ከአንድ ወር በፊት የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር አባል ኤፍሬም ማዴቦ ኤርትራ ሂዶ ከዊሃ እስከ ኦምሃጅር ከአርበኞች ጋር በሚል ርዕስ የጻፈውና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የናኘው መልዕክት ትዝ ያለኝ የትህዴን ሊቀመንበር የነበረው ታጋይ ሞላ አስገዶም ድርጅቱን ከድቶ ወደ ወያኔ ህወሃት ተመለሰ እንደተባለ ነው።
በተለያዩ የኤርትራ በረሃዎች ጫካዎች የመሸጉትን አርበኞች በጽሁፉ እያስቃኘን የትህዴን ካምፕ ደርሰው በነዓምን ዘለቀ ዲጄነት የተከፈተው የጥላሁን ገሰሰ ሙዚቃ ሲያዳምጡ በነበረበት ቅጽበት እንዲህ ሲል ሳያውቍም ይሁን አውቆት ተንብዮታል።
“አልማዝን አይቼ እልማዝን ሳያት”፤ “እንጉዳዬ ነሺ” “አመልካች ጣት” “መሳቁን ያስቃል” . . . ብቻ ምን አለፋችሁ የጥላሁን ሙዚቃ ተዥጎደጎደ። ጥላሁን ገሠሠ አስመራ ላይ የሚጠብቀንን ቀጠሮ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ እኛነታችንን አስረሳን። ቢበዛ አንድ ሰዐት ብለን የመጣን ሰዎች ከሦስት ሰዐት በላይ ከደምህት ጓዶቻችን ጋር ቆየን። በመጨረሻ የጉዟችን መሪ “አንድ ለመንገድ” ብሎ ከተቀመጠበት ተነሳ። እሱ ሲነሳ “እንክርዳድ እንክርዳድ የተንከረደደ፤ ስንዴ መስሎ ገብቶ ስንቱን አሳበደ” የሚለዉ ዘፈን እያለቀ ነበር። ነአምን. . . ነአምን ብዬ ስጣራ . . . “One for the road” ይቀረናልኮ አለ ነአምን . . . እንሂድ የምለዉ መስሎት። ይህንን ሙዚቃ እንደ እንክርዳድ ተቀላቅሎን ለሚያሳብደን የዳያስፖራ ቱልቱላ መርጫለሁ አልኩት። ሳቅ አለና ከቴፑ ጋር መጫወቱን ቀጠለ። እርግጠኛ ነኝ ተቦርነ በየነ ወይም መሳይ መኮንን አንድ ቀን “እንክርዳድ እንክርዳድን” በኢሳት ያሰሙናል። አይደል ተቦርነ?
በመጨረሻ የኛም መሄጃ የሙዚቃዉም መገባደጃ ደረሰ። “One for the road” የተባለለት ሙዚቃ (ዘፈን) ገና ሲጀምር ሰማሁና ኢችንማ አምላክ ነዉ የመረጠልን አልኩ በልቤ። ያ በቁሙ “አጥንቴም ይከስከስ” ብሎ ያስተባበረን ጥላሁን ገሠሠ አሁንም ከላይ ከሰማይ ቤት “ቃልሽ አይለወጥ እባክሺ….ን” እያለ ቃል እንድንገባባ አደረገን። ተራ በተራ ከአርበኛ ሞላ አስገዶም ጋር እየተቃቀፍን “ቃልሽ- አይለወጥ- አባክሽን” ብለን ተለያየን። ቃል የዕምነት ዕዳ ነዉ ብዬ ነበር የጀመርኳችሁ፤ አሁንም ቃሌ ይሄዉ ነዉ። ቃላችን አይለወጥ! ቸር ይግጠመን።
ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር
አይ ሙዚቃ አመራረጥ ለነዓምን፤ አይ አጻጻፍ ለኤፍሬም !!! ቃልሽ አይለወጥ በሚለው የጥላሁን ገሰሰ ዘፈን ከዛሬው ከዳተኛ ከሞላ አስገዶም ጋር የተሰነባበታችሁት ቃሉን እንደሚያጥፍ ታይቷችሁ ነው ብዬ የነብይነት ማዕረግ ልሰጣችሁ ወደድኩ። “One for the road” የተባለለት ሙዚቃ ለሞላ አስገዶም መሸኛ ይመስላል። እንክርዳዱ ማን እንደሆነ በውስጠ ወይራ አጻጻፉ ገባን።
