Sunday, March 30, 2014

የቀድሞው የጋምቤላ ፕሬዚዳንት ደቡብ ሱዳን ከሆቴል ውስጥ ታፈኑ “ወያኔ እጅ ገብተዋል” ጎልጉል by ምንሊክ ሳልሳዊ

የጋምቤላ ክልልን ሲመሩ ቆይተው ባለመስማማት የኮበለሉት የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት ደቡብ ሱዳን ከሆቴል ውስጥ ታፍነው መወሰዳቸው ተጠቆመ። ዜናው በገለልተኛ ወገን ባይገለጽም ኖርዌይ በስደት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይ በኢህአዴግ በጥብቅ የሚፈለጉ ሰው ነበሩ።
በመለስ ዜናዊ ውሳኔ በአኙዋክ ተወላጆች ላይ በጅምላ የተከናወነውን ጭፍጨፋ አስመልከቶ ተቃውሞ በማሰማት የኮበለሉት አቶ ኦኬሎ ወደ ደቡብ ሱዳን ከማምራታቸው በፊት ኬንያ እንደነበሩ፣ ከኬንያ ወደ ደቡብ ሱዳን ለምን እንደተጓዙ የዜናው ምንጮች በይፋ ከመናገር ተቆጥበዋል። ስማቸው እንዲደበቅላቸው የጠየቁ የጋምቤላ አስተዳደር ባልደረባ ለጎልጉል የአካባቢው ዘጋቢ እንደተናገሩት አቶ ኦኬሎ ደቡብ ሱዳን ሆቴል በተቀመጡበት መታፈናቸውን አረጋግጠዋል።
“ወያኔ እጅ ገብቷል” ሲሉ ያከሉት እኚሁ ሰው “አቶ ኦኬሎ ብረት በማንሳት ወያኔን ለመታገል ከተነሱ ጋር ተቀላቅለዋል በሚል ስማቸው መመዝገቡንና ወደ ደቡብ ሱዳን ማቅናታቸው በመታወቁ ህወሃቶች እጅ ሊወድቁ ችለዋል” ብለዋል። ምንጩ ይህንን ይበሉ እንጂ አቶ ኦኬሎ አክዋይ ወደ ደቡብ ሱዳን ያቀኑበትን ምክንያት በርግጠኛነት ሃላፊነት ወስዶ የገለጸ ወገን አልተደመጠም። ኢህአዴግም ቢሆን የቀድሞውን ሹመኛ ስለመያዙ ይፋ ያደረገው ነገር የለም። ከደቡብ ሱዳን ቀውስ ጋር በተያያዘ የኑዌር ተወላጅ ከሆኑት ሬክ ማቻር ጦር ጋር በመሰለፍ የሳልቫ ኪርን ሃይል ሲወጉ ከተገደሉ ወታደሮች መካከል የኢህአዴግን ሰራዊት መለያ የለበሱ ኑዌሮች መገኘታቸው ውዝግብ አስነስቶ እንደነበር ያመለከቱት ምንጭ “ደቡብ ሱዳን እየወጋት ካለው ኢህአዴግ ጋር አብራ የቀድሞውን የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳደር ከምድሯ ላይ እንዲታፈኑ መፍቀዷ ቅሬታ ያስነሳል” ብለዋል።
ከቤተሰባቸው ተነጥለው በስደት ከሚኖሩበት ኖርዌይ ወደ ደቡብ ሱዳን ያመሩት የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ደቡብ ሱዳን በህወሃት ሙሉ ቁጥጥርና ፈቃድ የምትንቀሳቀስ አገር መሆኗን እያወቁ ወደዛ ማቅናታቸውን ባሥልጣኑ “ታላቅ ጥፋት” ብለውታል። ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። በቅርቡ አቶ ኦሞት ኦባንግ መኮብለላቸውና በብዙዎች ዘንድ አውሮጳ እንዳሉ ቢነገርም በትክክል ያሉበት አገር በይፋ አለመታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።
ምንሊክ ሳልሳዊ | March 28, 2014 at 10:45 pm | URL: http://wp.me/p2gxmh-4fp



Comment   See all comments

Sunday, March 23, 2014

20 ዓመት ሙሉ ውህደትና ጥምረት ያልሰመረለት የተቃዋሚ ጎራ (ኤልሳቤጥ እቁባይ እና አለማየሁ አንበሴ)


