መግቢያ
ይህ ፅሁፍ ስለአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ምንነትና አመጣጥ እንዲሁም ባለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕልውናና እድገት ላይ ያሳደረውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህላዊ ተጽእኖ ይዳስሳል። በማጠቃለያውም ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ያለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በአንድነት እንዲወጡ ይጠይቃል። ጠለቅ ያለ ምርመራ ማድረግ ለሚፈልጉ በማጣቀሻዎች ሥር ያሰፈርኳቸውን መፃሕፍትና ድረገጾች መመርመር ጠቃሚ ነው።
ካርል ማርክስ፣ ቭላድሚር ሌኒን እና የ”ሠራተኛው መደብ (ፕሮሌታሪያት)” አምባገነናዊ መንግሥት አመሠራረት
በ1917 ዓ. ም. እ.አ.አ. በቭላድሚር ሌኒን የሚመራው የሩሲያ ኮሚኒስት ፓርቲ (ቦልሼቪኮች) በጥቅምቱ አብዮት (ኦክቶበር ሬቮሉሽን) የሩሲያውን ዳግማዊ ኒኮላስን መንግሥት ከሥልጣን በማውረድ “የሠራተኛውን (ፕሮሌታርያት) መንግሥት” መሠረተ። ሶቪየት ሕብረትም ተፈጠረች። በጊዘው በቦልሼቪኮች የተመራው አብዮት“ሠራተኛውን መደብ ወይም ፕሮሌታሪያቱን” ሥልጣን ላይ ቢያመጣም የሩስያው ሠራተኛ (ፕሮሌታርያት)ብዛት፣ ጥንካሬና የንቃት ጥልቀት እንደሌሎቹ ካፒታሊዝም የጎለመሰበት የአውሮፓ ኡገሮች ሠራተኞች ስላልነበረ በሌኒን የሚመራው የሩሲያ ኮሚኒስት ፓርቲ የሠራተኛው መደብ ፊታውራሪ (Vanguard of the proletariat) ሆኖ የሠራተኛውን ጥቅም እንዲያስጠብቅ ሞግዚት ሆኖ ራሱን ሾመ። ምንም እንኳን በ1840ዎቹ የሠራተኛውን አምባገነናዊነት ፅንሰ-ሀሳብ የቋጨው ካርል ማርክስ፣ ማንኛውም በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት አምባገነን ስለሚሆን ፕሮሌታርያቱም ሥልጣን ከያዘ የሠራተኛው አምባገነንነት (Proletariat Dictatorship) ይፈጥራል ብሎ ነበር። ሆኖም በሩስያው የጥቅምት 1917 አብዮት አምባገነንነቱ የፕሮሌታርያቱ መደብ መሆኑ ቀርቶ የፊታውራሪው ሞግዚት የኮሚኒስት ፓርቲው ተቆናጠጠ። ከአብዮቱ በፊት በኮሙኒስት ፓርቲ ምሥረታ ወቅት አንዱ ውይይት የነበረው ሩሲያ ገና ከፊውዳል ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ስላልተላቀቀችና ሩስያ ውስጥ ጠንካራና ብቁ ፕሮሌታርያት ባለመኖሩ ማርክሳዊ ርእዮተአለምን ሙሉ በሙሉ መተግበር አይቻልም በሚለው ሃሳብ ዙርያ ነበር። የነሌኒን ውሳኔውም በሩሲያ ውስጥ በቅድሚያ የፕሮሌታሪያቱን አምባገነናዊ ሥርዓት በመመሥረት አብዮቱ በሁለት ደረጃዎች ተካሂዶ ወደ ኮሚኒዝም መሸጋገር አለበት የሚል መርሆ ተከተሉ። ለዚህም የሚሆን የተለየ ድርጅት መመሥረት እንዳለበትና ይህም ድርጅት “የሠራተኛውና የጭሰኛው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አምባገነንነት” እንዲሆን ተደነገገ። በዚህ ፅንሰ ሃሳብ፣ ፓርቲው በማዕከላዊ ቁጥጥር የጠነከረ እንዲሆንና አመራሩም በርዕዮተ አለሙ ባመኑ አብዮተኞች ብቻ እንዲሆን ተወሰነ። እነዚህም አብዮተኞች በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተደራጅተው መዋቅሮች ዘርግተው በገበሬውና በፋብሪካ ሰራተኞች ውስጥ ሰርገው በመግባት ትግሉን ይመራሉ ብሎ በማሰብ ነበር። ይህም ሥርዓት የሠራተኛውን (ፕሮሌታሪያቱን) የሥልጣን በላይነት አስጠብቆ ወደኮሚኒስት ሥርዓት ለመሸጋገር ያዘጋጀዋል ተብሎ ታምኖበት ነበር። ሌኒንና የኮሚኒስት ፓርቲው ጨቅላው የሠራተኛው መደብ በተደራጁ የቀድሞው መንግሥትና ፀረ-አብዮተኞች (አድሃርያን) በቀላሉ ሊገለበጥ ይችላል የሚል ፍርሃት ነበራቸው።
