Tuesday, September 22, 2015

ፕሮፓጋዳ ዓይን ያወጣ ውሸት ማቅረብ አይደለም።የሚሰራ መሆን አለበት። ጎብልስና ወያኔ

                              

ጎብስ_ደብረጽዮን
ፕሮፓጋዳ ዓይን ያወጣ ውሸት ማቅረብ አይደለም።የሚሰራ መሆን አለበት። ጎብልስና ወያኔ

ከቢላል አበጋዝ
ዋሽግቶን ዲ ሲ
ሰኞ ፣ ሴፕቴምበር 21 ቀን 2015
የወያኔ ትልቁን “ኩዴታ” ጥምረት ውህደትን “በሾኬ የጣለበትን” የወሬ ጋጋታ እንግዲህ አለፍነው። ተመስገን። ሰማይ አልተደረመሰም። የወያኔ ቲቪ ሰዓት እላፊ ሰራ። በዳያስፖራ ያሉ የወያኔ አሽከሮች “የፍየል ወጠጤ” ዓይነት መልክት አስተጋቡ። ወያኔን አትንኩብን አሉ። የአንድን ሰው መክዳትን ድል አድርገው ሊያደናቁሩ ተሟሟቱ። አዲስ የተሻሻለች ህወሃትን የሚሹ ምሁራንም የቆሙበት በግልጥ ታየ። ሌሎችም ጥምረት ውህደቱን ተቹ። ህብረት እንፍጠር ያላችሁ ሳይገባችሁ ነው አሉ። የሞላ መክዳትት ወሬ ጥቂቶችን አናዞ እያለፈ ነው።መጭውን የወያኔ “የረቀቀ ስለላ ውጤት” እስክንሰማ እንጠብቃለን።የሞላ አስከዶም ተገቢው ጎራ መዘነቅ ወሬው ቶሎ ከሰመ::ከዚህ የሚያልፍ አይደለም።ግን መጥኔ ለአዲሳባ!
ፕሮፓጋዳ ጥበብ ነው።ተንኮልም አለበት። ወያኔ ደግሞ በተንኮል እንጂ በጥበብ አይታማም። ፕሮፓጋዳ ዓይን ያወጣ ውሸት ማቅረብ አይደለም።የሚሰራ መሆን አለበት።ፕሮፓጋዳን በስልት ከያዙት ጋር ሲተያይ፡ ወያኔ ዛሬ ገና በድንጋይ ዘመን እየኖረ ነው።የወያኔ ፕሮፓጋዳ በመለስ አገዛዝ ይሻል ነበር።የአስራ አንድ ከመቶው “ዓመት ካመት እድገት”፤”አልሸባብ ሊወረን ነው””በቀን ሶስቴ መብላት”ትዝ የሚሉ ናቸው። ዛሬ በሞላ መክዳት የሆነውን የህወሃት ግርግር መለስን መቃብሩ ውስጥ ሆኖ የሚያወራጨው ነው።የሞላ መክዳት ጊዜ አለመግዛቱን መለስ ቶሎ ይረዳው ነበርና።አንድ የትጥቅ እንቅስቃሴ ብርታቱን የሚያገኘው ወይ በተሰዋ፤ በተሰዋች ጓድ ነው፤ወይ በከዳ፤ በከዳች ጓዲት ድርጊት የአባላት መብገን ነው። ከርእዮትና ከዓላማ ጎን ለጎን እኒህ ያሉት ተጨባጭ ክስተቶች ናቸው ትግልን ወደፊት የሚገፉት።የሞላ አስከዶም መክዳት በጊዜ መሆኑ ከፍ ካለ ጥፋት የሚሰውርና ለደምሂት ሰራዊት ጠብቆ መዋቀሪያ እድል ማስገኘቱ ይታመናል። ታች ከምናየው የፕሮፓጋዳ ሊቅ ከነበረው የአዶል ሂትለር ባለሟል አባባል ብዙ ታዝበን የወያኔንና አሽቃባጮቹን ጅል ድርጊት እንታዘባለን።ህዝባዊ ትግል የተራ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሚሆነው በህወሃቶች ጭቅላት ውስጥ ብቻ ነው።ህዝባዊ ትግል በተራ ፕሮፓጋዳ የሚገታ ቢሆን እንዴት ከየካቲት ስልሳ ስድስት አንስተን ከዚህ ደረስን? ፕሮፓጋዳንና ድንፋታ ለደርግ የእለት ተለት ተግባር አልነበረም ?እስቲ  ወደ ዮሴፍ ጎብልስ እንሂድ። እሱ እንዲህ ይላል፡
