እየተቃወሙ ለመኖር…!
August 9, 2015
ይገረም አለሙ
የአርበኞች ግንቦት 7 ቃልን ወደ ተግባር የማሸጋገር እንቅስቅሴ ያሸበረው ወያኔን ብቻ አለመሆኑን ከተቃውሞው ጎራ ከሚሰማው የተቀዋሚ ተቀዋሚዎች ጩኸት እያየን ነው፡፡ ርጥቡ ሬሳ ደረቅ ያስነሳ አንዲሉ ይህ ሰሞነኛ ጩኸት የተረሳ እንዲታወስ የተተወ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኖ የአንዳንዶቹ ጯሂዎች የትናንት ማንነት ድብቅ ዓላማና ፍላጎት ጭምር ጸሀይ እንዲሞቀው እየተደረገ ነው፡፡ የማለባባስ አጉል ባህላችንን ተራምደው የይሉኝታ ገመዳችንን በጥሰው ስም እየጠቀሱ መረጃና ማስረጃ እያጠቀሱ አካፋን አካፋ ለማለት ለደፈሩ ወገኖቼ ያለኝን አክብሮት እገልጻለሁ፡፡ እያለባበስን አርባ አመት አልቅሰናልና በቃ ማለት ይኖርብናል፡፡
አደባባይ ወጥተው የሚጮኹትም ሆኑ ከኋላ ሆነው የሚገፉት የየግል ፍላጎታቸውም ሆነ አንድ የሚያደርጋቸው ምክንያት ምንነትና አንዴትነት በተለያዩ ሰዎች ተጽፋል፡፡ እውነት ናቸውና መስማማቴን እየገለጽሁ ያልተገለጸ የመሰለኝን ልጨምር፡
ስማቸው ብዙ ነው (ፖለቲከኛ ፣ጋዜጠኛ፣ነጻ ማህበር፣ወዘተ) መገኛቸው ሀገር ውስጥም ውጪም ነው፤ዓላማቸው ቢችሉ ምን-ይልክ ቤተ መንግሥት መታየት ካልሆነም በተቀዋሚነት ካባ አንድም ክብር ሁለትም ብር እያገኙ መኖር ነው፡፡ ተባብሮ መስራት አይሆንላቸውም፡ እነርሱ የሚመሩት ወይንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋወዋሪ የሚቆጣጠሩት ካልሆነ በስተቀር ማናቸውም ትግል (ሰላማዊውም የጠብ-መንጃውም) አንድ ርምጃ ሲራመድ ማየት አይፈልጉም፡፡
ሲያልሙት የኖሩትን ሥልጣን ለማግኘት የሚቻለው ደግሞ አንድም በምርጫ አንድም በጡንቻ ነው፡፡እነርሱ በሁለቱም መንገድ ለመሄድ አይችሉም፡፡(አንዳንዶቹ ሁሉን ሞክረው የከሸፈባቸው ናቸው፡፡) የምርጫው ነገር እንኳን ለእነርሱ ፓርቲ መስርተው በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው መቀመጫቸውን ሀገር ቤት አድርገው ለሚፍጨረጨሩትም አልተሳካም፡፡ ሀገር ቤት በሚገኙ ተቀዋሚዎች ተከልለው ያደረጉት ሙከራም አልተሳካም፡፡ ( የኢትዮጵያ ዴሞክራሲዊ ኃይሎች ህብረት ይጠቀሳል) የጡንቻውን መንገድ ቢያልሙትም አልሆነላቸውም፤ አይሆንላቸውም፡፡ ከሌሎች ጋር ተባብረው በተቀዋሚነት ተከብረው ለመኖር፤ ከተቻለም ተከልለውም ቢሆን ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ለመድረስ መከጀላቸው ባይቀርም መሪነቱን እነርሱ ካልያዙት ወይንም እንቅስቃሴው በቀዳሚነት የእነርሱን ዓላማና ፍላጎት የሚያሳካ ካልሆነ በጅ አይሉምና፡ በዚህም መንገድ ስንዝር መራመድ አልቻሉም፤አይችሉምም፡፡
