Monday, September 18, 2017

ፋሽስት ሆይ! ጠገዴ አንድ ቤተሰብ፣ ድንበሩም ተከዜ ነው! (ልሳነ ግፉዓንና የጠለምት አማራ ማንነት ጥምረት ኮሚቴ)


Welkait Tsegede

ፋሽስቱ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባርና ተላላኪው ብአዴን በአዲሱ አመት ዋዜማ ለመላው የጎንደር ህዝብ የሰጡት ስጦታ ቢኖር ሰላምና አንድነትን ሳይሆን አካሉ የሆነውን የጠገዴን ማህበረሰብ ለሁለት እንደ ቅርጫ መቀራምትን ነው።
ታላቋን ኢትዮጵያ የማፍረስና ህዝቧን የማተራመስ ተልዕኮ እንደ ቀደምት ባንዳ አባቶቹ ከጠላቶቻችን የተሰጠው የትግራዩ ወራሪ ቡድን የአማራን ህዝብና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ኢላማው አድርጎ በውድ ሃገራችንና በኩሩው ህዝባችን ላይ መርዙን መዝራት ከጀመረ እነሆ 26 የፅልመት አመታት ተቆጠሩ።
ከሽፍትነት ዘመኑ ጀምሮ ታሪካዊና ለም የሆኑትን የጎንደር መሬቶች በተቀዳሚነት ኢላማው ያደረገው ወራሪው ተ.ሃ.ት የተከዜን ወንዝ በመሻገር የወልቃይትን መሬት ከረገጠበት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በወገናችን ላይ ያደርስ የነበረው ዝርፊያ፣ እስራት፣ ድብደባና፣ ግድያ እስከ ዛሬም ድረስ የቀጠለ ሲሆን በተለይም ከአንድ አመት በፊት የወልቃይትን ህዝብ ሙሉ ውክልና ይዘውና የህዝብን ጥያቄ አነግበው በሰላማዊ መንገድ ፍትህን የጠየቁ የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ መሪዎችና አባላት በሽብርተኝነት ተወንጅለው በዋና ዋና የህወሃት የማሰቃያ ካምፖች ውስጥ መከራን እየተቀበሉ የሚገኙ ሲሆን፤ወረራውንና መስፋፋቱን በፍፁም ጭካኔና ማንአለብኝነት የቀጠለው ይህ እኩይ ቡድን ወደ ጠገዴና ጠለምት ያደረገውን ወረራ የተቃወሙትን ታሪክ ነጋሪ የሃገር ሽማግሌዎችን፣ ትውልድና ሃገር ጠባቂ ጎልማሳዎችን፣ እንዲሁም ሃገርና ታሪክ ተረካቢ የሆነውን ወጣት ትውልድ በግልፅና በስውር በመጨፍጨፍ ካጠፋ በኋላ ዕርስታችንን በሃይል ወደ ትግራይ በመጠቅለል በይፋ የምትገነጠለው ትግራይ አካል ከተደረገ እነሆ ሃያ ስድስት የሰቆቃ አመታት አሳለፍን።
ምንም እንኳ ህዝባችን በፋሽስቱ ህወሃት የጭቆና አገዛዝ ስር ሆኖ ቃላት ሊገልፁት በማይቻላቸው መከራና ስቃይ ውስጥ ቢገኝም ጭቆናንና ባርነትን አሜን ብሎ መቀበል ከአባቶቹ አልወረሰምና በሚቻለውና ባገኘው ቀዳዳ ሁሉ ተጠቅሞ የጠላቱን እኩይ ሴራ በማክሸፍ ላይ ይገኛል። ይሁንና ይህ ህዝባዊ ተጋድሎ እረፍት የነሳውና ኢትዮጵያን የማፈራረስና ትግራይን የመገንጠል ሰይጣናዊ ተልዕኮ እያኮላሸበት የሚገኘውን የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ለማዳከምና ከፋፍሎ ለማጥቃት በማለም አንድን ቤተሰብ የሆነውን የጠገዴ ማህበረሰብ ለሁለት በመክፈል ግማሹን ጠገዴ ሌላኛውን ግማሽ ፀገዴ በማለት ለያይተው የሚቻላቸውን ክፉ ተግባር ሁሉ ሲፈፅሙብን ኖረዋል።
ይሁን እንጂ ምንግዜም ቢሆን ጀግና መውለድ የማታቆመው የጎንደር እናት ዛሬም እንደ ትላንቱ አንድ ጠገዴ!!! ብለው በተነሱ ልጆቿ አማካኝነት ህዝባዊ ትግሉን በማፋፋም የፋሽስቱን ጎራ እያንቀጠቀጡት ይገኛሉ። “ወላድ በድባብ ትሂድ” እንዲሉ በጠገዴ የቁርጥ ቀን ልጆች የማያወላዳ ጥያቄ የተሸበረውና የዘመናት ሴራው በዜሮ የተባዛበት የተገንጣዩ ጎራ ከጳጉሜ 1, 2009 ዓ.ም ጀምሮ አንዳች የአማራ ህዝብ ድጋፍ በሌለውና እርሱ ህወሃት በአምሳሉ ጠፍጥፎ ከሰራው ብአዴን ተብዬ የአሻንጉሊቶች ስብስብ ጋር በመሆን አንዱን የጠገዴ ቤተሰብና ዕርስቱን ለሁለት በመከፈል መቀራመታቸውን በየፊናቸው እያወጁ ይገኛሉ።
የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ጥያቄ ግልፅና አንድ ነው። ይሃውም ህዝቡ ጎንደሬ/አማራ፣ መሬቱ የጎንደር፣ ድንበራችን ተከዜ ነው! የሚል ነው። ከዚህ ታሪክና ማንነትን መሰረት ካደረገ ህዝባዊ ጥያቄ አንዳች ጎደሎና እንከን የታከለበት ሽርፍራፊ ምላሽ ህዝባችን እንደማይቀበል የአለፉትን ሃያ ስድስት የፅልመትና የጭቆና ዘመናትን በፅናት በማለፍ ዛሬ እንደ አዲስ አይነቱንም ሆነ ይዘቱን ቅንጣት ሳይቀር ዳግም በወጣቱ ትውልድ መነሳቱ አብይ ማረጋገጫ ነው።
