ኢትዮጵያን በቁጥጥሩ ስር ያዋላት የትግራይ ዱር አራዊት ቡድን ዛሬ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየጫነ ያለውን የአፓርታይድ አይነት ስራት እነ ኒልሰን ማንዴላ ከደቡብ አፍሪካ ምድር ከስሩ መንግለው ለመጣል እጅግ ብዙ መስዋእትነትና ምእተ አመት የሚጠጋ ጊዜ ነበር የወሰደባቸው።
ምእራቡም ሆነ ምስራቁ አለም ለአፍሪካውያኑ የነጻነት ትግል ፈጥኖ እውቅናና ድጋፍ አለመስጠቱና በተለይ ምእራቡ ከነጮቹ ጋር ተመሳጥሮ በተዘዋዋሪ እነሱን መደገፉ ትግሉ ረጅም ጊዜ እንዲወስድና የነጻነቱም ቀን እንዲርቅ ቢያደርገውም፤ በትግሉ መሪዎች ፍጹም ቆራጥነትና ለሞት መዘጋጀት እንዲሁም በህዝቡ አንድነትና ጽናት አፓርታይድ ተወግዶ የደቡብ አፍሪካ ህዝብ መሪ መሾምና መሻር ችሏል በነጻነት።
እርግጥ በኢትዮጵያ የበላይነቱን የተቆጣጠሩት የህውሀት ዘረኛ ሰዎች ከደቡብ አፍሪካ ነጮች ጋር ሊያነጻጽራቸው የሚያስችል ስልጣኔና ለነጩ አለም ቀረቤታ አላቸው ባንልም፤ ለሀያላኑ መንግስታት በሎሌነት እስከቀረቡና የሚታዘዙትን እስከፈጸሙ ድረስ ድጋፋቸውን እንደማይነፍጓቸው ባይናችን እያየነው በመኖር ላይ ነን። ይሁንና ከሁሉም በላይ ለወያኔ መቅበጥና ከልከ ማለፍ፤ ለነሱ የልብልብ ማግኘትና በላያችን ላይ መግነን ተጠያቂው እራሳችን ነን። አንድ ሆነን በቶሎ እነሲህን የኢጣሊያ ጣእረመንፈስ ነጋሲያን ፋሺሽቶች ማስወገድ ተስኖን የህዝቡን ደም እየጠቡ፤ የሀገሪቱን ሀብት እየዘረፉ መወፈራቸውን ቀጥለዋል።
የደቡብ አፍሪካውን የጥቂት ነጮች አፓርታይ መንግስት ለማስወገድ ኤ ኤን ሲ በ1912 ዓም ኢ ኤ አ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ከአርባ አመት በላይ ሰላማዊ የትግል ስልት ነበር ሲከተል የቆየው። ህዝባዊ እንቢታ፤ እቤት የመዋል አድማ፤ የሥራ ማቆም አድማ፤ ይለፍ ወረቀት ሳይዙ በጅምላ ሆ ብሎ የተከለከለ ቦታ ሄዶ መታሰር፤ ወዘተ…. ያሁሉ ግማሽ ምእተ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የተካሄደው ሰላማዊ ትግል የህዳጣኑን መንግስት ጭቆናና ጭካኔ አባባሰው እንጂ ለደቡብ አፍሪካ ህዝብ የፈየደው ነገር አልነበረም።
ኋላ ላይ ግን እነማንዴላ ሀሳባቸውን ለመቀየር ተገደዱ። ሰላማዊው ትግል በትጥቅ ትግል መደገፍ እንዳለበት አመኑ። ይህንንም ወሰኑ። የሽምቅ ውጊያ ለመጀመር በርካታ የ ኤ ኤን ሲ ታጋዮች ማንዴላን ጨምሮ ወደተለያዩ ሀገሮች ለወታደራዊ ስልጠና ተሰማሩ። ማንዴላም ወደ ኢትዮጵያ አቀና። እናም እ ኤ አ በ1961 ዓም የ ኤ ኤን ሲ ወታደራዊ ክንፍ በማንዴላ መሪነት ተመስርቶ በመንግስቱ የኢኮኖሚና ወታደራዊ ተቋማት ላይ አደጋ መጣል ጀመረ።