የአፋር ሕዝብ ንቅናቄ፣ ትህዴን፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄና አርበኞች ግንቦት 7 የጋራ አገር አድን ንቅናቄ መመስረታቸውን በተመለከተ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም በኢሳት ራዲዮ ተጠይቀው በድርጅቶቹ አባላት መሃል ማፈግፈግ ቢከሰት እንኳ አገር አድን ሰራዊቱ እንደሚታደገው አብራርተዋል። ይቺንም ትንቢት ብያታለው። ለዚህም ካስረኛው የቃለመጠይቁ ደቂቃ በኋላ እንደተረዳነው ከሁሉም ድርጅቶች ተውጣጥቶ ከተቋቋመው አገር አድን ሰራዊት ተመልሶ ወደ እናት ድርጅቱ ልመለስ ማለት አይቻልም። አራቱ ድርጅቶች በጋራ ንቅናቄው ሰራዊት ይዋጣሉ እንጂ ለምሳሌ ትህዴን ብዙ ሰራዊት ያለኝ እኔ ነኝ እና በኔ ስም ተጠሩ ቢል የሚሰማው የለም።ሞላ አስገዶም ትግሉን የከዳውም ትህዴንን እንደንብረቱ ቆጥሮ መሪ ካላደረጋችሁኝ ብሎ ከሌሎች ጋር ተጣልቶ ከሆነም ወደፊት የምናየው ነው።
ለማንኛውም የነፕሮፌሰር ብርሃኑ ምሁራዊ አካሄድ የህወሃትን ካባ ለብሰው ኤርትራ ለመሸጉት ቅጥረኞች አልተመቻቸውም። የተደላደለ የ አሜሪካ ኑሯቸውን ትተው እነ ኤፍሬም በረሃ ይወርዳሉ ብለው እነ ወዲ አስገዶም አልጠበቁትም። ህዝቡ ለውጥ እንደሚፈልግ ተረዱት።ነገም ዛሬም የሚወተውቱት ስለ እውነተኛ ዲሞክራሲ ነውና ሆዳሞች ጨነቃቸው።ስለዚህ ሳይነቃባቸው ፈረጠጡ።
በመጨረሻም የ አርበኖች ግንቦት ሰባት አመራሮች ኤርትራ ከገቡ የተሰበሩ ሁለቱን የህወሃት ሴራዎች እንይና ለዛሬ ይብቃን።ዙሩ ከሯል። ሃምሌ 10 እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ኤርትራ ገብተው ሃምሌ 20 የኤርትሪያውንን መረጃ ሙሉ በሙሉ ለኢትዮጵያ ሲያቀብል ለበርካታ ዓመታት የኖረ እና በኤርትሪያ የወያኔ ተቃዋሚ የነበሩ ሰዎችን እያደነ ሲገድልና ሲያስር የነበረ የመላዋ ኤርትሪያ የፀጥታ ኃላፊ በቁጥጥር ስራ ውሏል። ያኔ ከአሜሪካ የሄዱት አመራሮች ያለደህንነት ስጋት እንዲንቀሳቀሱ የወያኔ ቀኝ እጅ የነበረው የጸጥታ ሃላፊ መያዝ ፍንጭ ሰጥቶ ነበረ። አሁን ደሞ የተቃዋሚ ጦር ሰራዊት የት ህ ዴን መሪ በመሆን ለህወሃት ሲሰራ የነበረው ሞላ አስገዶም ተጋልጧል።ይህ እንግዲህ ብስሉ ከጥሬው ገና ከጅምሩ የተለየበት፤ ምርቱ ከ እንክርዳዱ በመጀመሪያው የውህደት ወንፊት የተጣራበት ወቅት ነው። በነዓምን የተጋበዝነውን ቃልሽ አይለወጥ እባክሽን የሚለውን የ ጥላሁን ገሰሰን ዘፈን ለሌሎቻችን እየጋበዝኩ ቃል የዕምነት ዕዳ ስለሆነ እንዳናጎድለው አሳስባለው።ቃል ብናጥፍ ግን የሚጎልብን ራሳችን ላይ መሆኑን ግልጽ ነው። ታጋይ እንጂ ትግል አይሞትም
No comments:
Post a Comment