቀረም እያለ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ የተከፈለው ከመንግሥት አሠራር ውጭ ፣ ያለምንም መደበኛ ውል፣ ሥራው ተሠርቶ እንደተፈጸመ ተደርጎ መቶ እጅ ክፍያን በመፈጸም ነው፡፡
ሜቴክ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ግን ሥራው መስተጓጎል ገጥሞታል፡፡ ገንዘቡን ጠፍቶበታል፡፡
ፕሮጀክቱ የሚጠይቀው የሰው ኃይል እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ ሁኔታ መሠራት ቢኖርበትም ሜቴክ በወቅቱ ያዘጋጀውን ጨረታ በመሰረዝ የቀድሞው የሕወሓት ታጋዮች መቋቋሚያ እንዲሆናቸው በሚል ሥራውን ያለጨረታ አሳልፎ ሰጥቷቸው ነበር፡፡
ኾኖም ነባር ታጋዮች ለተሰጠው እድል አመስግነው ሥራውን በወቅቱ የተረከቡ ቢሆንም የስራውን ስፋት ከግምት በማስገባት ለሌላ ሦስተኛ አካል ‹‹ሰብ ኮንትራት›› መስጠት እንዳለባቸው ከስምምነት ደርሰው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በግምት ከአዲስ አበባ እስከ ዝዋይ ያክላል የሚባለውን ይህን ሰፊ በደን የተሸፈነ ቦታ መመንጠር የሚችሉ በሺ ለሚቆጠሩ የተደራጁ ወጣቶች ሥራውን በስምምነት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ስምምነቱም ወጣቶቹ እንዴትም ብለው ምንጠራውን በብቃት እንዲወጡና ክፍያ ሲፈጸም ግን ሰባ በመቶውን ለነባር ታጋዮች እንዲያካፍሉ የሚል ነው፡፡
ይህን ስምምነት ተከትሎ በሺ የሚቆጠሩና ራሳቸውን በ72 ማኅበራት ያደራጁ ወጣቶች ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘምተው ነበር፡፡ መቶ ሚሊዮን ብር ለሥራ ማስኬጃ ቅድመ ክፍያ የተቀበሉት እነዚህ ወጣቶቹ በከፍተኛ ሞራልና ተስፋ ወደ ስፍራው በመዝመት፣ ከአጎራባች አካባቢዎችና በተለይም ከጎጃም የጉልበት ሠራተኞችን በገፍ በመመልመል የዛፍ ቆረጣውን ሥራ ጀምረውት ነበር፡፡
‹‹በባህላዊ መንገድ ዛፎቹን መመንጠር የጀመርነው ዘመናዊ መጋዞች ከአየር ንብረቱ ጋር ስላልተጣጣሙልን ነው›› ይላል በዚህ ሥራ ተሠማርተው ከነበሩ ማኅበራት የአንዱ አስተናባሪ ለዋዜማ ሲናገር፡፡ ‹‹እውነት ለመናገር የገንዘቡን ትልቅነት እንጂ የሥራው ስፋት ሳንረዳ ነበር የገባንበት›› የሚለው ይኸው ወጣት በእድሜ ልክ የማያገኙትን ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ውሎና አዳራችንን ጫካ ውስጥ በቀለሷቸው ድንኳኖች ለማድረግ ተገደው እንደነበር ያስታውሳል፡፡
1500 ኪሎ ሜትር እስኩዌር እንደሚሸፍን የሚነገረው ይህ ደን ግድቡ ካለበት ወደ ኃላ በትንሹ 200 ኪሎ ሜትር ይሸሻል፡፡
በስድስት ወራት ብቻ 56ሺ ሄክታር ደን ጨፍጭፈን ከጨረስን በኃላ በስምምነታችን መሠረት ሁለተኛ ዙር ክፍያ ስንጠይቅ ‹‹አትቸኩሉ›› ተባልን የሚለው ይህ ወጣት የመጀመርያ ክፍያውን በዋናነት ለቁሳቁስ መግዣና ለዕለት ቀለብ ስላዋልነው ሁለተኛውን ክፍያ በጉጉት ለመጠበቅ ተገደን ነበር ይላል፡፡
‹‹ቀላል ሥራ አልነበረም፡፡ 12ሺ የጉልበት ሠራተኞች ተሳትፈውበታል፡፡ ዛፎችን ለመገንደስ ትልልቅ መጋዞች ሊቋቋሙት ባለመቻላቸው በሺ የሚቆጠሩ መጥረቢያዎች ከተገዙ በኋላ በሰው ጉልበት ነበር ሥራው ያሠራነው፡፡ 12ሺ የጉልበት ሠራተኞች ቁርስ ምሳና እራት እንዲሁም የበረሀ ድንኳን ማቅረብ፣ ሕክምናና ሌሎች ፋሲሊቲዎችን መስጠት የኛ ድርሻ ነበር፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ሂደት ሰዎች ሞተውብናል፤ እባብ የነደፋቸው የጉልበት ሠራተኞች፣ ወንዝ የወሰዳቸው ዛፍ ቆራጮች አሉ፡፡›› ሲል ፈተናው እንዴት አስቸጋሪ እንደነበር ለዋዜማ ተናግሯል፡፡