ስለሆነም ያላቸው ምርጫ ላለፉት ሀያ አመታት ሲተገብሩትም ያየነው ተቀዋሚ እየተባሉ መኖር ነውና በሰላማዊ ትግል በተአምር፣ ወይንም በተቃራኒው መንገድ በጦር የወያኔ ሥልጣን ቢቀየር ይህን ስለማያገኙ ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ ሲጀመር ፈጥነው ይዘምቱበታል፡መገንባቱን ሳይሆን ማፍረሱን፣ ማቀራረቡን ሳይሆን ማለያየቱን፤ መደገፉን ሳይሆን ማደናቀፉን የተካኑበት ናቸውና እስካሁን በአብዛኛው ተሳክቶላቸዋል፡፡ ዛሬ ግን ተነቅቶባቸዋልና ድብቅ ማንነታቸውን ያጋልጡ፣ ቀሪ ህይወታቸውን ያበላሹ ለልጆቻቸው መጥፎ ስም ያቆዩ እንደሁ አንጂ የሚሳካላቸው አይመስለኝም፡፡
ፊሺካው ተነፍቷል ጦርነቱ ተጀምሯል በተባለበት ማግስት በፍጥነት ተጠራርተው ከጀመሩት ጫጫታ ውስጥ አንዳችም መፍትሄ ጠቋሚ ሀሳብ አለመኖሩ ከመነሻው በተቃውሞው ሰፈር ይገኙ እንጂ ለውጥ ናፋቂ ሳይሆኑ ወሬ አሟሟቂ፤ የተግባር ሳይሆን የምላስና የብዕር ታጋዮች መሆናቸውን የመሰከረ ነው፡፡ ትናትም ሆነ ዛሬ ሰላማዊውንም ሆነ የጠብ-መንጃውን ትግል የሚቃወሙት ተቀዋሚ እየተባሉ ሆነው ሳይሆን እያስመሰሉ፣ እየታገሉ ሳይሆን እያውደለደሉ ክብርም ብርም የሚያገኙበት ሜዳ እንዳያጡ በመስጋት ነው፡፡ ግን ለምን? እነርሱ በተቃዋሚነት እንዲኖሩ የወያኔ እድሜ መርዘም አለበት? የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንባ ገነን አገዛዝ ውስጥ መኖር አለበት ?ከእነርሱ ፍላጎትና ከሀገር ነጻነት የቱ ይበልጣል?፤የቱ ይቀድማል፡? በእውነቱ አሳፋሪም በታሪክና በትውልድ የሚያስጠይቅም እኩይ ተግባር ነው፡፡
ይህ አድራጎት ዛሬ የተጀመረ አይደለም፤ እንደውም ከአንዳንዶቹ ጋር አብሮ ያረጀ ነው፤ ትንሽ የቅርብ ግዜ ማሳያዎችን አንመልከት፡
ማሳያ አንድ፤ በ1992 ዓም ኢዴፓ የሚባል ፓርቲ ተመስርቶ በአጭር ግዜ ሰፊ እንቅስቃሴ አደረገና እውቅና አገኘ፤ በዚህ መልኩ እየገነነ ከቀጠለ በግልም ሆነ በድርጅት እስከመኖራቸውም እንዳይረሱ የሰጉት እነዚህ የወያኔም የተቀዋሚውም ተቀዋሚዎች የለመዱትንና የተካኑበትን የማደናቀፍ ዘመቻቸውን ከፈቱበት፤ የፓርቲው አመራሮች ቢቸግራቸው በእነዚህ ሰዎች በተወጠነውና በምድረ አሜሪካ በተዘጋጀ ጉባኤ ተካፋይ ሆነው የኢዴኃህ አባል ሆኑ፡፡ ሊቀመንበሩ ዶ/ር አድማሱ ገበየሁ የህብረቱ ዋና ጸኃፊ ለመሆን ቢበቁም ከመነሻው የተገባው በእምነት ሳይሆን የሰዎቹን አፍራሽ ዘመቻ በመፍራት ነበርና ብዙም ሳይቆይ ፓርቲው ከህብረቱ ወጣ፣ መኢአድ ለጉባኤ የላካቸው አባላቱ ሀገር ቤት ሳይመለሱ ነበር ጉባኤው በእነዚህ ሰዎች ሴራ መጠለፉን ገልጾ የጉባኤውን ሂደት በመቃወም ጥያቄ አቅርቦ፤ጥያቄው ካልተመለሰ እንደማይቀጥል ያስታወቀው፡፡ ኢዴኃህም የቡና ውሀ ሆነ፡፡ (በምርጫ 97 የሰሩትም የሚረሳ አይደለም፡፡)
