Monday, January 7, 2019

"በአንድ ሀገር ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ክልሎች ሊኖሩ አይገባም" ፕሮፌ. ብርሃኑ


Sunday, January 6, 2019

ያልተገራው የማንነት ፖለቲካችን እና አደጋው (ተበጀ ሞላ (PhD)


The Poison of Ethnic Federalism in Ethiopia’s Body Politic
መግቢያ
በሀገራችን የዘውጌ ፖለቲካ ያለ ልክ ጦዟል።  በየማዕዘኑ ዘውጌ-ተኮር አፍራሽ ፉከራ እና ዲስኩር እየሰማን ነው። ፖለቲካኞቻችንም ሃሳብ ከመሸጥ ይልቅ ስሜት መግዛት ላይ አትኩረዋል።  በግዜ እልባት ካላገኘ ይሄ አካሄድ ሀገር አልባ እንዳያስቀረን ያስጋል። ለመሆኑ የዘውጌ ፖለቲካ ታሪካዊ መሰረቱ ምንድነው? ከኛ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃርስ አክራሪ ዘውጌነት ምን አደጋ አለው? አሳታፊ የሆነ የዜግነት ፖለቲካ እዉን እንዲሆን ምን የተሻለ መንገድ አለ? ይህ አጭር መጣጥፍ እነዚህን ነጥቦች በጨረፍታ ይዳስሳል። በፅሁፉ ዉስጥ ዘውጌ፣ ዘውግ እና ብሔር የሚሉት ቃላት እንደ ቅደም ተከተላቸው ethnic፣ ethnicity እና nation የሚሉትን የእንግሊዝኛ ቃላት ይተካሉ።  ሃሳቤን ማንነትን በማብራራት እጀምራለሁ።
ማንነት ምንድን ነው?
ማንነት ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ራሳችንን የምንገልፅበት መለያችን ነው። በዋናነት ማንነት ለራስ በሚሰጥ እይታ ይገለፃል። ማንነት ዘርፈ-ብዙ ነው።  ነጠላ ማንነት ያለው ሰው የለም። አንድ ግለሰብ በፆታው፣ በሃይማኖቱ፣ በቋንቋው፣ በዘውጉ፣ በሙያዉ፣ በፖለቲካ እምነቱ እና አሰላለፉ፣ ወዘተ ማንነቱን ሊገልፅ ይችላል። ከሁለንተናዊው ሰውነቷ ባሻገር ሶፊያ  ባንድ ግዜ ሙስሊም ፣ መምህር፣ ስልጤ፣ ኢትዮጵያዊት፣ የአፍሪካ ሴት ልትሆን ትችላለች። በመሆኑም ‘ይህ ቡድን ወይም ያ ግለሰብ የተለየ ማንነት አለው’ ሲባል የግድ ስለ ዘዉግ አያወራን ላይሆን ይችላል። በሌላ አነጋገር ማንነት እንደ ቀይ ሽንኩርት ተደራራቢ ነው። አንዱን ንብር ልጦ ጥሎ (ረስቶ) ሌላውን መብላት (ማስጮህ) የባለቤቱ ምርጫ ነው።
ሰው ነን እና ኑሯችን ከሌሎች ጋር የተቆራኘ ነው። ስዉር በሆነው የግል ማንነታችን እና ሁለንተናዊ (universal) በሆነው ሰዋዊ ተፈጥሯችን መካከል ራሳችንን በበርካታ የጋርዮሽ እርከን እናገኘዋለን። ከቤተሰብ ጀምረን ከፍ ስንል በዘመድ አዝማድ ከዛም ሲያልፍ በጎሳ (clan)፣ በዘውግ (ethnicity)፣ በነገድ (tribe)፣ በብሔር (nation) እና በዘር (race) ማንነታችንን እንገልፃለን። አንደ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ደግሞ የዉጭ ሰዎች በብሔራዊ ማንነታችንን (national identity) ይለዩናል።
በሊብራል ዲሞክራቲክ ሃገራት እንደ አዲስ ያቆጠቆጠውን አክራሪ ብሄርተኝነት ተከትሎ ስለ ማንነት ፖለቲካ ብዙ ትንታኔ አየተሰጠ ነው። እዉቁ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ፍራንሲስ ፍኩያማ እና አፍሪቃዊው ፈላስፋ ክዋሜ አፕያህ በቅርቡ በማንነት ላይ ያሳተሟቸው መፅሃፍት ተጠቃሽ ናቸው።  