20 ዓመት ሙሉ ውህደትና ጥምረት ያልሰመረለት የተቃዋሚ ጎራየሐሙሱ የመኢአድና አንድነት ውህደት ሳይጀመረ ፈረሰ
ምርጫን ብቻ ግብ ያደረጉ ጥምረቶች ዋጋ አይኖራቸውም
የፓርቲዎች ውህደት ባይሳካም የተገኘው ልምድ ቀላል አይደለም
ለተቃዋሚዎች አለመጠናከር ኢህአዴግ ተጠያቂ ነው
“በሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካ ብዙ ዘመን አስቆጥሯል ማለት
ባይቻልም በአሁኑ ጊዜ ፓርቲዎች ማደግ ሲገባቸው እየቀጨጩ ነው፣ በሜዳው ላይ መኖር የማይገባቸው ፓርቲዎችም አሉ፡፡ ፕሮግራማቸው አንድ ሆኖ እንኳ ተከፍለው መንቀሳቀሳቸው ትክክለኛ አካሄድ ካለመሆኑ በተጨማሪ ለገዥው ፓርቲም የስልጣን እድሜን እየሰጠ ነው ያሉት ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራረርነት ቆይተው አሁን ላይ ከፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸው ያገለሉት ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም ናቸው፡፡
አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) እና የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ውህደት ይፈፅማሉ ተብሎ ሲጠበቅ መኢአድ ለአንድነት በፃፈው ደብዳቤ፣ ውህደቱ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን አስታውቋል፡፡ በመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኃሪ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ የፕሮግራምና የደንብ ጉዳይ፣ የስያሜ፣ የኃላፊነት፣ አንድነት ከመድረክ ጋር ስላለው ግንኙነት እንዲሁም የንብረት ጉዳዮችን በተመለከተ ተጨማሪ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል፡፡
ረቡዕ እለት ደብዳቤው እንደደረሳቸው የገለፁት የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ ስዩም መንገሻ፤ እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም የሁለቱም ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በመኢአድ ፅ/ቤት ተገናኝተው ባካሄዱት የጋራ ውይይት ላይ ድርድሩ ማለቁን በማመልከት፣ ውህደቱ ከመጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም እንዳያልፍ አሳስበው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
“አባላቱ በጥቃቅን ምክንያት ውህደቱን እንዳታሰናክሉ የሚል ማሳሰቢያ ሠጥተውን ነበር” ያሉት አቶ ስዩም፤በዚህ መሰረት አንድነት አስፈላጊ ዝግጅቶችን አጠናቆና  የሆቴል አዳራሽ ተከራይቶ ካጠናቀቀ በኋላ ደብዳቤው እንደደረሰው ተናግረዋል፡፡ “አሁን ኳሱ በመኢአድ እጅ ነው ያለው” ያሉት አቶ ስዩም፤ በአንድነት በኩል እንደ ምክንያት የተጠቀሱት ጉዳዮች በድርድሩ እልባት አግኝተዋል የሚል እምነት አለ ብለዋል፡፡
የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኃሪ በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በወጣ አንድ ጋዜጣ ላይ በአንድነት በኩል “ከመድረክ ጋር እንቀጥላለን” የሚል መግለጫ በመሰጠቱ ውህደቱን ልናዘገየው ተገድደናል ብለዋል።    “ድርድሩ ቆሟል ማለት አይደለም፤ይቀጥላል ነገር ግን መኢአድ በደብዳቤው የጠየቃቸው ካልተሟሉ ውህደቱ ላይፈፀም ይችላል” ብለዋል-ፕሬዚዳንቱ፡፡
ውህደት፣ቅንጅት፣ጥምረት…
ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ከተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የመላ አማራ ህዝብ ድርጅት (መአኅድ) ሲሆን ነሐሴ 5 ቀን 1994 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት በመለወጥ መኢአድ በሚል ስያሜ እንደሚንቀሳቀስ ይፋ አደረገ፡፡ ይሄኔ በአባላቱ መካከል ክፍፍል ተፈጠረ፡፡ መኢአድ ሆኖ ከተዋቀረ በኋላ በልዩነት ከፓርቲው የወጡ ሰዎችም ኢዴአፓን አቋቋሙ፡፡  ኢዴአፓ፤ከኢዲዩ፣ ከኢዳግ እና ከመድህን ጋር ውህደት ፈፅሟል፡፡ መስከረም 20 ቀን 1997 ዓ.ም ኢዴአፓ (ከመኢአድ የወጣ) እና መድህን መዋሀዳቸውንና  በግንቦት ወር የሚከናወነው ምርጫ፤ ነፃና ሚዛናዊ እንዲሆን  በመንግስት በኩል መሟላት ያለባቸው ጥያቄዎች ቢኖሩም በምርጫው እንደሚሳተፉ ገለፁ፡፡
ውህደታቸውን ተከትሎም ዶክተር አድማሱ ገበየሁ ፕሬዚደንት፣ ዶክተር ኃይሉ አርአያና ዶክተር ጎሹ ወልዴ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም አቶ ልደቱ አያሌው ዋና ፀሀፊ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ በዛው ሰሞን ኢዴአፓ፣መድህንና መኢአድ ለመዋሃድ ያደረጉት ሙከራ ጫፍ ላይ ከደረሰ በኋላ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ጥቅምት 1997 ዓ.ም ኢዴአፓ መድህን፣ መኢአድ ኢድሊ እና ቀስተ ደመና ቅንጅትን መስርተው ኢህአዴግን በግንቦቱ ምርጫ በብርቱ ለመፎካከር መዘጋጀታቸውን አስታወቁ፡፡ ህዳር 9 ቀን 1997 ዓ.ም አራቱ ፓርቲዎች በምርጫው ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ በሚል ስያሜ ለመወዳደር መወሰናቸውን በፊርማቸው አረጋገጡ፡፡ በምርጫው ቢሸነፉ እንኳን ተዋህደው አንድ ፓርቲ የመሆን የረጅም ጊዜ እቅድ እንዳላቸውም አስታወቁ፡፡ ቅንጅቱ አልፎ አልፎ ከሚሰሙ ልዩነቶች ውጪ ብዙዎችን ከጎኑ በማሰለፍ እና  ደጋፊዎችን በማሰባሰብ፣ ኢህአዴግን የሚገዳደር ጠንካራ ፓርቲ ሆነ፡፡ ምርጫው ግንቦት ተካሂዶ ሰኔ ላይ የልዩነት ወሬዎች በስፋት መውጣት ጀመሩ፡፡ በዚያው ወር መኢአድ በውስጣዊ ችግር መተብተቡ የተነገረ ሲሆን ድርጅቱን ከመፍረስ ለመታደግ ኮሚቴ አቋቁሞ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ የቅንጅቱ ክፍፍል እየተብላላ ቆይቶ ጥቅምት ላይ ከኢዴአፓ መድህን አቶ ልደቱ አያሌውንና አቶ ሙሼ ሰሙን አገደ፡፡
የቅንጅት አመራሮች ከታሰሩ በኋላ የተወሰኑ  ፓርላማውን የተቀላቀሉ የቅንጅቱ ተመራጮች  ኢዴፓ፣ የፓርላማ ቡድን፣ መኢአድ  እና ቅንጅት በሚል ተከፋፍለው መቀመጫቸውን ያዙ፡፡ ምርጫ 2002 ዓ.ም ሲቃረብም ምርጫን ዓላማ ያደረጉ የትብብር ስምምነቶች፣ ግንባር እና መድረክ መፍጠር እንዲሁም መቀናጀት ይፋ ተደረጉ፡፡ ህዳር 25 ቀን 2002 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት በግንባር ደረጃ ተቀናጅተው እንደሚንቀሳቀሱ ገለፁ፡፡ የካቲት 21 ቀን 2002 ዓ.ም በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ አምስት የኦሮሞ ድርጅቶች- የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ አንድነት ነፃነት ግንባር፣ የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ፣ የኦሮሚያ ነፃነት ብሄራዊ ፓርቲ እና የመላው ኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ለቀጣዩ ምርጫ በቅንጅት ለመንቀሳቀስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ፡፡