“ፕሮፓጋዳ ሰዎችን መሳብ፤ማሳመን እውነት  ነው ብየ ለተቀበልኩት፤ ይህ ነው ፕሮፓጋዳ ማለት ። ሲጀመር መግባባት አለ። ይህ መግባባት ፕሮፓጋዳን እንደ መሳሪያ ተጠቅሞ መግባባትን(ስብከትን) ወደ ፖለቲካ ይቀይረዋል።ማቸነፍ ዋናው ነገር ነው።ፕሮፓጋዳ የተራ ሰዎች ምግባር አይደም።የሙያተኞች ነው።ደስ የሚል ወይም በንድፈ ሃሳብ ትክክል መሆን የለበትም። የሚያስደንቁ፤የተዋቡ ንግግሮችን ባደርግ ሴቶችንም እምባም ባስረጭ ግድ አሰጠኝም።የፖለቲካ ንግግር ዓላማው ማሳመን ነው።እኛ ትክክል ነው የምንለውን።ክፍለ ሃገር ሆኘ የምለው በርሊን ሆኘ ከምለው ይለያል።ቤይሩት ሆኘ የምናገረው ፋረስ አዳራሽ ሆኘ ከምለው አይመሳሰልም።ይህ የንድፈ ሃሳብ ሳይሆን የተግባር ጉዳይ ነው። የጥቂት ገልጃጆች ማህበር ሳይሆን ሰፊውን ህዝብ የሚያንቀሳቅስ ነው የምንሻው።ፕሮፓጋዳን ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል። አእምሮን ማራኪ መሆን የለበትም።የፕሮፓጋዳ ተግባር ምሁራዊ እውነቶችን መፈተሽ አይደለም።እዲህ ያለው ፍተሻ የራሱ ጊዜና ቦታ አለው።እኔ እዲህ ያለውን እውነት የምፈትሸው ከቢሮዬ ተቀምጨ  እንጂ ከስብሰባ አዳራሽ ሆኘ አይደለም።”(1)
ወያኔ ህውሃት በሙስና የተዘፈቀና የተጠላ መንግስት ነው። ፕሮፓጋዳ አያሰነብተውም። ከላይ የጠቀስኩት ዮሴፍ ጎብልስ የናዚን ፓርቲ አላዳነም።ጎብልስን የጠቀስኩት ወያኔዎች የምትሰሩት የገልጃጃ ስራ እንጂ ፐሮፓጋንዳ አይደለም ለማለት ነው።ስራችሁ አያተርፍም።ዙሪያው ገደል ሆኖባችኋል። ከጭካኔአችሁ የኢትዮጵያ ህዝብ በውሸታችሁ ነው የሚለያችሁ።ስለዚህ በጥቅም ከምትደልሉት በተቀር ሌላው ዛሬ በምን ይደግፋችሁ?ይህ የናተው ግዛት ሲያልፍ(በቅርቡ) “የውሸት ዘመን” የሚባል ታሪክ ይነገራል ብንል ስተት አይሆንም።የወያኔ ፕሮፓጋንዳ የቱ ይማርካል? ከህወሃት አበደን ምንም አይወጣም። ሺ ደምስ ቢለጠም ስኒ የምትሞላ አያመርትም።የህወሃት ፕሮፓጋዳ እውር ሌላውን እውር የሚመራበት ድራማ ነው።
