Friday, November 2, 2012

ከሃገር ወዳድ የትግራይ ተወላጆች የተሰጠ ጥብቅ ማሳሰቢያ


መጽሐፈ ኢያሱ 3:9 “ለእስራኤል ልጆች የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ አለ” ሲል አውጇል::

Ethiopian flag (Alemayehu G. Mariam)ሕወሃት ከተመሠረተ ጀምሮ የትግራይን ሕዝብ ከእግዚአብሔርና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሲያጋጨው መቆየቱን: እኛ አገር ወዳድ የትግራይ ተወላጆች በየአጋጣሚው ስናስጠነቅቅ መቆየታችን ይታወሳል:: እግዚሃብሔር ግን ዛሬ በሕዝብና በቤተክርስቲያን ላይ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩትን እርሱ ወስዷል::ለቀሪዎቹ “ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ” ይላል::ስለዚህ የሕወሃት መሪዎች ካለፈው ጥፋታችሁ ተምራችሁ ወድ ሕዝባችሁና ወደ አገራችሁ እንድትመለሱ አጥብቀን እናሳስባለን::
ከዚህ በፊት በተለያዩ ዌብሳይቶች ላይ አንዲት ገጽ ጽሁፍ አስነብበን ነበር::ዛሬም የሕወሃት አባላትና ደጋፊዎች ልብ እንዲገዙ እንመክራለን::ምክንያቱም ሕወሃቶች በእድሜአቸው ትልቅ ቢሆኑም ከአለፈው ጥፋታቸው ሊማሩ አልቻሉም::ይህን ጽሁፍ እንድናውጣ ያስገደደን ነገር ቢኖር ባለፈው አቶ ስብሃት ነጋ በተናገሩት ላይ ተንተርሰን ሲሆን እርሳቸው አሁንም ውጭ እንደሚመጡ ስላወቅን የሕወሃትን ደጋፊዎችና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ለማስጠንቀቅ ነው::
ለፈው አቦይ ስብሃት “ገዛ ተጋሩ” በተባለው ፓልቶክ “ሥልጣኑ ከአማራውና ከኦርቶዶክሱ በመራቁ ደስ ብሎናል::” ሲሉ መናገራቸው አንዳንድ የዋህ ወገኖች ምስጢሩ ሳይገባቸው ተደስተውበታል:: እኛ አገር ወዳድ የትግራይ ተወላጆች ግን በአንጋገራቸው በጣም አዝነናል::አሁንም ይህን የከፋፍለህ ዘዴአቸውን በሥራ ላይ ለማዋል ወደ አውሮፓ ሊመጡ መሆናቸውን ስምተናል::አሁንም የሕወሃት ደጋፊ የሆናችሁ ወገኖች የአቶ ስብሃት ነጋን የረቀቀ የከፋፍለህ ግዛ ሴረኝነት እንድትረዱ እናሳስባለን::ቢቻል በገማ እንቁላል ቲማቲም እንድንቀበላቸው አለያም ደግሞ አቶ ስብሃት የሚዘሩትን የከፋፍለህ መርዝ ለመስማት እንዳትሄዱ እናሳስባለን::
ሕወሃትና አቦይ ስብሃት እንኳን ለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና ቁምንለታል ለሚሉት ለትግራይ ሕዝብ አይጨነቁም::በእነርሱ አባባል ዛሬ ትግራይ 57 ወረዳዎች ሲኖሩአት 38ቱን ወረዳዎች የሚያስተዳድሩት የአድዋ አውራጃ ተወላጆች ናቸው::ለምሳሌ ትግራይ አራት ዞኖች ሲኖራት የነዚህም አስተዳዳሪዎች የአድዋ ተወላጆች ናቸው::ታዲያ ለ17 ዓመታት አብረዋቸው ለታገሉ የትግራይ ልጆች ያልሆኑ እንዴት ለሌላው ኢትዮጵያዊ ሊቆረቆሩ ይችላሉ?
በሌላ በኩል ደግሞ ለውድ ኢትዮጵያውያን በቅድሚያ አንድ ሃቅ እንድትረዱልን ለማሳሰብ እንወዳለን::የሕወሃት መሪዎች በሚፈጽሙት ሴራ የትግራይ ሕዝብ ያለፈለት የሚመስላችሁ ወገኖች ብዙ ናችሁ::የሕወሃት መሪዎች ነክተውና ነካክተው ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን በቁጣና በስሜት እንድትናገሩና እንድትጽፉ ያደርጋሉ::ከዚያም ያንን እየጠቀሱ የትግራይ ሕዝብ ከነርሱ ጋር እንዲቆም ቅስቀሳ እያደረጉበት ነውና ሕዋሃቶች በሄዱበት ጎዳና እንዳትሄዱ ካለን ልምድና ተመክሮ ለማሳሰብ እንወዳለን::