ከምሥረታውም ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ዴሞክራሲን ለሁሉም ሕብረተሰብ ያለአድሎ ለመተግበር ሳይሆን በሥልጣን ላይ ላለው ድርጅት አምባገነናዊ አገዛዝን ለማመቻቸት ነው። በተጨማሪም በፓርቲው ውስጥም ሆነ በፓርቲው ሥር ባሉ ድርጅቶች ውስጥ ነጻ የሆነና የተለያዩ ወይም የሚቃረኗቸው ሐሳቦች መወያየት ፓርቲውን ይከፋፍለዋል የሚል እምነት ስለነበረ የፓርቲውን የበላይነት ለመጠበቅ ሲባል ተቃራኒ ሃሳቦችንና ተቃዋሚ አንጃዎችን አይፈቅዱም።
በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት(አምባገነንነት) ሥር የፖሊቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሚሊታሪ መዋቅሮች ተጠያቂነታቸው ለገዥው ፓርቲ ወይም መሪ ነው። በዚህ ሥርዓት ውስጥ የገዢ ፓርቲው ወይም መሪው እነዚህን መዋቅሮች የራሱን አምባገነንነት እና ህልውና ለማረጋገጥ እንደፈቀደው የማዘዝና በተቃወሙትም ላይ ሽብር መፍጠር እንደተገቢና እንደመብቱ ይቆጥረዋል። ሌሎችንም በሥሩ የፈጠራቸውን መዋቅሮች እንደዚሁ ርእዮተ ዓለሙንና የፖለቲካ መስመሩን ለማስከበርና ተቃዋሚዎችን ለመጨቆን ይጠቀምባቸዋል። በእውነተኛ ዴሞክራሲ ላይ የተመሰረተ ሥርዓት የህዝቡን ሰብዓዊ መብቶች ልዑላዊነት ሲያረጋግጥ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ ያለምንም ተፅዕኖ ሃሳብን መግለፅን፣ በፈለጉበት እንዲኖሩ፣ ተወካዮቻቸውን ያለመንግሥት ተፅዕኖ እንዲመርጡ ሲያከብርና ሲጠብቅ በማዕከላዊነት ላይ የተመሠረተው “ዴሞክራሲ” ደግሞ የገዢው መንግሥት ፍፁማዊ አገዛዝ ያስከብራል።
ቀዝቃዛው ጦርነት፣ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እና የቅኝ ሐገራት ነፃነት እንቅስቃሴ
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድምደማ በኋላ በሶቪየት ሕብረት የሚመሩ የሶሻሊስት ሐገሮች በአንድ ወገን፤ በአሜሪካ መሪነት የተሰማራው የምዕራቡ የካፒታሊስት ሐገሮች ደግሞ በሌላው ወገን በመሆን እስከ 1990ዎቹ የቆየ የቀዝቃዛው ጦርነት (cold war) ያካሄዱ ነበር። በዚህም ጦርነት ጊዜ ሶቪየት ሕብረት የምስራቅ ብሎክ (Eastern Bloc) ወይም የኮሚኒስት ብሎክ የሚባል ቡደን ፈጥረው የዴሞክራቲክ ሶሻሊዝም ንቅናቄዎችን ለማስፋፋትና ኮሚኒዝምን የዓለም ሥርዓት ለማድረግ (ስለዚህም ኢምፔሪያሊዝምን ለማጥፋት) ራዕያቸውን ሲተገብሩ በአሜሪካ የሚመራው የካፒታሊስት ሐገሮች ቡድን ደግሞ የምዕራብ ብሎክ (Western Bloc) ተብሎ የሶቪዬት መስፋፋት ለመግታት ተሰልፈው ነበር። ሁለቱም ኃያላን ቡድኖች በዚሁ ጊዜ ዘመናዊ የጦር መሳርያ መገንቢያና ማከማቻ፤ የጦር ሰራዊታቸው ማሰልጠኛና ማጠንከሪያ፤ የፕሮፓጋንዳና የስለላ ጦርነት ማካሄጃ አደረጉት። ሁለቱም ጎኖች ለሚደግፉት ሃገር ወይም ተዋጊ ግንባር ገንዘብ በመስጠትና መሳርያ በማስታጠቅ ጦርነታቸውን በወኪል ተዋጊዎች (Proxy Warriors) ማድረጉን መረጡ።