ማንም ደካማ መንግስት በፕሮፓጋዳ አልዳነም።ወታደራዊ ደርግንም ፕሮፓጋዳ አልታደገውም።ዋንቻው  ዮሴፍ ጎብልስ እና ጌታውንም አላዳነም። ታአማኒነት ከሌለ ፕሮፓጋዳ ዋጋ የለውም። ተአማኒነት ታገኙበት የነበሩት ሃያ አራት ዓመታት አባክናችኋል።ተቃዋሚው እውነት ከሱ ጎን ስለሆነች ፕሮፓጋዳ አይነዛም።ራቡ እውነት ነው።የኑሮ ውድነቱ የሚታይ ነው።ስደቱ ምስክር አያስጠራም።መፈናቀል፤ሰቆቃ፤ግድያው ያንገሸግሻል።ህዝቡ በምቾት ተንደላቃችሁ በሙስና ተጨማልቃችሁ እንቀጥላለን በሚል ተስፋ የምትወራጩትን ህወሃቶች ይገረምባቸዋል።”እኒህ ጉዶች !” ይላል።እያለ እንደከረመው።
የሰሞኑ ወሬ መሰረት የሆነው ሞላ አስገዶም አሳዛኝ ነው።እንዴት ዓላማውን እንኳን አፍታቶ ማስረዳት የማይችል ሰው የሞቀ ኑሮውን ለዓላማው ሲል ሁሉን ትቶ በረሃ የወረደውን ይዘልፋል?እንደ አንድ ህብረተሰብ ወያኔ(መለስ) ከመጣ ወዲህ የነገሰው ጻረ ምሁርነት ውጤት ነው።ሞላም የዚህ ዝቅጠት ውጤት ነው።ወያኔ ያልተረዳው እንደ ህዝብ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ከጊዜያዊ ወሬ ሸመት ማለፋችንና ውጤት ተኮር መሆናናችንን ነው።ድንበር ቆርሶ ሰጥቶ፤አርሶ አደሩን(ሃረሽታይ!)ከመሬቱ አፈናቅሎ ለውጭ ከበርቴ ቸብችቦ ስለ አገር አለማፈራረስ ማውራት እብደት ነው።እብዶች ስልጣን የያዙባት አገር ዛሬ ኢትዮጵያ ናት። ይህ ደግሞ አስጊ ነው። ለመሳለቅ አይደለም::ህወሃት በስልጣን ከቀጠለ ሊሆን የሚችለው ዘግናኝ ነው።
እስቲ ይህን እንጠይቅ።ደምሂት አስራ አራት ዓመት የፈጀ የንቧይ ካብ ነው የሞላ አስከዶም ባንዴ የሚንደው?ይህ እራሱንስ ሞላን አያስገምተውም ?እሺ ሰባት መቶ አስከትሎ ከዳ የተባለውን ብናምን አብዛኛውን ጦር ይዞ እንዳልወጣ የሚያመላክተው ወዲያው በማግስቱ ስለሌላ ውጊያ ሰማን።ገና ደግሞ ዝርዝሩን እንሰማ ይሆናል።አንድ ቀን ደግሞ አንድ የአውሮፓ ወይም የሌላ አገር ጋዘጠኛ ሁሉን ይዘረዝረው ይሆናል። ልክ ስዊድናውያኑ እነ ሺብዬ የኡጋዴኑን የወያኔ ግፍ እንደዘረዘሩት ማለት ነው።ምናልባት የሞላም ወታደራዊ ወንጀል ይዘከዘክ ይሆናል።
ሞላ ወንጀል ፈጽሟል።ለራሱ ምቾት በማድላት ጔዶቹን ከድቷል።የሞራል ብቃት፡የአስትሳሰብ እርጋታና ማጣቱና  ከቅሌት አለመራቁ በጣም አዋርዶታል።የህወሃት መሪዎች ከተዘቀጡበት ቁልቁለት ይዘውት ተንሸራተዋል።ሞላ ሌላው ቀርቶ እዚያው አስራ አራት ዓመታት አባክኖ ከሄደበት አገር የነበረው ታሪክ ያገናዘበ አልመሰለኝም።በ1980 መጀመሪያ የጀብሃ ወይም የኢልፍ ጦር ተበተነ።ትልቅ ገናና ጦር ነበር።ግን ኤርትራ የነበረውን ሁኔታን አልወሰነም።ጦርነትም አልቆመም።ታሪክ ጉዞውን ቀጠለ።እኔ እስከማውቀው በራሳቸው ድክመት የጠፉ የትጥቅ እንቅስቃሴዎች ጀብሃ፤ኢህአሰ እና የታሚል ነብር ይባሉ የነበሩ የሲሪላንካ ተዋጊዎች ነበሩ።የተቀረው ለታሪክ ምሁራን እተዋለሁ።መልእክቴ ጦር እዲህ በዋዛ አይበተንም።ነገ ጎንደር፤ትግራይ ወሎ ላይ ሲያርበደብዳችሁ የማን አገር ጦር መጣብን ልትሉ ይሆን? ይህን ጎርፍ በዛሬው ውሸት ልትገድቡት?ሰዓት ቆጣሪ ዘግን በእጅ በመያዝ የጊዜን(ታሪክን)ግስጋሴ ማቆም ይቻላልን?
የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ መበታተን ዓላማው ከሆነ ህብረት ጥምረት ከጓሮው እንዲበቅል ለምን ይፈቅዳል?ማነው የመበታተንን፤የመክፋፈልን እቅድ በመንግስት ደረጃ የሰራበት ወያኔ ወይስ በሙስና ያልታማው የኤርትራ መንግስት? የኤርትራ መንግስት የወያኔ ወዳጅ ነበር።ይህን እናውቃለን። ዛሬ ግን አይደለም።በወያኔና በኤርትራ መንግስት መካከል ያጥፊና ጠፊ ቅራኔ ነው ያለው።የጥምረት ውህደት ሀይሎች ይህን ሳይገነዘቡ የዓመታት ጥረት አላደረጉም።ጋዜጠኛ ነኝ ያለ እንደ ኢሳት መሄድ የሚከለክለው አለ ማለት አይቻልም።አይቶ ነው ማውራት።የተረፈው የሻይ ስኒ ውስጥ ማእበል ነው።
ወያኔ ህወሃት ከኤርትራ በኩል ከሚመጣበት ጥቃት ይልቅ የራሱ ጉድለት ቁልቁለት እያወረደው ነው::የጥንታዊ ገናናው የሮማውያን አገዛዝን ምን ምክንያቶች ጣሉት?ሞላ አስገዶም አንዳንዴ እንኳን እያነበበ፤ እየተማረ ቢሆን ኖሮ በኤርትራ የቆየው የሮማውያን አገዛዝ ከአምስት መቶ የገነነባቸው ዓመታት በኋላ የተንኮታኮተው በሙስና፤በኑሮ ውድነት፤ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና  ወታደራዊ ሽንፈቶች መሆኑን ይረዳ ነበር። የህወሃትም እጣ ይህ እንደሆነ ይረዳ ነበር።ጣሊያን በምን ምክኛት ሊቸነፍ በቃ? በሰራው ግፍ አልነበረም?
ሞላ ሲከዳ በኤርትራ የተመቸ ኑሮውን ነው ያስታወሰው።ጓዶቹ የተጋዳይ ኑሮ እሱ ተንደላቆ እንደነበረ ተናግሯል።ይችኑ ምቾት ፍለጋ ህሊናውን ሸጠ።የትግሉ የታሪክ ጉዞ ግን አይቆምም።የሞላ አስከዶም ተገቢው ጎራ መዘነቅ ወሬው ቶሎ ከሰመ::የወያኔ የጅል ፕሮፓጋ መሪ ተዋናይ በመሆን የአስራ አራት ዓመታትን ትግል በክዳት መደምድም ዝቅ ያለ የአእምሮ እሴት ውጤት ነው።ወያኔ አይለወጥም።አይታረምም።አያቸንፍም።ፕሮፓጋዳው ጅል ነው!
1)     https://en.wikiquote.org/wiki/Joseph_Goebbels

አነድነት ሀይል ነው!
ድል ለመብቱ ለነጻነቱ እየታገለ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ!
ኢትዮጵያ  በህዝቦችዋ አንድነትና ፍቅር ለዘለዓለም በነጻነት ትኑር!

No comments:

Post a Comment