የነጮቹ መንግስት የትግሉ ትኩሳት እየተሰማው በመጣ ቁጥር ወያኔ እንደሚያደርገው በየጊዜው አዳዲስ ህግ ማውጣትና ድርጅቶችን ሁሉ ማገድ፤ ህዝቡንና ታጋዮቹን ማሳደድ፤ ማሰርና ማዋከቡን በሙሉ ሀይሉ ቀጠለ። የትግሉን መሪዎች የደረሰበትን በቁጥጥር ስር አዋለ ያልተያዘውም ከሀገር መሰድድና ትግሉን ከጎረቤት ሁኖ መምራት ግድ ሆነበት። የታሰሩት መሪዎች የሀገር ክህደትና መንግስትን በሀይል ለማስወገድ መሞከር በሚል ክስ ለሞትና ለድሜልክ እስራት ያዘጋጃቸው ጀመር አፓርታይድ ።
እ ኤ አ አቆጣጠር 1962 ዓም ማንዴላ ያለፍቃድ ከሀገር ወተሀል፤ ህዝብን ለአድማ አነሳስተሀል ተብሎ አምስት አመት ተፈርዶበት እስር ላይ እንደነበረ ነበር ይህ አዲሱ ክስ የተደረበለት። ከዘረኞች ፍርድ ቤት ለነጻነት ታጋዮች ፍትህ የለምና ከረጅም ጌዜ ከንቱ ክርክር በኋላ እነማንዴላ ጥፋተኞች ናቸው ብሎ ነጩ ዳኛ ፈረደ። የፍርዱን ልክ ከመበየኑ በፊት ተካሳሾች የፍርድ ማቅለያ ክርክራቸውን እንዲያሰሙ በታዘዙት መሰረት ማንዴላ አራት ሰአት የፈጀ ታሪካዊና ድፍረትና ሀቅ የሞላበት ንግግር በጽሁፍ አቅርቦ ነበር።
በዚያ የመጨረሻዋ የፍርድ ቀን ለችሎቱ የተናገረውን ማንዴላ በጻፈው መጽሀፍ ውስጥ አሳጥሮ አቅርቦታል። ያ የአላማ ጽናትና ቆራጥነት የተሞላበት ንግግር አንዷለም አራጌን እስክንድር ነጋን ያስታውሳል። በሀገራችን ካለው ሁኔታ ጋር ምን ያህል እንደሚመሳሰል ለማስገንዘብ ወደ አማርኛ መልሸዋለሁ።
ማንዴላ ተከሳሽ ሳጥን ውስጥ ቆሟል። ተራው ደርሶ የክርክሩን ማክተሚያ ያነብ ጀመር።
አንደኛ ተከሳሽ ነኝ። በባችለር ኦፍ አርት የመጀመሪያ ዲግሪ አለኝ። ጆሀንስበር ውስጥ ከሚስተር ኦሊቨር ታንቦ ጋር በሽርክና ሆነን ለተወሰኑ አመታት የጥብቅና ሙያ ሰርቻለሁ። በ 1961 ግንቦት መጨረሻ ላይ ህዝብን ለአድማ ማነሳሳት እና ካለፍቃድ ከሀገር መውጣት በሚሉ ክሶች የአምስት አመት ፍርድ ተፈርዶብኝ በእስር ላይ የምገኝ ፍርደኛ ነኝ።
ነሀሴ ወር 1962 ለእስር እስከተዳረኩበት ድረስ በጉዳዩ ከፍተኛ ሚና የተጫወትኩና ኡምኮንቶ ሱዚዌ፤ የኤ ኤን ሲን ወታደራዊ ክንፍ ለማደራጀት ከረዱት መካከል አንዱ መሆኔን እቀበላለሁ።
ከሁሉ በፊት መንግስት በመግቢያው ላይ በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው ትግል፤በውጭ ሀይሎች ወይም በኮሙኒስቶች ተጽእኖ ስር ያለ ነው የሚለውን ሀሳብና ግምት ባጠቃላይ ስህተት ነው ለማለት እሻለሁ። ያደረኩትን ነገር አድርጌአለሁ። እንደ ግለሰብም እንደ ህዝብ መሪነትም። ይህንን ሳደርግ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ባለኝ ተሞክሮና በፍጹም አፍሪካዊ ኩራትና ክብር እንጂ የውጭ ወገኖች ባሉትና በሚሉት ተመርቼ ተነሳስቼ አይደለም።