በሕወሃት ወታደራዊ ተቋም ውስጥ ሲያገልግሉ የነበሩትን አባላቶቹን ወደ ውጭ አገር ለስለላ ልኳል::እነዚህ የሕወሃት ሰላዮች ባረፉበት ቦታ ሁሉ የመኖሪያ ፈቃድ እስኪያገኙ ድረስ ፀረ-ሕወሃት ወሬ ሲነፉ ይቆያሉ::ከዚያም ማን ሕወሃትን እንደሚጠላ ካወቁ በኋላ አንድ ባንድ የግለሰቦቹን ማንነት በያሉበት አገር ላለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሪፖርት ያደርጋሉ::ዛሬ በዲያስፖራ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን አንድ እንዳይሆኑ የሚከፋፍሉና የሚለያዩ እንዚህ መንግሥት የላካቸው ሰላዮች ናቸው::ካስፈለገም ያሉበትን አገርና ስማቸውን ከነማዕረጋቸው ዘርዝረን ለማጋለጥ ዝግጁ ነን::
የሕወሃት አባላትና ደጋፊዎች ባለፈው ዓመት በአንድ ወር ውስጥ ሁለት አገርንና ቤተ ክርስቲያንን ያጠፉ ቀንደኛ ግለሰቦችን አምላክ ሲወስዳቸው አይተው ትምህርት ሊሆናቸው ይገባ ነበር:: ሕወሃቶች ግን ከጥፋታቸው መማር አልቻሉም:: አሁንም በኢትዮጵያውያን እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የምታደርጉትን ጫና እንድታቆሙ እናሳስባለን::አንዱን ሃይማኖት ከሌላ ሃይማኖት አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር ጋር ማጋጨቱን እንድታቆሙ በሰፊው የትግራይ ሕዝብ ስም እናሳስባለን::
የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብሮ የኖረ ለወደፊቱም የሚኖር ሕዝብ ነው::ለዚህም ሻቢያ በአይደር ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት ሲፈጽም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕወሃት ላይ ያለውን ቂም ወደጎን በመተው ሰፊው የትግራይን ሕዝብ አክብሮ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ጉልበት ያለው በጉልበቱ መዝመት የሚችለው ዘምቶ አቅም የሌለው በቤተ ክርስቲያንና በመስጊድ አምላኩን ተማጽኗል::ሕወሓትን ግን ይህን አንድነቱንና አብሮነቱን ለመለያየት የምታደርጉትን ሴራ እናወግዛለን::
የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያን ታሪክ አክባሪ እንጂ እናንተ እንደምትሉት የመቶ ዓመት ታሪክ አላት አይልም::የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያ አገራችንን ሊወር የመጣን ጠላት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ሁኖ ድባቅ የመታ ሕዝብ ነው::ይህ አኩሪ ታሪኩን ልታጠፉበት እየጣራችሁ መሆናቸውን ከተረዳን ውለን አድረናል::ከዛሬ ጀምሮ ይህን ሴራችሁን እንድታቆሙ በድጋሚ እናሳስባለን::
የትግራይ ሕዝብ ሆይ! ታሪክን እወቅ! አገርህን አክብር እንጂ የሕወሃትን ቅስቀሳ እንዳትሰማና ከሌላው ኢትዮጲያዊ ወገንህ ጋር እንዳትጋጭ እናሳስብሃለን::
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
በሲያትልና አካባቢዋ የምንኖር የትግራይ ተወላጆች ኢትዮጵያዊያን ሕብረት::

No comments:

Post a Comment