በዚሁ የቀዝቃዛ ጦርነት ወቅት ብዙዎች በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የአፍሪካ፣ የእስያና የደቡብ አሜሪካ ሐገሮች የነፃነት ትግል ሲያካሂዱ ርዳታ ያገኙት ከሶቪዬት ሕብረት ነበርና ከነፃነት በኋላ ብዙዎቹም የሶቪየት ሕብረትን ፈለግ በመከተል አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሶሻሊዝም በመገንባት ላይ ተሰማሩ። አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሶሻሊዝም የፖለቲካ ኃይል በጥቂቶች እጅ አከማችቶ በማዕከላዊነት ላይ የተመሰረተ አምባገነናዊ አገዛዝን አሰፈነ። እነዚህም ሐገሮች ከአፍሪቃ አንጎላን፣ ዚምባብዌን፣ ሞዛምቢክን፣ ሳኦ ቶሜ ፕሪንሲፕ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ናሚቢያ፣ ጊኒ ቢሳዎና የመሳሰሉትን ሲጨምር፤ ከደቡብ አሜሪካ ኩባ፣ ኒካራጉዋ፣ ግሬናዳና የመሳሰሉት ሆነው፤ ከእስያ ደግሞ ኢንዶቻይና የመሳሰሉት ነበሩ። ቻይናም በኮሚኒስት ፓርቲው በኩል የሯሳን ማኦይስት ሞዴል መሥርታ እነኮሪያ፣ ቬትናም፣ አልባኒያና የመሳሰሉትን ከኋላዋ አስከተለች።
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አፈጣጠር የአንድን ድርጅት የበላይነት ለማረጋገጥ ነው።
ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በደርግ ዘመን
ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ የአፍሪቃ ሐገሮች በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ሥር ባትወድቅም ብዙ የአውሮፓ መንግሥታት ቅኝ ሊያደርጓት ብዙ ሞክረዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጣሊያን ከሐገራችን ተባርሮ የመልሶ ግንባታው ሲጀመር የኢኮኖሚ አርዳታና የመከላከያ ኃሎቿን መገንቢያ ከምዕራብ ሐገሮች ስታገኝ ቆይታ ከ1966 አብዮት በኋላ ሥልጣን የተቆናጠጠው “ጊዜያዊ” ወታደራዊ መንግሥት በማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ርዕዮተ ዓለም በመጠመቁ ከምዕራብ ፊቱን ወደሶቪዬት ሕብረት አዞረ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሁሉም የእርዳታና መሳርያ ምንጩ የምስራቁ ብሎክ ሆነ፣ አገዛዙም እንደዚሁ። ውጤቱም ሐገሪቷ በወታደርዊ አምባገነንነትና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማጥ ውስጥ ለ17 ዓመታት ማቀቀች። ይህም የ17 ዓመታት አባዜ ሐገሪቷን በሁሉም ዘርፍ አድክሟት ለሕወሐት ሰለባ ዳረጋት። የተገላቢጦሽ ደግሞ የሕወሐት አማካሪ፣ ደጋፊና መሳሪያ አቀባይ የምዕራቡ ብሎክ ሐገሮች፣ በተለይም አሜሪካ ሆነች። ከደደቢት ጀምረው አዲስ አበባ እስከገቡ ድረስ በአሜሪካው የስለላ ድርጅት እንክብካቤነት አድገው የደቀቀች ኢትዮጵያን ወረሩ ።
አምባገነናዊ ማዕከልነት በሕወሐት-ኢሕአዴግ እጅ እያደረሰ ያለውን ሰቆቃ እያየን ነው። የሕወሐት-ኢሕአዴግ ስንኩል ሕገመንግሥትም በሕዝብ ፊት “ሕጋዊነትን” እንዲያገኝ ይህንኑ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አምባገነንነት መሥርቶ ላለፉት 27 ዓመታት ሕዝቡን የመከፋፈያና የራሱን ሕይወት ማራዘሚያ አድርጎታል። በነዚህ ዓመታት የሠራተኛውም ሆነ የገበሬው መደብ ሥልጣን መያዝ ቀርቶ ስማቸውም አይጠቀስም። ለሰብዓዊ መብት ታጋዩ ፕሮፈሰር አለማየሁ ገብረማርያም ይህንኑ የሕወሐት አምባገነንነት “… a thugocracy privatelymanaged and operated for theexclusive benefit of bloodthirsty thugtators.” (6) ብሎ ሰይሞታል።
ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት :- የሕወሐት-ኢሕአዴግ ቆርጦ ቀጥል ሥርዓት
የሕወሐት-ኢሕአዴግም መንግሥት የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን አገዛዝ የሚደግፉትን መሾሚያ፣ የሚቃወሙትን መደፍጠጫ፣ ሕዝቡን በዘርና በጎሳ መከፋፈያ መሳሪያ አድርጎታል። በሥሩም የተፈጠሩት የተለያዩ ድርጅቶች የሕወሐት-ኢሕአዴግ አምባገነናዊነት ምሰሶ ከመሆን ሌላ እውነተኛ ዴሞክራሲን የሚያሳድጉ ተቋሞች መሆን አይችሉም። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊት ኢ-ዴምክራሲያዊ ስለሆነ የመድብለ ፓርቲንና ሁሉን የሕብረተሰብ ክፍሎች የያዘ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በተግባር አይቀበልም። ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈፃሚው አንድ ሲሆን የሚያገለግለውም በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ነው። ሕጉንም የሕወሐት-ኢሕአዴግ መንግሥት አንዳመቸው ሲለውጠውና አዲስ ሕግም ሲደነግግ ነበር። በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እነዚህ ሦስት አውታሮች አብሮ መሥራት ብቻ ሳይሆን እርስበርስ በመቆጣጠር የአገሪቷን ሕጋዊ ጉዳዮች ያካሂዳሉ። በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሦስቱም አውታሮች እንደአሻንጉሊት ክሮች የሚስበው የሕወሐት-ኢሕአዴግ መንግሥት ነው። በተጨማሪም የተለያዩ የኢኮኖሚው አውታሮችን፣ ምክር ቤቱን፣ የደህንነት ጥበቃውን፣ የመከላከያ ሰራዊቱን እና የመሳሰሉትን ለራሱና ለደጋፊዎቹ ጥቅም ያውላል።
ዶክተር መረራ ጉዲና “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ሕልሞች – የኢህአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ” በተሰየመው መጽሐፋቸው ውስጥ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የፈጠራቸውን (ያስከተላቸውን) ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ለልማት ብልፅግና አንቅፋት የሆኑትን አሥር ነጥቦችን በትክክል አስፍረዋል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ ነጥብ “… የኢህአዴጉ ‘አብዮታዊ ደሞክራሲ’ ከሁሉም በላይ መንግሥትንና የመንግሥት ተቋማትን የአንድ ፓርቲ የግል ሃብት የሚያደርግና የመንግሥት ተቋማት ዋና ሥራቸው መሪዎችን ሥልጣን ላይ ለማቆየትና በሕግ የሚታወቀውን መንግሥትን ተክቶ የሚሠራ መንግሥት መፍጠሩ ነው። የዚህ ሁሉ ችግሮች እናት ሁሉ….. ደግሞ ከኢህአዴግ ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ’ የሚመነጨው የአንድ ፓርቲ የበላይነት (hegemony) ሕልም ነው።”(1)
ሕወሐት ለራሱ አመቻችቶ የፈጠረውን ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊ አምባገነንነት የ1968ቱን ማኒፌስቶ እቅድ ከግብ ለማድረስ እየተጠቀመበት ነው። ኢትዮጵያን በዘር ከከፋፈሏትና የሕዝቡንም አንድነት ካዳከሙት የሕወሀት-ኢሕአዴግ ተግባሮች ጥቂቶቹን ከዚህ በታች ቀርፌ አቅርቤአለሁ።