እንደ ፍኩያማ እምነት የሰው ልጅ ለእዉቅና (recognition) የተለየ ቦታ አለው። ለማንነት የሚሰጥ እዉቅና ከክብር ጋር ይያያዛል። ማንነቴ ተገቢዉን እዉቅና ዋጋ አላገኘም ብሎ ያመነ ግለሰብም ሆነ ቡድን ይደራጃል፣ ይታገላል። አፕያህ በበኩሉ ማንነት እንደ ዘረመል (gene) የሚወረስ ሳይሆን እንደ ፀጉር በቅጥ ተሰርቶ ማድመቂያ የሚሆን ስሪት ነው ሲል ይከራከራል ። የዘውጌ ማንነት በዋናነት ተወራሽ መለያወችን (primordial characteristics) መሰረት ያደረገ ነው። አባላቱ ‘እኛና እነሱ’ ብለው የሚለዩባቸው ቋንቋ ፣ ወግና ልማድ እንዲሁም ግዛት (ancestral territory) ይጋራሉ። ሆኖም ማንነት ተፈጥሯዊ አይደለም — ሰው ሰራሽ ነው።  አዲስ ግዛት በመዉረር፣ ባህልን በማሻሻል እና ታሪክን ለራስ በሚመች መልኩ በመከለስ የዘውጌ ማንነት ይፈጠራል። ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ኃይል፣ ትውፊት እና ዲስኩር ዋና መሳሪያዎች ናቸው።  ካለፉት 30 አመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሕዳር እየሆነ ያለዉን ያስተዋለ ይህን እዉነታ  አይስተውም።
የብሔር ፖለቲካ አመጣጥ በጨረፍታ 
ብሔር እና የብሔር ፖለቲካ መነሻ አዉሮፓ ነው። በዘርፉ ጥልቅ ምርምር ያደረገው ሊህ ግርንፈልድ እንደሚለው nation (ብሔር) የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ምንጩ natio የሚለው የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉሙም ‘የተወለደ’ ማለት ነው። የጥንት ሮማዉያን ቃሉን ካንድ አካባቢ የመጡ የዉጭ ሃገር  ሰዎችን ለመግለፅ ይጠቀሙበት እንደነበር ተዘግቧል። በዋናነት መጤነትን ስለሚገልፅ ትርጓሜው የክብረነክነት ባህሪ ነበረው። ሁላ በመካከለኛው የአዉሮጳዉያን ታሪክ ብሔር የሚለው ስያሜ በቋንቋ ወይም በትዉልድ ቦታ  ከሚመሳሰሉ አካባቢዎች የመጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመግለፅ ይዉል ነበር ። ተማሪዎቹም የትዉልድ ቄያቸውን መሰረት አድርገው መተጋገዝ እና በክርክርም ወቅት አንድ ላይ መቆም መለያቸው ስለነበር ብሔር የሚለው ስያሜ ያንድ አካባቢ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሃሳብ እና ዓላማ ለሚጋሩ ማህበረሰቦች (communities) መጠሪያ ሊሆን በቃ።  ቆይቶም ሃሳቡ ወደ ቤተክህነት ጉባኤ ዘልቆ ገባ እና ሌላ ትርጉሙ አገኘ: ልሂቃንን ለመግለፅ ዋለ። በ16ኛው ዘመን እንግሊዞች  ብሔርን እና   ‘ሕዝብ’ን በእብረታ (አንድ ላይ) መጠቀም እንደጀመሩ  ይነገራል። ይህ ለውጥ ሃገራዊ ብሄርተኝነት (civic nationalism) የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም እንዲሆን ርሾ የጣለ ነበር።
ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ግን ብሔር የሚለው ቃል ‘ልዩ ሕዝብ’ የሚል ትርጉም ያዘ። በፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ሩስያ ቃሉ ዘውግን፣ ግዛትን እና የፖለቲካ ታማኝነትን አጣምሮ የያዘ ማህበረሰብ የሚገልፅ ሆነ።  በተለይ ደግሞ በፈረንሳይ አብዮት ማግስት የተቀነቀነው ‘የብሔር ጥያቄ’ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ  ጀምሮ በግራ-ዘመም ፖለቲከኞች ቁልፍ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል።  ብሔር እና ብሔረሰብን ዋና የፖለቲካ ጉዳይ  አድርጎ ለመጀመርያ ያቀረበው የሶቪየቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን ማርክሲዝም እና የብሔር ጥያቄ በሚለው ፅሁፉ (1913 እአአ) ብሔር መሰረቱ የግድ ዘር፣ ነገድ ወይም ዘውግ ላይሆን ይችላል ይላል። በዋንናነት የኦቶ ባወርን (በወቅቱ ስመ-ጥር የነበረ ኦስትርያዊ ፖለቲከኛ) ሥራ መሰረት አድርጎ፣ ስታሊን   ብሔር ማለት ታሪካዊ ሂደት፣ ቋንቋ፣  አሰፋፈርና ስነ-ልቦና የሚጋራ እና የምጣኔ ሀብት ትሥሥር ያለው ማህበረሰብ ነው ሲል አብራርቷል።