አንድነት ከተቋቋመ በኋላም በታህሳስ 2001 ዓ.ም “መርህ ይከበር” የሚል መሪ ቃል ያነገቡ ወገኖች ከፓርቲው ወጥተው ሰማያዊ ፓርቲን አቋቋሙ፡፡ በሰኔ 2000 ዓ.ም መድረክን ለማቋቋም መምከር ተጀመረ፡፡ የካቲት 2001 ዓ.ም ደግሞ የስድስት ፓርቲዎች ጥምረት ተመሰረተ፡፡ መስከረም 24 ቀን 2003 ወደ ግንባር ተሸጋገረ፡፡ በያዝነው ዓመት አንድነት ከመድረክ የታገደ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ  ከመኢአድ ጋር ውህደት ለመፈፀም በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
“ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ፓርቲዎች የተጓዙበት መንገድ ሲገመገም፣ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ተጨባጭ ውጤት አላመጣም፡፡ ንቅናቄያቸውም በየጊዜው እየቀጨጨ የሚሄድ ሲሆን  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ አብሮ ለመስራት ያላቸው ተነሣሽነትና ፍላጐት የተዳከመ ብሎም ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ የደረሰ ነው” ይላሉ - የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኃሪ፡፡
ባለፉት 23 አመታት በሀገሪቱ ያሉ ዋና ዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲቀናጁ፣ ሲጣመሩ፣ ሲዋሃዱ  ሲፈርሱ ነው የኖሩት፡፡ አቶ አበባው እንደሚሉት፤ለዚህ ምክንያቱ ከሃገራዊነት ስሜት ይልቅ የግለሰቦች ስሜትና ፍላጐት አይሎ መውጣቱ ነው፡፡ “የተሞከሩት ቅንጅቶች እና ጥምረቶች በሙሉ ሴራ ያልተለያቸው፤ የግለሰቦችን ፍላጐት ብቻ ጠብቀው የተፈጠሩ በመሆኑ በትንሽ ተንኮል ይፈርሳሉ፡፡ ዛሬ  ይህ ተንኮል ይበልጥ መልኩን ቀይሮ ተባብሮ ለመስራት ሳይሆን አንዱ ሌላውን ፓርቲ ለመውረስ ነው የሚጥረው” ብለዋል - አቶ አበባው። በ1997 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ከፍተኛ የፖለቲካ መነቃቃት የፈጠረው ቅንጅት፤ የፈረሰበት ምክንያትም በዚህ መሰሉ ሴራ ነው ይላሉ - ቅንጅቱ ፓርቲዎች ሠምና ወርቅ ሣይሆን ውሃና ዘይት ሆነው የተቀናጁበት መሆኑን በመጠቆም፡፡
በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት መኢአድ የስበት ማዕከል ሆኖ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ አበባው፤ፓርቲው ከሌሎች ጋር ለመጣመርና ለመዋሃድ ያደረጋቸው ሙከራዎች ያልሰመሩት ፓርቲዎች ወደ መኢአድ ሲመጡ በቅንነት ሳይሆን ህልውናውን በሚፈታተን መልኩ ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ሠላማዊ ትግሉ በእነዚህ ምክንያቶች ውጤት አልባ ሆኖ ቆይቷል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለውጤት አልባነቱ ኢህአዴግም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ ይወቅሣሉ፡፡ “የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆነ ገበሬ፣ መሬት እና የግብርና ግብአቶች እንዳያገኝ፣ የመንግስት ሠራተኛ ከሆነ ከስራው እንዲፈናቀል፣ እርዳታ ፈላጊ እርዳታ እንዳያገኝ እየተደረገ፣ ሰዎች በነፃነት መብታቸውን እንዳያስከብሩና በፈለጉት የፖለቲካ ፓርቲ ጥላ ስር እንዳይሰባሰቡ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ፈጥሯል” ሲሉ ይኮንናሉ፡፡ ኢህአዴግ  ባለፉት 23 አመታት በትጋት ተቃዋሚዎችን ለማቀጨጭና ከተቻለውም ለማጥፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሲሠራ፤ ህብረቶችንና ቅንጅቶችን በሴራ ሲያፈርስ ነው የኖረው ሲሉም አምርረው ይወቅሳሉ፡፡
“ለዲሞክራሲ ምቹ የሆንን ሰዎች አይደለንም” የሚሉት አቶ አበባው፤ ከጥቂት አመታት በፊት በጦርነት ሲታመሱ የነበሩ እንደ ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን የመሳሰሉ ሃገሮች እንኳ ከኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ ዲሞክራሲን እየተገበሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ ተቃዋሚ ሆኖ ለዲሞክራሲ የሚደረግ ትግል ውስጥ ውጤት ለማምጣት ብዙ ሂደቶችን ማለፍ እንደሚጠበቅ ገልፀው፤ በዚህ ረገድ የሚፈለገውን ያህል ተስፋ የሚሠጥ ባይሆንም ህዝቡን በማነቃቃት ረገድ ተቃዋሚዎች የነበራቸው ሚና የሚዘነጋ አለመሆኑን አቶ አበባው አመልክተዋል፡፡
ቀደም ሲል የመኢአድ አባል በመሆን በፓርቲው ውስጥ ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ በተፈጠሩ አለመግባባቶች አዲስ ፓርቲ ወደማቋቋም ከተሸጋገሩት አቶ ልደቱ አያሌውና ሌሎች ግለሰቦች ጋር በመሆን የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን (ኢዴፓ) የመሠረቱት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ ባለፉት 23 አመታት በመቀናጀት፣ ግንባርና ጥምረት በመፍጠር ረገድ ውጤት ያመጣና አላማውን ያሳካ ፓርቲ አላየሁም ሲሉ የአቶ አበባውን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ በትንሹ ሊጠቀስ የሚችለው 1997 ላይ የተፈጠረው ቅንጅት ብቻ ነው የሚሉት አቶ ሙሼ፤ እሱም ቢሆን ጠንካራ ስላልነበረ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ መሆን እንዳልቻለ ይገልፃሉ፡፡ በዋናነትም የፓርቲዎች ጋብቻ ውጤታማ የማይሆነው ጥምረታቸው ከፕሮግራም፣ ከአላማ እና ከግብ አንድነት በሚመነጭ ሳይሆን ኢህአዴግን ተሰባስቦ ለማሸነፍ ካለ ፍላጐት ወቅታዊ ጉዳይን ብቻ መነሻ አድርጐ የሚፈጠር በመሆኑ ነው የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ምርጫ ሲደርስ ብቻ ፓርቲዎች ለመቀናጀትና ለመጣመር መሯሯጣቸውም ይህን ያመለከታል፣ ምርጫን ብቻ ግብ ያደረጉ ጥምረቶች  ደግሞ ከምርጫው በኋላ ዋጋ አይኖራቸውም ብለዋል፡፡
“የውህደት ጥምረት እና ቅንጅት ምስረታ ውጥኖች ከሚከሽፉባቸው ምክንያቶች መካከልም ፓርቲዎች አንድነቱን ከመፈለግ ባሻገር ማን አመራር ይሁን በሚለውና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በቂ የስነ ልቦና ዝግጅት አለማድረጋቸው እና አርቆ አለማሰባቸው ዋናው ነው” ይላሉ አቶ ሙሼ፡፡