ታዲያ ይህን ታሪካዊ እውነታ አንዴ “በወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢ” ኮሚቴ አማካኝነት፣ ሌላ ጊዜ “ጠገዴ አንድ ነው” በሚለው የጠገዴ ህዝብ ጥያቄ ሳይወድ በግዱ እንዲጋፈጠው የተደረገው ፍሽስቱና ተስፋፊው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር “የማይተማመን ጓደኛ በየወንዙ ይማማላል” እንዲሉ ለሃያ ስድስት አመታት በሃይል ከልሎ ሲበዘብዛቸው የኖሩትን የጠገዴ ወገኖችን በተለይም ዕርስታችን የሆኑትን የግጨውና የጎቤ ጎንደሬ/አማራ መንደሮችን ትግሬ ያደረገ የትግራይን ድንበር ከአማራ ጋር ተካልያለሁ በማለት ሎሌዎቹን ሰብስቦ ከበሮ እየደለቀና ሻምፓኝ እየተራጨ ይገኛል።
እኛ በመላው ዓለም የምንገኝ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆች ዛሬም እንደትላንቱ በአንድነት ከህዝባችን ጐን በፅናት በመቆም የትግል አጋርነታችንና አንድነታችን እየገለፅን ከጳጉሜ 1, 2009 ዓ.ም ጀምሮ በህወሃትና በብአዴን መሪዎች አማካኝነት የታወጀው ጠገዴን ከሁለት በመክፈል በተለይም የጎንደር/አማራ ለምና ታሪካዊ የሆኑትን የግጨውና የጎቤ መንደሮችን ወደ ትግራይ መከለል ፍጹም ሰብአዊነት የጎደለውና አንድን ቤተሰብ ለሁለት የሚከፍልና የሚለያይ ጭራቃዊ ተግባር በመሆኑ የምንፀየፈው አጥብቀን የምናወግዘው መሆኑን እየገለፅን፤ ትላንት ከቀጣሪዎቹ በተሰጠው ኢትዮጵያን የማፈራረስ ባንዳዊ ተልዕኮ አንዱ የሆነውን ኤርትራን የማስገንጠልና የህጋዊና ዓለም አቀፋዊ ድንበር ባለቤት የማድረግ ሴራና ድራማ በቅጡ መከወን ያልተቻለው ፍሽስቱ ሟች መለስ ዜናዊ  ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊያስፈፅም አልጀርስ ላይ ከኤርትራ ጋር የተስማማበትንና በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ከጅምሩ አጥብቆ የተቃወመውን መሰሪ ውል ሲያፈርስ እንደ ዋነኛ ምክንያት ሲቀላምድ የነበረው “አንድ ቤተሰብ ለሁለት የሚከፍል” ፍርድና የድንበር ማካለል አልቀበልም በማለት ነበር።
ዛሬ የሙት መሪያቸው ራዕይ ወራሾች ነን በሚል በየመድረኩ ሲምሉና ህዝብን ሲያደነቁሩ የሚውሉ ውልደ ፋሽስቶች ህዝባችን በወኪሎቹ አማካኝነት “እኛ አንድ ቤተሰብ ነን!” “ጠገዴ አንድ ነው!” በሚል ያቀረበው ህዝባዊ ጥያቄ ለአልጀርሱ በተባው የክህደት ምላስና ህሊናቸው “አንድ ቤተሰብ ለሁለት የሚከፍል” ፍርድና የድንበር ማካለል አንቀበልም ማለትን እረስተው ህዝባችንን ዛሬም ድረስ ዘመን መለወጫን እየጠበቁ ያስለቅሱታል። ዕርስታችንም ታላቋን ትግራይ ለመመሥረት በሚል ቅዥት ወደ ትግራይ በማካለል ለሕዝባቸው የአዲስ ዓመት ስጦታነት ያውሉታል።
ይሁን እንጂ ዛሬም ህዝባችን በፍፁም ጨዋነት ያቀረበው ሰላማዊና ህጋዊ ጥያቄ ፍትሃዊ ምላሽ ሳይሰጠው በመቅረት በተገንጣዮች የእብሪት እርምጃ አሁንም እንዲለያይ በግፍ የተፈረደበት ቤተሰባችን ዳግም አንድ ሆኖ በሃገሩ ላይ በነፃነትና በእኩልነት መኖር እስኪችልና ሰላሙና አንድነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ትግላችን ከምንግዜውም በላይ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ለፍሽስቱ ህወሃትና ለተንበርካኪው ብአዴን አመራሮች፣ አባላትና፣ ደጋፊዎች እያሳወቅን፤ በዚህም ምክንያት ለሚደርሱት ማንኛቸውም ሃገራዊና አካባቢያዊ ችግር ብቸኛ ተጠያቂው ፋሽስቱ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባርና ተላላኪው የብአዴን አመራር አካላት መሆናቸውን ከጥብቅ ማሳሰቢያ ጋር እንገልፃለን።
ጠገዴ አንድ ቤተሰብ፣ ድንበሩም ተከዜ ነው!
ልሳነ ግፉዓንና የጠለምት አማራ ማንነት ጥምረት ኮሚቴ
መስከረም 1, 2010 ዓ.ም
ሰሜን አሜሪካ

No comments:

Post a Comment