ማሳያ ሁለት፤ ቅንጅት ሲመሰረት መሪነቱን እንያዝ እንዳይሉ ከመስፈርቱ አንዱ በሀገር ቤት ያሉ የሚል በመሆኑ፣ እነርሱ ደግሞ አብዛኛዎቹ ከሀገር ውጪ ስለሚኖሩና ሀገር ቤት ፓርቲ ስለሌላቸው አልተቻላቸውም፤ በእጅ አዙር አንዳይቆጣ ጠሩት ከቅንጅት የወቅቱ ጥንካሬ አንጻር ለዛ የሚያበቃ አቅም አልነበራቸውም፡፡ እናም በሚያውቁት በለመዱትና በተካኑበት ስልትና መንገድ ብዙ ዘመቱበት፤ ወዳጅ መስለው በመቅረብ መጥፎ እየመከሩ አቅጣጫ ለማሳት፣ በአመራሩ መካከል መጠራጠር ለመፍጠር ብሎም ቅንጅትን ከመረጠው ሕዝብ ለማጣላት ከውጪም በሀገር ውስጥም በመልእክተኞቻቸው በኩል ብዙ ሰርተዋል፡፡ የቅንጅት አመራሮች ለፓርላማ ሳይሆን ለወህኒ ሲዳረጉም ተደስተዋል፡፡
ማሳያ ሶስት፤ የቅንጅት አመራሮች ከእስር ከወጡ በኋላ የፈጠሩት አለመግባባት እስከ መለያየት እንዲያደርሳቸው ከሁለቱም ወገን ደጋፊ መስለው በመሰለፍ የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል አይነት የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በወቅቱ በዌብ ሳይቶች በጋዜጦችና በማህበራዊ ድረ-ገጾች ወዘተ ላይ የተጻፉትን ማየት በየፓልቶኩ በያራዲዮው የተነገሩትን ማደመጥ በቂ ነው፡፡
ማሳያ አራት፤ የቅንጅት ከፊሉ ወገን ተሰባስቦ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ሊቀመንበሩ አድርጎ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ የተሰኘ ፓርቲ መስርቶ በአጭር ግዜ በሀገር ውስጥም ሆነ አውሮፓና አሜሪካ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተበለጥን ሰይጣናዊ ስሜታቸው አገርሽቶ የከፈቱት ዘመቻም የሚረሳ አይመስለኝም፡፡(በአብዛኛው የሚዘምቱት ሀገራዊ ድርጅት ላይ ነው)
አንድነት የቅንጅት ወራሽ መሆኑና ( ቅንጅት የሚለው ስምና ሁለት ጣት ምልክት ወያኔዎችን ያባንናቸዋል)ከጅምሩ ያገኘው ተቀባይነት ያሰጋው ወያኔ ወ/ት ብርቱካንን ዳግም ሲያስር ለእነዚህ ሰዎች ፌሽታ ነበር፡፡አጋጣሚውን በመጠቀምም ቀሪዎቹን አመራሮች ከቅርብም ከሩቅም ወዳጅ መስለው በመቅረብ በምክርም በገንዘብም በሌላ ሌላውም ከወዲያ ወዲህ እያላጉ የት ይደርሳል የተባለውን አንድነት ሽባ አደረጉት፡፡ የእነርሱም የወያኔም ሴራ ተደማምሮ አንድነት አምስት አመት ሙሉ ታሞ በምርጫ 2007 ዋዜማ ግብአተ መሬቱ ተፈጸመ፡፡ እናቃብራችሁ አንኳን አላሉም፡፡