ፓርቲያቸው ኢዴፓ ከተመሰረተ ጀምሮ ከሶስት ፓርቲዎች ጋር ስኬታማ ውህደት መፍጠሩን አቶ ሙሼ ይጠቅሳሉ፡፡ ከኢዳግ፣ ኢዲዩ እና ከመድህን ጋር ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ውጤታማ ውህደት መፈጠሩን ያስታወሱት አቶ ሙሼ፤ ከመኢአድ ጋርም በ1996 መጨረሻ አካባቢ ለመዋኃድ የተደረገው የድርድር ሂደት 90 በመቶ ከደረሰ በኋላ መክሸፉን ከፓርቲያቸው ያልተሳኩ ተሞክሮዎች አንዱ ነበር ይላሉ፡፡ በወቅቱ መኢአድ እና ኢዴፓ በበርካታ ጉዳዮች ላይ የተስማሙ ቢሆንም በስራ አስፈፃሚ ውስጥ ትልቁ ድርሻ የማን ነው? የሚለውን መሰረታዊ ጉዳይ ጨምሮ ምን አይነት የመንግስት አወቃቀር ሊኖር ይገባል፣በመሬትና በቋንቋ ጉዳይ ላይ እንዲሁም በፓርቲው ስያሜ ልዩነት ተፈጥሮ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ መኢአድ በወቅቱ የመንግስት ስርአቱ ፕሬዚዳንታዊ ይሁን ሲል ኢዴፓ የለም ፓርላሜንታዊ ይሁን በማለቱ የተፈጠሩ የፕሮግራም ልዩነቶችን መነሻ አድርጎ እስከ መዘላለፍና መወነጃጀል የደረሱ አለመግባባቶች መፈጠራቸውንም አቶ ሙሼ ያስታውሳሉ፡፡ ፓርቲያቸው ከቅንጅት ጋር የፈጠረው ጥምረትም በአላማ እና በአካሄድ ልዩነት መክሸፉን አመልክተው፣ ፓርቲው ካደረጋቸው ውጤታማ ውህደቶች መካከልም ከኢዲዩ ጋር የነበረውን ይጠቅሳሉ። በአንዳንድ ግለሰቦች ምክንያት እክል አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም  መፍትሄ አግኝቶ አብሮ መጓዝ እንደተቻለ ያስታውሳሉ፡፡
የእስከ ዛሬው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉዞ ጠቅለል ብሎ ሲገመገም፣ ህዝብን ተስፋ ያስቆረጠ ነበር ያሉት አቶ ሙሼ፤ ከዚህ በኋላም ቢሆን አንድ ላይ ለመስራት ከፍላጎት ባሻገር የስነልቦና ዝግጅት ሳይደረግ የሚፈጠሩ ውህደቶች እና ጥምረቶች ከሚፈለገው ውጤት ላይ መድረስ አይችሉም ይላሉ፡፡ “የተጠናቀረ ፓርቲ መፍጠር ቀላል አይደለም” የሚሉት አቶ ሙሼ፤ 23 ዓመት ኢህአዴግን የሚገዳደር ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር የሚያስችል በቂ ጊዜ ነበር ለማለት አያስደፍርም ብለዋል፡፡ “ማህበረሰቡ ምርጫ ያስፈልጋል ብሎ እንዲያስብ፣ ገዥው ፓርቲ ልጓም አልባ እንዳይሆን በማድረግ በኩል ተቃዋሚዎች የማይናቅ ድርሻ ነበራቸው” ይላሉ አቶ ሙሼ፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በሃገሪቱ ለተስተዋለው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ በስልጣን ላይ ካለው ኢህአዴግ በበለጠ ተቃዋሚዎች ተጠያቂዎች ናቸው የሚሉት ደግሞ የአንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ናቸው፡፡ ህብረት፣ ቅንጅት፣ አማራጭ ኃይሎች፣ መድረክ እየተባለ እስከዛሬ ቢዘለቅም ያስገኘው ውጤት ሲገመገም በዜሮ የሚጣፋ ነው የሚሉት ሊቀመንበሩ፤የፓርቲ አመራሮች ከአመት አመት ከስህተታችን ሳንማር የኢትዮጵያን ህዝብ በድለነዋል፤ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጉጉቱንም አጨልመንበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለኢህአዴግ ጠንካራ መሆን የተቃዋሚዎች ድክመት አስተዋፅኦ ማበርከቱን በአፅንኦት የሚገልፁት ኢ/ሩ፤ ውጤት አልባው ሂደት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቁ አሳዛኝ ታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“በሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካ ብዙ ዘመን አስቆጥሯል ማለት ባይቻልም በአሁኑ ጊዜ ፓርቲዎች ማደግ ሲገባቸው እየቀጨጩ ነው፣ በሜዳው ላይ መኖር የማይገባቸው ፓርቲዎችም አሉ፡፡ ፕሮግራማቸው አንድ ሆኖ እንኳ ተከፍለው መንቀሳቀሳቸው ትክክለኛ አካሄድ ካለመሆኑ በተጨማሪ ለገዥው ፓርቲም የስልጣን እድሜን እየሰጠ ነው ያሉት ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራረርነት ቆይተው አሁን ላይ ከፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸው ያገለሉት ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም ናቸው፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪው ከሆነ የፓርቲዎች ስኬትና ውድቀት የሚያጋጥም ከመሆኑም በላይ በሀገራችን ጠንካራና አስተማማኝ ተቀናቃኝ ፓርቲ ለመፍጠር ጊዜው አልረፈደም፡፡ ከዚህ በፊት የተደረጉ የጥምረት፣ ህብረት፣ ቅንጅት--- ሙከራዎች ፍፃሜ አልሠምር ካለባቸው ምክንያቶች አንዱ የፓርቲ ስልጣን ጥመኝት ነው ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤“ጥመኝነቱ ምናልባትም ብሔራዊ ፀባያችን ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል፡፡ እንደተቀሩት አስተያየት ሠጪዎችም ባለፉት 23 አመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላለመጠናከራቸው ኢህአዴግን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ጠንካራ ከነበረው ቅንጅት መፍረስ ጀምሮ አሁን ድረስ የሚደረጉ ተመሳሳይ ሙከራዎች ስኬት አልባ ለመሆናቸውም የገዥው ፓርቲ ረጅም እጅ አለበት ሲሉ ዶ/ር ያዕቆብ ይወቅሳሉ የፓርቲ አመራሮችን በቅንጅት ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ለእስራት መዳረጉን በዋቢነት በመጥቀስ፡፡
ከኦነግ ታጋይነት እስከ ኢህአዴግ ከዚያም የአገሪቱ ፕሬዚዳንትነት በመጨረሻም የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፤የፓርቲዎቹ የውህደት እና ጥምረት ስኬታማ ባይሆኑም የተገኘው ልምድ የማይናቅ ነው ይላሉ፡፡ ለፓርቲዎች ጥምረት ውጤት አልባነት ዶ/ር ነጋሶ በምክንያትነት ከጠቀሷቸው መካከል በፓርቲዎች መካከል የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ፉክክሮች፣ የስልጣን ጥመኝነት፣ የአላማ እና የአደረጃጀት ግልጽ አለመሆን፣ ህዝቡ ከዳር ሆኖ ከመተቸት ባለፈ በየአደረጃጀቱ ገብቶ ተጽዕኖ ለመፍጠር አለመቻሉ እንዲሁም በፓርቲዎች ላይ ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ህዝባዊ አደረጃጀቶች አለመኖራቸው ይገኙበታል፡፡
የእስከዛሬ የፓርቲዎች የቅንጅት፣ ጥምረት እና ውህደት ውጤት አልባ ናቸው የሚለውን ሃሳብ የሚጋሩት ዶ/ር ነጋሶ፤በግንባር ደረጃ ከተሄደ ግን እስከ ዛሬ ሁለት የግንባር አደረጃጀቶች መኖራቸውን ያስቀምጣሉ። አንደኛው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ሲሆን ሌላኛው “መድረክ” ነው፡፡ የመድረክን ውጤታማነት በተመለከተ በሂደት የምናየው ይሆናል ብለዋል ፤ዶ/ር ነጋሶ፡፡
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳንና የቀድሞውን የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ስየ አብርሀን  በማካተት የቅንጅት አመራሮች ከእስር ከተፈቱ በኋላ የተወሰኑት አመራሮች አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ የሚል ፓርቲ አቋቋሙ። ምርጫ 2002 መቃረቡን ተከትሎ አንድነት ፣ ኦፌዴን ፣ ኦብኮ፣ አረና ተሰባስበው መድረክን አቋቋሙ፡፡
maleda times | March 22, 2014 at 9:27 am | URL: http://wp.me/p2gxmh-498
Comment   See all comments