በወጣትነት ዘመኔ ትራንስኪ ውስጥ የጎሳችን አረጋውያን ስላለፈው የጥንት ዘመን ታሪክ ወግ ሲነግሩን እሰማ ነበር። ሽማግሌዎች ከሚያወሷቸው የሗላ ታሪካችን ከኔ ጋር የሚያመሳስሉት የነበረው “ ያባትን ሀገር “ ለመከላከል ያደረጓቸውን ጦርነቶች ሲያነሱ’ የእነ ደንጌ እና ባንባታ፤ ሂንሳና ማካና፤ ኩንቲና ዳላሲል፤ ሞሾሾና ሲሁሁኔ ስሞች ሲጠቀሱ፤ የመላው አፍሪካ ክብርና ኩራት ሆነው ይሞገሱ ይወደሱ ነበር። ያኔ ያን ታሪክ ሥሰማ ተስፋ አደርግ ነበር። ለህዝባችን የነጻነት ትግል የበኩሌን ጥቂት አስትዋጾ እንዳበረክት፤ ህይወት አንድ አጋጣሚ ትቸረኝ ይሆናል እያልኩ። በዚህ ጉዳይ ላይ ክስ ሲመሰረትብኝ እንደጥፋት የተጠቀሰውን ሁሉ እንዳደርግ መነሻና ግፊት የሆነኝ ይኸው የኋላ ታሪካችን ነበር።
ይህን እያልኩ የአመጹን ጥያቄ አነሳና ፈጥኜ ጥቂት ዘለግ ላለ አፍታ ያለውን ነገር ላስረዳ ግድ ይለኛል። እስካሁን ለችሎቱ ከተነገሩት ነገሮች ገሚሱም እውነት ገሚሱም እውሸት ናቸው። የሆነው ይሁንና ሻጥር ( በመንግስት የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ አደጋ መጣል) ማቀዴን አልክድም። ይህንንም ሳቅድ በግዴለሽነትና በዘፈቀደ መንፈስ ተሞልቼ ወይም ደግሞ አመጽን የምወድ ሰው ሁኜ አይደለም። የረጅም ዘመን አንባገነንነት ያስከተለውን የነጮች ብዝበዛና ጭቆና የተንሰራፋበትን የፖለቲካ ሁኔታ በሰከነ አእምሮና በተረጋጋ ሁኔታ ስገመግም ከኖርኩ በኋላ ነው በውጤቱ ይህን እርምጃ ለማቀድ የወሰንኩት።
ለችሎቱ ለማስረዳት የሞከርኩት ይህን የአመጽ እርምጃ ስንወስድ ሀላፊነት ሳይሰማንና ያልተጠበቀ ውስብስብ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ሳናስብ ቀርተን እንዳልነበር ነው። አንድም አይነት ጉዳት በሰው ህይወት ላይ እንዳይደርስ ለማድረግ መወሰናችንን አጽንኦት ሰጥቼ ነበር።
እኛ ኤ ኤን ሲዎች ምንጊዜም የቆምነው ከዘረኝነት የጸዳ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ነው። ጎሳዎችን እስካሁን ካሉበት ሁኔታ በባሰ መልኩ ከሚያራራርቅ ማናቸውም ድርጊት እንታቀባለን። ጠጣሩ እውነታ ወይም ሀቅ ግን የሀምሳ አመት ሰላማዊ ትግል ለአፍሪካውያን ያተረፈው ያስገኘው ነገር ቢኖር እየበዛ እየበዛ የመጣ የመጨቆኛ ህግና እያነሰ እያነስ የሄደ መብት ብቻ ነው። ለዚህ ችሎት ይህን መረዳት ቀላል ላይሆን ይችላል። ህዝቡ ለረጅም ዘመን ሀይል ስለታከለበት አመጽ ሲነጋገር መኖሩ እሙን ነው። የአመጽን አማራጭ ተተው በሰላማዊ ትግሉ እንዲቀጥሉ እኛ የ ኤ ኤን ሲ መሪዎች ብንመክርም፤ ከነጮች ጋር ተዋግተው የሀገራቸው ባለቤት ስለሚሆኑባት ቀን ይወያያሉ። ግንቦትና ሰኔ 1961 ዓም ገሚሶቻችን ይህን እየተነጋገርን በነበረ ወቅት ከዘረኝነት የጸዳ መንግስት እንዲኖረን ለማድረግ የሰላማዊ ትግሉ ፖሊሲ ምንም ውጤት እንዳላመጣ መካድ አልተቻለም ነበር። ተከታዮቻችን በዚህ ፖሊሲ ላይ መተማመን እያቃታቸው፤ የሀይልን አመጽ እንደአማራጭ በአእምሮ ውስጥ ማጎልበት ጀመሩ። የሚረብሽ የአሽባሪነት እሳቤ።