ማሳያ አምስት፤ ሰማያዊ – ይህኛውም ፓርቲ በ2004 ዓም ተመስርቶ በአጭር ግዜ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ለስድስት አመት የተዘጋን የሰላማዊ ሰልፍ ክልከላ በር አስከፈተ ተብሎ ስሙ ሲናኝ የሌላው መግነን የእኛን መኮስመን ያስከትላል የሚል ከይሲ አስተሳሰብ ያላቸው እነዚህ ወገኖች ዘመቻ የጀመሩት ከመቅጽበት ነው፡፡
ይሉት ቢያጡ ሰበብ ቢቸግራቸው ከሌሎች ጋር ተባብሮ መስራት አለበት ብቻውን የትም አይደርስም አሉ፡፡ አልተሳካላቸውም እንጂ ይህን ሰበብ አድርገው በፓርቲው ውስጥ ክፍፍል እስከመፍጠር ደርሰውም እንደነበር ይታወቃል፡፡ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል፡፡አንድ ፓርቲ ጠንክሮ እንዳይወጣ ወይንም ፓርቲዎች ተባብረው በግንባርም ይሁን በውህደት ጠንክረው እንዳይታገሉ ካደረጉዋቸው ምክንያቶች አንዱ የእነዚህ ወገኖች ሴራ ነው፡፤
እነሆ አሁን ደግሞ የተለመደውንና መታወቂያቸው የሆነውን አፍራሽ ተግባር ጀመሩ፡፡ የኢሳይያስ ማንነትና የሻዕቢያ ምንነት የታያቸው ዛሬ ነው ? ጅብን ሲወጉ በአህያ ተከልሎ እንደሚባለው ይህ ሰበብ ነው፡፡ ዋና አላማው ኢሳይያስንና ሻዕቢያን ከለላ አድርጎ በነጻነት ትግሉና ታጋዮቹ ላይ መዝመት ነው፡፡
ተቃውሞአቸው ምንድን ነው፡፡
ተቃውሞአቸው ምንድን ነው፡፡
የሚያነሱት ነገር ለክርክር እንዳይቀርብ ለመለስ ምትም አንዳይመች ተቃውሞአቸው ስልታዊ መንገዳቸው የጎንዮሽ ነው፡፡የሚደግፉትም ሆነ የሚቃወሙት ነገር በግልጽ አይታወቅም፤ ዛሬ ያመሰገኑትን ነገ ይኮንኑታል፤ባከበሩ ማግስት ያዋርዳሉ፤ የእነርሱ የሆነ ሁሉ ቅዱስ በተቃራኒ የቆመ ወይም ለእነርሱ ያልተመቸ ሁሉ ርኩስ ነው፡፡ እነርሱ ሞክረውት አላስኬድ ባላቸው መንገድ ሌሎች መሄድ ከቻሉ በቅናት ያራሉ፡ እነርሱ ሊወዳጁት ያልቻሉትን ሰው ወይንም ድርጅት ሌሎች መወዳጀት ከቻሉ የውግዘት ናዳ ያወረዳሉ፤ እነርሱ ሞክረውት ያቃታቸውን ሌሎች ለማሳካት ከጀመሩ የማጥላላት ጥሩንባ ይነፋሉ፤ በታላቁ መጽኃፍ ትንቢተ ኢሳይያስ ም፣48 ቁ.22 ላይ “ክፉዎች ሰላም የላቸውም” ተብሎ እንደተጻፈው በክፋታቸው ለራሳቸው ሰላም አጥተው ሌላውንም ሰላም ያሳጣሉ፡፡
የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ተብሎ አንዳይተው፣ ዓላማችን ላሉት ስኬት አስበው ወቅት ጠብቀው የሚሰሩ መሆናቸውን አይተናል እያየንም ነው ፡፡ የተለመደ ተግባራቸው ነው ተብሎ ተንቆ አንዳይተው ብእራቸውም ሆነ ምላሳቸው የሚረጨው መርዝ ለትግሉ ውጤታማነት ሆነ ከድል በኋላ ለሚፈለገው መረጋጋት ብሎም ለኢትዮጵያውን አንድነት ጠንቅ ነው፡፡ መፍትሄው አላማችሁ ገብቶናል በቃችሁ ማለት መቻል ነው፡፡ይሄ ካልበገራቸውም ማንነታቸውን ጸሀይ ማሞቅ፡፡
No comments:
Post a Comment