በዚህ መልኩ ቅርፅ የያዘው የብሔር ፖለቲካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ  ከአዉሮጳ ወደ ሌሎች ክፍለ-ዓለማት በሰፊው ተዛመተ። የአፍሪካ ልሂቃን በሌላ አዉድ ስለ ብሔር የተፃፈውን እና የተነገረውን ሁሉ ገልብጠው ለዘውግ ፖለቲካ አዋሉት።  የኛዎቹ ዋለልኝ መኮንን እና መለስ ዜናዊም ይህንኑ ነበር ያደረጉት። ሃሳቡን ሲዋሱ አግባበ ነገሩን ግን አላገናዘቡም። ከላይ እንደተባለው ብሔር (nation) የሚለው ቃል በታሪክ ሂደት ብዙ ግዜ ትርጉሙ ተለዉጧል፥ ለሮማዉያን የመጤ ሰዎች መጠሪያ ነበር። ቆይቶ  ሃሳብ እና ዓላማ የሚጋሩ ስብስቦችን ለመግለፅ ዋለ።  ኋላ ደግሞ የሃይማኖት እና ማህበራዊ ልሂቃን ስያሜ ተደረገ። ከዛም እንግሊዞች ‘ሉዓላዊ  ሕዝብ’ የሚለውን ፖለቲካዊ ትርጉም አስያዙት። በዘመነ አብዮት ደግሞ ብሔር ማለት ‘ልዩ ሕዝብ’ ማለት ሆነ። የ ‘ያ ትውልድ’ ዘውጌዎች እና የዛሬዎቹ ደቀመዝሙሮቻቸው ‘ብሔር’ ነን ሲሉ “ሌሎች ጋር ምንም የማንጋራ ‘ልዩ’ ሕዝብ ነን” ማለታቸው ነው። ኢትዮጵያን በቅጡ ለሚያውቅ እሳቤው የተዛባ ነው። ከሀገራዊ ብሔርተኝነት (civic nationalism) እደገት እና ታሪክ አንፃር ሲታይ ብሔር ማለት እጣ ፈንታው አንድ የሆነ፣ ከሚያለያዩት የዘውጌና ሌሎች ማንነቶች ባለፈ ጠንካራ የጋራ እሴቶች ያሉት ሕዝብ ማለት ነው። ስለዚህ ፖለቲካችን በብሔር ደረጃ ከሆነ የምናወራው ስለ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ስለ ዘውጌ ማንነት ሊሆን አይችልም።
የኢትዮጵያ ብሔር እና ብሔረሰብ እነማን ናቸው?
እንደማንኛውም መድብለ-ዘውጌ ማህበረሰብ (multi-ethnic society) በኢትዮጵያ ከዘዉዳዊዉ ስርዓት ግርሰሳ ጀምሮ፣ በተለይ ደግሞ ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን ከወጣ ወዲህ ‘የብሔር ጥያቄ’ ዋና የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። የሶቭየትን (1936/1977 እአአ) እና ዩጎስላቪያን (1946/1974 እአአ) ህገ-መንግስቶች ፈለግ ተከትሎ ወታደራዊው ስርዓት በሕገ-መንግስቱ (አንቅፅ 2) ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ሀገር መሆኗን አስቀምጦ ነበር። በተመሳሳይ አራተኛው (አሁን በሥራ ላይ ያለው) ህገ-መንግስት በሀገሪቱ  ሉዓላዊ  የሰልጣን ባለቤቶች  ‘ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ናቸው ይላል። ነገር ግን በሕገ-መንግስቱ የሰፈሩት አንዳንዶቹ  የፖለቲካ ቃላት አስማሚ እና ግልፅ ብያኔ የላቸውም። ለምሳሌ ስታሊን ለብሔር የሰጠውን ብያኔ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ‘ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን’ የሚለውን ፈርጅ (category) ለመግለጽ ተጠቅሞበታል። አንቅፅ 39(5) ‘ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ’ ማለት “ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የማንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልዉና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የስነ-ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓምድር የሚኖሩ ናቸው” ብሎ ይፈታዋል።  