የ ኤ ኤን ሲ ወታደራዊ ክንፍ ህዳር 1961 ዓም ተመሰረተ። ይህን ውሳኔ ስናስተላልፍና በተከታታይ እቅዳችንን ስንነድፍ የ ኤ ኤን ሲ ሌጋሲ ከአመጽ በጸዳ ትግል ህብረ ዘርነት እውን የሚሆንበት ሀሳብ አብሮን እንዳለና እንደያዝነው ነበር። ሀገሪቱ በጥቁሮችና በነጮች መካከል ወደሚቀሰቀስ የርስበርስ ጦርነት በሚያስኬድ ጎዳና ላይ እየተጓዘች እንዳለች ይሰማናል። ነገሩን የምንመለከተው በማስጠንቀቂያ ደወል ነው። የርስ በርስ ጦርነት ማለት ኤ ኤን ሲ የቆመለትን እሴት ማውደም ማለት ነው። የርስ በርስ ጦርነት ከተነሳ ማናቸውም ዘር ሰላም የማግኘት እድሉ እጅግ የከፋ ይሆናል። ጦርነት የሚያስከትለውን የከፋ ነገር ለማወቅ በደቡብ አፍሪካ ታሪክ ውስጥ በቂ ምሳሌ አለን። በደቡብ አፍሪካ አንግሎ – ቦር ጦርነት ያስከተለው ጠባሳ ለመሻር ከሀምሳ አመት በላይ ወስዷል። ዘር በዘር ላይ ተነስቶ ከሁሉም በኩል በቀላል የማይገመት ህዝብ በሚያልቅበት ሁኔታ ጦርነት ቢካሄድ ጠባሳው ለመሻር ምን ያህል ዘመን ይፈጃል?
በተግባር አይተን እንዳመነው፤ አመጽ፤ ለመንግስት፤ ህዝባችንን በጅምላ መጨረስ የሚያስችል ገደብ የሌለው እድል ይሰጠዋል። በርግጥም የደቡብ አፍሪካ ምድር፤ አፈር፤ ዱሮ በንጹሀን አፍሪካውያን ደም ጨቅይቷል። ሀይልን በሀይል መክተን ራሳችንን ለመከላከል የመዘጋጀት የረጅም ጊዜ ስራ መስራት ተግባራችን እንደሆነ ይሰማናል። ጦርነት አይቀሬ ከሆነ ጦርነቱ መመራት ያለበት ለህዝባችን ሁኔታ በተመቸ መልኩ እንዲሆን እንሻለን። ለኛ አንድ ነገር ያጎናጽፋል፤ እናም በሁለቱም ወገን አነስተኛ የህይወት መስዋእትነት የሚያስከፍል ይሆናል ብለን ያልነው የሽምቅ ውጊያ ነው። ለዚሁ ዝግጅት ለማድረግ ወሰንን።
ነጮች በሙሉ የግዴታ ወታደራዊ ስልጠና ይሰጣቸዋል። ለጥቁሮች ይህ ነገር አይደረግም። የሽምቅ ውጊያውን ሊመሩ የሚችሉ፤ ወታደራዊ ስልጠና ያላቸው ሀይሎችን መገንባት መሰረታዊ እሳቤአችን ነው። ሳንዘገይ ለዚህ መዘጋጀት አለብን።
ውይይታችን በዚህ ደረረጃ ላይ እንዳለ በአፍሪካ ሀገሮች ልዩ ልዩ ጉባኤዎችን ለመካፈልና ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ካገር እንደወጣሁ አስረዳሁ። የሽምቅ ውጊያ ቢጀመር ከህዝቤ ጋር አብሬ ለመቆም ለመዋጋት እንድችል፤ ወታደራዊ ስልጠና መውሰዴን ተናገርኩ።( ማንዴላ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደው ኢትዮጵያ ነበር ) በ ኤ ኤን ሲና በወታደራዊ ክንፉ መካከል ያለውን የሚለያቸውን መስመር ለችሎቱ ገለጽኩ። ሁለቱ እንዴት የተለያዩ መሆን እንዳለባቸው እንዳደረግን ተናገርኩ። ፖሊሲያችን ነበር። ተግባር ላይ ለማዋል ቀላል አልነበረም። በህግ መታገድ መታሰር ሁሉ ስለነበረ ሰዎች በሁለቱም ውስጥ መስራት ነበረባቸው። የኮሙኒስት ፓርቲውና ኤ ኤን ሲ አንድ ዓላማ አላቸው የሚለውን የመንግስት ክስ ተከራሬዋለሁ።