አንደኛ – ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በመጠቀም እንደ ደቡብ አፍሪቃው አፓርታይድ ሥርዓት ሕዝቡን በጎሳ፤ በቋንቋ፤ በክልል ከፋፍለው በማዳከም፤ የጨቋኝና ተጨቋኝ ብሔሮች ግንኙነት ፈጥረው የሐገሪቷን አንድነት አቃወሱት። ይህም ሕወሐት የራሱን ክልል ለማልማትና ሌሎቹ፣ በተለይም አማራውና ኦሮሞው፣ ኦሮሞውና ሱማሌው፣ ደቡቦችም እርስበርስና ከጎረቤቶቻቸው ደም አንዲፋሰሱ በማድረግ ብዙ ችግሮችን ፈጥረዋል። በሕወሐት-ኢሕአዴግ የተፋፋመው የዘር ክፍፍል ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ህመም መሆኑ እንደማይቀር አይጠረጠርም።
ሁለተኛ – የሥርዓቱን የብዝበዛና የሌብነት መርበብ ዘርግተው የሐገሪቷን ሐብት ለግላቸውና ለደጋፊዎቻቸው መበልፀጊያ አድርገው የኢትዮጵያን ሕዝብ በኢኮኖሚያዊ ገደል አፋፍ ተንጠልጥሎ እንዲሰቃይ አደረጉት። ያለገደብ አንዲያድጉና እንዲዘርፉ የተለቀቁት እንደ ሜቴክ፣ ኤፈርት፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽንና የሌሎችም ትላልቅ ኩባንያዎች የዝርፊያ መናኸሪያዎች ሆነው የባለሥልጣናትን፣ የዘመዶቻቸውንና የአጎብዳጆቻቸውን የውስጥና የውጭ ባንኮች አካውንቶች አንዲሞሉና የቅምጥል ኑሮ እንዲኖሩ አድርገዋል።
ሦስተኛ – ከማዕከላዊ መንግሥት ውጭ ለመሥራት የሞከሩ፣ ሥርዓቱን በተቃወሙ፣ አረመኔያዊ ተግባራቸውን ለዓለም ለማጋለጥ የታገሉት ጦማሮችን፣ ዓይን ባወጣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሽብርተኝነት ወንጀል ሰብስበው በየእሥር ቤት ከተቱ፤ ገረፉ፤ ሰለቡ፤ አሰደዱ፤ ገደሉ። ይህንንም ግፍ ሲፈፅሙ በአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅና በፀረ-ሽብር ሕግ ጥላ ሥር ተደብቀው ነው። የሕወሐት ፀረ ሽብር ሕግ በ1967 ዓ. ም. ከታወጀው የደቡብ አፍሪቃው ፀረ ሽብር ሕግ ጋር ተመሳሳይ ነው። የፕሪቶሪያው ዘረኛ መንግሥት እነዊኒ ማንዴላንና ሌሎችንም አፓርታይድን የሚዋጉ አካሎች በዚህ ሕግ ተጠቅመው ነበር ሲያስሯቸው፣ ሲገርፏቸውና ሲገድሏቸው የነበረው።(2)
አራተኛ – ሕወሐት-ኢሕአዴግ በወታደራዊ ትጥቅ፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና፣ በምክር ርዳታ ሰጥተው ለሥልጣን ያበቋቸውን የምዕራብ ሃገሮችን ለማስደሰት ሲሉ የነፃ ገበያን (free market) ከዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊ አምባገነንነት ጋር አዳቅለው መላቅጡ የጠፋበት የኢኮኖሚ መዋቅር ፈጠሩ። በኢትዮጵያ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ከነፃ ገበያ ጋር ለማደባለቅ መሞከር አምባገነኖች ጡንቻ ለማጠንከርና ከላይ በተጠቀሱት የመንግሥት ሞኖፖሊዎች መበዝበዝን መርዳትና ሌላውን የግል ነጋዴዎችን እንዳይንሰራፉ ለማድረግ ነው። ያልተገደበ ዴሞክራሲያዊ ነፃነት (የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ እንደልብ የመንቀሳቀስና በንግድ ሥራ መሠማራት) በሌለበት ሁኔታ ከራሱ አምባገነናዊ ጥቅም ውጭ የማይፈቅድን ሥርዓት ነፃ ገበያን በተግባር ላይ ሊያውል አይችልም(1,5)።