ፅንሰ-ሃሳቡ በቀጥታ ከስታሊን ፍች አለያም ከመሰል ምንጭ የተቀዳ በመሆኑ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማን ብሔር፣ ማን ብሔረሰብ፣ ማን ሕዝብ እንደሆነ በግልፅ አልተቀመጠም። በ1984 ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ (ቁጥር 7/1984) ደግሞ ብሔርና ብሔረሰብ ተተካኪ እንደሆኑ አድርጎ አስቀምቷቸዋል። አንቅፅ 2(7) “‘ብሔር’ ወይም ‘ብሔረሰብ’ ማለት በአንድ ኩታ ገጠም መልክዓ ምድር የሚኖር አንድ የመግባብያ ቋንቋና የአንድነት ስነልቦና ያለው ሕዝብ ነው” ይላል። በተመሳስይ መልኩ የሚድያ ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞች ብሔርና ብሔረሰብ የሚሉትን ቃላት የዘውጌ ቡድኖችን (ethnic groups) ለመግለፅ ይጠቀሙበታል።
የዘውጌ ማንነትን የተረዳንበት እና ፖለቲካዊ ጥያቄውን ምላሽ ለመስጠት የሄድንበት መንገድ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያልተዛመደ በመሆኑ አሁን ላለንበት ችግር ደርሰናል። የክልል መንግስታት ምስረታና ስያሜ ጥሩ ማሳያ ነው ። ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ መሰረት በትግራይ ክልል ትግራዋይ፣ ኩናማና ሳሆ የሚባሉ የዘውጌ ቡድኖች ይኖራሉ። በደቡብ ትግራይ ያሉ ራያዎችም አማርኛ፣ ኦሮምኛና አገዉኛ ይናገራሉ። በአማራ ክልልም እንዲሁ የአማራ፣ አገው፣ ኦሮሞ፣ አርጎባ እና ሌሎች ማሕበረሰቦች ይኖራሉ። ኦሮምያም በዉስጡ በርካታ የዘውጌ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ይዟል።  የጋምቤላ እና  የቤንሻንጉል  ጉሙዝ ክልሎችም  የተለያዩ የዘውጌ ቡድኖች መኖርያ ናቸው።  ነገር ግን የክልላዊ መንግሥታት ስያሜ እና ክለላ ይህን የብዝሃነት እዉነታ አያንፀባርቅም። የትግራይን ክልላዊ መንግስት  “ብሔራዊ ”  በሚል  ከፍታ አስቀምጦ  ጋምቤላን “የብሔረሰቦችእና ህዝቦች  ክልል ብሎ መሰየም  የምስቅልቅሉ ሁነኛ ማሳያ ነው።  ከፊት ለፊት ሲታይ ችግሩ  የፅንሰ-ሃሳብ ግልፅነት (conceptual clarity) ሳይኖር ህገ-መንግስቱ በመተርጎሙ የመጣ ይመስላል። ሸፍጥ የለበትም ብሎ መደምደም ግን አይቻልም።
በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ ዊል ኪምሊካ የተባለ የዘርፉ ተመራማሪ በመድብለ-ዘውጌ ማህበረሰብ  ዉስጥ በቁጥር እና ንቃተ-ህሊና ከፍ ያሉ የዘውጌ ቡድኖች ብሔር ሲባሉ ቀሪዎቹ ብሔረሰብ (nationality) ተብለው ሊሰየሙ ይቻላል ይላል። ነገር ግን ፍረጃው ሳይንሳዊ አይደልም፣ አያሳምንም። አንድ ዘውግ አናሳ የሚባለው መቼ ነው? ሰያሚውስ ማነው? ፖለቲካዊ ንቃተ-ሕሊናስ በምን ይለካል? ኢትይጵያ ዉስጥ ኦሮሞ እና አማራን ብሔር፣ ጋሞ እና ስልጤን ደግሞ ብሔረሰብ ብሎ ለመለየት አሳማኝ ቀመር የለም።
 አክራሪው የዘውጌ  ፖለቲካችን  የሳታቸው አምስት ቁምነገሮች 