የ ኤ ኤን ሲ ርእዮተ ዓለም መርህ ምን ጊዜም አፍሪካዊ ብሄረተኝነት ነው። “ ነጭን ወደ ባህር ንዳው “ የሚለው አይነት የአፍሪካ ብሄረተኝነት ጩኽትም አይደለም። ኤ ኤን ሲ የቆመለት አፍሪካዊ ብሄረተኝነት፤ አፍሪካውያን በምድራቸው ምሉእ ሆነው በነጻነት እንዲኖሩ የሚያስችል ጽንሰ ሀሳብ ነው። የ ኤ ኤን ሲን ዓላማና አቋም የሚያንጸባርቀው ሰነድ በ ኤ ኤን ሲ የጸደቀው የነጻነት ቻርተር ሰነድ ነው። በምንም መልኩ የሶሻሊስት መንግስት እቅድ አይደለም። ለሀገሪቱ ታሪክ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር ኤ ኤን ሲ መቼም አብዮታዊ ለውጥን ደግፎ አያውቅም። እስከማውቀው የካፒታሊዝምንም ስራት አውግዞ አያውቅም።
ከኮሙኒስት ፓርቲው በተለየ መልኩ ኤ ኤን ሲ በአባልነት አፍሪካውያንን ብቻ ነው የሚቀበለው። ዋና አላማውና ግቡም አፍሪካውያን አንድነትና የተሟላ የፖለቲካ መብት እንዲቀዳጁ ማድረግ ነው። የኮሙኒስት ፓርቲ ዋና አላማ በሌላ መልኩ ካፒታሊስቶችን ማስወገድና በሰራተኛው መደብ መንግስት መተካት ነው። የኮሙኒስት ፓርቲ ለመደብ ልዩነት አጽንኦት ሲሰጥ ኤ ኤን ሲ በህብር አብረው የሚጓዚበትን ሁነት ይፈልጋል።
እርግጥ ነው በ ኤ ኤን ሲና በኮሙኒስት ፓርቲው መካከል የቅርብ ትብብር አለ። ትብብሩም የጋራ የሆነ ግብ መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው። ጉዳዩ የነጮችን የበላይነት ማስወገድ ነው። ይህ ማለት በሁሉም አቅጣጫ የጋራ አቋምና የጋራ ግብ እንዳለ ያረጋግጣል ማለት አይደለም። የአለም ታሪክ በተመሳሳይ ምሳሌዎች የተሞላ ነው። ምናልባትም ስሜት የሚሰጠው ስዕል፤ ታላቋ ብሪታንያ፤ አሜሪካና ሶቬት ህብረት ናዚ ሂትለርን ለመውጋት ያደረጉት ትብብር ነው። ሂትለር ብቻ ካልሆነ በስተቀር፤ ቸርችልን ወይም ሩዝቬልትን ወደ ኮሙኒስትነት ተቀየሩ ብሎ ማንም ሰው ለመናገር የሚደፍር አይኖርም። ወይም ደግሞ አሜሪካና እንግሊዝ የኮሙኒዝምን ስራት ለማስፈን እየሰሩ ነው የሚል አይኖርም። ልምድ ያላቸው አፍሪካውያን ፖለቲከኞች ኮሚኒስቶችን ለምን ጥሩ ወዳጅ አድርገው እንደሚቀበሏቸው ስር የሰደደ መጥፎ አመለካከት በነሱ ላይ ላላቸው የደቡብ አፍሪካ ነጮች መረዳት በጣም ሊከብዳቸው ይችላል። ለኛ ግን ምክንያቱ ግልጽ ነው። በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለብዙ አስርት አመታት ጥቁሮችን እንደሰው ለማስተናገድ የተዘጋጁ፤ ኮሙኒስቶች ብቻ ነበሩ። እኩልነታቸውን የተቀበሉ፤ አብረውን ለመብላት ለመጠጣት የተዘጋጁ፤ አብረውን ለማውጋት፤ አብረውን ለመስራትና ለመኖር የተዘጋጁ። በዚህም ምክንያት ዛሬ ብዙ አፍሪካውያን ናቸው ኮሙኒዝምን ከነጻነት ጋር እኩል አድርገው የማየት ዝንባሌ ያላቸው።