አምስተኛ – የምርጫ ቦርዱን እንደራሳቸው መሳርያ በመጠቀም የምርጫ ውጤቶችን በማስለወጥ ሲሸነፉ በማጭበርበር አሸናፊ ሆኖ መቅረብ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትን በማሰርና በመግደል እውነተኛና አድልዎ የሌለበት ምርጫ እንዳይካሄድ አድርገዋል። ይህም የማጭበርበሪያ የምርጫ ቦርድ በነሱ ቁጥጥር ሥር ሆኖ የነሱ ዕድሜ ማርዘሚያ አንጂ ገለልተኛና አድልዎ የሌለበት ምርጫን ለማስተግበር አልነበረም። በዶክተር መረራ አገላለጽ የምርጫው ቦርድ ለሕወሃት ሥልጣን ላይ መቆያ ከሆኑት ሁለት ምርኩዞች አንዱ ሆኖ ቆይቷል። ሁለተኛው ምርኩዝ የጠመንጃ አፈሙዝ ነው።
ስድስተኛ – በካድሬዎቻቸውና በስለላ መርበቦቻቸው በሰፈርና በቤተሰብ ውስጥ ጠልቀው በመግባትና ሕዝቡን ለረጅም ዘመናት ያስተሳሰረውን የባሕል “ድርና ማግ” በመበጣጠስ፤ የሕዝብን መሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች በመወንጀል ከሥልጣን አውርደው የራሳቸውን ካድሬዎችና ታማኞች በመትከል፤ ሕዝቡ እርስ በርሱ እንዳይተማመንና በጥርጣሬና በፍርሃት እንዲጠላላ አድርገውታል። ይህ ዓይነቱ የከፋፍለህ ግዛ ተንኮልና የራሳቸውን ጎሳ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የባህል ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን በመያዝ የበላይነትን እንዲያገኙ የማድረግና የሌላውን ሕዝብ በነዚሁ አውታሮች የበታች እንዲሆኑ በመጨቆን፣ ቀድሞ የነበረውን የሕብረተሰብ ክፍል በማባረር ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በመተካት ከፍተኛ የህብረተሰባዊ ምህንድስና (ሶሻል ኢንጂነሪንግ) በማከናወን ላይ ተሰማርተዋል። በዘርና በብሄር ለይቶ ሰውን የበላይነትና የበታችነት መፍጠር የባርያ ሥርዓት ባሕርይ ነው።
የለውጥ ጭላንጭል
ኢትዮጵያና ሕዝቧ ከ40 ዓመታት በላይ በፈጀ አምባገነናዊ አገዛዝ ሥር ተቆራምተው ብዙ መቶ ሺዎች ሕዝብ ካለቀ በኋላና ያንኑም ያህል በስደት ከተበታተነ በኋላ አሁን የለውጥ ጭላንጭል እየታየ ነው። ይህም የለውጥ ጭላንጭል ሊመጣ የቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ትግል በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት ወደማይመለስበት ደረጃ (critical juncture) ላይ በመድረሱና ምንም ዓይነት ጊዜያዊ አዋጅም ሆነ የጠመንጃ ጋጋታ ሊያቆመው አለመቻሉ ነው። ይህም ሕዝባዊ አመጽ የገዢውን ፓርቲ ከመሠረቱ አናግቶት የጠቅላይ ሚንስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝን በ”ፈቃደኝነት” ከሥልጣን መውረድን አፋጥኖ የዶክተር አብይ አሕመድን ወደሥልጣን መምጣት ጥርጊያ መንገድ ከፍቷል።
ክቡር ጠቅላይ ሚንስቴር ዶክተር አብይ አሕመድ ድርጅታቸው ቢወድም ባይወድም ያለፉትን የሕወሐት-ኢሕአዴግን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የመንግሥት ሽብርተኝነት አምኖ በግልፅ ጥፋቱን በመቀበል ራስን የማነፅና ሥሕተቶችን የማረም ጉዞ ጀምሯል። ይህ ሂደት በራሱ የኢትዮጵያን ሁኔታ ልዩ ያደርገዋል። አንድ አምባገነናዊ ገዢ ፓርቲ በምንም ዓይነት ሁኔታ ቀጥቅጦ ሲገዛው ለኖረው ሕዝብ እራሱን አጋልጦና ስህተቱን በግልፅ አምኖ ይቅርታ በመጠየቅና ለውጦች ለመተግበር የተነሳበት ሁኔታ በታሪክ ጥቂት ነው።