በሰው ልጅ ታሪክ ለረጅም ግዜ ፖለቲካዊ ቅቡልነት (legitimacy) ምንጩ እግዚአብሔር ወይም ስርወ-መንግስት ነበር። ባንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች አሁንም የስልጣን ምንጭ ደም ወይም ፈጣሪ ቢሆንም በአብዘሀኛው ዘመናዊ ፖለቲካ መሰረቱ በማንነት ዙሪያ የተሰባሰበ ሕዝብ ነው። የሙያ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ጥቁሮች ፣ ወግ አጥባቂዎች ወዘተ በፖለቲካው ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩት በማንነት ስም በሚሰበስቡት ድምፅ ነው። በኢትዮጵያም የስልጣን ምንጭ እግዜር ነበር። ቆይቶ ርዕዮተ-ዓለም ሆነ። አሁን የሁሉም ነገር ምንጩ ዘውግ ሆኗል። መጀምርያ የስታሊንን የብሔር ፖለቲካ የሸመደዱ የ1960ቹ ተማሪዎች የዘውዱን ስርዓት በብሔር እና መደብ ጭቆና ስም ታገሉት።  የመደብ ጭቆናው በወታደራዊ መንግስት ሲመለስ ዘውጌዎቹ የብሔር ጥያቄ አንጠልጥለው በረሃ ገቡ፣ አሸነፉበትም። አሸናፊዎቹ በተራቸው ፍላጎታቸውን በሌሎቻችን ላይ ጫኑ። ተጨቋኞቹ ሌላ ዙር ትግል አድርገው ዛሬ ላይ ደርሰናል። አሁንም የፖለቲካ ችግራችን እንደተወሳሰበ ነው።  በኔ እይታ ያልተገራ እና መሬት ያልያዘ  የዘውጌ ፖለቲካ ለችግራችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። አምስት መከራከርያ ነጥቦችን ላንሳ።
አንደኛ ማንነት ሰው ሰራሽ እንደመሆኑ ቋሚ አይደልም። የታሪካዊ ግስጋሴ (historical progress)  በህዝቦች ዉህደት እና የባህል ዉርስ ይገለፃል። ለምሳሌ ብሔር የአዝጋሚ እድገት (evolution)  ዉጤት ነው። ለረጅም ጊዜ በሚዘልቅ  ጥልቅ የህዝቦች መስተጋብር ምክንያት ቤተሰብ ወደ ጎሳ፣ ጎሳም ወደ ዘዉግ፣ ዘዉግም ወደ ብሔር ያድጋል። ቁሳዊ ልማት እና የባህል ሽግግርም እንዲሁ ወሳኝ ነው። በነዲክት አንደርሰን ‘ብሔር ምናባዊ ማሕበረሰብ’ ነው ሲል ስሪትነቱን ለመጠቆም ነው።  ዛሬ ጥቁር፣ ነጭ፣ ምስራቃዊ (oriental) ወዘተ የምንላቸው የሰው ዘር ፈርጆች እንኳ ከሁለት ሚሊንየም በፊት አልበሩም። በምዕራብ አዉሮፓም ጎሳ፣ ዘውግ እና ነገድ  ታሪካዊ ሂደቱን ተከትሎ ወደ ብሔር አድጓል ።  ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ እና ጣልያን የመሳሰሉት ሃገራት የግዛት ወሰናቸውን ከብሔር ክልል ጋር በማጣጣም ወጥ መንግስታዊ  አስተዳደር ወይም ብሔረ-መንግስት (nation-state) መስርተዋል።  የፈረንሳይ ብሔር ጉዓል፣ ሮማን፣ ብርቶን፣ ተኦቶን የመሳሰሉ ነገዶችን እና ጎሳዎችን በሂደት አዋህዶ የተፈጠረ ነው። የጣልያን ብሄርም እንዲሁ ሮማን፣ ኢትራስካን፣ ተኦቶን፣ ግሪክ እና አረብ ዘር ያላቸውን ህዝቦች ያዋሐደ ነው። በሌላ በኩል የህዝቦች መስተጋብር ዉስን በሆነባቸው፣ ለረጅም ግዜ ጎልቶ የወጣ ጠንካራ የፖለቲካ ማሕበረሰብ ባልተፈጠረባቸው እና በቁሳዊ ልማት ወደ ሁላ በቀሩ የኤሽያ እና የአፍሪካ ሃገራት ዉስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ ጎሳዎች እና ዘውጌ ማህበረሰቦች መኖራቸው ማኅበረሰባዊ አዝጋሚ ለዉጥ ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ ይጠቁማል። ለምሳሌ በኢንዶነዢያ ከ700 የሚበልጡ እንዲሁም በናይጄሪያ ከ500 የሚልቁ የዘውጌ ቡድኖች ይገኛሉ። የነዚህ ህዝቦች መስተጋብር ፍጥነት እና ዉጤት የሚወስነው በትምሀርት፣ በባህል ና በፖለቲካው ዘርፍ  በሚሰሩ የጋራ እሴት ግንባታ ስራዎች ይሆናል። የሀገራችንም ዕጣ ፈንታ ከዚህ የተለየ አይደለም።