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ከአውሮፓ ህብረት የ13ሚ. ብር ድጋፍ አገኙ


ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ  ከአውሮፓ ህብረት የ13ሚ. ብር ድጋፍ አገኙ
ያሬድ ዘለቀ Lamb ለሚለው ፊልሙ 12ሚ. ብር አግኝቷል
የኃይሌ ገሪማ “የጡት ልጅ” ቀረፃ  በሰኔ ወር ይጀመራል
የሁለቱም ፊልሞች ቀረፃ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው 
ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የፊልም ፕሮዱዩሰርና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ፤ “የጡት ልጅ” በሚል ርዕስ ለሚሰሩት አዲሱ ፊልማቸው የሚውል የ500 ሺህ ዩሮ (13ሚ. ብር ገደማ)  ድጋፍ ከአውሮፓ ህብረት አፍሪካን ካረቢያን ፓሲፊክ ፈንድ ያገኙ ሲሆን በፈረንሳይ የሚኖረው የፊልም ባለሙያ ያሬድ ዘለቀም Lamb ለሚለው ፊልሙ  መሥሪያ የ495 ዩሮ (12ሚ. ብር ገደማ) ድጋፍ አግኝቷል፡፡
ሳንኮፋ፣ አድዋ እና ጤዛ በተሰኙት ፊልሞቻቸው በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተደናቂነትን የተጎናፀፉትና በርካታ ሽልማቶችን የወሰዱት ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ፤ በቀደምት ኢትዮጵያውያን አኗኗር ላይ የሚያተኩረውን “የጡት ልጅ” የተሰኘ አዲስ ፊቸር ፊልማቸውን ለመስራት የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ ድጋፍ የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ፣ የካሪቢያንና የፓስፊክ ሀገራትን የፊልም ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ከምደባው ገንዘብ ማግኘታቸውን የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ደልጌሽን የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር አቶ ሰለሞን ከበደ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
በለጋ ዕድሜዋ በፊውዳል ባላባቶች ቤት በባርነት ማገልገል በጀመረች አንዲት ልጃገረድ ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥነውና ቀረጻው በመጪው ሰኔ ወር  በባህር ዳር እና በጎንደር ከተሞች የሚጀመረውን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ፣አንድ ዓመት ከስምንት ወር  እንደሚፈጅ ታውቋል፡፡
ተቀማጭነቱን በጀርመን ያደረገውና “ፊልም ፎርም ኮሎኝ ጂኤምቢኤች” የተባለው የፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ የፊልም ኩባንያ፤ ከአውሮፓ ህብረት ያገኘውን የ500 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ ከሚገኘው “ነጎድጓድ” የተሰኘ የፊልም ድርጅትና ከሃይቲው ቬልቬት ፊልም ግሩፕ ጋር በአጋርነት ለሚሰራው ለዚህ የፊልም ፕሮጀክት እንደሚያውለው ተጠቁሟል፡፡
ከአቶ ሰለሞን ከበደ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ይሄን ፊልም  በማዘጋጀት፣ በመቅረጽና በማከፋፈል ሥራ ላይ  ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችና የፊልም ባለሙያዎች ስልጠና የሚያገኙበት አውደጥናቶች ይዘጋጃሉ፡፡
በፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ ከሚሰራው “የጡት ልጅ” በተጨማሪ፣ የዘንድሮውን የአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ ያገኘው ሌላው ኢትዮጵያዊ የፊልም ዳይሬክተር ነዋሪነቱን በፈረንሳይ ያደረገው ያሬድ ዘለቀ ሲሆን “ላምብ” በሚል ርዕስ ለሚሰራው ፊቸር ፊልሙ የ495 ሺህ ዩሮ (12ሚ. ብር ገደማ) ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡
ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ያደረገው የያሬድ “ግሎሪያ ፊልምስ ፕሮዳክሽን”፤ ከኢትዮጵያው “ስለም ኪድ ፊልምስ” እና ከአይቮሪ ኮስቱ “ዋሳካራ ፕሮዳክሽንስ” ጋር በአጋርነት የሚሰራ ሲሆን  ለዚህ የፊቸር ፊልም ፕሮጀክት፣ የ495 ሺህ ዩሮ ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡
እናቱን በልጅነቱ በሞት ከተነጠቀ በኋላ፣ ከአንዲት የበግ ግልገል ጋር ጥብቅ ወዳጅነት በፈጠረ አንድ ኢትዮጵያዊ ብላቴና ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥነው “ላምብ” ፊልም፤በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተሰርቶ የሚጠናቀቅ ሲሆን  ቀረጻው ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡
አጠቃላይ ስራው ከኢትዮጵያና ከአይቬሪኮስት በተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን በሚመራው በዚህ ፊልም ላይ የሚሳተፉት ኢትዮጵያውያን ተዋንያን ሲሆኑ የገንዘብ ድጋፉ የተደረገውም የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ ለማጠናከርና በዘርፉ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ክህሎት ለማሳደግ በሚል እሳቤ መሆኑን ከአውሮፓ ህብረት የኤትዮጵያ ደልጌሽነ የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ከተለያዩ የአፍሪካ የካሪቢያንና የፓስፊክ አገራት ከሚገኙ አመልካቾች የሚቀርብለትን ፊልምና የተለያዩ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል በመገምገም፣ ለተመረጡ ፕሮጀክቶች በየአመቱ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው የአውሮፓ ህብረት፤ ዘንድሮም በተለያዩ ምድቦችና ዘርፎች ለመረጣቸው 37 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በመጀመሪያው ምድብ “የጡት ልጅ” እና “ላምብ’ን ጨምሮ ለዘጠኝ የተለያዩ የአፍሪካና የካረቢያን አገራት ፊቸር ፊልሞች እንዲሁም በሞዛምቢክ ለሚሰራ “ፍሮም ዎር ኤንድ ፒስ” የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ዶክመንታሪ ፊልም የገንዘብ ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡
በዚሁ ምድብ ውስጥ ለተካተቱ ስምንት የተለያዩ አገራት የሲኒማና ኦዲዮ ቪዥዋል፣ የኔትወርኪንግና የፌስቲቫል ዘርፍ ፕሮጀክቶች፤ የማከፋፈልና የፕሮሞሽን ስራ ለማከናወን የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ተበርክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በባለሙያዎች ስልጠናና በሙያ ክህሎት ግንባታ መስክ ከቤልጂየም፣ ከኡጋንዳ፣ ከጣሊያን፣ ከታንዛኒያና ከፈረንሳይ ለቀረቡ አምስት የሲኒማና ኦዲዮ ቪዥዋል ዘርፍ ፕሮጀክቶች ጠቀም ያለ ገንዘብ ተሰጥቷል፡፡
በሁለተኛው ምድብ በክዋኔ ጥበባት፣ በፌስቲቫል ዝግጅት፣ በኔትወርኪንግ፣ በባህል አስተዳደርና በቅርስ ጥበቃ ዘርፎች ለቀረቡ ስድስት ፕሮጀክቶች የማከፋፈልና የፕሮሞሽን ወጪ የሚውል ገንዘብ የተሰጠ ሲሆን፣ በክዋኔ ጥበባት፣ በባህል ልማት፣ በሙዚቃ ኢንዱስትሪና በቅርስ ጥበቃ ዘርፎች ለቀረቡ ሰባት ፕሮጀክቶችም የስልጠናና የሙያ ክህሎት ግንባታ ገንዘብ ተለግሷቸዋል፡፡ በፓሲፊክ አገራት የባህል እድገት ለመፍጠር ለተቀረፀ አንድ ፕሮጀክትም የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
maleda times | March 20, 2014 at 7:01 pm | URL: http://wp.me/p2gxmh-47y
Comment   See all comments