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢደገፍም ከራሱም ፓርቲ ውስጥ ተቃውሞ ደርሶበታል፤ በአደባባይ የግድያና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተደርገውበታል። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ይህንን ለውጥ ከግቡ ለማድረስ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። እሱና ደጋፊዎቹ ለለውጡ መቆማቸውን በወሰዱት እርምጃዎች አሳይተዋል፤ እያሳዩም ናቸው። በግፍ የታሰሩ ተቃዋሚዎችንና የሚዲያ ሰዎችን ፈተዋል፤ ሰብዓዊ መብትን የጣሱና የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሰቃዩትን ሰብስበው በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ጀምረዋል፤ የካቢኔና የአመራር ለውጥም እያካሄዱ ነው። ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ድርጅቶች እንዲመለሱና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረቱ ላይ እንዲሳተፉ በሩን ከፍተዋል፤ የሐገሪቷን የመከላከያ ኃይልም ከአንድ ፓርቲ አገዛዝ ለማላቀቅ አየሠሩ ነው፤ በሌብነት ሐገሪቷን ያራቆቱትንም እያሳደዱ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም ብዙ የሚያረኩ ድርጊቶችን አስመዝግበዋል። ከ18 ዓመታት በላይ የፈጀውን የኤርትርያና የኢትዮጵያን ፍጥጫ ወደሰላም አድርሰዋል።
በተቃራኒውም ጥቅማቸው የተነካባቸው የገዢው ፓርቲ ተጠቃሚዎችና ደጋፊዎቻቸው አንዲሁም ከሐገሪቷ ውጭ ሆነው ሃገሪቷን ሊበታትኑ የሚፈልጉ ድርጅቶች ለውጡን ለመቀልበስ ሌት ተቀን እየጣሩ ናቸው። ፀረ-አንድነት ወሬዎችን በአስመሳይ ሶሻል ሚድያ በመዝራት፤ ገንዘብና ትጥቅ በመስጠት ሐገሩን በዘርና በቋንቋ ለያይተው ለማጋደል እየሠሩ ናቸው። የሕወሐት አባላትና ሎሌዎቻቸውም የአብዮታዊ ዴሞክራሲና ሕገመንግስቱ ይከበር እያሉ እያለቀሱም ናቸው። በዚህም ለቅሷቸው ምን ለማለትና ለማድረግ እንደሚፈልጉ ማወቅ አያዳግትም። ግምገማና ተሃድሶ! እያሉም ደጋግመው የሚጮሁ የሕወሐት ሰዎችም እስከዛሬ ድረስ በዚያው በግምገማና ተሃድሶ ሕዝቡን ሲያታልሉት ኖረው የሃገሪቷን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ሰብዓዊ መብቶችን ተሰምቶ ከማይታወቅበት አሳፋሪ ዝቅጠት ውስጥ ከተውታል። ከመጀመሪያው በተጣመመ መሠረት ላይ የተገነባውን መዋቅር ምንም ዓይነት ግምገማና ተሃድሶ ሊፈውሰው እንደማይችል ለማየት ተስኗቸዋል። እነሱ ግምገማና ተሃድሶ ባደረጉ ቁጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰቆቃ እየባሰበት እንጂ እየቀነሰለት አልሄደም። ለሕወሐት ደላሎችና ካድሬዎች ግምገማ እናድርግ ማለት “ጨቁነናችሁ አላበቃንምና ዘይቤያችንን አድሰን ለበለጠ ብዝበዛ እንድንመለስ ሌላ ዕድል ስጡን” ማለት ይመስላል።
መዘንጋት የሌለብን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሁንም የሕወሀት-ኢሕአዴግ መንግሥት አምባገነናዊ የአገዛዝ ስልት ሆኖ እንዳለ ነው። የአሁኑም አምባገነናዊ ሥርዓት በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተካትና ሕገመንግሥቱ ዴሞክራሲን እንዲደግፍ መሻሻል ወይም መለወጥ ይኖርበታል። ስለዚህም ይህን ለውጥ ወደፊት ማራመድና እውነተኛው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ተግቶ መሥራት የሁላችንም ሃላፊነት ነው።
ይድረስ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች
ቁጥራችሁ የበዛ አገር አቀፍ እና ክልላዊ ፓርቲዎች ተደራጅታችሁ እንዲሁም ሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ተሳትፋችሁ የሕወሐት-ኢሕአዴግን መንግሥት ስትጋፈጡት ቆይታችኋል። ለዚሁምበድርጅትም ሆነ በግለሰብአስከፊ ስቃይ ተቋቁማችሁ ለአገራችሁም ፍቅር ከፍተኛ ዋጋ ከፍላችኋል። በተቃራኒውም ሲታይ ልዩነቶቻችሁ የጠነከረ ድርጅት አንዳትፈጥሩና በሕብረት እንዳትታገሉ እንቅፋት ሆኖባችኋል። ይህም እውነታ ሕዝቡንም በመከፋፈል በጠነከረ አንድነት አንዳይታገል አድርጓል። ይህንንም ድክመት የሕወሐት-ኢሕአዴግ መንግሥት የራሱን ሥልጣን ላይ ማራዘሚያ አድርጎ ተጠቀሞበታል። አሁንም ልዩነታችሁን ወደጎን አስቀምጣችሁ ይህን የለውጥ ዕድል ተጠቅማችሁ ጠንካራ ድርጅት በመመሥረት ለሐገራችን ዴሞክራሲያዊ መንገድ መቀየስ ይኖርባችኋል። ይህንም ማድረግ ባትችሉና የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደገና ለጭቆና ቀንበር አሳልፋችሁ ብትሰጡ ውርደቱ የናንተና የናንተ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብም ይፋረዳችኋል። በዶክተር አብይና ረዳቶቹ በሩ ተከፍቷል። ለምን ጊዜ ያህል ተከፍቶ እንደሚቆይ የሚወሰነው በእናንተና በኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በምንም መንገድ የ97ቱም ሆነ የ2002ም ሆነ የ2007 የምርጫ ቀውሶች መደገም የለባቸውም። ከአሁን ወድያ የምርጫ ሳጥኖች ተስፋ በቆረጠ ሕዝብ “የስድብና የተበላሹ የምርጫ ወረቀቶች”(5)ተሞልተው ማሸነፍ የሌለበት ፓርቲ የሚያሸንፍበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ኢትዮጵያ ወደፊት የመራመድ እንጂ ወደኋላ የመመለስ ምርጫ የላትም።
ማጣቀሻዎች፡
- ዶክተር መረራ ጉዲና – የኢትዮጲያታሪክና የሚጋጩ ህልሞች – የኢህአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ, እ ኢ አ 2008 እትመት
- Nelson Mandela – Long Walk to Freedom
- ኤርሚያስ ለገሠ – የመለስ ልቃቂት
- በተለያዩ አከባቢዎች ለሚቀሰቀሱግጭቶች ህወሓቶች እና አክቲቪስቶች ተጠያቂ ናቸው! Seyoum Teshome October 27, 2018 – https://ethiothinkthank.com/2018/10/27/the-role-of-tplf-elites-and-activists-in-inciting-ethnic-conflict/
- ሀብታሙ አያሌው – ከህወሓት ሰማይ ሥር, 3ኛ እትም
- ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም – “The End of Thugtatorship and Rise of the Rule of Law in Ethiopia”. November 19, 2018. https://ecadforum.com/2018/11/19/the-end-of-thugtatorship-and-rise-of-the-rule-of-law-in-ethiopia/
- Daren Acemoglu & James A. Robinson -Why Nations Fail –
- https://www.britannica.com/topic/democratic-centralism
- http://nazret.com/blog/index.php/2006/12/10/ethiopia_tplf_revolutionary_democracy
- https://www.opride.com/2017/12/29/ethiopia-eprdf-ditch-democratic-centralism-avoid-civil-war/
No comments:
Post a Comment