ሁለተኛ ለአክራሪ ዘውጌዎች የመገንጠል መብት (አንቅፅ 39)  ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ነው፣ ግዜውን ጠብቆ እንደሚበትንነን አልታያቸውም፣ አልያም ብንበተን ግድ አይላቸውም። ጎርፍ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንዲሉ፣ ከኛ ቀድመው በሃሳቡ ላይ ሙክረት (experiment) ያደረጉ ከስህተታቸው ለመማር እንኳ ዕድል ሳያገኙ ጠፍተዋል። ፕሬዚደንት ጆሲፕ ቲቶ በ1974 (እአአ) የብሔሮች እና ብሔረሰቦች የመገንጠል መብት በሕገ-መንግስት እንዲረጋገጥ ሲያደርግ ሃገሩ ዩጎዝላቪያ ከ17 ዓመታት ቡሁላ እንደምትበተን አልተረጠረም። የሶቭየት መሪዎችም በ1977 (እአአ) ባሻሻሉት ህገ-መንግስት የህብረቱ አባላት ባሻቸው ግዜ የመገንጠል መብት እንዳላቸው ሲዉጁ ከ14 ዓመታት ቡሁላ ግዛታቸው ከ15 ቦታ እንደሚፈረካከስ አልታያቸውም። ሃሳቡ እነሱን እንዳጠፋቸው እያወቅን ራሳችንን ለማዳን ሌላ አማራጭ መንገድ አለመከተላችን ግራ ያጋባል (የኛ ህገ-መንግስት ሲጸድቅ ከዩጎዝላቪያ እና ሶቭየት ህብረት ፍርስራሽ አዳዲስ ሃገራት እየተመሰረቱ እንደነበር ልብ ይሏል)። ሌላው አስገራሚው እና ከንካኙ ነገር ደግሞ ከ80 በላይ የዘውጌ  ቡድኖች በሚኖሩባት ሀገር የመገንጠል ሀገ-መንግስታዊ መብት  የተረቀቀው ሁለት ቡድኖች ብቻ በሚወክሉት ህወሓት እና ኦነግ ነበር። ብዙሃኑ ድምፅ አልበረውም። ዳግም ዕድል ሊሰጠው ይገባል። በኢትዮጵያ ጉዳይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርሻ እንዳለው በተግባር መገለፅ አለበት።
ሶስተኛ አክራሪ የዘውጌ ፖለቲካ ለዉህድ፣ ንዑስ እና ተደራቢ ማንነት ቦታ የለውም፤ ትኩረቱ ነጠላ፣ ጠባብ እና ‘ንፁህ’ ማንነት ላይ ነው። ከዘውግ ባሻግር ሕልዉና ያላቸውን እንደ አዲስ አበባዉያን ያሉ ኮስሞፖሊታን ማህበረሰቦች እና የተውልድ ሃረጋቸውን ከተለያዩ የዘውጌ ቡድኖች የሚስቡ ግለሰቦችን ፍላጎትና ምርጫ አያስተናግድም።  አንድ ተጨባጭ ምሳሌ ላንሳ፣ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ የሚኖር ራያ የሚባል ማህበረሰብ አለ። በታሪክ አጋጣሚ በትግራይ እና አማራ ክልሎች ለሁለት ተከፍሎ ይኖራል። በቅርቡ የራያን ሕዝብ ወደ አንድ አስተዳደራዊ መዋቅር ለማምጣት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ሁለት ኃይሎች ፅንፍ ይዘው ቆመዋል። ህወሓት “ራያ የሚባል ማንነት የለም፣ ራያ ትግሬ ነው” ሲል፣ አብን (አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) ደግሞ “ራያ የሚባል ማንነት የለም፤ ራያ አማራ ነው” ብሎ ሌላ ጫፍ ይዟል። የራያን ኦሮሞነትም የበለጠ ለማጉላት የሚጥሩ የዘዉጌ ፖለቲከኞች አሉ። እዉነታው ግን ራያ ከአማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አፋር እና አገው የሚወለድ ሕብራዊ ዉህድ ማንነት ያለው ሕዝብ ነው። ከማህበረሰቡ  ባህላዊና ታሪካዊ መስተጋብር አንፃር ለራያ የሚስማማው ዜግነትን መሰረት ያደርገ ብሄርተኝነት ነው። የማንነት ሁሉ መለክያ የግድ ዘውግ ብቻ መሆን ስለሌለበት የራያ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ባነሰ ማንነት ራሱን ይግለፅ ከተባለ ራያ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። ከዚህ ዉጭ በአንድ ዘውግ ወይም ‘ብሔር’ ስም ይጠራ  ቢባል የዘውግ ሃረጋቸውን  ከሌላ አቅጣጫ የሚስቡ የማህበረስቡን ክፍሎች ማግለል ይሆናል።  የዚህ ክትለት (implication) ግልፅ ነው፡ ራያን የመሰሉ ዉህድ ኢትዮጵያዉያን በማንነት ፖለቲካ ባግባቡ አይስተናገዱም፣ ይጠባቸዋል።