Friday, March 21, 2014

መኢአድ የቅድመ ውህደት ፊርማውን አደናቀፈ



                          አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)                                                     
  UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
በመኢአድ በኩል የቀረበው ቅድመ ውህደት ያለመፈረም ሰበብ አሳዛኝና የሕዝቡን ጥያቄ ያኮሰሰ ነው!!
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ  ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
 
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ለረዥም ዓመታት የሕዝብ ፍላጎትና  አንገብጋቢ የሆነውን ተቃዋሚዎች ‹‹ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ›› ጥያቄ   ለመመለስ በስትራቴጂና አምስት ዓመት ዕቅድ ውስጥ በማካተት መንቀሳቀስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የውህደት ጉዳይ ለአንድነት ፓርቲ የአንድ ሰሞን ጥያቄ ሳይሆን ስትራቴጂክ ግብ ነው፡፡ የዚሁ አካል የሆነ እንቅስቃሴ በመኢአድና አንድነት ፓርቲዎች መሐከል መካሄድ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሂደቱን ለመቋጨት በርካታ ድርድሮችና የደብዳቤ ልውውጦችም  ቢከናወንም እነሆ አሁንም ተጨባጭ ውጤት በተግባር አለመታየቱ የሁለቱም ፓርቲ አባላት በእጅጉ እያሳዘነ ነው፡፡

በተለይ በቅርቡ እየተካሄደ ከነበረው ተግባር መካከል ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)    መጋቢት 1 ቀን 2ዐዐ6 ዓም የተፃፈልንን  ደብዳቤ መሠረት በማድረግ የሁለቱ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች እንዲገናኙ የተጠየቀውን ጥያቄ በደስታና በላቀ መንፈስ  ተቀብለነዋል፡፡ በዚሁ መሠረት      መጋቢት 4 ቀን 2ዐዐ6 ዓም  በሰጠነው የደብዳቤ መልስ ላይ እንደገለጽነው  በአንድነት ፓርቲ እይታ አመራሩ  የፊት ለፊት ውይይት የምንፈልገውና ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ  መጋቢት 7 ቀን 2006 ዓ.ም በመኢአድ ጽ/ቤት በተጠራውና የሁለቱ ፓርቲዎች የብ/ም/ቤት አባላትና የላዕላይ ም/ቤት አባላት በተገኙበት ለታሪክ በተቀረፀ ወሳኝ ስብሰባ ሠፊ የኃሳብ ልውውጦች ተካሂደው የፓርቲዎቹ ከፍተኛ አመራሮች የሚከተሉትን አስገዳጅ የውሳኔ ሃሳብ አቅርበው ነበር፡፡
በዚሁም መሠረት፡-
  1. የሁለቱም ፓርቲዎች አባላት አላስፈላጊ ጥቃቅን ጉዳዮችን በማንሳት ውህደቱን አታጓቱ ውህደት የማትፈፅሙ ከሆነ እኛ አባላት በራሳችን ውህደት እንፈፅማለን የሚል ጥብቅ ተማፅኖና ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል፡፡
  2. በአጠቃላይ የሁለቱ ፓርቲዎች ፕሬዚደንቶችና አደራዳሪ ሽማግሌዎች በገቡት ቃል መሠረት ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም ቅድመ ውህደት የመግባቢያ ሰነድ እንዲፈረም ከስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡
  3. የሁለቱ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች የውህደት አስፈፃሚውን ጠቅላላ ጉባኤ ጠሪ ኮሚቴ አባላት የሚሆኑትን የስም ዝርዝር፣ የፊርማው ስነ ሥርዓት በሚከናወንበት እለት እንዲያመጡ ተስማምተን ነበር፡፡
በከፍተኛ አመራሮችና በሁለቱ ሥራ አስፈፃሚዎች ውሳኔ መሠረት የሁለቱ ፓርቲ ፕሬዝደንቶች ተስማምተው፣ የቅድመ ውህደት መግባቢያ ሰነድ በሁለቱ ፓርቲዎች የድርድር ኮሚቴ አባላት መካከል ተፈራርመን፤ ሆቴል ተከራይተንና ከአዲስ አበባ አስተዳደር የሕዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል  የዕውቅና  ሠነድ አግኝተን  የመጨረሻ የስነ-ስርዓቱን መርሃ-ግብር በመጠባበቅ ላይ እያለን  በድንገት በመኢአድ ፕሬዝደንት  በኩል  በቁጥር መ/ኢ/አ/ድ 278/06 መጋቢት 9 ቀን 2006 ዓ.ም በእለቱ የቅድመ ውህደት ፊርማውን መፈረም እንዳማይችሉ የሚገልጽ ደብዳቤ ለፓርቲያችን  መድረሱ በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡  ከደብዳቤው እንደተረዳነው  መጋቢት 7 ቀን 2006 ዓ.ም የፓርቲዎቹ ከፍተኛ  አመራሮች ከበርካታ የሃሳብ ልውውጥ በኋላ የደረሱበትን ውሳኔ  የሚቀለብስ፣ የሁለቱ ፓርቲዎች ተደራዳሪዎች እየተስማሙ በቃለ ጉባኤ ያፀደቁትንና ከሁሉም በላይ የሁለቱ ፓርቲ  ተደራዳሪዎች ለቅድመ ውህደት ባዘጋጁትና ባፀደቁት የመግባቢያ ሰነዶች ላይ የሰፈሩ ነጥቦችን እንደ አዲስ  በማንሳትና በጥቃቅን ጉዳዮች በመጠመድ የቅድመ ውህደቱ እንዳይፈረም ተደርጓል፡፡ ለዚህ ታሪካዊና የሕዝብ ጥያቄ መደናቀፍ  ምክንያቱ የመኢአድ ፕሬዚንት ሲሆኑ  ይህን ሁኔታ   በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለሚገኙ  ለሁለቱ ፓርቲዎች አባላት፣  ደጋፊዎች፣ በግል ተነሳሽነትና በሀገር ተቆርቋሪነት ስሜት ሁለቱን ፓርቲዎች ለማደራደር ሲደክሙ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችና ለሕዝቡ ጥሩ ዜና ባይሆንም ላለመፈረሙ   ኃላፊነቱን የሚወስዱት የመኢአድ አመራሮች በተለይም ፕሬዝደቱ  መሆናቸውን  ማሳወቅ እንወዳለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ  ለውህደቱ መሳካት የመኢአድ አባላትና ከፊል አመራሩ  እያሳዩ ለሚገኘው ፍላጎትና ጥረት ፓርቲያችን መልካም አክብሮቱን መግለፅ ይወዳል፡፡

መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

maleda times | March 20, 2014 at 3:47 pm | URL: http://wp.me/p2gxmh-47o
Comment   See all comments

Sunday, March 16, 2014

በሕወሓት ጄኔራሎች እና በብኣዴን የጦር መኮንኖች መካከል ውጥረት ነግሷል::


ጄኔራል አበባውን ወደ ሲቭል ባለስልጣንነት የመቀየር እቅድ ተይዟል::

ምንሊክ ሳልሳዊ :- ህገመንግስታዊ ጥያቄ ባነሱ ከጄኔራልነት እስከ ሻምበልነት ማእረግ ባላቸው የቀድሞው የኢሕዴን ታጋዮች እና የአሁን የብኣዴን የጦር መኮንኖች እና በሕወሃት ጄኔራሎች መካከል ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥያቄዎችን ያማከለ እና ህገመንግስታዊ ስርኣትን ተከትሏል የተባለለት ጥያቄዎችን ተከትሎ ከፍተኛ ውጥረት መከሰቱን የመከላከያ ምንጮቻችን ጠቁመዋል::
ባለፉት ሰሞናት የተደረጉት ስብሰባዎች በከፍተኛ አለመግባባት የተበተኑ ሲሆን በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በስፋት የፓርቲ ስራዎች እንጂ ሃገራዊ ስራዎች እየተሰሩ አይደለም የሚሉ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊቱ ለህገመንግስቱ መከበር ተገኢ መሆን አለበት በአሁን ወቅት ለአንድ የፓርቲ አመራር እና ለፕሮፓጋንዳ ተገኢ ሆነናል የሚሉ ተመሳሳይ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በሰራዊቱ ውስጥ ያለውን የእድገት የትምህርት እና የደምወዝ መብትን በተመለከተም ከፍተኛ ክርከር ቢደረግም ካለመግባባት መኮንኖቹ ጥርስ እንደተነካከሱ ወደየመጡበት ተበታትነዋል::
የሰራዊት አባላትን ለመቀነስ በተደረገው ጥናት መሰረት ለምን ሁለት ብሄር ላይ አተኮረ የሚሉ ጥያቄ እንዲሁም የስኮላርሺፕ አድሏዊነት በተመለከተ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን እንዲሁም ከአንድ ብሄር ለትምህርት ተመርጠው የሚላኩ መኮንኖች በዛው ሳይመለሱ ይቀሩና ነገሩ ይድበሰበሳል የሚሉ አስጨናቂ ጥያቄዎች ተከታትለው ቢነሱም ከመድረኩ መልስ ሳይሰጥባቸው ተድበስብሰው አልፈዋል::ከአንድ ብሄር ብቻ ተመርጠው ለትምሕርት አውሮፓና አሜሪካ ከሄዱት መኮንኖች 80 ከመቶ ያልተመለሱ ሲሆን ይህ ጉዳይ ተድበስብሶ ሌላው ብሄር ስኮላሺፕ እንዳያገኝ ምክንያት እየተፈጠር በዚያው ስለምትከዱ ሃገር ውስጥ በቂ አካዳሚ ስላለ እዚህ እንድንማር ይደረጋል::ስኮላሺፕ የሚሰጣቸው ለማይመለሱ መኮንኖች ነው የሚሉ አቤቱታዎች ተሰምተዋል::
በሕወሓት ጄኔራሎች እና በብኣዴን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መካከል የተነሳውን ፍጥጫ ተከትሎ ጄኔራል አበባውን ወደ ሲችል ባለስልጣንነት ለማዘዋወር የታቀደ መሆኑን የገለጹት ምንጮሽች በአሁን ሰአት ጄኔራሉ እንደ ቁም እስረኛ አብዛኛው ጊዜያቸውን በመኖሪያ ቤታቸው እንደሚያሳልፉ እና ወደ ቢሯቸው አልፎ አልፎ እንደሚገቡ ታውቋል::
የሳሞራ የኑስን ስልጣን ይረከባሉ ተብሎ የሚጠበቀው ጄኔራል አበባው ጄኔራል ዮሃንስን ወደ ሳሞራ ሕወሓት በሹመት አቅርቦ ካመጣቸው በኋላ ይተለያየ ተጽእኖ እየተደረገባቸው ቢሆንም የብኣዴን ፓርቲ አመራሮች ሁኔታውን በቅርብ እየተከታተሉ ነው ቢባልም ምንም አይፈጥሩም የአሽከርነት ሚና ካልሆነ በስተቀር ሲሉ ምንጮሹ ገልጸዋል::የጄኔራል አበባው ስልጣን ማቆም እና ወደ ሲቭል ባለስልጣንነት መቀየር በሃገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ላይ የሚያመጣው ለውጥ እንዳይኖር ሁኔታዎች እየተገመገሙ መሆኑ ታውቋል::ከዚህ ቀደም በተለያየ ወቅት ወደ ውጪ ለእረፍት ለመሄድ ጥያቄ ያቀረቡት ጄኔራል አበባው በተለያየ ምክንያት ሲሰናከልባቸው የቆየ ሲሆን እሳቸውን እና መሰላቸውን ከሰራዊቱ በዘዴ እና በብልሃት ገፍቶ ለማስወጣት በስፋት እየተሰራ መሆኑን ምንጮቹ ጠቁመዋል::ካሁን ቀደም ሜጄር ጄኔራል የነበሩት አባዱላ ገመዳ አቶ ተብለው ወደ ሲችል ባለስልጣንነት ሲዘዋወሩ ሁለት ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎች ደግሞ ወደ እስር ቤት መወርወራቸው አይዘነጋም::
maleda times | March 16, 2014 at 9:08 am | URL: http://wp.me/p2gxmh-41U
Comment   See all comments