ቃል የተገባልን ክፍያ በጣም ሲዘገይብን ግን እኛን ከቀጠሩን ታጋዮች ጋር ሆነን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በደብዳቤና በአካል መጠየቅ ጀመርን ሲል ሂደቱን ያስረዳል፡፡
‹‹በመጨረሻም ከጄኔራል ክንፈ ጋር ቀጠሮ ተይዞልን መነጋገር ስንጀምር ገንዘቡ ለሌላ አጣዳፊ ነገር ውሎ ሊሆን ስለሚችል ያንን እስካጣራ እናንተ ሥራችሁን ቀጥሉ እንዳሏቸው ይናገራል፡፡ ሥራችንን ምን ይዘን እንደምንቀጥል አልገባንም ነበር ይላል፡፡
ከዚያ በኋላ በነበሩ ተከታታይ ስብሰባዎች ግን ነገሮች እየተበላሹ እንደመጡና ነባር ታጋዮችና ጄኔራሉ ሊግባቡ አለመቻላቸውን ያብራራል፡፡
‹‹ለዚህ ሥራ ተብሎ 2 ቢሊዮን ብር ለሜቴክ እንደተከፈለው እናውቅ ነበር፤ ብሩ ግን ሳይባክንባቸው እንዳልቀረም›› የሚለው ይኸው ወጣት ‹‹ምክንያቱም የሜቴክ ሰዎች ሲነግሩን ብሩ እኮ የለም፣ ከየት ነው የሚከፈላችሁ? ይሉን ነበር፤ እኛ ግን አላመናቸውም ነበር›› ይላል፡፡
‹‹እንዲህ አይነት ትልቅ ብር ባከነ ሲባል ለማመን አስቸጋሪ ነበር››
ነገሮች እየተካረሩ እንደመጡ ሲያስረዳም፣ ‹‹እኔ ማኅበሩን በመወከል አልፎ አልፎ ስብሰባዎቹ ላይ እገኝ ነበር፡፡ በትግርኛ ኃይለቃል ሲለዋወጡ እንሰማለን፡፡ በተለይም በአንድ ወቅት የጄኔራሉ የቅርብ ቤተሰብ ነው የሚባል የቀድሞ ታጋይ ‹‹የዕድል ጉዳይ ሆኖ ነው አንተ እዚህ ወንበር ላይ፣ እኔ ዊልቸር ላይ የተመጥነው›› ብሏቸው ስብሰባ ረግጦ እንደወጣ አልተመለሰም ይላል፡፡
ጄኔራሉም ከዚያ በኋላ ስሜታዊ በመሆን ‹‹ይሄ አገራዊ ፕሮጀክት ነው፣ ገንዘብ ገንዘብ አትበሉ፤ እኛ ጨረታ ማውጣት አቅቶን አይደለም፤ እናንተን እናግዝ ብለን ነው የሰጠናችሁ›› ሲሉ መናገራቸውን ያብራራል፡፡
በጄኔራሉ ተስፋ የቆረጡት ታጋዮች ፖስታ ቤት ቅጥር ግቢ ወደሚገኘው የዶክተር ደብረጽዮን ቢሮ በቀጥታ በመግባት መፍትሄ እንዲፈልጉላቸው ጠይቀዋቸው ‹‹ክንፈን አናግሬው እኔ ራሴ መልስ ይዤላችሁ እመጣለሁ፣ በጭራሽ አታስቡ›› ብለው በእርግጠኝነት መልሰዋቸው ነበር ይላል፡፡ ሆኖም ዶክተሩ ቃላቸውን ባለመጠበቃቸው የኛ ተወካዮች አቶ አስመላሽ ጋር በመሄድ እንዲያሸማግሏቸው ተማጽነው ይህም ውጤት ሳያስገኝ ቀርቷል፡፡
ይህን የሰሙት ጄኔራሉ የኛን ተወካዮቹን ለመጨረሻ ጊዜ አስጠርተው፣ ‹‹ስማችንን በየቢሮው እየሄዳችሁ ታጠፋላችሁ፣ ነገሩን በእልህ ለመጨረስ ካሰባችሁ እኛ እንብሳለን›› በማለት እንዳስፈራሯቸው ይናገራል፡፡
ከዚህ የተራዘመ ሂደት በኋላ ብዙዎቹ ተስፋ ቆርጠው ነገሩን እርግፍ አድርገው የተዉ ሲሆን 12 የሚሆኑ ማኅበራት ግን እውቅ ጠበቆችን በመያዝ ፍርድ ቤት ክስ መመስረታቸውን ይኸው ወጣት ይናገራል፡፡ ሌሎች ማኅበራት መክሰስ ያልፈለጉት በሌላ ሳይሆን ፍርሃት ስላደረባቸው ነው ይላል፡፡ ‹‹ሜቴክን ከሰን የት እንደርሳለን›› ያሉ ነበሩ፡፡ የመጣው ይምጣ ብለው የከሰሱም ነበሩ ይላል፡፡