አራተኛ አክራሪ የዘውጌ ፖለቲካ ሃገራዊ ብሔርተኝነትን እንደመዳረሻ አያይም። ይባስ ብሎም የትግል ኢላማው ለአንድነት በሚሰሩ የፖለቲካ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ ነው። የኦሮሞ፣ የትግራይ እና የአማራ ዘውጌዎች  ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል አድርገው በተነሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ የሚያደርጉት አፍርሽ ቅስቀሳ የዚሁ ችግር ማሳያ ነው። በመሰረቱ ሃገራዊ ብሄርተኝነት እና የዘውጌ (ethnic) ማንነት አይቃረኑም። በብልሃት ከተያዙ ተመጋጋቢ ሆነው መኖር ይችላሉ። ዮሩባው ናይጄሪያዊነቱን፣ ፑንጃቢው ህንዳዊነቱን እንዳልጣለ ሁሉ ኦሮሞውም ሆነ አማራው ኢትዮጵያዊነቱን እና ንዑስ ማንነቱን አስማምቶ  መኖር ይቻለዋል። መሬት ላይ ያለው እውነታም ይህንኑ እንድናደርግ ያስገድደናል። ከፖለቲካው ዲስኩር ባሻገር፣ በተግባር ሀልዉናችን የተሳሰረ ነው።
በመጨረሻም የማንነት ፖለቲካ ‘የኔ’ ከሚለው ቡድን ያልተገደበ እሽታ ይጠብቃል። ልዩነትንና   የሃሳብ ፍጭትን አያስተናግድም። ይህ አጉል ተስፋ ከሰዋዊና ማህበረሰባዊ ተፈጥሯችን ጋር አይገጥምም።  የሰው ልጅ ከራሱ ጋር እንኳ  ፍፁም አንድነት መፍጠር አይችልም። የ10 ደቂቃ ጥሞና  (meditation) ለማድረግ የተቀመጠን ይህን እዉነታ በተግባር እናውቀዋለን። እንደ ነፋስ የሚበተነውን ሃሳባችንን ሰብስበን ማቆም ፈታኝ ነው። ይህ እንግዲህ ከራስ ጋር ለመግባባት የሚደረግ ትግል ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ጃቆስ ላካን the mirror stage በሚለው የሰውን ልጅ እድገት  ባብራራበት ንደፈ ሐሳቡ ዉስጣዊ ስሜት እና ዉጫዊ ስሌት ብዙውን ግዜ አይጣጣሙም፣ እንዲያ ሲሆን ጭንቀት ይፈጥራል ይላል። ለምሳሌ ዘውጌ-ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴ ግለሰቡ ራሱን የሚያይበት ማህበራዊ መስታዉት ነው። እንደ አባል ተስፋውን እና ምኞቱን ይገልፅበታል፣ ያነብበታል። እንደግለሰብ ደግሞ መስታዉቱ የማያሳይለት ዉስጣዊ ፍላጎት እና ትግል ይኖረዋል። የዉስጡን እና የዉጩን  ሙሉ ለሙሉ  ማገጣጠም የሚቻል አይደለም።  ፖለቲካዊ አንድምታው በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ ከሌሎች ፍፁም አንድነትን መጠበቅ እንደሌለብን ነው። ዘውጌዎች ይህን እዉነታ አይቀበሉም። የነሱን ቋንቋ የሚናገር ሁሉ እንደነሱ እንዲያስብ፣ እንዲሰማው እና እንዲያደር ይጠብቃሉ።
ከዚህ ወዴት
ዘግይቶም ቢሆን ኢህአዴግ ሃገራዊ ማንነትን ችላ ማለት የሚያስከትለው አደጋ ተገልጦለት ነበር። በስልጣን ላይ የነበሩት ኃይሎች ከሁለት ዓመት በፊት አዲስ ራዕይ በምትባል የንድፈ-ሃሳብ መፅሄታቸው በኢትዮጵያዊነት ተኮትኩቶ ያላደገ ወጣት የዘውጌ ወጀብ ቀስቅሶ ሊያጠፋቸው አንደደረሰ ተናዘዋል። የፈሩት አልቀረም፣ ድምፅ አልባው አብዮት ገፍቶ ዳር ጥሏቸዋል። ዉጤቱም ተስፋና ስጋት ወልዷል። በደቡብ ማቆምያ የሌለው የክልልነት ጥያቄ፣ በሰሜን የምናየው እልህና ፍጥጫ፣ በምስራቅ በኩል ሕይወት የቀጠፈው የወሰን ግፍያ፣ በምዕራብ የሚርመሰመሰው ደም አፍሳሽ አማጺ፣ በመሃል የሚራገበው ፅንፈኛ ዘውጌነት ወዘተ ከለት ወደለት የለውጥ ተስፋችን በስጋት እንዲደበዝዝ አድርጎታል። በግዜ ካተገራ በየአቅጣጫው የጦዘው ግለኝነት ሃገር ሊያፈርስ ይችላል።