Thursday, March 13, 2014

የኛዎቹ አንቲገኖች

የሠላማዊ ትግልን ምንነት እና ሁነት በጥልቀት ያጠኑ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ወደ ጥንታዊ ግሪክ ኪናዊ- ትውፊት እስከማመላከት ይዘልቃሉ፡፡ የአንቲገንን ተግባር በምሳሌነት በማጣቀስ፡፡ በዚያ ዘመን ግሪክ በእርስ በርስ ጦርነት ትታመስ ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ በወቅቱ ሀገረ-ግሪክን ይገዛ የነበረው ኤዲፐስ ንጉስ፣ በእርስ በርስ ጦርነቱ የሞተ ማንኛውም ሰው አስከሬን እንዳይቀበር የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ የንጉሡ ከውሃ የቀጠነ ሕግ ያልተዋጠላት አንቲገን ግን የመጣው ይምጣ ብላ ትዕዛዙን ጣሰች፡፡ በጦርነቱ ሕይታቸው ካለፈ ሁለት ወንድሞቿ የአንዱን (የፖሊንሰስን) አስከሬን ቀበረች፡፡ በዚህም የተነሳ ተጠያቂ ሆና ንጉሡ መንበር ፊት እንድትቀርብ ተደረገ፡፡ ንጉሡም ለወጉ ያህል ቃሉን (ሕጉን) የተላለፈችበትን ምክንያት እንድታስረዳና ለቀረበባትም ክስ መከላከያ ካላት እንድታቀርብ ጠየቃት፡፡ እናም የሚከተለውን መልስ ሰጠች፡- “… ታማኝነት ለእግዚአብሔር ሕግ እንጂ ለምድራዊው ንጉስ ለአንተ ሕግ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ ደግሞ የሞቱትን ወገኖች አስከሬን እንድንቀብር ያዛል፡፡ ስለዚህ መጠየቅ ያለብህ አንተ እንጂ እኔ አይደለሁም፤ የእግዚአብሔር ቃል የሚፃረር ሕግ ያወጣኸው አንተ ነህና፡፡…” አንቲገን ከላይ የሰጠችውን ምላሽ ብቻ ተናግራ አላበቃችም፡፡ እውነትን ተመርኩዛ ንጉሱን ባለማወላወል ተጋፈጠችው፡፡ “… ይልቅስ ከተማው በሙታን ክርፋት ተጥለቅልቆ ወረርሽኝ እንዳይከሰትና እንዳይስፋፋ ሙታኖች እንዲቀበሩ ትዕዛዝ ስጥ፡፡…” አለችው፡፡ በዚህ ቁርጠኛ ምላሿ በንዴት የጦፈው ኤዲፐስ ንጉስ ከቅጣት ሁሉ እጅግ የከፋውን የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈባት፡፡ ሳትሞት ከነሕይወቷ እንድትቀበር ወሰነ፡፡ “በማይሻር ንጉሣዊ ቃሉ” መሰረት አንቲገን በቁም ተቀበረች፡፡ እኛስ? አሁን፤ እኛም በኤዲፐስ ንጉስ ዘመን በጥንታዊቷ ግሪክ ውስጥ ያለን ይመስለኝ ይዟል፡፡ በግልፅ “ምንም ዓይነት የመብት ጥያቄ አትጠይቁ” የሚል አዋጅ አልወጣም እንጂ፤መንግስት ምንም ነገር ላለመስማት የወሰነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ አሁን አሁን ሳስበው መንገድ ላይ እየሄድን ጨጓራችንን ቢያመን እና ብናቃስት፣ (ለነገሩ ምን ጨጓራ አለን? ተቃጥሎ አልቋል) “የማይፈለግ ድምፅ ማሰማት” በሚል በፖሊስ ተይዘን ዘብጥያ የምንወርድ ይመስለኝ ይዟል፡፡ ለዚህ አባባሌ ምክንያት አለኝ፡፡ ከቀናት በፊት በተደረገው የሴቶች ታላቁ ሩጫ ላይ የተሳተፉ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት “አላስፈላጊ ድምፅ በማሰማት” ወይም እየሮጡ የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው በፖሊስ ተይዘው እስርቤት መጣላቸውን ሰማሁ፡፡ አዘንኩ፡፡ እነዚህ ወጣት ሴቶች ለእኔ “አንቲገንን” ማለት ናቸው፡፡ የሚገርመው በዚህ ዘመን በግንባር ቀደምትነት የመብት ጥያቄን ከሚያነሱ ግንባር ቀደም ታጋዮች መሃል የሚበዙት እና ጎልተው የሚንቀሳቀሱት ሴቶች መሆናቸው ነው፡፡ ከእኛ ወንዶቹ በላይ ሴቶቹ “እምቢ ለመብቴ” ለማለት ቁርጠኞች መሆናቸውን ስንቶቻችን ልብ ብለን ይሆን?....(ይህንን ጉዳይ ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ) ሌላው ቀርቶ እዚህ ማህበራዊ ድረገፅ ላይ በሰከነ መንገድ በመወያየት ረገድ፤ በተለያየ መድረኮች ላይ በግንባር ቀደምትነና በቁርጠኝነት በመሳተፍ ሴቶች እህቶታቻችን ዓይነተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አለመናገር ንፉግነት ነው፡፡ …. የሆነ ሆኖ እየሮጡ መናገር፣ እየሮጡ መብትን መጠየቅ ሊያሳስር አይገባም ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህ የ“እኛዎቹ አንቲገኖች” (ሴት ታጋዮች) ይፈቱ፡፡ የመብትን ጥያቄ ዜጎችን በተለይም ሴት እህቶችን እና እናቶችን በማሰር ማዳፈን አይቻልም፡፡ ክብር ለሴት ታጋዮች!! .
maleda times | March 12, 2014 at 7:41 pm | URL: http://wp.me/p2gxmh-3Y2