እኔ ምንጊዜም ራሴን እንደአፍሪካዊ አርበኛ የምመለከት እንጂ ኮሙኒስት አለመሆኔን ለችሎቱ አስረዳሁ። መደብ አልባ ስራት በሚል አስተሳሰብ መማረኬን ወይም ደግሞ የኮሙኒስት አስተሳስብ ተጽእኖ እንዳሳደረብኝ አልካድኩም።
ካነበብኳቸው የኮሙኒዝም ጽሁፎችና ከተወያየሗቸው ማርክሲስት ግለሰቦች እንደተረዳሁት ኮሙኒስቶች የምእራባውያንን የፓርላማ ስራት ኢዲሞክራሲያዊና አድሀሪ እንደሚሏቸው ተገንዝቤአለሁ። በተቃራኒው ግን እኔ የዚያ አይነቱ አሰራር አድናቂ ነኝ።
ማግና ካርታ ( መሰረታዊ መብት ማረጋገጫ ሰነድ)፤ ፔቲሽን ኦፍ ራይት፤ ቢል ኦፍ ራይትስ፤ የሚባሉት ሰነዶች በመላው ዓለም የሚገኙ ዲሞክራቶች ዘንድ በክብር የሚያዙ ሰነዶች ናቸው። ለብሪታንያ የፖለቲካ ተቋማት ታላቅ አክብሮት አለኝ። ለሀገሪቱ የፍትህ ተቋማትም እንደዚያው። የብሪያንያን ፓርላማ በዓለም ከፍተኛው ዲሞክራሲያዊ ተቋም አድርጌ ነው የምመለከተው። የፍትህ ተቋማቷ ራስ ገዝነትና ያለ ወገንተኝነት መስራት አድናቆቴን ሳያጭሩ የቀሩበት ጊዜ የለም። የአሜሪካን ኮንግረስ፤ የሀገሪቱ ስልጣን ክፍፍል፤ የፍትህ ተቋማቷ ራስ ገዝነት ተመሳሳይ አድናቆት በውስጤ ያጭራሉ።
በደቡብአፍሪካ ውስጥ በጥቁሮችና በነጮች ህይወት መካከል ያለውን አስደንጋጭ ልዩነት ዘረዘረኩ። በትምህርት፤ በጤና፤ በገቢ፤ በየፈርጁ ጥቁሮች በህይወት ለመቆየት ብቻ በሚያስችል ደረጃ ሲኖሩ፤ ነጮች በአለም ያለውን ከፍተኛ ደረጃ ይኖራሉ። እናም ህይወት በዚሁ መልኩ እንድትቀጥል የማድረግ ዓላማ አለ። “ነጮች” አልኩ። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያሉት ጥቁሮች በሌላው አፍሪካ ካሉት ጥቁሮች የተሻለ ኑሮ የሚኖሩ ናቸው ብለው ያስባሉ። የኛ እሮሮ አልኩ፤ ከሌላው የአፍሪካ ህዝብ ጋር ስንነጻጸር ድሆች ነን አይደለም። በሀገራችን ውስጥ ካሉት ነጮች ጋር ስንነጻጸር ድሆች ነን ነው። ይህንን የተዛባ ሁኔታ እንዳናርም እንዳናስተካክል በህግ ተከልክለናል ነው።
አፍሪካውያን በሀገራቸው ክብር ያጡበት ሁኔታ ነጮችን የበላይ የማድረጉ ፖሊሲ ቀጥተኛ ውጤት ነው። የነጮች የበላይ መሆን የጥቁሮችን የበታችነት ያስከትላል። የነጩን የበላይነት ለመጠበቅ የሚወጣው ህግ ይህን እምነት ስር እንዲሰድ ያደርገዋል። በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ማናቸውም ዝቅተኛ ስራ በጥቁሮች ነው የሚሰራው። አንድ ነገር መነሳት ወይም መጽዳት ካለበት ያን ስራ እንዲሰራለት ነጩ ጥቁሩን ገልመጥ ገልመጥ ብሎ ይፈልገዋል። አፍሪካዊው የርሱ ተቀጣሪ ሆነም አልሆነም።