ከዚህ ስጋት በመነሳት  ይጠቅሙ ይሆናል ያልኳቸውን ሶስት ነጥቦች አንስቼ ሃሳቤን ላጠቃል። አንደኛ በኔ እይታ ለኛ የሚሻለን በመድብለ-ዘውጌ ዴሞክራሲ (multi-ethnic democracy) ማዕቀፍ ሀገራዊ ብሄርተኝነትን ኮትኩቶ ማሳደግ ነው። በህንድ እና መሰል ሃገራት ተተግብሮ እንዳየነው መድብለ-ዘውጌ ዴሞክራሲ ሃገራዊ እና የዘውጌ ማንነቶችን ሚዛን ጠብቆ የመያዝ ብቃት አለው። የግለሰብ እና የቡድን መብቶችን አጣጥሞ ያስተናግዳል። መርሆው ተጓዳኝ እና ተደራቢ ማንነት ያላቸውን የተለያዩ የማህበረሰቡ አባላት በእኩል ዜግነት የሚያስተናግድ የፖለቲካ ስርዓት እዉን ማድረግ ነው። አካታችነቱ እንዳለ ሆኖ ስኬታማ መድብለ-ዘውጌ ዴሞክራሲ ለጋራ እሴቶች ግንባታ እና ጥበቃ ልዩ ትኩረት ይሰጣል። በስምምነት የሚፈጠር የጋራ እሴት ማዕከላዊ ይሆንና የዳርቻውን ማንነት  በአዝጋሚ ስበት ያስገባል። በሂደቱም በማንነት ላይ ሳይሆን መርህ ላይ የቆመ፣ የግለሰብና  የቡድን መብቶችን አማዝኖ የሚያስተናግድ  የዜግነት ፖለቲካ እዉን ይሆናል።
ሁለተኛ በዜግነት ፖለቲካ የተቃኘ መድብለ-ዘውጌ ዴሞክራሲ ለመገንባት ህገ-መንግስቱን ማሻሻል ቁርጠኝነት የሚጠይቅ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው። ከማሻሻያው ሥራ በፊት ግን ሕዝባዊ ምክክር ያስፈልጋል። ልሂቃኑ  የሃሳብ መሪነቱን ድርሻ ይዘው አወዛጋቢ የሆኑት ጉዳዮች በስፋት ዉይይት ቢደረግባቸው ህዝቡ በእዉቀት ተመስርቶ ለማሻሻያው ድጋፍም ሆነ ተቃዉሞ ማድረግ ይችላል። ሁሉም ባለድርሻ አካልት (ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን ወዘተ) ቁልፍ በሆኑ ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ላይ ባደባባይ ሲሟገቱ  አስተፃምሮው (the synthesis) ለዉሳኔ የሚጠቅም አሳማኝና አስተማማኝ እዉቀት ይፈጥራል። የሀገርን ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ በእዉቀት ላይ ተመርኩዞ የሚሰራ ፖለቲካ አማራጭ የለውም።
በመጨረሻም በፖለቲካ መግለጫችን፣ ትንታኔችንና ዲስኩራችን የምንጠቀማቸው ቃላት እና ፅንሰ-ሃሳቦች ግልፅና አግባቢ መሆን ይኖርባቸዋል። ዓለም በቃል ይፈጠራል ነውና በትርጉም ካልተግባባን በተግባር መተላለፋችን የግድ ነው። ለምሳሌ ከላይ እንደጠቀስኩት ህገ-መንግስቱ ‘ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ’ ብሎ የሚጠራቸው ስብስቦች በተጨባጭ እነማን እንደሆኑ ግልፅ አይደልም። ፅንሰ-ሃሳቡ ከነፍቹ ከዉጭ ተቀድቶ የገባ በመሆኑ ከኛ እውነታ ጋር አልገጠመም። ሌላም የተለመደና ችግር ያለበት አባባል አለ። ከተለያየ የዘውጌ ቡድኖች (ethnic groups) ብንወለድም ኢትዮጵያውያን ዘራችን አንድ ነው፣ ጥቁሮች ነን።  ስለዚህ በተለምዶ እንደሚባለው በሽታችን  ዘረኝነት ሳይሆን አክራሪ ዘውጌነት (ethnic extremism) ነው።  ችግራችንን በትክክለኛ ስሙ  መጥራት አንድ እርምጃ ወደ መፍትሔው ስለሚያቀርበን የፖለቲካ እና የፖሊሲ  ውይይታችን ለጠራ ሃሳብና አመንክዮ ትኩረት መስጠት አለበት።