ወደ ፍርድ ቤት ከሄዱት ማኅበራት የተወሰኑት ጉዳዩን እንዲይዙላቸው እውቅ ጠበቆችን መቅጠራቸውንና ከነዚህም መሐል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአቃቢ ሕግ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ እሸቱ ወልሰማያትና ቀድሞ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩም ይገኙበታል ይላል፡፡
ኾኖም የፍርድ ሂደቱ ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደ ሲሆን ዳኞች ጉዳዩ እያሰጋቸው ነው መሰለኝ ቶሎ ቶሎ ይለዋወጡ ነበር ብሏል፡፡
አንዱ በፍርድ ቤት ጉዳዩን አከራካሪ ያደረገው ለማኅበራቱ መከፈል ያለበት የምንጣሮ ሥራ የቦታ ስፋት መለካት ያለበት በጂፒኤስ ነው ወይስ በሜትር የሚለው ሲሆን ሜቴክ በጂፒኤስ ይለካልኝ ሲል ማኅበራቱ በሜትር ነው መለካት ያለበት የተስማማነውም በዚህ መንገድ ነው ብለው ተከራክረዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም የመሬቱ አቀማመጥ ወጣ ገባ ስለሚበዛው በጂፒኤስ ቦታውን መለካት አካባቢው ጠፍጣፋና ሜዳማ እንደሆነ ታሳቢ እንደሚያደርግና የምንጣሮውን ልፋት ግምት ውስጥ የማይከት ያደርገዋል ባይ ናቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያዋ ዳኛ የኢትዮጰያ ካርታ ሥራዎች ድርጅት ሞያዊ አስተያየት እንዲልክ በማዘዛቸው የከሳሽ ጠበቆች ቦታው በሜትር መለካት እንዳለበት የሚያስረዳ ደብዳቤ ከዚሁ መሥራያ ቤት አምጥተው ለውሳኔ ቀጠሮ ሊሰጥ ሲል የሜቴክ ጠበቆች ከተመሳሳይ መሥሪያ ቤት ቦታው በጂፒኤስ መለካት እነዳለበት የሚያስረዳ ሌላ ተጻራሪ ደብዳቤ አጽፈው በማምጣት መቻላቸው ፍርድ ቤቱን አስገርሟል፡፡ ሁለቱም ደብዳቤዎች የተፈረመባቸው በተመሳሳይ ሰው መሆኑም ሌላ አግራሞትን ፈጥሯል፡፡
ችሎቱን የምታስችለው ዳኛ በጉዳዩ በመደመም ችሎቱን ድንገት በትና የወጣች ሲሆን ከዚህ ዕለት ጀምሮም ችሎቱን የሚያስችሉት ዳኛ መቀየራቸው ተነግሯል፡፡ ዳኛዋ ከዚህ ውሳኔ ያደረሳቸው ምናልባት ቀደም ብለው የሜቴክ ኃላፊዎች መጥተው እንዲመሰክሩ የሚለው ትእዛዝ ሊከበርላቸው ስላልቻለ ሊሆን ይችላል፡፡
እኚህ ዳኛ ለማኅበራቱ የሚያደላ ውሳኔ ሊወስኑ ይችላሉ በሚል ለውሳኔ ቀጠሮ ከመሰጠታቸው ቀደም ብሎ የሜቴክ ጠበቆች ‹‹የኛ ሠራተኞች ጉዳይ የሚታየው በጦር ፍርድ ቤት ነው›› የሚል ነገር ለችሎቱ ማሰማታቸው ዳኛውን ሳያስቀይማቸው እንዳልቀረም ይገመታል፡፡
ሜቴክ በኮንትራት ለሚሰጣቸው ሥራዎች በጊዜውና ተገቢውን ክፍያ መክፈል ባለመቻሉ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይቀርቡበታል፡፡
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ በስተምዕራብ 600 ኪሎ ሜትር በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ፣ ያዩ ወረዳ የድንጋይ ከሰል እያወጣ መሸጡ የሕዝብ ቅሬታን በመፍጠሩ በተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄን አስነስቶ ነበር፡፡
በሌላ ዜና የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን መስርተው ለስምንት ዓመታት ያስተዳደሩት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኜው ሰሞኑን የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ሳምንታዊው የቢዝነስ ጋዜጣ ፎርቹን ዘግቧል፡፡