ድህነትና የቤተሰብ መፍረስ የሚያስከትሉት ነገር አለ። የሚሄዱበት ትምህርት ቤት ስለሌላቸው፤ ወይም ትምህርት ቤት እንዲውሉ የሚያስችል ገንዘብ ወላጆቻቸው ስለሌላቸው፤ ህጻናት በየጎዳናው ሲንከራተቱ ይውላሉ። እቤት ውስጥም ተገኝተው ልጆቻቸው የት እንደሚውሉ ሊያዩ የሚችሉ ወላጆች የሉም። እናትም አባትም ያውም ሁለቱም ካሉ ቤተሰቡን በህይወት ለማቆየት ስራ ብለው ውጭ መዋል አለባቸው። ይህ የወደቀ የሞራል ደረጃን ያስከትላል። በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በየአቅጣጫው ህገወጥነት፤አመጽና ሁከት እንዲንሰራፋ ያደርጋል።
አፍሪካውያን በመላዪቱ ደቡብ አፍሪካ እኩል ድርሻ እንዲኖራቸው ይሻሉ። በህብረተሰቡ ውስጥ የደህነነት ዋስትናና ድርሻ እንዲኖራቸው ይሻሉ። ከሁሉም በላይ እኩል የፖለቲካ መብት እንዲኖረን እንሻለን። ያለዚህ መብት ስንኩልነታችን ዘለአለማዊ ነው የሚሆነው። በዚህች ሀገር ውስጥ ላሉት ነጮች ይህ አብዮታዊነት እንደሚመስላቸው አውቃለሁ። ምክንያቱም ብዙሀኑ መራጭ የሚሆነው ጥቁሩ አፍሪካዊ ስለሚሆን ነው ነጩ ዲሞክራሲን እንዲፈራ የሚያደርገው።
ይህ ኤ ኤን ሲ የሚዋጋለት ጉዳይ ነው። ትግላቸውም እውነተኛ ብሄራዊነት ነው። ባፍሪካውያን በራሳቸው ተሞክሮና በደረሰባቸው ስቃይ የተቀሰቀሰ የአፍሪካ ህዝቦች ትግል ነው። በህይወት የመኖር መብት ትግል ነው።
ንግግሬን አነበብኩ። እዚህች ነጥብ ላይ እንደደረስኩ ወረቀቶቼን ተከላካይ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጥኩና ፊቴን ወደ ዳኛው መለስኩ። ችሎቱ ፍጹም ጸጥ እረጭ አለ። የመጨረሻዋን ንግግር ከትውስታዬ ስናገር ፊቴን ከዳኛ ዴዊት ላይ ዘወር አላደረኩም ነበር።
በህይወት ዘመኔ ለዚህ የአፍሪካ ህዝብ ትግል ህይወቴን አሳልፌ ሰጥቻለሁ። የነጮችን የበላይነት እየተዋጋሁ ነው። የጥቁሮችን የበላይነት እየተዋጋሁ ነው። ሁሉም ሰው ተዋህዶ፤ ሰምሮና አብሮ እኩል እድል እየተጋራ አንድ ላይ መኖር አለበት የሚል አስተሳስብ አለኝ። የምኖርለትና እንደግብም ልለቀዳጀው ተስፋ የማደርግበት አስተሳሰብ ነው። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ለመሞት የተዘጋጀሁለት አስተሳሰብ ነው።
አሁን በችሎቱ ፍጹም ጸጥታ ሆነ። የመጨረሻዋን ከተናገርኩ በኋላ ቁጭ አልኩ። በችሎቱ ውስጥ የነበሩ ታዛቢዎች ሁሉ አይናቸው እኔ ላይ ያረፈ መሆኑ ቢሰማኝም ቤቱ ውስጥ ወዳለው ህዝብ ዘወር ብየ አላየሁም። ጸጥታው ለበርካታ ደቂቃዎች የዘለቀ ቢመስልም ግን ምናልባትም ከሰላሳ ሲኮንድ በላይ አልቆየም ነበር። በረጅሙ የሚተነፍስ፤ ቁናቁና የሚተነፍስ፤ የሕብር ጉምጉምታ፤ የሴቶች ለቅሶ ተከትሎ በፍርድ ቤቱ ውስጥ ይሰማ ጀመር….
“LONG WALK TO FREEDOM” NELSON MANDELA (PAGE 432-438)
lkebede10@gmail.com